Saturday, 21 July 2018 12:28

በኢትዮጵያ የአብዛኞቹ ዳያስፖራዎች ኢንቨስትመንት ስኬታማ አይደለም

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

 ጋሬጣ የሆነባቸው የመልካም አስተዳደር ችግር ነው ተብሏል

    ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች በሃገራቸው በ2 ሺህ 967 ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ላይ ቢሠማሩም ብዙዎቹ ስኬታማ ለመሆነን እንዳልቻሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርቱ አስታውቋል፡፡
ባለፉት 10 አመታት በተለያዩ የአለም ሃገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች በማኑፋክቸሪንግ፣ በግብርና እና በአገልግሎት ዘርፎች ኢንቨስት ለማድረግ ፈቃድ ቢያወጡም ስኬታማ ሆነው ስራ የጀመሩት አስር በመቶ ያህሉ ብቻ ናቸው ብሏል- የመንግስታቱ ድርጅት የአይኤልኦን ሪፖርት ዋቢ አድርጎ፣ ባወጣው ሠሞነኛው መግለጫ፡፡
 የኢንቨስትመንት ፈቃድ ከወሰዱ 2 ሺ 967 ዲያስፖራ ኢንቨስተሮች ውስጥ 234 ያህሉ  ብቻ ተሣክቶላቸው ወደ ስራ መግባታቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ በዚህም ለ4 ሺ 493 ኢትዮጵያውያን ቋሚ የስራ እድል፣ ለ13 ሺ 211 ጊዜያዊ የስራ እድል መፍጠራቸውን አመልክቷል፡፡ አጠቃላይ የኢንቨስትመንት አቅማቸውም 106 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን ይኸው ሪፖርት ይጠቁማል፡፡
በሃገሪቱ ኢንቨስት ለማድረግ መጥተው ያልተሳካላቸው 90 በመቶ የሆኑት ዳያስፖራዎች፣ በዋናነት ጋሬጣ የሆነባቸው የመልካም አስተዳደር ችግር ነው ብሏል- ሪፖርቱ፡፡ አብዛኞቹ ፕሮጀክታቸው በጅምር ደረጃ መቅረቱንም ሪፖርቱ ያትታል፡፡
የታክስ መብዛትና የውጭ ምንዛሬ እጥረት ሌላው የኢንቨስተሮቹ ተግዳሮች እንደነበሩም ተጠቅሷል፡፡
መንግስት ለዳያስፖራ ኢንቨስትመንት ተገቢውን ትኩረት መስጠት አለበት ያለው ሪፖርቱ፤ የማበረታቻ እርምጃዎች እንዲወሠዱም መክሯል፡፡
በዚሁ ሪፖርቱ ላይ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚያቸው በፍጥነት እያደጉ ካሉ ሃገራት ተርታ ብትመደብም፣ የዜጎቿ የነፍስ ወከፍ ገቢ ግን ከሌሎች የአፍሪካ ሃገራት አንፃር አነስተኛ ነው ተብሏል፡፡ ዜጎች የተሻለ ኑሮና ገቢ ፍለጋ ከሚሰደዱባቸው ሃገራት ውስጥ ኢትዮጵያ ከመጀመርያው ረድፍ እንደምትመደብም በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡

Read 2581 times