Print this page
Saturday, 21 July 2018 12:25

በስልጤ ዞን በህዝብ ተቃውሞ፣ 5 ባለስልጣናት ከስልጣን ታገዱ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

 በደቡብ ክልል የስልጤ ዞን ስልጢ ወረዳ ነዋሪዎች፤ የወረዳው ነዋሪዎች የጋራ መጠቀሚያ መሬት በባለስልጣናት ዘመዶች ከህግ ውጪ ተነጥቀናል ሲሉ ተቃውሞ ሲያሠሙ የሰነበቱ ሲሆን ተቃውሞውን ተከትሎ፣ አምስት የወረዳው ባለስልጣናት ከስልጣን ታግደዋል፡፡
በአካባቢው የተቃውሞ እንቅስቃሴ የተጀመረው ከሁለት ሳምንት በፊት መሆኑን ለአዲስ አድማስ የጠቆሙት የአካባቢው ነዋሪዎች፤ የተቃውሞ ምክንያትም፤ “የአካባቢው መሬት በህገ ወጥ መንገድ በባለስልጣናት የቅርብ ዘመዶች እየተመዘበረ ነው፤ የቀበሌ ቤት ሳይቀር ወደ ግል እየዞረ፣ የህዝብ ሃብት እየተዘረፈ ነው፤ አርሶ አደሩ በኢንቨስትመንት ስም በቂ ካሣ ሳይከፈለው እየተፈናቀለ ነው” የሚል መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
“38.5 ሄክታር መሬት በአንድ ከፍተኛ ባለስልጣን የቅርብ ዘመድ የግል ይዞታነት ስር ውሎ ያለ ልማት ተቀምጧል” የሚሉት ነዋሪዎቹ፤ መሬቱ ለአካባቢው ስራ አጥ ወጣቶች ተከፋፍሎ የስራ እድል ሊፈጠርበት ይገባል የሚል ጥያቄ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮና ለክልሉ ባለስልጣናት ማቅረባቸውን፣ ነገር ግን ለጥያቄያቸው ተግባራዊ ምላሽ እስካሁን እንዳልተሠጣቸው ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
የነዋሪዎቹ ተወካዮች ሠሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት ድረስ በመሄድ ጥያቄያቸውን ማቅረባቸውን ጠቁመው፤ ሆኖም የደኢህዴን ሊቀ መንበርና የፓርላማው አፈጉባኤ ወ/ሮ ሙፈርያት ከሚል፤ “በቦታው መጥቼ አነጋግራችኋለሁ” የሚል ምላሽ እንደሠጧቸው ተናግረዋል፡፡
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ፤ የወረዳው አመራሮች ከስልጣን እንዲነሡ ህዝቡ መጠየቁን ተከትሎ፣ የወረዳው አምስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በደኢህዴን ፅ/ቤት ከስልጣን መታገዳቸው ታውቋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ውጥረት ማየሉን የጠቆሙት አቤቱታ አቅራቢዎቹ፤ መንግስት ለጥያቄያቸው አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡


Read 3851 times