Saturday, 21 July 2018 12:36

አሜሪካ፤ ለጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አመራር ድጋፍ እሰጣለሁ ብላለች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(28 votes)

 የ100 ቀናት የለውጥ እንቅስቃሴያቸውን በአድናቆት እንመለከታለን - የአሜሪካ አምባሳደር

     ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች ጋር በሰብአዊ መብትና የዲሞክራሲ ጉዳዮች ላይ ሰሞኑን የመከሩት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክ ሬነር፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ባለፉት 100 ቀናት በሀገሪቱ ያስመዘገቡትን ለውጦች አገራቸው በአድናቆት እንደምትመለከተው አሰታወቁ፡፡  
አምባሳደር ማይክ ሬነር፤ “በመጀመሪያዎቹ 100 ቀናት የስልጣን ቆይታቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስደናቂ፣ ግልፅ፣ ጠንካራና ቀጥተኛ ተስፋ ሰጪ ንግግሮችን አድርገዋል፤ አዎንታዊ እርምጃዎችንም ወስደዋል” ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ሰብአዊ መብትን እንዲያከብር፣ ዲሞክራሲን እንዲያሰፋም ግልፅ አመራር መስጠታቸውን የጠቀሱት አምባሳደሩ፤ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የ100 ቀናት አስደናቂና ውጤታማ እንቅስቃሴ መንግስታቸው ድጋፉን የበለጠ እንዲያጠናክር እንደሚያበረታው አስታውቀዋል፡፡
መንግስታቸው በጠቅላይ ሚኒስትሩ እርምጃዎች በመደነቅ ከምንጊዜውም በላይ ከጎናቸው ለመቆም መወሰኑን አምባሳደሩ ገልጸዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የእስካሁን እርምጃዎች አነቃቂና አስደናቂ ናቸው፤ ለወደፊት በርካታ ተራማጅ እርምጃዎችን ለመውሰድ ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠናል ብለዋል - አምባሳደር ሬነር፡፡
“ዶ/ር ዐቢይ የሰጡት ተስፋ በቀጣይ ወደ ተግባር መቀየር አለበት” ያሉት አምባሳደሩ፤”ለውጡ ውጤታማ የሚሆነው ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት በኢትዮጵያውያን በራሳቸው ብቻ የሚመራ ከሆነ  ነው” ብለዋል፡፡
 በአጠቃላይ በሰብአዊ መብት አጠባበቅ፤ በዲሞክራሲ፣ በፖለቲካ ምህዳር ማስፋትና ተያያዥ እንቅስቃሴዎች ዙሪያ እንዲሁም ሌሎች እቅዶቻቸውን ለማሳካት በሚያደርጉት ጥረት የአሜሪካ መንግስት ድጋፍ አይለያቸውም - ብለዋል አምባሳደሩ በሰጡት ቃል፡፡  
አምባሳደር ማይክ ሬነር ከአዲስ ስታንዳርድ የእንግሊዝኛ ዌብሳይት ጋር ጁላይ 2 ቀን 2018 ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ በጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አማካኝነት የመጣውን ሁሉን አካታች የፖለቲካ እንቅስቃሴ አድንቀዋል።  “ጠ/ሚኒስትሩ፤ በበዓለ ሲመታቸው ወቅት ለዳያስፖራው፣ ለተቃዋሚዎችና በአሸባሪነት ተፈርጃው በአሜሪካ ለሚኖሩ ፖለቲከኞች ሳይቀር ወደ አገራቸው ገብተው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተፎካካሪዎች እንጂ ጠላቶች አይደሉም ሲሉ የተናገሩትም በእጅጉ የምንደግፈው ነው” ብለዋል- አምባሳደሩ በቃለ ምልልሱ፡፡
“ለውጥ ሂደት ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ አንዳንዴ ሰዎች ከሚያስቡት በላይ ብዙ ጊዜ ሊወስድ ይችላል። ነገር ግን ጠ/ሚኒስትር አቢይ ወደ ሥልጣን በመጡ አጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ አስገራሚ ለውጦችን እንዳመጡ አለማመን አንችልም።” ሲሉ አምባሳደር ማይክ ሬነር- ጠ/ሚኒስትሩን አድንቀዋል፡፡   

Read 9219 times