Print this page
Monday, 16 July 2018 00:00

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(1 Vote)

 “ጥያቄው የህልውና ጉዳይ ሆኗል፤ የመኖርና ያለመኖር፤ የነፃነትና ባርነት!!”
               
     የድሮ ቀልድ ነው፡፡ ሰውየው ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀረበ፡፡ … ከሶ፣ ተከሶ፣ መስክሮ ወይም ተመስክሮበት አያውቅም፡፡ ትኩረቱ ምርምርና ፈጠራ ላይ ብቻ ነው፡፡ ምድር የተሻለች የመኖሪያ ቦታ እንድትሆን ማገዝ!! … ለሰው ልጆችም ሆነ ለእንስሳት፣ ለዕፅዋትም ሆነ …. ለምንም!! … አገር፣ መታወቂያ፣ ዜግነት፣ ዘር፣ ሃይማኖት ስለሚባሉ ነገሮች አስቦ አያውቅም፡፡ ‹እንደ ወረደ› … የሚባል ዓይነት ሰው ነው። በመኪና ብልሽት አደጋ አጋጠመውና ፍርድ ቤት ቀረበ፡፡
“ስምህን ማን ልበል?” አሉ ዳኛው፡፡
ነገራቸውና መዘገቡ፡፡
“የመኖሪያ አድራሻ?”
ነገራቸው፡፡
“የትውልድ ቦታ?”
ዝም፡፡
“የት ነው የተወለድከው?”
“አውሮፕላን ውስጥ”
“እ…?”
“ከአውሮፓ ወደ ኤዥያ ሲበር የነበረ አውሮፕላን ውስጥ ነው የተወለድኩት”
… ዳኛው “ሰው የትም ቦታ ሊወለድ ይችላል” ሲሉ አሰቡና ቅጹ ላይ ባለው ቦታ “አስፈላጊ አይደለም” በማለት ፃፉ፡፡
“ዜግነት?”
“አላውቀውም”
“የወላጆችህ አገር የት ነው?”
“የአባቴ አባት አሜሪካዊ ነው፣ እናቴ ናይጄሪያዊ ናት፡፡ የእናቴ አባት ግብፃዊ፣ እናቱ ደግሞ ጃፓናዊ ናት” አለ፡፡
ዳኛው እየሳቁ፡-
“የተባበሩት መንግሥታት ልበል?” ሲሉ ጠየቁት፡፡
“እንደፈለጉ” አላቸው፡፡ “ዓለም አቀፋዊ” ብለው ፃፉ። ቀጥለውም አደጋ የደረሰበትን ሰው አድራሻ በቅፁ ላይ መሙላት ጀመሩ፡፡ ሰውየው ስለተጎዳ ኮማ ውስጥ ነው፡፡ ሌላ ሰው እንዳይጠይቁ የሰውየውን መብት መጋፋት አይችሉም፡፡ … አሰቡ አሰቡና እራሴ የማውቀውን ነው መፃፍ ያለብኝ ብለው፣ የሚያውቁትን እውነት ከተቡ፡፡ ምን ብለው ይሆን?
***
“ኃይል፣ ዕውቀትና በራስ መተማመን ያለው መሪ የሚወለደው ከወገኖቹ ጭንቀትና መከራ፣ ብሶትና ተስፋ ማጣት ብቻ አይደለም፡፡ ከንባብ ልምድና ከጥበብ ትጋት፣ ሌሎችንም ከመረዳትና ውስጣቸውን ከማዳመጥ፣ ለፍቅር ከመኖርና ለዕውነት ከመቆም፣ ለመብትና ለነፃነት ከመቆርቆርና ነገን ዛሬ ላይ ሆኖ ለማየት ከመቻልም ጭምር ነው” ይላሉ ሊቃውንት። አቅሙና ችሎታው የሚፈተነውም በሾህና አሜኬላ የታጠረውን፣ ምኞትና ግርግር ያቦካውን፣ የሚያዳልጥና የሚያደናቅፍ ጎዳና በጥንቃቄ ተሻግሮ ታላቁን ህዝባዊ ድል መስመር ማስያዝ ሲችል ነው በማለትም ጽፈዋል፡፡
“የጀርመን ተሃድሶ በፈጠረው ትርምስ ውስጥ ታላላቅ ሰዎች በቅለዋል፡፡ በፈረንሳይ አብዮት ግርግርና ውዥንብር ውስጥ እንደ ናፖሊዮን ዓይነት ኮከብ በርቷል…
“Out of the cheos comes the dancing star; out of the turmoil and nonsense of the French revolution, Napoleon; out of the violence and disorder of the renaisance, powerful individuals” በማለት!! … በኛም ሃገር የፀረ ፊውዳልና የፀረ ተስፋፊዎች ትግል ውስጥ የበቀሉ፣ ታላላቅ መሪዎች ነበሩ፡፡ … እነሱ እንዳሉ ሆነው፣ አሁን ባለንበት ዘመን “ጭቆና ይብቃ!” በማለት የተቀጣጠለውን ትግል የሚመሩ “ለአንድነት ቆመናል” የሚሉ ከዋክብት ቦግ ብለዋል፡፡
“ሃገር የዘመን ጉዞ ውልድ ናት፡፡ የበለፀገና የሰለጠነ ህዝብ የሚያስበውም አንድነቷና ሰላሟ ተከብሮና ተጠብቆ በነፃነቷ ሲደምቅ ነው፡፡” ይላሉ፡፡ … እሰይ!!
“አንድነት ትንንሽ ግዛቶችን ትልቅ ሃገር ያደርጋቸዋል። ግጭትና ንትርክ ደግሞ ትልልቆቹን ያፈርሳቸዋል፡፡ (By union the smallest state thrives, by discord the greatest are destroyed)” እንደሚለው … ዳንኤል ዌብስተር፡፡
ወዳጄ፡- ስንታመም ሃኪም ያስፈልገናል፡፡ ሃኪሙ ሊረዳን የሚችለው ስለ በሽታው የሚያውቅና በመስኩ የሰለጠነ (Specialist) ባለሙያ ሲሆን ነው፡፡ አለበለዚያ ህመማችንን ሊያወሳስበውና ሊያባብሰው ይችላል፡፡ ሃገር ስትታመምም ሊያክሟት የሚችሉት የሚያመዛዝን አእምሮ ያላቸው፣ ከስሜታዊነት የራቁ፣ ብልህና አርቆ አሳቢ መሪዎች ናቸው፡፡ መመሪያ ከመቀበልና መመሪያ ከማስተላለፍ ሌላ ችሎታ የሌላቸው ጉልት ባለስልጣናት፤ ከመንግሥት አስተዳደር መራቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ህመማችንን እንዳያባብሱ!!
በጥንታዊት ግሪክ ሚቲዮሎጂ የሚጠቀስ ባለ ብዙ ራስ ዘንዶ አለ፡፡ ሃይድራ!!  ተፋላሚዎቹ አንዱን አንገት ሲቆርጡበት በሌላው ይበላቸዋል፡፡ አንገቶቹ የተተከሉበት ደንደስ ካልተሰበረ ዘንዶውን ማሸነፍ አይታሰብም፡፡ … የሃገራችንም ችግር እንደዛ ነው፡፡ ሌብነትን ስትከላከል ዘረኝነት ያፈጥብሃል፡፡ ዘረኝነትን ስትዋጋ ረሃብና ችግር ይመታሃል፡፡ ረሃብና ስደትን ስትቋቋም አጉል እምነትና ልምድ ያንቅሃል፡፡ እሱን ስትታገል ኢ-ፍትሃዊነትና የመልካም አስተዳደር ዕጦት ያስጨንቅሃል፡፡ የስርዓቱ አበሳ ብዙ ነው፡፡ ስልጣኔ ባህል በሆነበት፣ ዓለም አቀፋዊነት እምነት በሆነበት፣ ዕውቀት የደግነትና የሩህሩህነት መገለጫ በሆነበት ዓለም ውስጥ የበኩላችንን እንዳናዋጣ ተብትቦ ይዞናል፡፡ ለዚህ ነው የጀመርነውን ትግል አፋፍመን Transform ከማድረግ ሌላ አማራጭ የለንም የምንለው!! … ጥያቄው የህልውና ጉዳይ ሆኗል፡፡ የመኖርና ያለመኖር፣ የነፃነትና የባርነት!!
***
ወደ ቀልዳችን ስንመለስ፣ ዳኛው የተከሳሹን ቃልና አድራሻ ፅፈው እንደጨረሱ፤ የተጎጂውን አድራሻ በቅፁ ላይ መመዝገብ ነበረባቸው፡፡ ሰውየው ደግሞ ኮማ ውስጥ በመሆኑ መናገርም ሆነ መስማት አይችልም፡፡ ስለዚህ የሚያውቁትን ዕውነት በፎርሙ ላይ አሰፈሩ፡፡
ስም፡ አይታወቅም
አድራሻ፡ ሆስፒታል
ዜግነት፡ ተላላፊ (transit) … በመኖርና ባለመኖር መካከል የሚገኝ - በማለት፡፡ … እንደ እኛ!!
ወዳጄ፡- “ራሳችንን በመሆን የምናገኘው እርካታ ሌላ ቦታ ፈልገን ከምናገኘው ደስታ ይበልጣል፡፡” (The happiness we receive from ourselves is greater than that which we obtain from our surroundings) የሚለን ታላቁ ሾፐን ሃወር ነው!! .. ቶማስ ካርላይል ደግሞ የግል ነፃነትን በራሱ እምነትና ሃሳብ እንዲህ ገልፆታል፡-
To be good is my religion,
All human beings are my brothers and sisters, whereever I can live in peace is my country!!
ሠላም!!

Read 1465 times