Print this page
Saturday, 14 July 2018 12:30

የሕይወት እምሻው “ፍቅፋቂ” ሐሙስ ተመረቀ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(4 votes)

“ፍቅፋቂ” በሚል ርዕስ የተዘጋጀው የሕይወት እምሻው ሁለተኛ መጽሐፍ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ፣ ሐምሌ 5 ቀን 2010 ዓ.ም. በዋቢ ሸበሌ ሆቴል ተመርቋል፡፡ የደራሲዋ ሁለተኛ ሥራ የሆነው ይህ የልቦለዶችና የወጎች ስብስብ መጽሐፍ፤ በ220 ገጾች ላይ የተዘራ ሲሆን 38 ዋና ዋና እና 20 መሻገሪያ ትረካዎችን ያካትታል፡፡
ደራሲዋ እንደ በኩር ሥራዋ ሁሉ በአዲሱ መጽሐፏ  ውስጥ በሚገኙ ትረካዎችም የኢትዮጵያዊያንን ፍቅር፣ ባህል፣ ፖለቲካ፣ የዕለት ተዕለት ሕይወት እያነሳች በቅርበትና በኪናዊ ለዛ ትበልታለች፤ እንደ አስገድዶ መድፈርና ድንግልናን የመሳሰሉ ጉዳዮችንም ተጠየቅ ውስጥ ትከታለች፡፡
ሕይወት ከደራሲነትም ባሻገር “ነቆራ እና ሌሎችም ወጎች ከሕይወት እምሻው ጋር” የተሰኘ ከመቶ ሠላሳ ሺህ በላይ ተከታዮች ያሉት የፌስቡክ ገጿ ላይም በቋሚነት በመጻፍ ትታወቃለች፡፡ በመጽሐፍት መልኩ መገለጥን ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከመጻፍ ጋር በማነጻጸር “ሁለቱ ፍጹም የተለያዩ ሂደቶች ናቸው” የምትለው ደራሲዋ፤ “ፌስቡክ ላይ መጻፍ ፍጥነት አለው፤ ስሜታዊና ቅጽበታዊም ነው፡፡ በአብዛኛው በጥሞና ከማሰላሰልና የፈጠራ ችሎታን ከመጠቀም የሚያቅብ ድርጊትም ሊሆን ይችላል፡፡ በአንጻሩ መጽሐፍ ማዘጋጀት ጊዜ ይወስዳል፣ ከፍተኛ ጥንቃቄና ተደራራቢ የአርትዖት ደረጃዎችንም ያልፋል” ትላለች፡፡
ከሦስት ዓመታት በፊት ባሳተመችው የመጀመሪያ መጽሐፏ “ባርቾ” የወጎችና የልቦለዶች ስብስብ፣ ኢትዮጵያዊያን ሊነጋገሩባቸው የማይደፍሯቸውን “አይነኬ” ጉዳዮች እያነሳች በዋዛና በቁምነገር በመተረኳ የበርካታ አንባቢዎች ልብ ውስጥ እንድትገባ አድርጓታል፡፡
ደራሲዋ ለወደፊትስ እጅሽ ከምን ለሚሏት ወዳጆቿ፤ “አንድ ረጅም ልቦለድ እየጻፍኩ ነው” ትላለች፡፡ “እኔ የምታወቀው ኳ! በሚያደርጉ በጣም አጫጭር ሥራዎች ስለሆነ ይሄ ከዚህ በፊት ያልታየሁበት ቀጠና ይሆናል፡፡ ከ‘ባርቾ’ እና ከ‘ፍቅፋቂ’ ጋር በይዘትና በቅርጽ የሚመሳሰል ሌላ ሦስተኛ መጽሐፍም አዘጋጃለሁ” ስትልም አክላለች፡፡
“ፍቅፋቂ” በሊትማን መጻሕፍት አከፋፋይነት ካለፈው ሐሙስ ጀምሮ በ92 ብር ዋጋ በገበያ ላይ ውሏል፡፡

Read 5871 times