Saturday, 14 July 2018 12:17

የጓደኛዬ ምልጃ!

Written by  አብይ ተስፋዬ አሳልፍ - (አተአ)
Rate this item
(8 votes)

ወቅትም ከወራት ፍቅር ይይዘዋል መሰለኝ፡፡ ልክ ሰኔ መግቢያ ላይ ያገኛትን ያረጀች በጋ የምትባል ፍቅረኛ፣ ክረምት የሚሉት ጉብል ጣቶቿን ይዞ ሙጭጭ፣ እኝኝ ይላል፡፡ መለያየት የጠላ ይመስል … እቀፊኝ ይላታል፣ ታቅፈዋለች፡፡ ማቀፍ ብቻም ሳይሆን አንጠልጥላ ታዝለዋለች፡፡ ነሐሴ ላይ ያገባታል። መስከረም ብቅ ስትል ግን ከጫጉላው ማግስት ጀምሮ ክረምት ሙሽራውን ይዘነጋታል፡፡ እንዲያውም አውርጂኝ እያለ ይነጫነጭና ይርቃል፡፡ በቃ ተይኝ ይላታል፡፡ መጸው ይመጣና የነሀሴን እጆች መጨበጥ፣ የክረምትን ጉንጮች መሳም ያዘወትራል፡፡ በጋ ታብዳለች፡፡ እዬዬው ይጀምራል፡፡
እናም ገና አልመጣም ያልነው ክረምት እኛ ሰፈር ከእንደገና በጉልበት ገብቷል፡፡  አዲስ ፍቅር ስለሆነ ሙዝዝ ይላል፡፡ አሁን እዘይኝ ያለው ክረምት ግን በኋላ ተይኝ ማለቱ አይቀርም፡፡ በዝናቡ እየተደበደብኩ ከሰፈር እንደወጣሁ፣ ወዳጄ ጋሙዱ መዞሪያ ካፌ በረንዳ ላይ ቆሞ ጠበቀኝ፡፡ ከዝናቡ ለአፍታም ቢሆን ለመጠለልና ሰላም ልለው ወደዚያው አመራሁ፡፡
‹‹… አልዓዛር እፈልግሃለሁ›› አለኝና እጄን ጎትቶ ቁጭ እንዳልን … ‹‹በለሊት ወጥቼ አንተን ነበር የምጠብቀው፡፡ እባክህ ይቺን ልጅ አነጋግርልኝ፤ ከቤት ከወጣች አራት ቀን አለፋት፡፡ እንድትመለስ እርዳኝ፡፡ አንድ በለኝ እንጂ፡፡ ዛሬውኑ አንድ ካላልከኝ አይመሽልኝም፡፡ ስራ መስራት አይሆንልኝም፡፡ አንተ ሞክረህ እምቢ፣ አሻፈረኝ ካለች ግን አናቷን ብዬ ገላግያት ነው ራሴን የማጠፋው  … ›› እያለ ዛቻና ልመናውን ያዘንበው ጀመር፡፡
‹‹ኸረ ተው አትዛት፡፡ መግደልን ምን አመጣው፡፡ አሁን ይህ ፍቅር ነው ወይስ ማስገደድ!›› አልኩ ግራ እየገባኝ፡፡
ጉሮሮው ላይ እየተናነቀው ጮክ ብሎ፤ ‹‹ታውቃለህ አይደል! እወዳታለሁ!››
ጋሙዱ የሚተዳደረው እንጦጦ አቀበት ላይ ድንጋይ ፈልጦ በመሸጥ ነው፡፡ ጋሙዱ ከዚህ በኋላ ሀያ አመት ከኖረ የእንጦጦ ዳገት ሜዳ ይሆናል ብዬ እጠረጥራለሁ፡፡ ሰውነቱ አለት የሚያክል፣ አለት ፈላጭ ነው፡፡ ሚስቱ ደግሞ የጠጅ ቤት አስተናጋጅ  ጉብል፡፡ የምንተዋወቀውም ‹ገደል ግቡ!› ጠጅ ቤት ነው፡፡
ፊቱን ትኩር ብዬ አጠናሁት፣ እያለቀሰ ይሁን አይሁን ማወቅ አልቻልኩም፡፡ ልጥልጥ ጥቁር ፊቱ በዝናቡ ስለታጠበ የተወለወለ ጀበና መስሏል፡፡ አልቅሶ ከሆነ፤ ዝናቡና እንባው ተቀላቅሏል ማለት ነው፡፡ ጥርሱን ነክሷል፡፡ ‹የዛተውን አያደርግም ብሎ መጠበቅ ሞኝነት ነው!› ስል አስባለሁ፡፡ ቢሆንም ግን ያፈቅራታል፡፡ ይህንን እኔም አውቃለሁ፡፡
የካፌው አስተናጋጅ የተጨማደደ ፊቱን በመንጋጭላዎች እንቅስቃሴ ለማላላት እየሞከረ መጣና ከፊታችን ቆሞ ‹ምን ልታዘዝ!› አለ፡፡ ጋሙዱ ቀና ብሎ በግልምጫ (ግንባሩን ቆጣጥሮ!) ሲያስተውለው እጁ ላይ ያንጠለጠላትን ፎጣ እያወዛወዘ ጠፋ፡፡ እናም ጥግ አካባቢ ቆሞ በፍርሃትና በሾለከች ፈገግታ መሃል ሆኖ በቆረጣ ያስተውለን ጀመር፡፡
ጋሙዱ በንዴት እንዲህ አለ፤ ‹‹ ምናባቱ በጠዋት ይነጅሰኛል፡፡ ስራ አጥቼ ነው አስር ብር ከፍዬ ሻይ የምጠጣው! አያስብም’ንዴ፡፡ ከንቱ!››
ፈገግታዬን መቆጣጠር አልቻልኩም፡፡ ገና በማለዳው ማን ይጨቃጨቀዋል፡፡ ሁሉም ይፈሩታል። ‹‹ወተት እንጠጣ፣ የዚህ ቤት ወተት ቆንጆ ነው፣ ሒሳቡን እኔ እከፍላለሁ›› አልኩ እየሳቅሁ፡፡
‹‹… አይ ቢሆንም፣ መቼም እንጠጣ ካልክ እሺ፤ አንተን ስለማከብርህ እንጠጣ! እነዚህ የሚያስከፍሉት ግን ልክ አይደለም ታውቃለህ!›› ረዣዥም ከንፈሮቹን ቁልቁል እየለጠጠ ፈገገ፡፡ ቀይ ድድና ነጭ ጥርስ፣ ከጥቁር ፊት ጋር፡፡ ስዕል ነው የሚመስለው፡፡ ደግሞ ያምራል፡፡
ወተቱን አዘዝኩና፤ ‹‹ደግሞ ምን ተፈጠረ እስኪ አስረዳኝ …›› አልኩት፡፡ ከሚስቱ ጋር በምን እንደተጣሉ ግራ ገብቶኝ ፡፡
***
እንደ ሞሪስ ‹ኢንቲሜት ቢሄቪየር› መፅሐፍ፣ ሰዎች የሚያልፏቸው ሶስት መሰረታዊ የለውጥ ደረጃዎች አሉ፡፡ እነርሱም፡-  ‹እቀፉኝ፣ አውርዱኝ እና በቃ ተውኝ!› ናቸው፡፡
ጨቅላ እያለን ሁላችንም እቀፉኝ እያልን ስንጮህ ነበር የኖርነው፡፡ እናም ሲያቅፉን ብቻ ነበር ሰላም የሚወርደው፡፡ ለጥቆ ትንሽ መንቀሳቀስ ስንጀምር፣ አውርዱኝ ማለት ይመጣል፡፡ መዳህ ከተጀመረ በኋላ ሁሌ አውርዱኝ ነው፡፡ ከሁሉ ነገር ነፃ ሆኖ ለመንቀሳቀስ መሞከር፡፡ ከነዚህ የሚለጥቀው ሶስተኛው ደረጃ ጉርምስና ከመጣ በኋላ የሚመጣው ነው፡፡ ለምንጠየቀው የምንሰጠው መልስ ሁሉ ተውኝ ይሆናል፡፡ ሁሉን እኔ እችላለሁና ተውኝ፡፡
እነዚህ መደበኛና የሚጠበቁ ነገሮች ናቸው፡፡ በሁሉም የህይወት መንገዶች ይታያሉ፡፡ በሰው ልጅ የዕድገት መንገድ፣ በፍቅር ህይወት፣ በትዳር መንገድ፣ በጓደኝነት …. ሁሉ አሉ፡፡ የሚገርመው ግን ብዙ ግዜ ተውኝ ካልን በኋላ መልሰን እቀፉኝ ልንል መቻላችን ነው፡፡
ስታፈቅር እቀፊኝ ትላታለህ፣ ሲሰለችህ አውርጂኝ፤ ከዚያ ደግሞ ተይኝ፡፡ ከዚህ ሁሉ በኋላ ግን ድንገት ሲያገረሽብህ መልሰህ እቀፊኝ እያልክ፣ እዬዬ ልትል ትችላለህ፡፡ እናም ነገሩ ሁሉ እንዲያው ይቀጥላል፡፡ … እቀፊኝ ውዴ፣ አውርጂኝ ፣ ተይኝ አልኩ’ኮ! (ብለህ ስታበቃ መልሰህ ‹እባክሽ እቀፊኝ› ትላለህ ወይም አውርዱኝ ብለህ  በዚያው ትጠፋለህ)
***
ጋሙዱም ‹አውርጂኝ ብሎ ወርዶ ሲያበቃ፣ ተጸጽቶ እቀፊኝ እያላት ነው ማለት ነው!› … እያልኩ ሳሰላስል የተጋጩበትን ጉዳይ እንዲህ ሲል አስረዳኝ፤
‹‹ባለፈው ለታ! ለሆነ ነገር ገንዘብ ስትጠይቀኝ በሰዓቱ አልነበረኝም፡፡ ምናባቷ እሷ አትሰራም እንዴ፡፡ እኔ ለሁሉ ነገር ከየት አመጣለሁ፡፡ እያልኩ እጮሃለሁ … ለካ እናቷን አሞባት ነበር፡፡ በአካል አላውቃቸውምኮ! ብቻ ሳሪስ አካባቢ ይኖራሉ ትለኛለች፡፡ ልታስተዋውቀኝ አልፈለገችም ነበር፡፡ ያው ‹ጠፍቼ ነው እዚህ የምኖረው፣ እናቴ እኔ ምን እንደምሰራ አታውቅም!› ትለኛለች፡፡ ግን አንዳንዴ ያው ጨላው ሲገኝ በሰው ትልክላቸዋለች፡፡
‹‹በማለዳ ተነስቼ ሳንቲም ልፈላልግ ስወጣ ዝናብ ይጥላል፤ ትንሽ እንደሮጥኩ አሲምባ ፋርማሲ አጠገብ ተጠለልኩ፡፡ ማለዳ ስለሆነ የሚተላለፍ ሰው ብዙም የለም፣ በአካባቢው የሚታዩት አንዲት አሮጊት ለማኝ ብቻ ናቸው፡፡ ከፋርማሲው በር አጠገብ ተቀምጠው፣  ጨርቃቸውን መሬት ላይ ያመቻቻሉ፡፡ አቅራቢያቸው ስለቆምኩ የሚሰሩትን አያለሁ፡፡ ፋርማሲው አልተከፈተም፡፡ ዘበኛው እንኳ ከሞቀ መኝታው አልተነሳም፡፡ ዝናቡ ትንሽ ማባራት ሲጀምር፣ ሴትየዋ አንድ እዳፊ ጨርቅ አነጠፉ፡፡ ከዚያ ከደረታችው ውስጥ በሳንቲም የተወጠረ ከረጢት አወጡና ጥቂቱን ከጨርቁ ላይ በታተኑ፡፡ የሚሰሩት ነገርና የያዙት ገንዘብ ብዛት ስላስገረመኝ ጠጋ አልኳቸው፡፡ እስከዚያ ሰዓት አላዩኝ ኖሯል፣ ደነገጡና እንዲህ አሉኝ፤
‹‹…ደግሞ እዚህም መጣችሁብኝ!…›› … ጥርስ የሌለው ጉንጫቸው እንደ ጨርቅ ይተጣጠፋል፡፡ ሲያዩኝ ፈርተውኛል፡፡
‹‹...ምን ማለትሽ ነው…›› አልኩ ተናድጄ፡፡ አለም ሁሉ አስጠልቶኛል፤ ከቤትም ከደጅም ጭቅጭቅ፡፡ የያዙትን ገንዘብ ለመንጠቅ ፈልጌ ነበር፡፡ የሚያየኝ ሰው አልነበረም፡፡ ገንዘብ ደግሞ በጣም አስፈልጎኛል፡፡
‹‹…ትናንት እዚሁ ሰፈር ነበር የዋልኩት ግን ማንም አልከለከለኝም፡፡ የደጋጎች ሰፈር ነው፤ ሰዎቹም ይሰጣሉ፡፡ ስለዚህ እኔም የቦታውን እንደሌላው ሰፈር እየከፈልኩ መክረም እችላለሁ፡፡ እባክህ ልጄ ተወኝ!›› … ግራ ገባኝ፡፡ እርሳቸው ቀጠሉ … ‹‹... ወደ ለገሃር ስሰራ ለሁለት ሳምንት አምሳ ብር፣ ለወር መቶ ብር ነው ለቦታው የምከፍለው፡፡ እናንተ ስንት ነው የምታስከፍሉኝ ፣ ልጄ እዘንልኝ አሮጊት ነኝ፡፡ ቀንስልኝና ልክፈል!…›› አሉኝ፡፡ ፈገግ አልኩ፡፡
‹‹...እዚህ ሰፈር ብዙ ገንዘብ ስለሚገኝ ለሁለት ሳምንት መቶ ብር ነው፤ ሳንቲም አይቀንስም።›› አልኳቸው በልበሙሉነት፡፡ ‹‹ከከፈልሽ በነፃነት መስራት ትችያለሽ፤ አለበለዚያ ጥበቃ አናረግልሽም። የትናንቱን ምረንሻል! ›› ቃላቱ ከየት እንደመጣልኝ አላወኩም፡፡ በአንዴ ሌላ ሰው የሆንኩ መሰለኝ! ያላሰብኩት ገንዘብ ደግሞ ከደጄ ቆሞ እያንኳኳ ነው፡፡
ከተቆጣጠረው ከረጢት በሚንቀጠቀጥ ቀጫጫ እጃቸው መቶ ብር አውጥተው ሲከፍሉኝ አላመንኩም። በጨመርኩ የሚል ሀሳብ ብልጭ አለብኝ፡፡ ተቀበልኩና ወደ ቤቴ በፍጥነት ሄድኩ፤ እናም ለሚስቴ ወርውሬላት ጠፋሁ፡፡ ፀፀት ቢቆጠቁጠኝም ደስ ብሎኝ ነበር፡፡ ለካ እንደዚህም መስራት ይቻላል ብዬ እያመንኩ ስራ ፍለጋ ተንቀሳቀስኩ፡፡ ማታ ስመለስ ሚስቴ በፈገግታ ነበር የተቀበለችኝ፡፡
ደስ እያለት እንዲህ አለችኝ … ‹‹…እናቴን ጤና ጣቢያ ወስጄ አሳከምኩ፤ አመሰግናለሁ ጋሙድዬ፡፡ ትንሽ የጎደለኝ ለመድሃኒት መግዣ ነው፣ እሱንም ነገ እንፈላልጋለን፡፡ አሁን ቡና እያፈላሁ ነው!.. ና! ግባ ትመርቅሃለች፣ በዚያውም ትተዋወቃታለህ!…›› … ለካስ እናቷን እቤት አምጥታቸው ነበር፡፡
ደስ እያለኝ ገባሁ፤ እናም መደብ ላይ የታጋደሙትን እናት ሳይ፣ ድንጋጤዬን መደበቅ አልቻልኩም፡፡ አፈጠጥኩ፡፡ እኒያ የሚለምኑት እናት ነበሩ፡፡ ለካስ ልጃቸውን ፍለጋ ነበር እኛ ሰፈር የሚንከራተቱት፡፡ የሚተዳደሩትም በልመና ነበር፡፡
ሲያዩኝ ደንግጠው ከተጋደሙበት ለመነሳት እየታገሉ፤ ‹‹…ደግሞ ምን አረኩ ልጄ፣ የሁለት ሳምንቱን ከፍዬ የለምን!…›› አይሉኝም፡፡ ደንግጬ ተመልሼ ጠፋሁ፡፡ እናም ገደልግቡ ሄጄ ጠጄን ስልፍ አመሸሁና ሰክሬ ገባሁ፡፡
ቤት ስገባ ሚስቴና እናቷ ከቤት አልነበሩም፡፡ ትታኝ ሄደች፣ በርግጥ አጥፍቻለሁ ግን ይቅር የማይባል ነገር አለ’ንዴ! ያው መቼም ለእርሳቸው ብዬ እኮ ነው! … ደግሞስ ለብዙ ግዜ ደብቃኝ ባትኖር መቼ እሳሳት ነበር፤ ብተዋወቃቸው ኖሮ አልሳሳትም ነበር››
የማወቅና ያለማወቅ፣ ቤተሰብ ወይም ዘመድ መሆንና ያለመሆን አልነበረም፡፡ ነገሩ የአመለካከትና የተሰራበት ነገር ውጤት ነው፡፡ መስረቅ የለመደ ይሰርቃል፣ መንጠልጠል የለመደ ይንጠለጠላል፣ መታዘል የሚፈልግ መውረድ አይፈቅድም። ስታወርደው እዘለኝ እያለ ያለቃቅሳል፡፡ ከፊቴ የተቀመጠውን ወተት እያማሰልኩ ሰማሁትና አንስቼ መጠጣት ጀመርኩ፡፡ እየገረመኝ፡፡ ጋሙዱን አውቀዋለሁ፣ ምናልባት ዱርዬ ቢሆንም አይዋሽም፡፡ በሶስት ጉንጭ ጨልጦ ወተቷን አጣጥሞ ሲያበቃ፣ ምን እንደምለው ለመስማት መቁነጥነጥ ጀመረ፡፡
***
እኔ ዝም አልኩ፣ አሁን ታዲያ ይህ ምንድነው! እቀፉኝ ፣ አውርዱኝ ወይስ ተውኝ፡፡ የለም … የለም … ይህ እንኳ ምድቡ ሌላ ነው፡፡ ይህንኑ እያሰላሰልኩ የዝናቡ ነጠብጣብ፣ አስፋልቱ ላይ ሲፈጠፈጥ አስተውላለሁ፡፡ እያንዳንዱ የዝናቡ ሰበዝ፣ ከአስፋልቱ ላይ ይፈጠፈጥና በጋራ ተደምሮ ቁልቁል ጎርፍ ሆኖ ይፈስሳል፡፡
‹‹…እና  … እባክህ አስታርቀኝ፡፡ ያው ታውቃለህ አንተን ነው የምታከብረው፡፡ ለአንተ ነው እሺ የምትለው!›› ሲል አከለበት፡፡ በግማሽ ልቤ እየሰማሁ ነበር፡፡
‹‹…እሺ›› አልኩ በለሆሳስ … ‹‹እሞክራለሁ!…››
ስድስት ሰዓት ላይ ወደምትገኝበት ሊወስደኝና ላናግርለት ተስማምተን ተሰናበትኩትና በዝናቡ መንገዴን ቀጠልኩ፡፡ ሆሆይ፤ ነገሩ እየገረመኝ ነበር። እናም እንዴት ላስታርቀው እንደምችል፣ እንዴት ላሳምናት እንደምችል፣ እንዴት እዝነት ልታረግለት እንደምትችል፣ ልቧን የሚያራራትን ብልጠቶች እያሰላሰልኩ፣ ደግሞ በልቤ በሰማሁት ነገር ላለመገረምም እየተጋሁ፣ ዝናቡ ቀስ እያለ እያረሰረሰኝ ወጥቼ ተጓዝኩ፡፡ አይ ህይወት…!
ፍቅርና ርህራሄ ለማድረግ ራስን በሌላኛው ቦታ አድርጎ ማሰብ ነው፡፡ ራሴን በዚያ ምስኪን ቦታ ባደርገው ምናልባት ምክንያትና እዝነት ይሆንልኛል።  በእርሱ ጫማ ለመቆም መመከር አለብኝ፣ ያን ግዜ ይቅርታን እንደምን እንደሻተ አውቃለሁ! ካለበለዚያ ጉዳዩስ ይቅርታ አያባብልም ነበር፡፡ አሁን እርሷ ምን ይሰማት ይሆን! መልሼ ላሳዝላት ነውና ማሰብ ነበረብኝ፡፡ ህይወት ነውና ነገሩ ሁሉ እንዲያ ነው። እቀፉኝና አንጠልጥሉኝ፣ አቅብጡኝና አጫውቱኝ፣ አውርዱኝና ተውኝ!!  በየተራ ይሆናል፡፡

Read 3654 times