Saturday, 14 July 2018 12:10

ሀገር በቀል አዲሱ የኢትዮጵያ ርዕዮተ ዓለም

Written by  ዶ/ር ዘላለም እሸቴ
Rate this item
(11 votes)

  ፍቅራቸው የነካው ሺህ ዓመት ንገሱ ሲላቸው፤ ሌላው እንዴት መንግስት ይሸጋገራል ብሎ ሲያወጣና ሲያወርድ፤  ሌላኛው ደግሞ አምባገነን ስርዓት እየመጣ ነው ብሎ ሲቃወም ይታያል። ለማያስተውል ሰው፤ የዶ/ር ዐቢይ መንግስት ወዴት ይሄድ ይሆን ብሎ ግራ ሊገባው ይችላል። ለእርሳቸው በቂ ጊዜ ሰጥተን ተልዕኳቸውን በሚመጥን መልኩ እንዲመሩን ዕድል ልንሰጥ ይገባናል፡፡ ይህ የእርሳቸው አመራር፣ የለመድነው ፍሬ አልባ የሽግግር መንግስት ሲባል ያየነው ዓይነት አይደለም። የፅሁፌ ጭብጥ ሀሳብ፤ ይህ የእርሳቸው መንግስት ያልነበረ፥ ወደፊትም ሊኖር የማይችል፤ በዓይነቱ በዓለም የመጀመሪያው የሆነ የአዋላጅ መንግስት ስርዓት እንደሚሆን ላስረዳ እሞክራለሁ። ከዚያ በሁዋላ የሐቅ ምርጫ ዳኛ ይሆንልናል። ዶ/ር ዐቢይ፤ አንድ መሪ በስልጣን ላይ የሚቆይበት ጊዜ ከሁለት ምርጫ በላይ መሆን የለበትም ያሉት፣ ያኔ ህግ ስለሚሆን ሀሳብ አይግባን።
የዲሞክራሲ ስርዓት አብዛኛው ሰው የመረጠውን መንግስት ይሰጠናል። ይህ ግን በራሱ መልካም መንግስት ያመጣል ማለት አይደለም። በዲሞክራሲ እንደ ምሳሌ የምትነሳው አሜሪካ፤ በጥቂት ቁጥር ልዩነት አንዴ ዲሞክራቲክ ፓርቲ አለያም ደግሞ ሪፐብሊካን ፓርቲ እየተቀያየሩ የሚነግሱባት ሀገር ናት። ሶስተኛ አማራጭ ፓርቲ እስካሁን አቅም አግኝቶ አያውቅም። ስለዚህም የሚመረጠው መንግስት ባብዛኛው ግማሹ ሕዝብ ያልመረጠው ነው። አንዱ ፓርቲ የገነባውን አንዱ እያፈረሰና እርስ በርስ እየተናቆረ ዲሞክራሲ በሀገረ አሜሪካ ይከናወናል። በዲሞክራሲ ጀምረው በአምባገነንነትም የጨረሱ እንደነ ቱርክ ያሉ ሀገራትም አሉ። ስለዚህ ዲሞክራሲ የሚባለው ጉዳይ ጅማሬ ይሆን እንደሆነ ነው እንጂ፤ በራሱ መድሃኒት አይደለም። ስለዚህ ከምናውቀው ዲሞክራሲ የተሻለ ራዕይ ይኖረን ዘንድ ያስፈልጋል። ለዚያ ደግሞ ኢትዮጵያ መንገድ የጀመረች ትመስላለች።
ያም ሆነ ይህ፥ ከዲሞክራሲ የበለጠ ስርዓት ዓለም ልታመጣ አልቻለችምና፤ የሁሉም ተስፋ በዲሞክራሲ መንግስትን መመስረት ሆኗል። ዲሞክራሲን ያልተለማመዱ እንደ እኛ ያሉ ሀገሮች ደግሞ፤ ከአምባገነንነት ስርዓት ወደዚህ የዲሞክራሲ ስርዓት ውስጥ ለመግባት እጅግ አዳጋች ሆኖባቸዋል። ይሄውና የንጉስ ሃይለስላሴን ስርዓት ወደ ዲሞክራሲ ለመለወጥ አርባ አራት ዓመታት ብናስቆጥርም ገና ፈቀቅ አላልንም። እንደ ኤሊ በዲሞክራሲ መንገድ ላይ ከምንቀራፈፍ፤ በእመርታ አዲስ ኢትዮጵያዊ የሆነ የመደመር ዲሞክራሲ እንዲወለድና እንዲጎለብት፤ አምላክ በዲሞክራሲ ምርጫ ወይም በዲሞክራሲ ሽግግር መንግስት አላስጀመረንም። ከዚያ ይልቅ የኢትዮጵያ አምላክ እጅ ያለበትና፤ ኢትዮጵያን ለማሻገር መለኮታዊ ተልዕኮ ጥሪ ያነገበ አዋላጅ መሪ እንደ ስጦታ ሰጥቶናል። እስከ ዛሬ ሞክረን ያልተሳካልንን አስተሳሰብ ጥለን፤ ተዐምራዊ ሽግግር ምን እንደሚመስል እንመልከት።
አዋላጅ መሪ
የሕዝብ የትግል ውጤት መንግስት እንዲቀየር ምክንያት እየሆነ፣ ከአንድም ሁለት ሦስቴ በአመፅ መሪዎች ተቀያይረው፣ ዛሬ ላይ ደርሰናል። ግን ለመጀመሪያ ጊዜ በሕዝብ ፀሎት፣ ውጤት አዋላጅ መሪ አግኝተናል። ዛሬ ለዶ/ር ዐቢይ አህመድ ያለንን ፍቅርና አክብሮት ያገኘነው በዲሞክራሲ ምርጫ  ሳይሆን በአምላክ ቸርነት ያገኘነው ዕድል ነው። ይህም ስጦታ ለአጭር ጊዜ (ለሽግግር) ብቻ ስለሆነ ስጦታው እጅግ ክቡር እንዲሆን ያልቀዋል፥ ብርቅዬም ያደርገዋል። እኚህም መሪ ይቅርታና ፍቅርን መሪ ቃላቸው አድርገው፤ የመደመርን ርዕዮተ ዓለም ፈጥረው፤ ሕዝብን ወደ አንድ ሀሳብ አምጥተዋል። የሕዝብን ልብ በፍቅር ገንዘባቸው አድርገዋል። ምድር እፎይ ብላለች። ተስፋና ደስታ ደንበኛችን ሆነዋል። ቆም ብለን ይህ የሆነው ነገር ከላይ የፈጣሪ ስጦታ ነው እያልን፤ ግን አሁንም ቸኩለን ሽግግር መንግስት ምናምን ስንል ይገርማል። የሽግግር መንግስት ሀሳብ ደካማነትን ከዶ/ር አብይ አመራር ጋር መደመር በሚለው ፅሁፌ ስለገለፅኩት እዚህ አልደግመውም። አሁን ላነሳው የፈለኩት፤ አሮጌ አስተሳሰብ እያስተናገድን በደካማ አስተሳሰብ ከምናነክስ፤ በአዲስ መንፈስ እንደተነቃቃን ሁሉ፤ የወደፊት መንገዳችንም በአዲስ አካሄድ እንዲሆን እንድንተጋ ነው። የዛሬዋን ኢትዮጵያ የሚመጥናት ሂደት፤ ከአዋላጅ መሪ ወደ አዋላጅ መንግስት መሸጋገር ነው። ስለ አዋላጅ መንግስት የምናወራው፤ አዋላጅ መሪ በማግኘት ስለታደልን ብቻ ነው። በሕዝብ ምርጫ መንግስት እስኪመሰረት ድረስ፤ ለዚህ ዓላማ ሃላፊነት የሚወስደው ይህ አዋላጅ መንግስት ነው።
አዋላጅ መንግስት
በቂ ጊዜ ተስጥቷቸው ሲያበቃ ምርጫ እስኪደረግ ድረስ፤ የዶ/ር ዐቢይ መንግስት ዓላማ ሊሆን የሚገባው፥ ሌሎችንም አዋላጅነትን አጥምቀውና ተባባሪ አዋላጆችን አሳትፈው፤ አዋላጅ መንግስት ሂደት ውስጥ መግባት ነው። ይህም አዋላጅ መንግስት፤ የዲሞክራሲ ስርዓት ዕመርታዊ እድገት ኖሮት፥ ምርጫ ሲደረግ ምዕራባውያኑን የሚያስንቅ አዲስ ዲሞክራሲያዊ አካሄድ በማስኬድ፤ ራሱን በመደመር ፍቅር ዲሞክራሲያዊ መንግስት እንዲተካ የሚያደርግ ነው። ለዚህም ስኬት መከላከያው፥ ዳኛው፥ ሚዲያው ለሕዝብ የቆመ ገለልተኛ እንዲሆን ስራ መሰራት አለበት። ለሐቅ ምርጫ መገለጥ መሠረት የሚሆኑት ሁሉ ስፍራቸውን መያዝ አለባቸው። ለዚህም ዶ/ር ዐቢይ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በማሳተፍ፤ የዲሞክራሲ የጀርባ አጥንት የሆኑትን ተቋማት መገንባት አለባቸው። ለዚህም ዶ/ር መረራ ጉዲናን ማሳተፋቸው እንደ ጥሩ ጅማሬ አብነት ይወሰዳል። ከዚህም ጋር ለነገ ይደር የማይባለው የሀገር ልማት እጅ ለእጅ ተያይዞ መሰራት አለበት። ለዚህም ዲያስፖራው ሀገሩን እንዲያለማ ያቀረቡት ጥሪ እንደ አብነት መጠቀስ ይችላል። ያገባኛል የሚሉት የሀገር ልጆች ሁሉ ሀገር ቤት ገብተው አዋላጅነትን መወጣት ይኖርባቸዋል። ይህ የዶ/ር ዐቢይ አዋላጅ መንግስት፤ ለሽግግር እንዲሆን ብቻ ተብሎ ከሰማይ የተሰጠን ነውና፥ በዓይነቱ በዓለም የመጀመሪያ ስለሆነ፤ ከሌላ ሀገር እየኮረጅን ሳይሆን አዲስ ሀሳብ እያፈለቅን ለአዲስ ዲሞክራሲ ውልደትና ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የፍቅር ውልደት ዘብ እንቁም። እንጨት እንጨት የሚል የጨለማ አስተሳሰብ አበቃለት።
የመደመር ዲሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም ምስጢር ገና የሚገለጥ ነው
ዶ/ር ዐቢይ ሰሚ ያጣ ሕዝብን ሰምተው፤ ታሪካዊ አደራቸውን ለመወጣት እየኳተኑ ይገኛሉ። ሰሚ ያጣ መሪ እንዳይሆኑ፤ የሚሉትን ልብ እያልን እንደመር። ደግሞም የመደመር ዲሞክራሲ ምንነት እርሳቸውንም ጨምሮ ሁላችንም ጥልቀቱን ገና አውቀን ያልጨረስነው ረቂቅ ምስጢር ነው። የመደመር ፍቅር ጅማሬያችን ኢትዮጵያን እንዲህ በደስታ ካሰከረ፤ የመደመር ፍቅር መጨረሻ ለዓለም በረከት ሊሆን የሚተርፍ ይሆንን? የመደመር ዲሞክራሲ አዲስ ርዕዮተ ዓለም ለመፍጠር፤ የኢትዮጵያ ልጆች አንድ ላይ ሆነው በመደመር፣ የቤት ስራ ወስደው፤ ለዓለም የሚተርፍ አካሄድ በተምሳሌነት ሊያበረክቱ ፍጥረት ሁሉ ይጠብቅ። መደመር የሚለው አስተሳሰብ የብርሃን አስተሳሰብ ነው። ብርሃን እውቀትና ፍቅርን ያጠቃልላል። ሰው የመደመር ብርሃን ሲበራለት፤ የሙሉነት እውቀት ይዞ፤ በፍቅር መያያዝ ይችላል። በብርሃን የመሆናችን ምስጢር የሚገለጠው ወገኖቻችንን መውደድ (ፍቅር) ስናውቅ (እውቀት) ነው።
ፈጣሪ የጀመረውን ሰው አይጨርሰው
በፍቅር እንደ ጀመርን በፍቅር እንጨርስ። በእውቀት እንደ ጀመርን በእውቀት እንዝለቅ። በብርሃን እንደ ጀመርን በብርሃን ግብ እንድረስ። ትላንት ፀልየን ዛሬ ድንቅን አየን። አሁንም ወደፊት እየፀለይን ድንቁን በቀጣይነት እናያለን። በኢትዮጵያ መደመር ላይ የሚነሳ፤ ከኢትዮጵያ አምላክ ጋር ይፋለማል።
የመደመር ፖለቲካ
የመደመር ፖለቲካ አገልጋይነት ነው። የስልጣን ኮርቻ ላይ ለመቀመጥ አይሮጥም፤ ሕዝብ ፈረስ አይደለምና። ዶ/ር ዐቢይ ዋነኛ ጥሪያቸው አዋላጅ ሆነው ለኢትዮጵያ አባት መሆን ነው። ሌላውም ተባባሪ አዋላጅ ለመሆን ይሽቀዳደማል እንጂ በስልጣን ጥማት አይነዳም። በአገልጋይነት መንፈስ ሆነን፤ ዲሞክራሲ እንዲወለድና ሕዝብ አገልጋዩን እንዲመርጥ የሕዝብን ጥቅም የሚያስቀድም አካሄድ መውሰድ ይገባል። በግል ጥቅም ጨለማው እየሰለጠነብን፣ ለስልጣን መናቆርና ማናቆር ይቀራል። የፖለቲካው ሃይል የሚገለጠው በፍቅር ነው። ለመሆኑ ሀገር በአንድ ቀን ይወለዳል ብሎ ያሰበ ማን አለ? ኢትዮጵያ በአንድ ቀን ተወልዳ፤ ሕዝብ በአንድነት የተያያዘው፤ በፍቅር ሃይል ነው። በዚህ አጭር ጊዜ ተዐምር የሰራው የፈጣሪ ስጦታ የሆነው የፍቅር ሃይል ነው። ጨለማ ብርሃንን መቋቋም አይችልም። ብርሃን ባለበት ሁልጊዜ ጨለማ ስፍራውን ይለቃል። በፍቅርም ይሸነፋል። ኢትዮጵያን አቅፎ አፍሪካን አሻግሮ በማየት ለመያዝ ይዘረጋል። በዚህ ፍቅር ጉልበት እየተረዳን፤ ለዓለም ትምህርት የሚሆን አዲስ ታሪክ እየፃፍን እንደሆነ ማን ያውቃል? አወይ መደመርና ብልሃቱ!
የመደመር ኢኮኖሚ
የመደመር ኢኮኖሚ መነሻው ሙሉነት ነው። እጅግ ከቁጥር በላይ ባለፀጋ እንደሆንን ከማወቅ ይጀምራል። ከምድር በታች አምላክ የሰጠን እጅግ ብዙ የተፈጥሮ ሀብት ታምቆ አለ። ከምድር በላይ አንድ መቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ከሀብት ሁሉ በላይ የሆነ ባለፀግነት አለን። ኢትዮጵያ ለሁሉ በቅቶ፤ ለሌላው የሚተርፍ ሀብት አላት። ስለዚህ የመደመር ኢኮኖሚ መነሻው ሙሉነት ነው። የተሰጠንን ምሉዕ ቸርነት እንዳንበላ እንቅፋት ሆኖብን የነበረው፤ የጎዶሎነትና የማጣት ስሜት የሚፈጥረው ስግብግብነት ነው። ምናልባት እኛ የማናውቀው በጊዜ የሚገለጥ፣ ብዙ ተዝቆ የማያልቅ የተፈጥሮ ሀብት ይቅርና፤ የምናውቀውን እንኳን በቅጡ ሳንጠቀምበት፣ ከመብላት ወደ መበላላት እንድንሻገር ሊገፋን የሚፈልገው ጨለማ ነው። ይህም ጨለማ አለማወቅና ጥላቻ የሚባል ነው። በዚህ ጨለማ ምክንያት፤ ሁሉ እያለን እንደሌለን ሲያኖረን ዘመናት አስቆጠረን። ይህ አልበቃው ብሎት፤ ሁሉ እያለን፥ እኛን ራሳችንን ወደ አለመኖር ሊወስደን ጨለማ ወጥመድ አዘጋጅቶልናል። ግን ማን ሞኝ አለ፤ ነቅተን ተደምረናል። ሌሎቹም ሲያመነቱ እንዳይረቱ ተደመሩ እንላለን። በመደመር ውስጥ፤ ኢኮኖሚያችን በዜሮ ባለበት ከመርገጥ ይልቅ፤ ከሙሉ ይጀምራል። አሮጌው ፖለቲካ ለኢኮኖሚያችን ድቀት ምክንያት እንደሆነ ሁሉ፥ አዲሱ የመደመር ፖለቲካ፣ ለአዲሱ የመደመር ኢኮኖሚ ብልፅግና ምክንያት ይሆናል።
ጊዜው ለኢትዮጵያ ብሩህ ነው
አትሩጥ አንጋጥ የተባለውን እያስተዋልን፤ ለአዲስ ነገር ልባችንን እናስፋ፥ አዕምሯችንንም እንክፈት። ላረጀ ድንቁርናና ጥላቻ ቦታ አንስጥ። ከእኩይ ተግባር እንቆጠብ፥ ልባችንንም እልከኛ አናድርግ። በረከቱ ለሁላችንም ነው። ለዚህ ብሩዕ ዕለት ላደረሰን ፈጣሪ ምስጋና ይድረሰው።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን አሰበ። ይጎበኛታልም።
የፀሐፊው አድራሻ፥ myEthiopia.com

Read 9107 times