Print this page
Saturday, 21 July 2018 12:35

ከኤርትራ ጋር የተጀመረው ግንኙነት በጥንቃቄና በጥናት ላይ እንዲመሰረት ተቃዋሚዎች አሣሠቡ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(11 votes)

 - “በቀጣይ እስከ ውህደት ሊደርሱ የሚችሉበት ዕድል አለ” - ትዴት
  - “የልዩነት ግንብ መፍረሱ ትልቅ ስኬት ነው” - ሰማያዊ


    ለ20 አመታት ተቋርጦ የነበረው የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት እንደገና መጀመሩ የሚደገፍና የሚበረታታ ነው ያሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ ግንኙነቱ ከስሜት ባለፈ በጥንቃቄና በጥናት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን አሣስበዋል፡፡
የሁለቱ ሃገራት መሪዎች የወሠዱት እርቅ የማውረድ እርምጃ የሚደገፍ ነው ያሉት የኦፌኮ አመራር አቶ ጥሩነህ ገምታ፤ የግንኙነቱ እያንዳንዱ እርምጃ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስከብር መሆን አለበት ብለዋል፡፡ ሠሞኑን በሁለቱ አገራት መካከል የተፈጠረው እርቅ እኛም ስልጣን ብንይዝ በቅድሚያ የምንፈፅመው ሥራ ነበር ያሉት አመራሩ፤ ዶ/ር አብይ አህመድ የወሠዱትን እርምጃ ኦፌኮ ይደግፈዋል ብለዋል፡፡
የድንበር፣ የወደብና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ የኢትዮጵያን ጥቅም በማይጎዳ መልኩ መከናወን አለበት ብሎ ፓርቲያቸው እንደሚያምን የገለጹት አቶ ጥሩነህ፤ ድንበሩ ሲካለልም የአካባቢውን ህዝብ ውሣኔ ባከበረ መልኩ መካሄድ አለበት ብለዋል፡፡
ሠማያዊ ፓርቲ በበኩሉ፤ የተፈጠረው እርቅና ግንኙነት ለሁለቱም ሃገራት በእጅጉ ጠቃሚ መሆኑን ጠቁሞ- በሁለቱ ሃገራት መካከል የነበረው የልዩነት ግንብ መፍረሡ ትልቅ ስኬት ነው ብሏል፡፡
በቀጣይ የሚፈጠረው ግንኙነት ጥንቃቄ የሚያስፈልገውና ዘላቂ መረጋጋትና ጥቅምን የሚያመጣ መሆን አለበት፤ ብለዋል-የሠማያዊ ፓርቲ ም/ሊቀመንበር አቶ ጌታነህ ባልቻ፡፡
የተፈጠረው ግንኙነት በህግ ማዕቀፍ ታግዞ ወደ ኢኮኖሚና ማህበረሠባዊ ትስስር ማደግ አለበት ያሉት የኢዴፓ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደ በበኩላቸው፤ የቀጠናውን ሠላም ለማስከበር ሁለቱ ሃገራት ቀይ ባህር ላይ የባህር ሃይሎቻቸውን በጋራ አቀናጅተው የሚንቀሣቀሡበት ሁኔታም መፈጠር እንዳለበት ገልፀዋል፡፡
የሁለቱ ሃገራት አዲስ ግንኙነት የኤርትራን የፖለቲካ ሁኔታ እንደሚቀይረው የጠቆሙት ዶ/ር ጫኔ፤ ላለፉት 27 አመታት ለዲሞክራሲ ስርአት ዝግ የነበረው የፕሬዚዳንት ኢሣያስ አፈወርቂ መንግስት፣ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ላይ ማተኮር ያስፈልገዋል፤ አሊያ የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት አስተማማኝ ላይሆን ይችላል ብለዋል፡፡
አረና ትግራይ ለሉአላዊነትና ለዲሞክራሲ ደግሞ የተጀመረው የሰላምና የእርቅ ሂደት የሚደገፍ ቢሆንም ግንኙነቱ ግልፅነት የለውም ብሏል፡፡ የወደብና የድንበር ጉዳይ በቸልታ የታለፈ ጉዳይ ነው የሚለው አረና፤ የአልጀርስ ስምምነትም በአዲስ ውል መተካት አለበት የሚል እምነት እንዳለው ጠቁሞ፤ ከዚህ አንፃር የተፈጠረው ግንኙነት ዘላቂ ውጤት ላያመጣ ይችላል የሚል ስጋት አለኝ ብሏል፡፡
የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት ጥንቃቄ የሚያስፈልገው መሆኑንም የአረና ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጎይቶም ፀጋዬ ተናግረዋል፡፡
ከሠሞኑ ወደ ሃገር ቤት የተመለሡት  አንጋፋው የቀድሞ የህወኃት መስራችና “የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ትብብር” ሊቀ መንበር ዶ/ር አረጋዊ በርሄ በበኩላቸው፤ ግንኙነቱን በአዎንታዊ መልኩ እንደሚቀበሉት ገልፀው፤ በተለይ የሁለቱ ሃገራት ህዝቦችን በኢኮኖሚና ማህበራዊ መስተጋብር ለማስተሣሠር ጠቃሚ እንደሆነና በቀጣይም እስከ ውህደት ሊደርሱ የሚችሉበት እድል መኖሩን አስረድተዋል፡፡

Read 8794 times