Saturday, 21 July 2018 12:32

ከዳያስፖራው ለሚሰበሰበው የትረስት ፈንድ ገቢ 20 የሃዋላ ድርጅቶች ተመርጠዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

 በቅርቡ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ለተከፈተው “Ethiopian Diaspora Trust Fund” ገቢ ማሰባሰቢያን እንዲያሳልጡ 20 የገንዘብ አስተላላፊ የሃዋላ ድርጅቶች መመረጣቸው ታውቋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለመገንባት በሚደረግ ጥረት ውስጥ የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ፤ ለዚህም ቢያንስ በቀን አንድ ዶላር እንዲለግሱ የጠየቁ ሲሆን ጥያቄውን ተከትሎ ከዳያስፖራው በኩል ፍላጎቶች በመታየታቸው የትረስት ፈንድ ሂሳብ ቁጥር መክፈት ማስፈለጉን መንግስት አስታውቋል፡፡
ለዚህ ገቢ ማሰባሰቢያም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተመረጠ ሲሆን “Ethiopia Diaspora Trust Fund” በሚል የተከፈተው የባንክ ሂሳብ ቁጥርም 1000255727625 መሆኑ ታውቋል፡፡
የገቢውን አሰባሰብ እንዲያሳልጡም 20 አለማቀፍ የገንዘብ አስተላላፊ ሃዋላ ኩባንያዎች ተመርጠዋል፡፡
እነዚህም ዌስተር ዩኒየን፣ ኤክስፕረስ መኒ፣ ቦሌ አትላንቲክ፣ መኒ ግራም፣ ዳሃ ብሺል፣ ካሽ ኤክስፕረስ፣ ዎርልድ ረሚት፣ ትራንስፋስት፣ ካሃ ኤክስፕረስ፣ ጎልደን መኒ፣ ላሪ ኤክስቼንጅ፣ ታዋካል መኒ፣ ዜኒጂ ኤክስቼንጅ፣ ፓኮ መኒ፣ ኢርማን ኤክስፕረስ፣ ባካል መኒ፣ ዲቫይን፣ ዳዊት መኒ፣ ታአንድ ረሚት እና አስጎሪ መኒ የሃዋላ አስተላላፊዎች መሆናቸው ታውቋል፡፡
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን የስዊፍት አድራሻ CBATETAA በመጠቀም ገንዘብ ማስገባት እንደሚቻልና በቅርቡም የገቢ ማሰባሰቢያ ድረ-ገፅ እንደሚዘጋጅ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡
በጉዳዩ ላይ ሙያዊ አስተያየታቸውን ለአዲስ አድማስ የሠጡት የምጣኔ ሃብት ምሁሩ ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በርሄ በበኩላቸው፤ የውጭ ምንዛሬ ችግርን ከማረጋጋት አንፃር በእርዳታ መልክ ዶላር መሠብሠብ ጠቃሚ ነው ብለዋል፡፡
ገንዘቡ በእርዳታ የሚሰበሰብ እንደመሆኑ እርዳታው በማን ይሠበሠባል? ለየትኛው ፕሮጀክት ይውላል? የእርዳታ ሠብሣቢው የቦርድ አባላት፤ አመራሮች እነማን ናቸው? የሚለውን ለህዝብ ግልፅ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፡፡ ግልፅ መደረጉ መተማመንን በመፍጠር የዳያስፖራውን ተሣትፎ ሊያሣድገው እንደሚችል ያስታወቁት ምሁሩ በአጠቃላይ የሃገሪቱን የኢኮኖሚ ችግሮች ለመፍታት ግን የፋይናንስ መዋቅር ማሻሻያዎች ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

Read 6423 times