Saturday, 14 July 2018 12:05

የለውጥ መሪዎችና ተፅእኖ ፈጣሪዎች ሚና

Written by  ወንድወሰን ተሾመ መኩሪያ
Rate this item
(2 votes)

(ጊዜው የሚጠይቀው ፈጣን ጉዳይ)
              
    በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ የነበረችው የእንግሊዝ ከተማ ሎንደን የቆሸሸች፣ በሰው የተጨናነቀች፣ መንገዶቿና መተላለፊያዎቿ እጅግ የጠበቡ፤ ከእንጨት ግድግዳ የተሰሩ ቤቶች የበዙባት ነበረች፡፡ እ.ኤ.አ. በሚያዚያ ወር 1665 የእንግሊዙ ንጉስ ቻርልስ (ሁለተኛ) ለሎንደን ከተማ ከንቲባ ፅ/ቤት አንድ ደብዳቤ ፃፉ፡፡ በዚህም ደብዳቤ ከተማዋ የእሳት አደጋ እንደሚያሰጋት ገልፀው፣ ከ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ በብዙዎች ሲጠየቅ የነበረው የሎንደን አዲስ የግንባታ ህግ (Building codes) በፍጥነት እንዲተገበርና የሎንዶን ቤቶች ወደ ጡብና የድንጋይ ቤቶች እንዲቀየሩ፤ በዚህም ሂደት ይህንን አቅጣጫ በመቃወም እንቅፋት የሚሆኑ ሰዎች ወደ ማረሚያ ቤት እንዲወርዱ አሳስበው ነበር፡፡
ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ ሲታይ ግን የሎንደን ከተማ ከንቲባ ምንም ያደረጉት ነገር አልነበረም፡፡ እ.ኤ.አ. መስከረም 2 ቀን 1666 ከሌሊቱ 7 ወይም 8 ሰዓት ገደማ ላይ ከአንድ ዳቦ መጋገሪያ ቤት የተነሳ እሳት ሎንደን ከተማን ማቀጣጠል ጀመረ፡፡  ከንቲባው ሰር ቶማስ ብሉድዎርዝ ከሌሊቱ 9 ሰዓት ከእንቅልፋቸው ተቀስቅሰው ስለ እሳት አደጋው ተነገራቸው፡፡ ሌሊት ላይ ከጣፋጭ እንቅልፋቸው በመቀስቀሳቸው እየተነጫነጩ ከቤት ወጥተው እሳቱን ተመለከቱ። ከዚያም ሌሎች በየአካባቢው የሚገኙ የከተማዋ ሃላፊዎች በቀላሉ ሊያጠፉት የሚችሉት እሳት እንደሆነ አሰቡና ተመልሰው ተኙ፡፡ ሎንደን እየተቃጠለች የከተማዋ መሪ እንቅልፍ ውስጥ መቆየትን መርጠው ነበር፡፡ ሌላው በአገሪቱ ውስጥ የሚከሰቱትን የእለት ተዕለት ሁኔታዎችና እንቅስቃሴዎች የሚመዘግበው ዝነኛው ሳሙኤል ፒፕስ፣ ሌሊት ላይ በቤት ሰራተኛው ተቀስቅሶ የእሳት ቃጠሎ እንደተነሳ ተነገረው፤ ከአልጋው ላይ ተነሳና በመስኮት በኩል ወደ ውጪ ተመለከተ፤ እሳቱ ሩቅ እንደሆነ ገመተና ተመልሶ ተኛ። ሎንደን ግን እየነደደች ነበር፡፡ እነዚህ ተፅእኖ ፈጣሪ ሰዎችና የህዝብ መሪዎች ለበጎው ሥራ ስላልፈጠኑ ታላቁ የሎንደን እሳት (The great fire of London) የሎንደንን ከተማ ሰማኒያ በመቶ ወደ አመድ ቀየረ፤ ከአንድ መቶ ሺ እስከ ሁለት መቶ ሺ ሰዎችን ቤት አልባ አደረገ፤ ስድስት ሰዎችም በቃጠሎው ሞቱ፡፡
“እሳት የሎንደን ከተማ ስጋት ነው” የሚለውን የንጉሱን ቃል ተከትሎ፣ የሎንደኑ ከንቲባ በፍጥነት አደጋውን ሊገቱ የሚችሉ አሰራሮችና ጥንቃቄዎች ላይ መሥራት ቢጀምሩ ኖሮ፣ አደጋው ከተከሰተም በኋላ ከንቲባውና ተፅእኖ ፈጣሪው ሳሙኤል ፒፕስ፣  ከአልጋቸው ላይ ተነስተው፣ የከተማዋን ሃብትና የሰው ሃይል አስተባብረው፣ በፍጥነት ወደ ስራ ቢገቡ ኖሮ ታላቁ የሎንደን እሳት ሊፈጠር ይችል ነበርን? ብለን መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ብዙዎች እንደሚገምቱት፤ ጉዳቱ በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንስ ነበር፤ የመሪዎች እና የተፅእኖ ፈጣሪዎች ቸልተኝነትና በምቾት ቀጠና (Comfort Zone) ውስጥ የመቆየት አባዜ፣ በአገርና በዜጎች ላይ የሚፈጥሯቸው ጉዳቶች ቀላል አይደሉም፡፡
በኢትዮጵያ በተጀመረው የፍቅር፣ የይቅርታና የመደመር አቅጣጫ ያልተደሰቱ ወገኖች፣ ለውጡን በተቃራኒው መንገድ ሊቀለብሱ ሌት ተቀን እየሰሩ እንደሚገኙ የለውጡ ሃዋሪያዎችና የመገናኛ ብዙሃን እየነገሩን ነው፡፡ እነዚህ ሃይላት ደግሞ በመንግስት አደረጃጀት ውስጥ ያሉ፣ ከዚህ ቀደም በነበረው አስተሳሰብና ድርጊት የተጠመቁ፤ ለውጡ እንዳይሳካ ተፅእኖ ለማሳደር ሌት ተቀን የሚሰሩ  እንደሆኑ ግንዛቤ ተወስዷል፡፡
ስለዚህ መሪዎችና ተፅእኖ ፈጣሪዎች በፍጥነት የፍቅር፣ የይቅርታና የመደመር  እሴቶችን ወደ አደባባይ ይዘው በመውጣት፣ ተቋማዊ አደረጃጀት በመፍጠርና ለለውጡ ግብአት የሚሆኑ አሰራሮችን በመዘርጋት፣ በተለያዩ ክፍተት በሚታይባቸው ጉዳዮች ዜጎችን በማሰልጠን፣ በማንቃትና በማደራጀት በፈጣኑ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መርከብ ላይ መሳፈር ይጠበቅባቸዋል፤ ጊዜ የለም! ይህ ካልሆነ ግን ክፉ አድራጊዎች እድል እያገኙ አገሪቷን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ሊወስዷት ይችላሉ፡፡
በአዲሱ የኢትዮጵያ የለውጥ አቅጣጫ ለመጓዝ መዘግየት የክፉ አድራጊ ሰዎችን ክፋት በፍጥነት እንዲሮጥ መፍቀድ ነው፡፡ ዜጎች በፍቅር በይቅርታና በአንድነት ናፍቆት ተሰቃይተዋል፤ በእኩልነትና በፍትህ ጥማት ጠውልገዋል፣ በብልፅግናና በሙላት ርቀት ደክመዋል፤ በስቃይና ተስፋ በመቁረጥ ውስጥ ሰንብተዋል፡፡ ናፍቆታቸው እውን እንዲሆን፤ ጥማታቸው እንዲረካ፣ እንዲበለፅጉና እንዲያድጉ፤ ስቃያቸው እንዲያበቃና ተስፋ እንዲያደርጉ በተለያየ ደረጃ ያሉ መሪዎች እና ተፅእኖ ፈጣሪዎች አዲሱን መንገድ እያበረቱ እንዲሄዱና አሮጌው መንገድ እንዲደክም በፍጥነት መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡
በነገራችን ላይ መሪና ተፅእኖ ፈጣሪዎች፤ በሰዎች አዕምሮ ላይ የሚፈጥሩት አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ አመለካከት፣ ድርጊትና ንግግር በቀላል የሚታይ አይደለም፡፡ በታሪክ ውስጥ ከፋፋይ መሪዎች የተከፋፈለ ህዝብ መፍጠር ችለዋል፤ የአንድነት መሪዎች ደግሞ አንድ ህዝብ መፍጠር ችለዋል፡፡
አሁን ኢትዮጵያ የተያያዘችው አዲሱ የመደመር መንገድ የለውጥ መሪዎችንና ተፅእኖ ፈጣሪዎችን አስፈላጊነትና  ሚና ከፍ ያደርገዋል፡፡ ለምን? ብሎ መጠየቅ አስፈላጊ ነው፡፡ የሚከተሉትን ሶስት ምክንያቶች መጥቀስ ተገቢ ነው፡-
1ኛ- ለውጡን ሰላም ወዳዱ የኢትዮጵያ ህዝብ እጅግ በጣም ይፈልገዋል፤
2ኛ- አሉታዊ ተፅእኖ ሊፈጥሩ የሚችሉ ሰዎች ደግሞ ለውጡን ለማደናቀፍ እጅግ ቆርጠዋል (በሚሊዮኖች በሚቆጠር የህዝብ ስብሰባ ላይ ቦንብ መወርወርና መሪውን ለመግደል መሞከር የተቆረጠ እንቅስቃሴ መኖሩን ያመለክታል)፤
3ኛ- የኢትዮጵያ ህዝብ ይህን ዕድል ያገኘው ከብዙ ዘመናት በኋላ በመሆኑ፣ ይህ ዕድል በአግባቡ ካልተመራ፣ የኢትዮጵያ ህዝብና የአገሪቱ መልክ ክፉኛ ይጎዳል፡፡ ይህን ዕድል መልሶ ማግኘት አዳጋችነቱ አያጠራጥርም፡፡  
በእነዚህ ሶስት ወሳኝ ምክንያቶች በየደረጃው ያሉ መሪዎችና ተፅእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች (ምሁራኖች፣ ተማሪዎች፣ የጦር መሪዎች፣ ወታደሮች፣ የአገር ደህንነት ባለሙያዎች፣ አርሶ አደሮች፣ የሃይማኖት ሰዎች፣አርቲስቶች፣ ባለሃብቶች፣ ጋዜጠኞች ወዘተ) በፈጣኑ መርከብ ላይ ተሳፍረው  የሚከተሉትን ሶስት ሚናዎች ሊጫወቱ ይገባቸዋል፡፡
1ኛ- መሪዎችና ተፅእኖ ፈጣሪዎች አሁን እየተቀኘንላቸው ያሉትን የፍቅር፣ የይቅርታና የመደመር እሴቶች በቤታቸው፣ በመስሪያ ቤታቸው፣ በተለያዩ መድረኮችና በሚዲያ አስፈላጊነታቸውን በማጉላት፣ በእነዚህ እሴቶች መኖር፣ እሴቶቹን ለሌላው ዜጋ በሚረዳውና በሚገባው መልኩ ማስተላለፍ፡፡ ሃብትን፣ እውቀትንና ክህሎትን በማስተባበር በአመለካከትና  በአዕምሮ ተሃድሶ ላይ አጥብቆ መሥራት፡፡
2ኛ- አዲሱን መንገድ መሸከም የሚችሉ ተቋማትን፣ አሰራሮችንና የሰው ሃይልን መገንባት ጊዜ የማይሰጠው አስቸኳይ ሚናቸው ሊሆን ይገባል፡፡
3ኛ- ከክፉ አድራጊዎች ይልቅ ፈጣኖችና ትጉሃን ሊሆኑ ይገባል፡፡ መልካም አድራጊዎች በዘገዩ መጠን ክፉ አድራጊዎች በፍጥነት ክፋታቸውን እንዲፈፅሙ ዕድል ይሰጣል፡፡
በዚህም ምክንያት እንደ ሎንደኑ ከተማ ከንቲባ ሰር ቶማስ ብሉድዎርዝ  እና ተፅእኖ ፈጣሪው ሳሙኤል ፒፕስ፤ ከተማ እየነደደ መልሶ መተኛትና በምቾት ቀጠና ውስጥ መሰንበት እንደማያዋጣ በመገንዘብ፣ በተለያየ ደረጃ የሚገኙ መሪዎችና ተፅእኖ ፈጣሪዎች  አዲሱን የዶ/ር ዐቢይን እና የጓዶቻቸውን የፍቅር፣የይቅርታና የመደመር መንገድ በፍጥነት በመቀላቀል፣ አዲሲቷን ኢትዮጵያን ለመፍጠር  ሊተጉ ይገባል፡፡
ቸር እንሰንብት!
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻቸው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል።

Read 1736 times