Saturday, 14 July 2018 12:04

“ከአንድ ማህፀን የወጣን ልጆች፤ ሁለት ዜጎች ሆነናል”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(3 votes)


    
 ጋዜጠኛ ዮናስ አብርሃምና ጋዜጠኛ በረከት አብርሃም በኢትዮጵያ ከአንድ ማህፀን የወጡ ታላቅና ታናሽ ወንድማማቾች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያዊ ባህልና ወግ ታንፀው እዚሁ ፊደል ቆጥረው ነው ያደጉት፡፡ በ1990 ዓ.ም በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል በተከሰተው ጦርነት ሳቢያ ኤርትራዊያን መላ ቤተሰቡ ወደ ኤርትራ ሲባረር፣ ጋዜጠኛ ዮናስ አብርሃም ከኢትዮጵያ ውጭ አገር የለኝም በሚል እዚሁ አገር ቀረ፡፡ ይህን ተከትሎም ከሥራ መባረርን ጨምሮ ብዙ መከራዎችን ተቀብሏል። ከአንድ እናት ማህጸን የወጣን ልጆች፣ ሁለት ዜጎች ሆነናል የሚለው ጋዜጠኛ ዮናስ፤ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት እሱ ከኢትዮጵያ ወገን ሆኖ፣ ወንድሙ ጋዜጠኛ በረከት አብርሃም በበኩሉ፣ ከኤርትራ ወገን በመቆም፣ ለቆሙበት ዓላማ መቀስቀሳቸውን ያስታውሳል፡፡
የእነዚህ ሁለት ወንድማማቾች ታሪክ፣ የኢትዮ ኤርትራ ግጭት ቤተሰቦችን ሁለት ቦታ ከፋፍሎና ለያይቶ ክፉ ጠባሳ ጥሎ ማለፉን ማሳያ ነው፡፡ ወደ ሥልጣን ከመጣ 3 ወራት ከጥቂት ቀናት ብቻ ያስቆጠረው የጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ አዲስ አስተዳደር፣ ለኤርትራ መንግስት ባደረገው የሰላም ጥሪ የተነሳ ግን ላለፉት 20 ዓመታት የዘለቀው የመለያየት መጋረጃ ተገፍፎ፣ የሰላምና የፍቅር ተስፋ በሁለቱ አገራት ሰማይ ላይ ፈንጥቋል፡፡
በሬዲዮ ፋና ለረጅም ዓመታት በጋዜጠኝነት የሰራውና “ትንንሽ ፀሐዮች” (እማማ ጨቤ) በተሰኘ ተከታታይ የሬዲዮ ድራማው የሚታወቀው ጋዜጠኛ ዮናስ አብርሃም፣ ከቤተሰቡ ጋር ሲለያይ የተሰማውን ስሜት፣ ያሳለፈውን የስቃይና የመከራ ዓመታት እንዲሁም በአጭር ጊዜ ውስጥ በሁለቱ አገራት መካከል በተፈጠረው አዲስ ግንኙነት ሳቢያ በፈነጠቀው ተስፋ ምን እንደተሰማው --- ለአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ እንዲህ  አውግቷታል፡-


    በሁለቱ አገራት በፈነጠቀው አዲስ ተስፋ በቅድሚያ እንኳን ደስ አለህ እላለሁ ---
እኔም በዚህ ሂደት ውስጥ ተለያይቶ ብዙ ስቃይ ላሳለፈው ቤተሰብ፣ ዘመድ፣ ወዳጅና በአጠቃላይ ለሁለቱ ወንድማማቾች ህዝብ እንኳን አብሮ ደስ አለን ለማለት እወዳለሁ፡፡
በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ምን ስሜት ፈጠረብህ?
ስሜቱ በቀላሉ የሚገለፅ አይደለም፡፡ ሁሉም ነገር እጅግ በሚገርም ፍጥነት ነው እየተከናወነ ያለው፡፡ በእኔም ሆነ በአብዛኛው ሰው ግምት፣ ይሄ ነገር ቶሎ ይመጣል የሚል ሀሳብ አልነበረም፡፡ ያንን ምኞት ሰማነው፣ በጣም ፈጠነና ይሄው እዚህ ደርሶ መገናኘት ተቻለ፡፡ ነገር ግን ያንን ግድግዳ አልፎ ለመሄድ የሚታሰብ አልነበረም፤ በእኔ ዕድሜም ይህ ይሆናል ብዬ አልገመትኩም፡፡ ግምቴ የነበረው ጉዳዩ ገና ቀጣይ አንድ ትውልድ ይፈልጋል፣ ከዚያ ሰዎች ዕድሜያቸው ከደከመና በተፈጥሮ ሞት ካለፉ በኋላ ቢሆን ምን ዋጋ አለው በሚል ተስፋ ቆርጠን ነበረ፡፡ አሁን ይህ መሆኑን ስመለከት፣ ስሜቱን መግለፅ አልችልም፡፡ ምክንያቱም ጉዳዩ የህዝቦች መለያየት ብቻ አይደለም፡፡ ብዙ ነገር ቀላል አይደለም፤ አሁን ደግመን ስንገናኝ ሰብአዊ ስሜቱ ከፍ ያለ ነው፡፡ ዘመድ ከዘመዱ፣ ወዳጅ ከጎረቤቱ፣ አብሮ አደጉ ከአብሮ አደጉ የሚገናኝበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ይሄ ከፍተኛ ስሜትን የፈጠረ ነው፡፡
ከ20 ዓመት በፊት የነበረው የቤተሰብህና የአኗኗራችሁ ሁኔታ ምን ይመስል ነበር---ከዚያስ  በምን ሁኔታ ነበር የተለያያችሁት?
እንግዲህ እኔና ወንድም እህቶቼ ተወልደን ያደግነው እዚህ አዲስ አበባ ነው፡፡ ተወልደን አይናችንን ስንገልጥ ያየነው ይህንን አገር ነው፡፡ ያደግነውም በኢትዮጵያዊነት መንፈስ ነው፡፡ ሁሉም ብሔርና የህብረተሰብ ክፍል የነበረበት አካባቢ እንደመወለዳችን፣ ስለ ብሔርና ዘር እንኳን ያን ጊዜ አናውቅም ነበር፡፡ ምናልባት ብሔር ያወቅነው ካደግን በኋላ ነው፡፡ በተረፈ በስፋት ይነገሩ የነበሩ ቋንቋዎች ማለትም ጉራጊኛ፣ አማርኛ፣ ትግሪኛና ኦሮሚኛ ሲነገር እንሰማ ነበር፡፡ ከዚህ ባለፈ ብዙ ነገር አናውቅም ነበር፡፡ በዚህ መልኩ ነው ያደግነው፡፡
እንዴት ተለያያችሁ ላልሺኝ፣ እንግዲህ በ1990 ዓ.ም እኔ በሬዲዮ ፋና በጋዜጠኝነት እሰራ ነበር፡፡ መጨረሻ ላይ እናቴን በጥቂቱ አየኋት እንጂ ሌሎቹ እንዴት እንደሄዱም አላውቅም፡፡ ምክንያቱም እኔም አንደ ኢትዮጵያዊነቴና እንደ ጋዜጠኝነቴ፣ ለሻዕቢያ ወረራ ቅስቀሳ እየዞርኩ እሰራ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ተደፍሯል፣ የሻዕቢያን ወረራ ለመመከት በሚሉ ስራዎች ላይ ተጠምጄ ስለነበር ነው፡፡ ከሄድኩበት ስመለስ ብዙ ነገሮች ተበላሽተዋል፡፡ ነገሩ በፍጥነት ነው የሆነው፤ ተበታትነው ነው የሄዱት፡፡
አንተ ግን ከዚያ በፊት ኤርትራዊያን እንደነበራችሁ ታውቅ  ነበር?
እኔ በወቅቱ ልዩነቱ ብዙ አይገባኝም ነበር፣ ቤተሰቦቼ ትግሬዎች መሆናቸውን ባውቅም በትግራይና በኤርትራ መካከል ያለው ልዩነት ብዙ አይገባኝም ነበር። ያን ያህልም ጉዳዩ ፕሮሞት የሚደረግ አልነበረም። ያው እኔ ኑሮን ለማሸነፍ ደፋ ቀና የምል ነበርኩ፡፡ ምክንያቱም የሃብታም ቤተሰብ ልጅ አልነበርኩም፡፡ አባቴ ቀደም ሲል የራሱ ድርጅት ነበረው፡፡ ታክሲና ተሽከርካሪዎችም ነበረው፡፡ ከዛ በኋላ ደግሞ ብዙ ቤተሰብ ለማስተዳደርና ልጅ ለማሳደግ እንደ ማንኛውም ሰው ተቀጥሮ ይሰራ ነበር፡፡ ይሄን ያህል ፖለቲካው የሚያሳስባቸው ቤተሰቦችም አልነበሩም፤ የተማሩም አይደሉም፡፡ ስለዚህ አገራቸውን ቢወድዱም የሚገርም አይደለም። እነሱ ያወሩታል፤ በወቅቱ እኛ አንጋራውም፡፡ እኛ የተሰራንበት መንገድ ይሄ ነው፡፡ ትግርኛ ለትዕዛዝ የሚሆኑ ጥቂት ቃላት እንጂ አንሰማም፡፡ እቤትም የስራ ቋንቋቸው አማርኛ ነበር፡፡ ብቻ ይሄ ቤተሰብ ሄደ፤ እኔ ቀረሁ፡፡ ሬዲዮ ፋና ላይ አስተዋፅኦዬም ይፈለግ ስለነበር በስራዬ ቀጠልኩኝ፡፡ ለኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ማቋቋሚያ፣ ለፀረ-ሻዕቢያ ምከታ፣ ለሉአላዊነትና መሰል ነገሮች መዋጮ ላይ እሳተፍ ነበር፡፡ እኔ ኤርትራዊ ነኝ ብዬ አላምንም፣ ቋንቋውን አልችልም፣ ቤተሰቦቼ መባረራቸውን እንኳን ለማንም ሳልነግር ፀጥ ብዬ ነበር የምኖረው፡፡ ልጅነቱ ስለነበረ መባረራቸው የሚታወቅም አልመሰለኝም፤ በኋላ ቆይቼ ሳስበው የዋህነት ነበረ፡፡ ምክንያቱም የመሥሪያ ቤቴ ሰው እንኳን እርስ በእርሱ እየተጠቋቆመ ነው ያወቀው፡፡
በዚህም ምክንያት ከስራህ ተባረህ እንደነበር ሰምቻለሁ …
ልክ የዚሁ የኢትዮ ኤርትራ ግጭት ዘገባና ቅስቀሳ ስራን ስጨርስ፣ ኤርትራዊ ስለሆንክ ከአገር ሉአላዊነት አኳያም ጥሩ ስላልሆነ ተብዬ ከስራዬ ተባረርኩ። የሚገርምሽ ሁሉ ነገር ተረጋግቶ ነበር፡፡ ጦርነቱም በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡ ብቻ ከሥራ ተባረርኩኝ፡፡ ቤታችን የግል አልነበረም፣ ተወስዷል፣ አጣድፈው ነው ያስወጧቸው፡፡ እኔም ከሥራ  እባረራለሁ የሚል ግምት አልነበረኝም፤ አልተዘጋጀሁም፡፡ የኔ መባረር በቃ በረንዳ ላይ የመውደቅ ያህል ልትቆጥሪው ትችያለሽ። በወቅቱ ገና አዲስ ስራ ጀማሪ ነኝ፡፡ ቤተሰቤ ሙሉ በሙሉ ሄደዋል፡፡ የተከራየሁት ቤት ያለኝን ነገር ሙሉ በሙሉ ወስደውታል፡፡ ሁሉም ነገር በፍጥነት ነው የተደራረበብኝ፡፡ መጀመሪያ ጓደኞቼ ቤት ማደር ጀመርኩ፤ እየቆየሁ ስሄድ በጣም ተቸግሬ በረንዳ ላይ መውደቅ ነበረብኝ፤ እጅግ ከባድና ዘግናኝ ጊዜ ነው ያሳለፍኩት፡፡ በዛን ወቅት ታናሽ ወንድሜ በረከት አብርሃም፣ እዛ ሄዶ ጋዜጠኛ ሆኗል፡፡ የሁለታችን እጣ ፈንታ የሆነው ይሄው ነው፡፡
ከምን ያህል ጊዜ በኋላ፣ በምን ዓይነት ሁኔታ ወደ ስራህ ተመለስክ?
 ወደ ስራ የተመለስኩት ከመንገድ ላይ ተጠርቼ ነው፤ ከመንገድ ተነስቼ ወደ ስራ ገባሁ፡፡ ምንም ማድረግ አልችልም፣ አማራጭ አልነበረኝም፡፡ ከስራ ውጭ ሆኜ ከ3 ዓመት ተኩል በላይ ቆይቻለሁ። ይሄን ያሳለፍኩት በጣም በአሰቃቂ ሁኔታ ነው። የሚገርምሽ በዛን ወቅት ሰው ኤርትራዊ ነኝ እያለ፣ ኦነግ መሆኑን እየገለፀና የተቃዋሚ ፓርቲ መታወቂያ እየያዘ ወደ ውጭ የሚሄድበት ጊዜ ነበር፡፡ እኔም ይሄ ሁሉ እድል ነበረኝ፡፡ ነገር ግን እኔ ኢትዮጵያዊ ሆኜ፣ በኢትዮጵያዊነት ነው ያደግሁት፡፡ እንደውም ይሄ ኢትዮጵያዊነቴ ሳይረጋገጥልኝ የትም ንቅንቅ አልልም ብዬ ነው፣ ያንን ሁሉ ስቃይና መከራ ያሳለፍኩት፡፡ የእውነትም የኔ ህልም፣ አጋጣሚዎችን ተጠቅሜ ወደ ውጭ መሄድ ሳይሆን እዚሁ ሆኜ የምሰራውን ስራ መስራት ነበር፡፡ ስለሆነም ያለምንም ረዳት፣ ያለምንም ሰው በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ያንን ሁሉ ዓመት ተሰቃይቻለሁ፡፡ ባደግሽበት በተወለድሽበት አገር ኢትዮጵያዊ አይደለሽም ስትባይ፣ የማንነት ቀውሱ ባዕድነቱ ሁሉ ይሰማሻል፡፡ በቃ ከባድ ነው፤ እንዴት እንደምነግርሽ አላውቅም፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያዊነት ድንቅና በቅኔ የተሞላ አስተሳሰብ ነው፡፡ ይህን የምልሽ በዛ በችግሬ ወቅት እኔንና ጉዳዩን ከሚያውቁት ይልቅ፣ እኔን ቀድመው ሳያውቁኝ የደረሰብኝን የሰሙ ኢትዮጵያውያን፣ ወንድም ነው ያደረጉኝ፡፡ የበሉትን እየበላሁ ዛሬ አንዱ ጋር፣ ነገ ሌላው ጋር እየሆንኩኝ ነው ያንን ክፉ ቀን ያለፍኩት፡፡
ከኖርኩበት አካባቢ ርቄ ሌላ አካባቢ ነው የቆየሁት። ጦርነቱ በርዶ ከተረጋጋ በኋላ ሰዎች ይህን ነገር ሊረሱት አልፈለጉም፤ የሚያውቁሽ ይበልጥ ይፈሩሻል፡፡ ብቻ ይህን ሁሉ ስቃይ ከኢትዮጵያውያን ጋር በፅናት ነው ያሳለፍኩት፡፡ ከዚያ ከመንገድ ላይ ወደ ሥራ ተመልሰሀል ተብዬ በመኪና ተጭኜ ነበር ወደ ስራ የገባሁት፡፡ ይሄ ማለት በ1994 ዓ.ም ነው፡፡
ተመልሰህ ወደ ስራ ስትገባ፣ የባልደረቦችህ አቀባበልና የአንተ ስሜት እንዴት ነበር?
እኔ ስራ መግባቱን ነበር የምፈልገው፡፡ እንዴት ወጣሁ? እንዴትስ ተመለስኩ? የሚል የመብት ጥያቄ የለም፡፡ እሱም ራሱ ደስ የማይል የራሱ ታሪክ አለው፤ ነገር ግን ወደ ስራ መመለሱ ያጣሁትን ኢትዮጵያዊነት መልሶ የማግኘትና አመኔታዬን የመመለስ ያህል ነበር የተሰማኝ፡፡ ስራዬን ቀጠልኩ፡፡ ወንድሜም ኤርትራ ሆኖ በቀዝቃዛ መልኩም ቢሆን በጋዜጠኝነቱ ፕሮፓጋንዳውን ቀጥሏል፡፡ እኔም ወራሪውና ዕብሪተኛው የሻዕቢያ መንግስት ማለቴን ቀጥያለሁ፤ እንደምሰራበት ጣቢያ ይህን የማለት ግዴታም አለብኝ። እሱም በዚህ ጉዳይ ላይ ጠንከር ጠጠር ያለ ስራን ይሰራ ነበር፡፡ እናያቸዋለን ያዩናል፡፡ እናደምጣቸዋለን ያደምጡናል፡፡ እሱ ለኤርትራ መንግስት ይሰራል፣ እኔ ለኢትዮጵያ መንግስት አሰራለሁ፡፡ ከአንድ እናት ማህፀን የወጣን ልጆች፣ ሁለት ዜጎች ሆነናል፡፡ እናም የሁለቱ አገራት መለያየት፣ ድንገት የሆነው ነገር፣ አንድ ቤተሰብ ማፍረስ ብቻ ሳይሆን አንድ ማህፀንም ውስጥ ገብቷል፡፡ አንዱን ኤርትራዊ አንዱን ደግሞ ኢትዮጵያዊ አድርጓል፡፡ ቤተሰቦቼ ኤርትራዊ ሆኑ፤ እኔ ኢትዮጵያዊ ሆኜ ቀረሁ፡፡ ይሄ ብዙ ፍዳና መከራ ያየሁበት የዘመኔ ታሪክ ነው፡፡ እናም ይህን ያጣሁትን ነገር ለማስመስከር ዳግም ኢትዮጵያዊ መሆን ከሚጠበቅብኝ በላይ መስዋዕትነት ጠይቋል፡፡ ምክንያቱም እልሁም ፍቅሩም ነበረ፡፡ ይህ የተደረገብኝ ነገር ደግሞ እኔ ሳልፈልገው የተደረገብኝ ስለነበር፣ በደንብ ኢትዮጵያዊ ሆኛለሁ፤ ለራሴ አስቤ አላውቅም፡፡ በሙያዬ ሁሉ ስሰራ የቆየሁት ኢትዮጵያዊነትን ነው፡፡ በስራዬም ማህበራዊና አገራዊ ነገር እንጂ ወደ ገንዘብ የሚወስድ ስራ ሰርቼ አላውቅም፡፡ ይህንን የምለው ስራዎቼን ሁሉ ህዝብ ስለሚያውቃቸው ስለሆነ በኩራት እናገራለሁ፡፡ ይሄ ሁሉ ምስቅልቅል ተፈጠረ፤ በዚህ ሂደት ውስጥ አለፍን ማለት ነው፡፡
ከዓመት በፊት ከወንድምህ ጋር እንዴት ተገናኛችሁ?
በቅርቡ “የሰላም መዝሙር ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ህዝቦች” በሚል እንቅስቃሴ የጀመረ ሰለብሪቲ ኤቨንትስ የተባለ ድርጅት ነበር፡፡ ይህ ድርጅት እኔን የሚጠራኝ እንደ ታዛቢና እንደ ጋዜጠኛ ነው፡፡ ምክንያቱም የኔ አገር ኢትዮጵያ ናት፤ ኤርትራ ደግሞ የቤተሰቦቼ አገር ናት፤ ምንም ባትሆን ክፉ ነገር ባይፈጠር ደስ ይለኛል። እንደገናም አሁን እነሱ እዛው ሆነው እኔም እዚህ ሆኜ መምጣትና መሄድ መቻሉ በጣም ደስታዬ ነው፡፡ የሰላም ግንኙነቱ ለእኔ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ የሆነ ሆኖ ወንድሜ የዛሬ አንድ አመት ገደማ፣ ከነበረው ጥሩ ቦታ በጣም በከባድ ሁኔታ ጠፍቶ ነው የመጣው። ከመጣ በኋላ ይሄ የሰለብሪቲ እንቅስቃሴ ሲጀመር፣ እሱ የኤርትራ ጋዜጠኞችንና የኪነ ጥበብ ሰዎችን ወክሎ ኮሚቴ ውስጥ ተካትቷል፡፡ እሱ ስለ ኤርትራ ሲያወራ፣ እኔ በኢትዮጵያዊ ጋዜጠኝነቴ ነበር የምቀዳው፤ ማንም ሰው አያውቅም ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ መረጃው እንዴት እንዳፈተለከ አላውቅም፤ በስብሰባው ላይ እንደ ምሳሌ አነሱንና፣ እኔም ታሪኩን ከ20 ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ አወራሁ፡፡ ይሄ በጣም የሚያሳዝን ታሪክ ነው፡፡
ከዚያ በኋላ ነው የዓለም አቀፍ የሚዲያ አውታሮችን ቀልብ የሳባችሁት?
ትክክል! ከዚህ በኋላ እነ አልጀዚራ፣ ቢቢሲና ሲኤንኤን ታሪኩ አስገርሟቸው፣ መነጋገሪያ አደረጉት፡፡
ወንድምህ በመልክ አልጠፋብህም?
አይ አልጠፋብኝም፡፡ አንደኛ እሱ የእኔ ቀጥታ ታናሽ ስለሆነ፣ ሁለትም ጋዜጠኛ እንደመሆኑ በቴሌቪዥን አየው ስለነበር አልጠፋብኝም፤ ይልቅ ታናናሾቹ ጠፍተውብኛል፡፡ የአንዳንዶቹ በልጅነት አዕምሮዬ ያለኝ ምስል ነው ያለኝ፤ የእናቴንም አላውቅም፡፡ ያኔ እነሱ ትንንሽ ነበሩ፤ አሁን አድገው ወልደዋል። አሁን ይሄ እርቅ ከመጣ በኋላ አንድ ፎቶግራፍ አይቻለሁ፤ የእናቴን ማለት ነው፡፡ አሁን ገና ወደፊት ነው የማያቸው፡፡ 20 ዓመት ቀላል አይደለም፤ ይሄ እከሌ ነው፣ ይህችኛዋ እከሌ ናት እየተባልኩ ልተዋወቅ እችላለሁ፡፡ ብቻ ጉዳዩ ባህሪሽን የሚለውጥ ነገር ነው። ጉዳዩ ልታስታውሺ የማትፈልጊው ግን የማትረሺው ነው፡፡
ከቤተሰብህ በሞት የጎደለ ሰው ይኖር ይሆን?
እምም ….! አሁን ላይ በጣም ከባድ ነው፡፡ ጉዳዩ ሃዘንን በቅጡ ለመወጣት አይመችም፤ አንዱ አንዱን ለማፅናናት መንገድም አልነበረም፡፡ ምንም መስማት አልፈልግም፤ ፍርሃት ላይ ነኝ፡፡ ከቻላችሁ ደግ ደጉን ንገሩኝ፣ መፍትሄ ማምጣት ለማልችለው ነገር ለምን እጨነቃለሁ በሚል ነበር የኖርኩት፡፡ ነገር ግን ብዙ ደስ የማይል ነገር አለ፡፡ ለምሳሌ እስካሁን እኔ ሀዘንም አልተቀመጥኩም፣ ከማንም ሰው ጋር አላወራሁበትም። በቅርቡ ነው ፌስቡክ መጠቀም የጀመርኩት፡፡ በዚሁ ፌስ ቡክ ላይ ነው የአባቴንም ሞት የሰማሁት (ዓይኑ በእንባ ተሞልቶ…) ይሄ አስደንጋጭ ነው፡፡ ሰዎች ሲነግሩኝ በቃ አላውቅም ---- አልሞተም ነው ያልኩት። አሁን ራሱ ለመደወል ፈርቻለሁ፤ ገና ብዙ ነገር ልሰማ እችላለሁ እያልኩ፡፡ ደሞም መስማቴ አይቀርም፤ ገና ስደውልም በቃ ጥሩ ጥሩውን ነገር ንገሩኝ ነው የምለው፡፡ ከዚያ ስረጋጋ ሁሉንም ሰምቼ፣ ሃዘኔንና እርሜንም በቅጡ አወጣለሁ፡፡ አሁን ግን ይሄ ደስታ እንዲደበዝዝብኝ አልፈልግም፡፡ አየሽ ትፈሪያለሽ፤ አሁንም እከሌ እኮ እንዲህ ሆነ ሲሉሽ ውስጥሽ ደስታሽን የሚጋፋ አስፈሪ ሃዘን ውስጥ ይገባላ፡፡ ይሄንን ደስታ ባግባቡ ማጣጣም እፈልጋለሁ፡፡
ከቤተሰብህ ውስጥ ወንድምህን ብቻ በቴሌቪዥን ስታይ ምን ነበር የሚሰማህ?
በጣም ይገርመኝ ነበር፡፡ ሁለታችንም የተሰለፍንበት ፅንፍ ለፅንፍ የሆነ ጎራ ደስ አይልም እንጂ ወንድሜ ግን እንደ ሙያተኛ ጠንካራና ጠጣር ስራ የሚሰራ ጎበዝ ጋዜጠኛ መሆኑን አስተውል ነበር፡፡ እኔ ለቆምኩበት ዓላማ ተፃራሪ ነው፡፡ ግን ደግሞ እሱም ለዓላማው በጥንካሬ ነው የሚሰራው፡፡ ዓላማው ከኔ ተፃራሪ ቢሆንም ለስራውና ለዓላማው በሙያው የበሰለ መሆኑ እንደ ታላቅ ወንድም ያስደስተኛል፣ ኩራትም ይሰማኛል። እኔም ብሆን ኢትዮጵያዊ ከሆንኩ፣ ኢትዮጵያዊ ሆኜ፣ ኡጋንዳዊ ከሆንኩ፣ ኡጋንዳዊ ሆኜ ነው መስራት ያለብኝ፡፡ ወንድማማቾች ነን ነገር ግን በዓላማ ደረጃ ሁለታችም በቆምንበት ነው መቆም ያለብን፡፡
ከቤተሰብህ ጋር ለመገናኘት መቼ ወደ አስመራ ልትሄድ አቅደሃል?
እንግዲህ የመጀመሪያው በረራ ላይ የምትሄደው አንተ ነህ እየተባልኩ ነው፡፡ ቆይ አብረን እንሄዳለን የሚሉ አሉ፡፡ ይህንን ምስጢር ሳያውቅ አብሮኝ የኖረ ብዙ ወገን አለ፤ ይህን ሲሰማ ሀዘን ላይ ወድቋል፡፡ እኔ ሀዘኔን ጨርሻለሁ፡፡ እንግዲህ አብረን ሄደን፣ አደይን እንጠይቃለን የሚለኝ በርካታ ወዳጅ አለ፡፡ ከሁሉ ጋር አብሬ ባልሄድ እንኳን ከሁሉም ጋር አብሬ እንደሄድኩ ነው የምቆጥረው፡፡ እንዴት እንደምሄድ እግዚአብሔር ነው የሚያውቀው፤ ነገር ግን እስከ መስከረም ባለው ጊዜ ሄጄ፣ ከቤተሰቤ ጋር አይን ለአይን እተያያለሁ፡፡ የፈጣሪ ፈቃዱ ይሁን፡፡  


Read 1604 times