Print this page
Saturday, 21 July 2018 12:29

ድብደባ የተፈፀመበት የድሬዳዋ መገናኛ ብዙኃን ባልደረባ ህይወቱ አለፈ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(10 votes)

 ሲፒጄ በፕሬስ ነፃነት ላይ የተቃጣ ነው ሲል ድርጊቱን አውግዟል

   የኤርትራ ፕሬዚዳንትን የአቀባበል ስነ ስርአት ለመዘገብ ከድሬደዋ ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ ላይ ሣሉ ድብደባ ከተፈፀመባቸው የድሬድዋ መገናኛ ብዙኃን የጋዜጠኞች ቡድን መካከል የቡድኑ ሹፌር ህይወታቸው ማለፉ የታወቀ ሲሆን የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪ ሲፒጄ ድርጊቱን በፅኑ አውግዟል፡፡
የጋዜጠኞች ቡድኑ ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ ላይ ሳለ ሚኤሶ ላይ ቅዳሜ ሃምሌ 7 ቀን 2010 ዓ.ም በቡድን በተደራጁ ግለሠቦች ድብደባ እንደተፈፀመባቸው መዘገቡ የሚታወስ ሲሆን በፅኑ ተጎድተው የነበሩት የመኪናው አሽከርካሪ በድሬዳዋና በሃረር ሆስፒታሎች ህክምና ቢደረግላቸውም ህይወታቸውን ማትረፍ ሣይቻል ቀርቶ ሃሙስ ቀትር ላይ ህይወታቸውን ማለፉ ታውቋል፡፡
ጋዜጠኞቹ ላይ ጥቃቱ የተፈፀመው “ሠላዮች ናችሁ” በሚል ውንጀላ መሆኑም ታውቋል፡፡
በጉዳዩ ላይ መግለጫ ያወጣው የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪው ሲፒጄ (CPJ)  ጥቃቱ በፕሬስ ነፃነት ላይ የተቃጣ ነው ሲል አውግዟል፡፡ አጥፊዎችም በአስቸኳይ ለህግ እንዲቀርቡ ጠይቋል፡፡
ሟች የ37 አመቱ አቶ ሱሌይማን አህመዲን፣ የአራት ልጆች አባት ሲሆኑ በድሬዳዋ መገናኛ ብዙኃን ድርጅት ውስጥ ለአምስት አመት ማገልገላቸው ታውቋል፡፡
አምስት አባላትን የያዘው የጋዜጠኞች ቡድን ቅዳሜ አመሻሽ 11 ሠዓት ላይ ከድሬደዋ መነሣቱንና ምሽት 4 ሠዓት ላይ ሚኤሶ አካባቢ ሲደርስ ለጥቃት መጋለጡን የመገናኛ ብዙሃን ድርጅቱ ባልደረቦች ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
የሟች የቀብር ስነ ስርአት ሃሙስ አመሻሽ 10 ሰዓት ላይ በድሬድዋ መፈፀሙን የጠቆሙት የመገናኛ ብዙሃን ባልደረቦች ትናንት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ኢብራሂም ኡስማንን ጨምሮ የከተማው ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በደረሠው ጥቃት ጉዳይ ከመገናኛ ብዙሃኑ ባልደረቦች ጋር ምክክር ማድረጋቸውን ታውቋል፡፡
የሟች ቤተሠቦችን በቋሚነት መደገፍ በሚቻልበት እና ለወደፊት ጋዜጠኞች ማድረግ ባለባቸው ጥንቃቄዎች ዙሪያ መመካከራቸውም ታውቋል፡፡

Read 3658 times