Saturday, 14 July 2018 12:08

የሪፐብሊካንና ዲሞክራት ጉራማይሌ ተጽዕኖ

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(0 votes)

 በወርሀ ጥቅምት 2017፣ አርባ አምስተኛ ፕሬዝዳንት ሆነው፣ የዓለማችንን ቁንጮ ሀገርን ለመምራት በዓለ ሲመታቸውን የፈጸሙት ዶናልድ ትራምፕ፤ የሥልጣን መንበሩን በተቆናጠጡ ማግሥት፣ አያሌ አወዛጋቢ አጀንዳዎችን ይዘው መምጣታቸው የሚታወስ ነው፡፡ በተለይ እትብታቸው የተቀበረበት ቀዬ ፊት የነሳቸው የደሀ ሀገር ተባራሪ ስደተኞች ላይ ኮስተር ያለ እርምጃ በመውሰድ ነበር ሥልጣናቸውን ያሟሹት:: ይህ ዓይነት ቅኝት ያላቸው የቀኝ ዘመም አክራሪ ፖለቲከኞች፣ ዶናልድ ትራምፕን ተከትሎ፣ በምድረ አውሮፓ ተጽዕኗቸው እየበረታ እንደመጣ ማሳያ የሚሆኑ ብዙ ምልክቶችን እያስተዋልን ነው:: በቅርቡ ለጥቂት የተሸነፉት የቀኝ ዘመም አክራሪዋ የፈረንሳይ እጩ ተወዳዳሪ ዶናልንድ ፔን እንዲሁም በኢጣሊያ ምርጫ  ከፍተኛ ድምጽ ማግኘት የቻለው የፋይቭ ስታር የፖለቲካ ቡድንን ዋቢ ማድረግ ይቻላል። ከዚህ በተጨማሪ ቁጥራቸው ቀላል በማይባሉ በምሥራቅና በምዕራብ አውሮፓ ሀገራት ˝ፖፕሊስት˝ ፖለቲከኞች፣ በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተደማጭነት እያገኙ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ አክራሪነት በምዕራቡ ዓለም እዚህም እዚያም በሚያስበረግግ ደረጃ መፈንዳት፣ ዞሮ ዞሮ የጦስ ዶሮ የሚያደርገው የታዳጊ ሀገሮችን ዜጎች ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ፖለቲካዊ ምስቅልቅሉ የዓለማችን ሁሉን አድራጊ ፈጣሪ በሆነችው አሜሪካ ሲሆን የተጽዕኖ ደረጃው እጅግ የበረታ ይሆናል፡፡
የትራምፕ አስተዳደር ከቀድሞው የዲሞክራቱ ፕሬዝዳንት ኦባማ ሥልጣኑን በተረከበ ማግሥት ለዓለም ሀገራት ሥጋት የሚሆኑ ጽንፍ የወጡ እርምጃዎችን እየወሰደ በአነጋጋሪነቱ እንደቀጠለ ነው፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ግን ይህንን ሰፊ ጥናትን የሚጠይቅ የፖለቲካ ንፍቀ ክበብን ማዳረስ አይደለም፡፡ ከዚህ ይልቅ የዲሞክራትና የሪፐብሊካን እጩ ፕሬዝዳንቶች ነጩን ቤተ መንግሥት ከተቆጣጠሩ በኋላ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ላይ የሚያሳድሩትን አዎንታዊና አሉታዊው ተጽዕኖ በኩርማን ምልከታ ለመጠቋቆም እሞክራለሁ፡፡

ወታደራዊ ደህንነትን በተመለከተ
ሪፐብሊካን ለወታደራዊ የደህንነት ዘርፍ የሚመድቡት ወጪ ከዲሞክራት ጋር ሲነጻጸር የላቀ ነው። ለአብነት ያህል በቡሽ ቤተሰብ አገዛዝ ዘመን በኢራቅና በአፍጋኒስታን ላይ ተደርጎ የነበረው ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቅ ወታደራዊ ዘመቻ በቀጥታ የሚቀዳው ከሪፐብሊካን የፖሊሲ ቅኝት እንደሆነ ይታወቃል፡፡  
የሀገራችንን አጠቃላይ የታሪክ ሂደት ዞር ብለን ስንፈትሽ፣ ከሪፐብሊካን ይልቅ በዲሞክራት አስተዳደር ዘመን ነበር አንጻራዊ ሳንካዎችን ለመጋፈጥ የተገደድነው፡፡ የዲሞክራቱ ጂሚ ካርተር አስተዳደር በ1969 ዓ.ም በሶማሊያ ወረራ ወቅት ደርግን ፊት መንሳት ለወታደራዊው ጁንታ ወደ ሶሻሊስት ካምፕ መቀየጥ ምከንያት ሊሆን ችሏል፡፡ ይህም የሀገራችንን ጂኦ-ፖለቲካዊ ቁመናን  በመወሰኑ  ረገድ የተጫወተው ሚና አሌ የሚባል አይደለም፡፡ ምናልባትም የደርግ አሰላለፉ ከምእራብያዊያኑ ጎን ቢሆን ኖሮ፣ ደርግን ለመውጋት ነፍጥ ያነሱት ኃይሎች የትግል ዘመን በእጅጉ በረዘመ ነበር፡፡
በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅትም የዲሞክራቱ የክሊንተን አስተዳደር ከኢትዮጵያ ጎን በይፋ ለመሰለፍ አልፈቀደም፡፡ ምናልባትም በኦባማ የሥልጣን ዘመን ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር የነበራት ግንኙነት አንጻራዊ በሆነ መልኩ በጥቅም የተሳሰረ ነበር፡፡ የኦባማ አስተዳደር የምሥራቅ አፍሪቃ ቀጠና ደህንነትን ለማስጠበቅ ኢትዮጵያን እንደ ኹነኛ አጋር በመወሰድ በሚሊተሪው ዘርፍ ሊጠቀሱ የሚችሉ የትብብር ሥራዎችን ሲሰራ ቆይቷል፡፡
በምሥራቅ አፍሪቃ ቀጠና አንጻራዊ በሆኑ መልኩ ጠንካራ መከላከያ እንዳላት የሚታመነው ኢትዮጵያ፣ ከትራምፕ አስተዳደር ጋር ምልክት የሚሆኑ ይፋ የወጡ ትብብሮችን እስካሁን አላስተዋለችም፡፡ በርግጥ የትራምፕ አስተዳደር ለቀጠናው የሰጠውን ትኩረት በተግባር ለመገምገም ጊዜው ገና ነው። በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ጥረት አማካኝነት ኢትዮጵያ ለሁለት አስርት ዓመታት በባላንጣነት ከፈረጀቻት ጎረቤት ሀገር ኤርትራ ጋር የፈጠረችው ሰላማዊ ግንኙነት፣ ምናልባትም የትራምፕ አስተዳደር በምሥራቅ አፍሪቃ ያለውን የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ እንደ አዲስ ለመከለስ ሳያስገድደው አይቀርም፡፡

ጤናን በተመለከተ
ሪፐብሊካንና ዲሞክራት ከሚለያዩባቸው ወሳኝ አቅጣጫዎች መካከል ጤናን በተመለከተ ከታዳጊ ሀገሮች ጋር የሚኖራቸው ትስስር ነው፡፡ የትራምፕ አስተዳደር ከዚህ ቀደም ከነበረው ከሪፐብሊካን አገዛዝ ዘመን ጋር እንኳን ለንጽጽር በማይበቃ ደረጃ ጽንፍ የወጣን የጤና ፖሊሲን በመከተሉ የተነሳ ሀገራችንን ጨምሮ በርካታ ከሰሃራ በታች ያሉ ደሀ ሀገራትን ሰለባ እያደረገ ነው። ሪፐብሊካን በአብዛኛው ከጥብቅ ክርስትያናዊ አስተምህሮት ለመነጨ ሞራላዊ ግዴታ ትኩረት በመስጠት ይታወቃሉ፡፡ በተለይ እንደ ጎርጎሲያኑ አቆጣጠር በ1984 በሪፐብሊካኑ ሮናልድ ሬገን አማካኝነት የተቀረጸው ግሎባል ጋግ ሩል (Global Gag Rule) ይህንን ክርስትያናዊ አስተምህሮት ለማስጠበቅ በሚል እሳቤ፣ ከጽንስ ማቋረጥ ጋር የሚሰሩ ግብረሰናይና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን አቅም ማሽመድመድን ተቀዳሚ ተግባሩ ያደርጋል፡፡
የዚህ የግሎባል ጋግ ሩል ዳፋው የሚወድቀው ዞሮ ዞሮ  እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገራት ውስጥ በሚኖሩ ደሀ ሴቶች ላይ ነው፡፡ በዚህ ፖሊሲ ሰበብ ከጽንስ ማቋረጥ ጋር የተያያዙ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ድርጅቶች፣ በሕገወጥ ውርጃ ምክንያት እንደ ቅጠል የሚረግፉትን እምቦቃቅላ ሴቶችን ከመመልከት ውጪ ሌላ አማራጭ እንዳይኖራቸው ተገደዋል። ከ2001 እስከ 2009 ዓ.ም ወደ ሀያ የሚጠጉ ደሃ የአፍሪካ፣ ኤሽያና መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት የሚገኙ ድርጅቶች ከአሜሪካ ለጤና ዘርፍ የሚጣለው ዳረጎት ስለነጠፈባቸው፣ የነበራቸው ምርጫ ወይ አገልግሎቶቻቸውን ማቋረጥ፣ ሠራተኞቻቸውን መበተን አልያም ጨርሶ ድርጅቶቻቸውን መዝጋት ሆኗል፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ  የአሜሪካንን የጤና እርዳታ ከሚያገኙት ሀገሮች መካከል በአምስተኛ ረድፍ ላይ ትቀመጣለች፡፡ የትራምፕን ጥብቅ የጤና ፖሊሲን ተከትሎ በመጪዎቹ ዓመታት በተለይ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሚከሰተው የጤና ቀውስ ምን ያህል አስከፊ እንደሚሆን ከወዲሁ ለመተንበይ ነብይ መሆንን አይጠይቅም፡፡

የዓየር ንብረት ስምምነትን በተመለከተ
በፈረንሳይ በተካሄደው ጉባኤ የዓለምን ሙቀት መጠን እስከ 1.5 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ድረስ ለማውረድ የዓለም መንግሥታት ቃል ኪዳን መግባታቸውም አይዘነጋም፡፡ ይህ ቃል ኪዳን ግን ብዙም ርቀት ሳይጓዝ ነው በወረቀት ላይ ብቻ እንዲቀር የተፈረደበት፡፡ ለዓለም ሙቀት መጨመር የአንበሳውን ድርሻ የምትወስደው አሜሪካ እንደሆነች ቢታወቅም በስምምነቱ ላለመገዛት ፊት በመሰለፍም ማንም አልቀደማትም፡፡ ትልቅ ተስፋ የተጣለበትን የፓሪሱን የአየር ንብረት ስምምነት፣ የትራምፕ አስተዳደር መሳለቂያ ነው ያደረገው። “የአየር ንብረት የሚባል ነገር የቃላት ጨዋታ ነው፤ ቻይና የአሜሪካኖች ግዙፍ ኢንዱስትሪዎች ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር የሸረበችው ሴራ ነው” ይላሉ ትራምፕ፡፡
የትራምፕ አስተዳደር በከሰልና በነዳጅ ማውጣት ከሚታወቁ ግዙፍ ኩባንያዎች ጋር የጠበቀ ግንኙነት ስላለው፣ ከኩባንያዎቹ የእጅ አዙር ተጽዕኖ ነጻ መሆን ይችላል ተብሎ አይታሰብም፡፡
ይህ የትራምፕ ቅጥ ያጣ ፖሊሲ ዞሮ ዞሮ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ደሀ ሀገሮችን ነው የችግሩ ገፈት ቀማሽ የሚያደርገው፡፡ አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ እንዲሉ፣ ወደ ከባቢ አየር የምንለቀው በካይ ጋዝ እዚህ ግባ የማይባል ሆኖ ሳለ፣ በዓየር ንብረት መዘበራረቅ ጦስ በዋነኛነት ተጠቂዎቹ ከበለጸጉት ሀገሮች ይልቅ እኛው እንደሆንን ይታወቃል፡፡ የሀገራችን የኢኮኖሚ መደላደል ግብርና ውጤታማነት በቀጥታ የሚተሳሰረው ከጤናማ የወቅቶች መፈራረቅ ጋር ነው፡፡ ስለዚህ የተዛባ የዓየር ንብረት በሚወልዳቸው እንደ “ኢሊኖ” እና “ላሊኖ” ሰበብ በሚከሰቱ የጎርፍ፣ የድርቅና የወረርሽኝ አደጋዎች ተጽዕኖ ምክንያት ከእጅ ወደ አፍ በማያልፍ ኢኮኖሚ ለማዝገማችን ምዕራባዊያኖቹ የራሳቸውን አስተዋጽኦ  አበርክተዋል፡፡

ማሰሪያ ነጥብ
በፖለቲካ መርህ መሠረት፤ ዘላለማዊ ብሔራዊ ጥቅም እንጂ ዘላለማዊ ወዳጅ ወይም ጠላት ሊኖር አይችልም፡፡ ዲሞክራቱም ሆነ ሪፐብሊካኑ የሚያስቀደሙት ብሔራዊ ጥቅማቸውን ነው። በፖለቲካ ጨዋታ ውስጥ እንደ ሀይማኖታዊ አስተምህሮት ለግብረገብነት የሚተርፍ ምህዳርን መፈለግ በየዋሀ ባለሟልነት ያስፈርጃል፡፡ ማንኛውንም አማራጭ ተጠቅሞ በአደባባይ በኩራት የሚያስቆም አስተማማኝ ብልጽግናን መላበስ የጨዋታው ማሽነፊያ የምስጢር ቁልፍ ነው፡፡ በዚህ ውጥንቅጥ የፖለቲካ የጨዋታ ሕግ ላይ በሚገባ ከሰለጠኑ፣ የራስንም ሆነ የሌሎችን ሀገራት ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ አስፈላጊው ስንቅን መታጠቅ ይቻላል፡፡
 የዲሞክራትና የሪፐብሊካን ፓርቲዎች በተመረጡ ቁጥር በሚዘበራረቅ የፖሊስ አቅጣጫ ዕጣ ፈንታችንን ለመወሰን የተገደድነው፣ ካለንበት ሁሉን አቀፍ የኋላቀርነት ቅርቃር ውስጥ ተሰንቅረን በመቅረታችን ነው፡፡ እስካሁን የጨዋታው ሕግ አልገባንም፡፡ ከቅርቃሩ እንዴት ነፃ እንውጣ የሚለው ጥያቄ፣ አሁንም ራስ ምታት እንደሆነብን ቀጥሏል፡፡ በቻይና ሞዴል እንጓዝ ወይስ የምዕራባዊያኖቹን የኒዮ-ሊብራሊዝም ቅኝትን ለመከተል በራችንን ወለል አድርገን እንክፈት ወይስ የራሳችንን አዲስ ያልተሞከረ የብልጽግናን መስመር እናፈላልግ? እንቆቅልሹ ይቀጥላል…..  

Read 1735 times