Saturday, 14 July 2018 12:02

‘ያም ሲያማ፣ ያም ሲያማ…’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)


     “--የምር ግን…ሁልጊዜ እኮ እየጓጓን መኖር አንችልም፡፡ በኢስታንቡል ድልድዮች እየጓጓን፣ በእነ ኒው ዮርክ ህንጻዎች እየጓጓን፣ በእነ ዴንማርክ የደስተኝነት ጣራ እየጓጓን፣ በስካንዲቪያ አገራት የሰላም አየር እየጓጓን፣ በእነ ታይላንድ ሆስፒታሎች እየጓጓን…በሁሉም እየጓጓን መኖር አንችልም፡፡ “እነሱ ሊያደርጉት ከቻሉ፣ እኛም ማድረግ እንችላለን” ማለት መቻል አለብን፡፡--”
   
    እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እንደ ጣት አሻራ ሁሉ የእያንዳንዳችን የምላስ አሻራ የተለየ ነው ይላሉ ሳይንቲስቶቹ፡፡ ለዚህስ እኛም መመስከር እንችላለን፡፡ ለምሳሌ ስብሰባ ላይ ጀርባ ካሉት ወንበሮች አካባቢ… “አቦ አትጨቅጭቁን፣ እንሂድበት!” የመድረክ መሪው ይቆጣሉ፡፡
“አሁን የተባለውን ማነው የተናገረው?” ዝም! ሁሉም በየሆዱ “ሞኝህን ጠቁሞ ጥርስ ሊገባልህ ነው!” አይነት ነገር ይላል፡፡
“ማነው የተናገረው?” ዝም! እንኳን ጠላት ጨምረን፣ አሁን ጠምደው የያዙንም ጀርባችንን ሊሰብሩት ደርሰዋል፡፡
“እንግዲያው እያንዳንድሽ የምላስ አሻራሽ ይወሰዳል፡፡ ያን ጊዜ የት እንደምትገቢ እናያለን”
እንዲህ ማድረግ ቢቻል ኖሮ እንዴት ደስ ይል ነበር! አለ አይደል…የሆነ አሉባልታ ሲነዛ ምንጭ ናቸው ተብለን የታሰብን ሰዎች ተሰብስበን፣ በ‘ምላስ አሻራ’ የሚረጋገጥ ቢሆን እንዴት አሪፍ ይሆን ነበር። አሉባልታ ትልቅ፣ በጣም ትልቅ ችግራችን ነው፡፡ አሉባልታ የሌለበት የህይወት ዘርፍ ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ ሸሚዝ በተለወጠ ቁጥር “ነገርኳችሁ እኮ! በስውር የሚሠራው ሥራ አለ፣ አለበለዛ ከየት አምጥቶ ነው እንዲህ አይነት ሸሚዝ የሚለብሰው?”
በፖለቲካችን አካባቢ የምንሰማቸው ‘ወሬዎች’ ወደ ቴሌቪዥን ድራማ ቢለወጡ  እስከሚቀጥለው ሚሌኒየም ባያደርሱ ነው! በአሉባልታ የሚፈታውና የሚታሠረው፣ ስልጣን ላይ የሚወጣውና ከስልጣን የሚወርደው፣ የሚጋባውና የሚፋታው…ወዘተ. መአት ነው፡፡
“ስማ እንንትናን ሸቤ አስገቡት እኮ!”
“አትለኝም! የት ሰማኸው?”
“በጣም ውስጥ አዋቂ ነው የነገረኝ”
“ታዲያ ለምንድነው እንዲሀ አይነት ዜና በሬድዮ፣ በቲቪ ምናምን ያልተነገረው?!”
“ተደብቆ ነዋ!”
“ለምን ይደበቃል! ከእንግዲህ ሁሉም ነገር በግልጽ ነው የሚካሄደው ተብሎ የለም እንዴ?!”
“እሱ ታሰረ ቢባል ችግር ሊፈጠር ይችላል ተብሎ ነው”
ታዲያላችሁ… አለ አይደል… “ሸቤ ገባ” የተባለው ሰው፤ የሆነ ስብሰባ ምናምን ላይ ‘ጉብ ብሎ’ በቴሌቪዥን ብቅ!
የበፊት አብዛኛው አሉባልታ ያው ግለሰብ ላይ ስለነበር ከፈለግን እንሰማለን፣ ካልፈለግን አንሰማም። “አይደለም አንድ፣ ለእኔ ስትል ለምን ሀያ አንድ ውሽማ አትይዝም!” አይነት ነገር ብለን ፋይሉን ልንዘጋ እንችላለን፡፡ ዘንድሮ ፖለቲካ ግን ተወደደም ተጠላም የእያንዳንዳችንን በር ውሎ አድሮም ቢሆን ማንኳኳቱ ስለማይቀር እንሰማለን፡፡
ከጥቂት ዓመታት በፊት አንድ ወዳጄ ‘ሰበር ዜና’ ያለውን ነገረኝ፡፡ ወደ ሐምሌ ነሀሴ አካባቢ ነው፡፡
“ስማ መስከረም ላይ ምን እንደሚሆን አልሰማህም?”
“አልሰማሁም፣ ምንድነው?”
“እንዴት አልሰማህም!” ያው በሆዱ… “የእኛ ብሎ ጋዜጠኛ!” ምናምን ሳይለኝ አልቀረም፡፡
“ንገረኝ፣ ምን ይሆናል?”
“ኮሚኒዝም ይታወጃል አሉ”
ሲነግረኝ በእርግጠኝነት ነው የነገረኝ፤ ደግሞም ለ‘ፍራንክ ቅርብ’ ስለነበር የነገረኝ “እሰይ ስለቴ ሰመረ!” ብሎ ሳይሆን “በቃ አለቀልን!” አይነት ነገር ነው፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ማህበራዊ ሚዲያ በመረጃ ልውውጥ ረገድ በጣም እየጠቀመ ነው፡፡ እንደውም የሚገርመው አሁን፣ አሁን ጠዋት ላይ በየአውቶብሱና በየካፌው ሰዉ ሁሉ ስማርት ስልኩ ላይ ኢንተርኔቱን ‘ሲበረብር’ ነው የሚታየው። ሰዋችን ምን ያህል መረጃ ፈላጊ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡ ሆኖም በርካታ ሸጋ ነገሮች ያሉትን ያህል የማንፈልጋቸውና እየሸሸናቸው ያሉ ነገሮችም ብዙ ናቸው፡፡ ከጠቃሚዎቹ መረጃዎች፣ ሃሳቦች፣ መጣጥፎች ምናምን ሌላ የሚያስደነግጡ ነገሮችም እየታዩ ነው። ምንም አይነት ‘መረጃ ይሁን ማስረጃ’ የሌላቸው ነገሮች ተጠቃሚውን በቀላሉ ወዳልተፈለገ አስተሳሰብ ሊከቱት ይችላሉ፡፡
በግለሰብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በማህበረሰቦችና ህዝቦች ደረጃ መጠራጠር ሊፈጥሩ ከሚችሉ ነገሮች እንራቅ በምንልበት ጊዜ ግን በተለዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ አተኩረው በ‘መረጃም’ ይሁን በ‘ሀሳብ’ መልክ የሚሰነዘሩ ነገሮች የምንፈልገው ግብ እንዳንደርስ ልጓም ሆነው እንዳይጎትቱን መጠንቀቁ የዜግነት ግዴታ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ሰብአዊነትም ነው፡፡ ስንዴውን ከእንክርዳድ መለየቱ አስቸጋሪ እየሆነ በመጣ ቁጥር በተሳሳቱ መረጃዎች የተሳሳቱ አመለካከቶች የማዳበርና ወደተሳሳሰቱ መንገዶች የመግባት አደጋውም ያንኑ ያህል ነው፡፡
አንድ የምዕራባውያን ቀልደኛ እንዲህ ብሎ ቀልዷል አሉ፡፡ “የቻይና ግምብ ከዓለም አስደናቂ ነገሮች አንዱ የሆነው ከአራት ሳምንታት በላይ ሳይበላሽ የቆየ ብቸኛ የቻይና ምርት በመሆኑ ነው” ብሏል፡፡ ሳይበላሹ የሚገኙ ነገሮች ማግኘት እድለኝነት ሆኗል። ተስፋዎቻችን እየጎለበቱ፣ ወደ ተግባርም እየተለወጡ እንዲሄዱ፣ እንደርስበት ያልነው ግብ ላይ እንድንደርስ፣ እንገነባለን ያልነውን አገራዊ መግባባት እንድንገባ ጠንካራና ሳይበላሽ የሚከርም ጽናት ያስፈልገናል፡፡
የምር ግን…ሁልጊዜ እኮ እየጓጓን መኖር አንችልም። በኢስታንቡል ድልድዮች እየጓጓን፣ በእነ ኒው ዮርክ ህንጻዎች እየጓጓን፣ በእነ ዴንማርክ የደስተኝነት ጣራ እየጓጓን፣ በስካንዲቪያ አገራት የሰላም አየር እየጓጓን፣ በእነ ታይላንድ ሆስፒታሎች እየጓጓን…በሁሉም እየጓጓን መኖር አንችልም፡፡ “እነሱ ሊያደርጉት ከቻሉ፣ እኛም ማድረግ እንችላለን” ማለት መቻል አለብን። (“ኢፍ ዘይ ካን ዱ ኢት፣ ዊ ካን ዱ ኢት!” እንዲሉ ‘ፈረንጆቹ።’) ለዚህ ደግሞ በመረጃና በሀሳብ ልውውጥ ላይ የምንረግጠውን ድንጋይ ለይቶ የማወቅ ነገር ግድ ይላል፡፡
“እየበላኸው ያለው ከረሜላ የሚጣፍጥ ይመስላል”
“አዎ፣ ይጣፍጣል”
“ምራቄን አመጣብኝ እኮ!”
መሀረብ አውጥቶ ይሰጠዋል፡፡
“ምን ሊያደርግልኝ ነው?”
“አፍህን ጥረግበት” አለውና አረፈው፡፡ ከመጓጓት አንደኛውን “ለእኔም አቅምሰኝ” ማለት አይሻልም! በቀደም ኔይማር እንደተንከባለለው፣ ዙሪያ ዙሪያውን መንከባለል ‘ጦም ያሳድራላ!’
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል……የእኛ ህብረተሰብ እኮ የሚረዳዳ፣ የሚተጋገዝ፣ አንዱ ሲያደናቅፈው ሌላው “እኔን ይድፋኝ!” የሚል፣ አንዱ ሲያስነጥሰው ሌላው “ይማርህ!” የሚል ነበር እኮ! እናማ ብዙ ነገሮችን ስናይ… አለ አይደል… “እነኛን ሁሉ እሴቶች ማን ወሰደብን!” እንላለን፡፡ (የፈረንጅ ጸሃፊ “አይቤን ማን ወሰደው?” ይላል፤ እኛ ግን “እኛነታችንን ማን ወሰደብን?” አይብ ‘ልጅና እንጀራ ልጅ’ ሳታደርገን በየቤታችን ተትረፍርፋ “አይቤን ማን ወሰዳት?” ለማለት ያብቃን፡፡) ምን ተፈጠረ…. የትብብር፣ የመተጋገዝ ገመዱን ማን በጠሰብን!…ይሄ ወደ ኋላ እየሄዱ ‘ማላዘን’ አይደለም…‘የትናንትን መናፈቅ’ አይደለም፡፡
እናማ…
ያም ሲያማ፣ ያም ሲያማ
ወገኔ ለእኔ ብለህ ስማ
የምትል ‘ዘመን ተሻጋሪ’ ስንኝ አለች፡፡ ዘንድሮ ‘እድሜ ለማህበራዊ ሚዲያ’… አለ አይደል… ‘ለእኔ ብለን’ ባንሰማም…ተለጥፎ ይገኛል፡፡
እኔ የምለው…ይሄ ዓለም ዋንጫ እኮ ‘ግንድ ግንዱን’ ገነደሰው አይደል! አሁን ሮናልዶና ሜሲ ገና በጠዋቱ ሻንጣቸውን ሸክፈው የአገራቸውን አውሮፕላን ይሳፈራሉ ብሎ ማን ያሰበ አለ! ግን ሆነ። ቀዳሚዎቻችን… “አይመጣምን ትተሽ ይመጣልን ያዢ” ይሉ የነበረው ‘አማርኛ ለማሳመር’ ብቻ አይደለም። ‘ይመጣልን ትተው አይመጣምን’ የያዙ በኳሱ ሜዳም፣ ከኳሱ ሜዳ ውጭም ውጤቱን እያዩት ነውና፡፡ በነገራችን ላይ… እነ ብራዚል፣ አርጀንቲና፣ ጀርመን፣ ጣልያን፣ ኔዘርላንድ የመሳሰሉት በየመንገዱ የተንጠባጠቡበት የዓለም ዋንጫ… አለ አይደል… ‘የጭቁኖች ዓለም ዋንጫ’ ነገር መሆኑ ነው እንዴ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1619 times