Saturday, 14 July 2018 12:20

ቡድን እና ህዝብ (እኔ እንዳስተዋልኩት)

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(3 votes)

 አንዳንድ ጊዜ፤ ከነጠላ እይታ የተሰናሰለ የሀሳብ ጋጋታ ሊከሰት ይችላል፡፡ … መጀመሪያ አንድ ነፍሳት መሬት ላይ አይቼ ነው ሀሳቡ የተጫረብኝ፡፡ ነፍሳቷ በፈረንጆቹ አጠራር “Kenyan fly” ተብላ ነው የምትጠራው፡፡ ስያሜዋን የነገረችኝ አንድ የቆዳ ሀኪም ናት፡፡ የዛሬ ዓመት አካባቢ ነፍሳቷ ጆሮዬ ስር በልታኝ አቁስላኝ ነበር፡፡ ነፍሳቷ በመሬት ላይ እየሄደች ክንፏን እያራገፈች ነው፡፡ በእግሬ ረግጬ በድጋሚ እንዳታቆስለኝ አደረግኋት፡፡ ቀጥሎ በእጄ አንስቼ አጠናሁዋት፡፡ ሳጠናት ቀለሟን ተመለከትኩ፡፡ ቀለሟ በደማቅ ብርቱካን አይነት ጀምሮ ወገቧ ላይ ሲደርስ በአረንጓዴ መቀነት ቀለም ይታሰርና ወደ ጭራዋ አካባቢ ደግሞ ተመልሳ፣ ብርቱካን አይነት ትሆናለች፡፡ ሶስቱን ቀለሞች ሳይ አንድ ባንዲራ ትዝ አለኝ፡፡ በቅርቡ አሸባሪ የሚል ፍረጃ ከተነሳላቸው ባንዲራዎች መሀል አንዱ ነው ትዝ ያለኝ፡፡ … ከዚህ ነጠላ ትዝታ ውስጥ ደግሞ ሌላ ትዝታ ተወለደ፡፡
በአዲስ አበባ ላይ ተጠርቶ በሚሊዮኖች የሚገመት ህዝብ የወጣበት የመስቀል አደባባዩ ትዕይንተ ህዝብ ነው በነፍሳቷ ቀለም አማካኝነት ወደ ሌላ የትዝታ ማህደር የጨመረኝ፡፡ ትዝ ይለኛል የህዝቡ ብዛት፡፡ ትዝ አለኝ ጨዋነቱ፡፡ ጨዋነቱ ትዝ ሲለኝ፣ “ኢትዮጵያዊ ጨዋነት” የሚለው ሀረግ ታወሰኝ፡፡ ሀሳቦች መፈጠር የጀመሩት ይሄኔ ነው፡፡ ከትንንሽ እይታዎች፣ ትዝታዎች ውስጥ ሀሳብ ጥያቄን ተመስሎ ሲፈጠር በቆምኩበት ሆኜ ተሰማኝ፡፡
ከዚህ በፊት በግለሰብ እንጂ በህዝብ ብዙ እምነት ያልነበረኝ ሰው ነበርኩኝ፡፡ ያስፈራኛል እንጂ አላምነውም ነበር፡፡ ምክኒያቱም ህዝብን አላውቀውም። ካለማወቄም የተነሳ እጠራጠረው ነበር፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰዎች ተሰብስበው ህዝብ አክለው ያየሁት፣ በዚህ ትዕይንተ ህዝብ ላይ ነው፡፡
ኳስ ሜዳ ላይ የእግር ኳስን ክለብ ለመደገፍ እስቴዲየም የሚገባ ብዙ ቁጥር ያለው የሰው ስብስብ “ህዝብ” ይባል ከነበረ … መስቀል አደባባይ የተሰበሰበው ምን ተብሎ ሊጠራ ነው? ብዬ ራሴን ጠየቅሁኝ፡፡
በዛ ላይ ክለብን መደገፍ ሀገራዊ ጉዳይን መደገፍ አይደለም፤ አውቃለሁኝ፡፡ የሰው ስብስቦች በህዝብ ስም የሚጠሩት ለአንዳች ጉዳይ ማስፈፀሚያ ነው። Collectives, mass, mob, herd… ወዘተ ተብሎ የሚጠራው ሰው ስብስብ፣ ህዝብ የሚባለውን ይገልፃል ወይንስ ራሱ በሰፊው ውስጥ ንዑስ ክፍል ሆኖ ይገልፃል?
እየጠየቅሁ ነው፡፡ ለማሰብ እየሞከርኩ ነው፡፡ … አይ ህዝብ፤ የሀገር መገለጫ ነው አልኩኝ፡፡ “ሀገር ያለ ህዝብ የለም” ሲሉ ከዚህ ቀደም እሰማለሁኝ፡፡ ተራ ስብከት እንጂ ተጨባጭ ነገር አይመስለኝም ነበር፡፡ ፈፅሞ ተሳስቻለሁ፡፡ ግን አይቼ ስለማላውቅ ነው፡፡ ማነፃፀሪያ አልነበረኝም፡፡
ግን አሁን ከተመለከትኩት ተጨባጭ ትዕይንተ ህዝብ ተነስቼ ማሰብ እችላለሁኝ፡፡ ተጨባጭ መረጃ አለኛ! … ህዝብ ይሄ ከሆነ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች በድምፅ ቆጠራ አገኘን የሚሉት ድምፅ የስብስብ (Collective) እንጂ የህዝብ አይደለም፡፡
ህዝብን የሚገዛው ምንድነው? ፍቅር ብዬ አልሸነግላችሁም፡፡ ፍቅር በጣም ጥልቅና አብስትራክት ቃል ነው፡፡ ሁሉም ከየሙያ ዘርፍ ከእየራሱ ቅንፍ እየተነሳ ወይንም እየተነዳ እንደ መሳሪያ ሊጠቀምበት የሚችል ቃል ነው፡፡ የሙዚቃ ፍቅር ህዝብን ይገዛል ግን እንደ መኖር ፍቅር አይሆንም፡፡ የሙዚቃ ፍቅር በህልውና መኖር ባልቻለ ህዝብ መሀል እንደ መሳሪያ ነው፡፡ ህልውናን እንደ ማስቀጠያ አማራጭ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል፡፡ “ሙዚቃ ህይወት ነው” የሚባለው፣ የሕይወት ፍቅር ቅድሚያ ባለበት ሁኔታ ነው፡፡ “የሀገር ፍቅር” ሀገር ህልውናውን በአብሮነት የማስቀጠያ ስፍራ እስከሆነ ድረስ ፍቅሩ የህዝብ ይሆናል፡፡ የህዝብ ፍላጎት ሰላም ብቻ ነው ማለትም ተመሳሳይ ጥቁምታ የሚሰጥ ነው፡፡ ሰላም በህልውና ለመቀጠል ቁልፍ ነገር መሆኑ፣ “ህዝብ” የተባለው ስብስብ ከማንም የበለጠ ይገባዋል፡፡
ህዝብ አይሳሳትም፡፡ ቡድን ሊሳሳት ይችላል፡፡ ግለሰብ ለሚከተለው ሀሳብ ሲል ሚዛኑን ወደ አንድ ሊያጋድል ይችላል፡፡ ለምቆምለት ሀሳብ እሞታለሁ ወይም እገድላለሁም ሊል ይችላል፡፡ ተሳስቶ ሌሎችን ሊያሳስት ወይም ሊያሳምንም ረጅም ርቀት ሊሄድ ይችላል፡፡ በህዝብ ውስጥ ያሉ ንዑስ ስብስቦችን በዚህ መንገድ በርዕዮተ አለም ወይም በእምነት አልያም በባህል መቆጣጠር ይቻላል፡፡ ህዝብን በአጠቃላይ ማሳሳት ወይም ማሳመን ግን አይቻልም፡፡ ህዝብ ጥቅሉ ነገር ነው፡፡ እውነት ህዝብ መሆኑን ለማረጋገጥ አንደኛው አማራጭ ትዕይንተ ህዝብ መጥራት ነው። ሌላኛው የህዝብን ቁጥር ወክሎ የሚያሳይ ውክልና በምርጫ ካርድ መልክ መሰብሰብ ነው፡፡ … የምርጫ ካርዱ ብዙ አስቸጋሪ ነገር እንዳለበት ከዚህ ቀደም በተከታታይ በተካሄደው ምርጫ አይተናል፡፡ መራጩ ተመራጩን አያገኝም ወይም ተመራጩ በመራጩ አይወከልም፡፡
አሁን ሳስብ እንደተገለፀልኝ ከሆነ፣ ህዝብን በአጠቃላይ አካትቶ የሚጨምር የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ሊኖር አይችልም፡፡ የህዝብ መሰረታዊ ፍላጎት በህይወት መቀጠል ነው፡፡ አምስት ሚሊዮን ህዝብ በአደባባይ ወጥቶ አንድ የእግር ኳስ ክለብን አይደግፍም፡፡ በቁንፅል አስተሳሰብ በእስቴዲየም አውድ ገብቶ የሚደግፈው ደጋፊ (mob) ነው፡፡ አንድ ዓይነት አርማና አንድ አይነት የድጋፍ መዝሙር ሊያሰማ ይችላል፤ መጠነኛው ስብስብ፡፡ እንደ ክለብ ነው፡፡ እንደ ፓርቲ ደጋፊ፡፡ በአንድ የእምነት አውድ ስር ለማምለክ እንደሚሰበሰብ ሀይማኖተኛ፡፡ በእነዚህ መጠነኛ ስብስቦች በእምነት የተመሳሰሉ ወይም በሁለት ፅንፍ እምነቶች ተቧድነው የሚነቃቀፉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ህዝብ ግን አይደሉም፡፡ ሀገር ተብለው በደፋር ትርፍ ፈላጊ ሲሰበኩ ሊውሉ ቢችሉም የተገለፀውን ናቸው  ማለት ግን አይደለም፡፡
በመስቀል አደባባይ የተሰበሰበው “ህዝብ” ውስጥ ብዙ ንዑስ ቡድኖች ነበሩ፡፡ በፌስቡክም ሆነ በሌላ የሀሳብ ማንሸራሸሪያ የማይግባቡ የነበሩ ሀሳቦች፣ በአካል ተክለ ቁመና ተወክለው ወደ አደባባይ ወጥተው ሲቆሙ ግን መቻቻልን አሳይተዋል፡፡ “ህልውና” (existance) ከሀሳብ (consciousness) እንደሚቀድም እንደ አንድ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችል እንደሆነ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ህዝብ ማለት በህልውና መቆየት የሚችል አካል ማለት ነው፡፡ በሀሳብ ባይስማማ እንኳን በአካል አንድ ላይ መቆየት እንደሚያዋጣ ያውቃል፡፡ ህዝብ በህልውና ለመቆየት የተሻለውን ሀሳብ ይደግፋል፡፡ የተሻለውን ሀሳብ በተሻለ አቀራረብ የሚነግረውን እንደ መሪ ይቆጥራል፡፡ ከልቡ ይደግፋል።
አንድ ሀይማኖትን የሚደግፍ ከማይደግፈው ጋር … ወይም አንድ ቋንቋ የሚናገር ከማይናገረው ጋር … የአንድ ሰንደቅ ቀለም የያዘው ሌላ ቀለም ይዞ ከወጣው ጋር ባይስማማ እንኳን መጣላት እንደማያዋጣ የሚያውቀው የሰውነት ስብስብ መገለጫ፣ ለእኔ “ህዝብ” ብዬ የምጠራው ነው ከእንግዲህ፡፡
በአንድ ሀገር ላይ በቡድኖች መንስኤነት የሚቀሰቀስ ግጭት ከፍ ወዳለ እልቂት ካመራ እኮ ህዝብ የሚባለው አካል ብዙውን ጊዜ መሰደድን ነው የሚመርጠው። ህዝብ በሰላም ነው መኖር የሚፈልገው፡፡ ሰላምን የሚሰጠውን አነፃፅሮ ይደግፋል፡፡ እውነተኛ ድጋፍ ከሆነ በአደባባይ ወጥቶ ቁጥሩን በተጨባጭ ያሳያል። ከዚህ ቀደም፤ መሪው ከህዝብ የመጣ መሆኑን በተለያየ ዘዴ አሳምኖ፣ ከዛ በቀጣይ ህዝብን ከሀገሩ እያጎሳቆለ የሚያሳድድ ሆኖ በተጨባጭ ተገኝቷል፡፡ ህዝብና ህዝብ በቀላል አይጠላላም፡፡ ቢጠላላ እንኳን በቀላሉ አይጋጭም፡፡ የሚጋጨው ቡድኑ ነው፡፡ ቡድኑ በህዝብ ስም፡፡ ቡድኑ “Collective” ነው፡፡ “ስብስብ” ህዝብ አይደለም፡፡ ስብስብ እምነት አለው፡፡ አላማ አለው፡፡ አላማውን ህዝብ ሊቀበልም ላይቀበልም ይችላል፡፡ የሚቀበለው የአላማው ደራሲ የወንዙ ልጅ ስለሆነ ከመሰላችሁ ተሳስታችኋል፡፡ የወንዝ ልጅነት በህዝብ ስፋት ሲታይ ጠባብ፣ ንዑስ፣ ቁንፅል ነው፡፡ ህዝብን የወንዝ ልጅ የሚያደርገው በህልውና መኖር የሚያስችለው ከባቢ ብቻ ነው፡፡ ይኼ ከባቢ መልክአ ምድርን ሊታከክ ይችላል፣ ሃይማኖትን ሊታከክ ይችላል፡፡ ባህልን ሊታከክ ይችላል፡፡ ወይም የዘር እና ዘረ - መል መወራረስን የሚያመለክት ከደም መዋለድ ሊሆን ይችላል፡፡ ሁሉም በጥልቅ ሆኖ የተሸመነ ሊሆን ይችላል፡፡ የሽመናው ጥበብ መሰረታዊው ጥለት ምንድነው? ከተባለ ግን እኔ የምመልሰው፣ “በህልውና መኖር መቻል” ብዬ ነው፡፡
ልክ የእግር ኳስ ጨዋታው ከህልውና በኋላ እንደሚመጣው፣ ህዝብም የሚገዛበትን ፅንሰ ሀሳብ የሚያፀድቀው ከህልውና በኋላ ነው፡፡ ሰፊውን በተለያየ የአመለካከት አንፃር የቆመ ቡድን ተቀብሎ በአንድ ህልውና ማቆየት የቻለ ፖለቲካ፣ የሀገር ወካይ ቢሆን አይገደኝም፡፡ ፖለቲካ ተሰርቶ እና ተባርኮ ከሲና ተራራ ወደ ህዝብ የሚወርድ ፅላት እንደሆነ እና ስለ እንከን አልባነቱ በአስፈለገው ምጡቅ መስተሀይል ሊያስመሰክር ይችላል፡፡ ዲሞክራሲ ወይንም ፌዴራሊዝም … አልያም ሌላ የውል ማሰሪያ የዳቦ ስም ሊወጣለት ይችላል፡፡ በተቻለ መጠን በሰላምና ህልውና ብዙሀኑን እንደ አንፃራዊነቱ የሚያካትት ከሆነ ህዝብ ይቀበላል፡፡ ጥቂቶች በውሉ አስተሳሰብ አምነው የተጠመቁና ለማንቃትም የተደራጁ ሊሆኑ ይችላሉ። ህዝብ የሚፈልገው በህልውና መቆየትን ነው፡፡ በህልውና ለመቆየት ብልሀቱን ከራሱ ነዋሪው የበለጠ አቃለሁ የሚል ይመጣል፡፡ ቡድን ሆኖ ይመጣል። መሳሪያ ይዞ ይመጣል፡፡ ፅላት ይዞ ይመጣል። ህዝብ በህልውና መቆየት እስከቻለ መውጣትና መግባት እስከቻለ “አውቃለሁ ባይ”ን አይቃወምም። ህልውናው ባለመሆን ሊጣስ መሆኑ በደመነፍስ ሲገባው ግን ምላሽ ይሰጣል፡፡ ይሰደዳል፡፡ ይጎሳቆላል። ያደፍጣል፡፡ በህልውና ለመቀጠል የሚቻለውን ሁሉ ያደርጋል፡፡ በህልውና ለመቀጠል ያለው ብቸኛ አማራጭ፣ ህልውናውን አደጋ ውስጥ የተከተተበትን አካል ማስወገድ እንደሆነ የሚሰብክ ቡድን ከተነሳም ለህልውናው ሲል ይደግፋል፡፡
የደገፈውን ምክኒያት ወደ ግብ የሚያደርሱ ልጆቹን ከጉያው አውጥቶ፣ አዲስ ሀሳብ ይዞ ለመጣው የለውጥ አመንጪ ቡድን ይሰጣል፡፡ ግን ህዝብ በአጠቃላይ ተነስቶ ገጪውን ለመጋጨት አይወጣም፡፡ ገጪን መልሶ መግጨት በህልውና በቀጣይ መቆየት ለሚፈልግ አዋጪ እንዳልሆነ ያውቃል፡፡ ህዝብ ግራ ጉንጩን ሲመቱን ቀኙን ይሰጣል፡፡ ወደ መንግስተ ሰማይ ለመግባት ሳይሆን፣ በህልውና ለመቆየት ሲል ነው፡፡ ህዝብ ታጋሽ ነው፡፡ ግለሰብ ወይም ቡድን ትዕግስቱ አፍንጫው ላይ ሊሆን ይችላል፡፡ አፍንጫ ለመምታትም የግለሰብና ቡድን አፍንጫ የተሻለ ግልፅ ቦታ ላይ ተቀምጦ የሚገኝ ነው፡፡ እምነቱም ተክለ ሰብዕናውም በቀላሉ ይታያል፤ ይገኛል፡፡
ህዝብ ግን እሩቅ ነው፡፡ ቡድኖችና ግለሰቦች ያልፋሉ - “ሀገር” እና ህዝብ ግን ይቀጥላል” የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ ወይም ለዚህ ይመስለኛል፡፡ በህልውና የመቀጠያ ብልሀቶቹን በደንብ የሚያውቅ ህዝብን … በቀላሉ ለመበጥበጥ አይቻልም፡፡ የብዙ ዘመን ታሪክ ያለው መሆኑ ለእኔ የሚያስወታውሰኝ የብዙ ትዕግስትና የመጠነኛ ወሳኝ እርምጃዎች ባለቤት መሆኑን ነው፡፡ ህዝባዊ ንቅናቄ ከፕሮፓጋንዳና አስመሳይ ማደራጀቶች ባለፈ የማይከሰተው ህዝብ በቀላሉ ስለማይነቀነቅም ሆነ ስለማይነቃነቅ ነው፡፡
እግዚአብሔር ፍቅር ከሆነ፤ ህዝብ የእግዚአብሔር ፍቅር መገለጫ ነው፡፡ ሰፊው ህዝብ ከእነ ብዙ ቻይ እና ብዙ አቀፍ ውጥንቅጡ፡፡ የሰፊውን ህዝብ ውጥንቅጥ “ውበት” ብሎ በመግለፅ ለመደለል ለሚፈልጉ መብታቸው የተጠበቀ ነው፡፡ እኔ ግን ትኩረቴ አብሮ መኖርና በህልውና መቆየት ላይ ነው፡፡ ‹ውበት› ያለው ህዝብ፣ ውበቱን ይዞ በህልውና መቆየት ካልቻለ … የውበቱ ታሪክ የሚጠቅመው ለአንትሮፖሎጂስቶች ወይንም ታሪክ ዘካሪዎች ብቻ ነው፡፡

Read 1104 times