Saturday, 14 July 2018 11:56

የድንበር ጉዳዮች ትኩረት ይሻሉ

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(1 Vote)

 ባለፈው ሣምንት በሰሜን ምዕራብ እና በደቡብ ኢትዮጵያ በሚገኙ ሁለት የጠረፍ ከተሞች በተለያዩ መነሾዎች የተከሰቱት ጠንከር ያሉ ግጭቶች በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት ማስከተላቸው ሰምተናል፡፡ እነዚህ ግጭቶች የተከሰቱት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተዘጋጀው የጠረፍ ከተሞችን ችግሮች የመዳሰስ እና የፖሊሲ ምክረ ሐሳቦችን የመቀመር  ዓላማ ይዞ የተካሄደው አውደ ጥናት በተጠናቀቀ ማግስት ነበር፡፡   
ኢትዮጵያ ሞያሌ፣ ቋራ እና መተማን ከመሳሰሰሉ የጠረፍ ከተሞች የመጡ ሰዎች ተሳታፊዎች በዚሁ ጉባዔው ተሳታፊ እንደነበሩ እና ከአዲስ አበባ ወደ መጡበት በመመለስ ሳይ ሳሉ ነበር ግጭቶቹ ተከሰቱት -- የመተማው ግጭት ሰኔ 27 2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሞያሌው ደግሞ በማግስቱ ሰኔ 28 2010 ዓ.ም፡፡ በቋራ እና መተማ አካባቢ የተከሰተው ግጭት በመከላከያ ኃይል ጣልቃ ገብነት ቢቆምም፣ ግጭቱን ለዘለቄታው ለመፍታት እንዲያስችል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ለሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሐሰን አል በሽር የላኩትን መልዕክት መላካቸው ታውቋል፡፡
ከቋራ እና መተማው ግጭት አንድ ቀን ቀደም ብሎ ውጥረት ተለይቷት በማታውቀው የኢትዮጵያ ሞያሌ ከተማ የተከሰተው ጎሣን መሠረት ያደረገ ግጭት መሆኑን እና የመተማው ደግሞ ከእርሻ መሬት ጋር የተያያዘ እንደሆነ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የጠቀሱ ሲሆን፤ ከሁለቱ ከተሞች የመጡት የጉባዔው ተሳታፊዎች በስብሰባው ላይ ከሰጡት አስተያየት መረዳት እንደሚቻለው ግጭቶች በተደጋጋሚ  ይከሰታሉ፡፡
የድንበር ነገር ከህገ ወጥ ንግድ፣ ከህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ከጸጥታ ወዘተ ጋር የሚያያዝ ብቻ ሳይሆን፤ ሥር የሰደደ ከታሪክ ጋር የተያያዘ ችግር የሚታይበት ነው፡፡ በዚህ የተነሳ በወዲያኛው ሣምንት መጨረሻ (ሰኔ 23 እና 24) ይህኑን የድንበር አካባቢ ጉዳይ የሚፈትሽ አንድ አውደ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተካሂዶ ነበር፡፡ በዚህ አውደ ጥናት በርካታ የጥናት ጽሑፎች የቀረቡ ሲሆን ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የተለያዩ ወገኖች በመጋበዝ ሰፊ ውይይት ተደጓል፡፡
የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶ/ር ፍቃዱ አዱኛ የድንበር ጉዳይ መንግስትን በተለይም የጸጥታ መዋቅሩን (መከላከያን፣ ፖሊስን፣ ደህንነትን) ብቻ የሚመለከት አጀንዳ ተደርጎ እንደሚታይ ጠቅሰው፤ ይህ አመለካከት ሊቀየር እንደሚገባ እና የድንበር ጉዳዮችን ቀለል አድርጎ ማየት እንደሚገባ እና ከድንበር ጋር ተያያዥ ለሆኑ የተለያዩ ችግሮች በውይይት መፍትሔ ማፈላለግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
በዚህ አውደ ጥናት የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የፌዴራል ገቢዎች እና ጉምሩክ ባለስልጣን፣ የፌዴራል ጉዳዮች እና የአርብቶ አደር ልማት ሚኒስቴር፣ ኢሚግሬሽን፣ አራ (AARA)፣ የስደተኞች እና የስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር ተወካዮች የተገኙ ሲሆን፤ የጉዳዩ ዋና ባለቤቶች የሆኑት የጠረፍ ከተማ ነዋሪዎችም በአውደ ጥናቱ ተካፋይ ሆነዋል፡፡ በዚሁ መሠረት ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ከኩርሙክ፣ ከመተማ፣ ከሞያሌ እና ከሽሬ የመጡ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ የዞን ወይም የወረዳ መስተዳድር የሥራ ኃላፊዎች ታድመዋል፡፡
በተጨማሪም ወደፊት በሚካሄዱ ጥናቶች ተሳታፊ ይሆኑ ዘንድ ለጠረፍ ከተሞቹ ቅርብ የሆኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በአውደ ጥናቱ ተሳታፊ መሆናቸውን  የገለጹት ዶ/ር ፍቃዱ አዱኛ፤ ከጎንደር፣ ከአሶሳ እና ከቡሌሆራ ዩኒቨርስቲዎች የተጋበዙ ምሁራን በአውደ ጥናቱ እንዲሳተፉ መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ እንዲሁም ከኡጋንዳ ማካሬሬ ዩኒቨርስቲ፣ ከሱዳኑ ካርቱም ዩኒቨርስቲ እና ከኖርዌ ዩኒቨርስቲ የተወከሉ ምሁራን በአውደ ጥናቱ ተካፋይ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡
በድንበር አካባቢ ያሉ ማህበረሰቦችን ህይወት ለማሻሻል፤ እንዲሁም ከጸጥታ፣ ከስደት፣ ከህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፤ ከህገ ወጥ ንግድ ጋር ተያያዥ የሆኑ ችግሮችን ለማስወገድ የሚያስችሉ የተለያዩ ጥናቶች፤ በኢትዮ-ኬንያ ድንበር በምትገኘው ሞያሌ እና በኢትዮ- ሱዳን ድንበር ባለችው ኩርሙክ ላይ ያተኮሩ ጥናቶች ከዚህ ቀደም መካሄዳቸውን የጠቀሱት የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶ/ር ፍቃዱ ገልጸዋል፡፡ ‹‹የምሥራቅ አፍሪካ የጠረፍ ከተሞች እንቅስቃሴ›› (Borederland Dynamics in East Africa) በሚል ርዕስ በተካሄደው ጥናት በክፍለ አህጉሩ የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ተሳታፊ መሆናቸውን እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአንትሮፖሎጂ ትምህርት ክፍል በተለያዩ የሐገራችን የጠረፍ አካባቢዎች ያካሄደውን ጥናት መነሻ በማድረግ የፖለሲ ምክረ ሐሳብ (Policy brief) በማዘጋጀት ለሚመለከታቸው የክልል እና የፌዴራል የመንግስት ተቋማት እንዲደርስ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቀዳሚ ሥራ ዕውቀት ማመንጨት (Knowledge production) መሆኑን ያስታወሱት ዶ/ር ፍቃዱ፤ ‹‹እኛ ዕውቀት አመንጭተን በዓለም አቀፍ የጥናት መጽሔቶች በማሳተም ብቻ መወሰን የለብንም ብለን፤ አባቶ እና እናቶች ከመተማ፣ ከቦረና፣ ከሞያሌ፣ ከኩርሙክ እና ከሽሬ መጥተው ያዳምጡ ብለን ጋብዘናል፡፡ እነሱም ይኼ ጉዳይ አልታየም፤ ይኼ ይጨመር ይኼ ይቀነስ እንዲሉ ዕድል ፈጥረናል›› ብለዋል፡፡
ይሁንና የመንግስት ተቋማት የተላከላቸውን የፖሊሲ ምክረ ሐሳብ ተመልክተው ‹‹የጻፋችሁት ነገር ጥሩ ነው፤ መጥፎ ነው›› የሚል ምላሽ አለመስጠታቸው ቅር እንዳሰኛቸው ገልጸው፤ በንጽጽር የዩጋንዳ መንግስትን ምላሽ አንስተዋል፡፡ የሥራ ባልደረባቸው የሆኑ አንድ የዩጋንዳ ማካሬሬ ዩኒቨርስቲ መምህር፤ ‹‹የምሥራቅ አፍሪካ የጠረፍ ከተሞች እንቅስቃሴ›› በሚል ርዕስ በሚካሄደው የጥናት ፕሮጀክት የተካሄዱን ምርምሮች መሠረት በማድረግ ለዩጋንዳ መንግስት የፖለሲ ምክረ ሐሳብ (Policy brief) መላካቸውን እና ከፕሬዚዳንቱ ጽሕፈት ቤት ‹‹የላካችሁልን የፖሊሲ ምክረ ሐሳብ ደርሶናል፡፡ ኑና እንነጋገር›› የሚል የፈጣን ምላሽ እንደ ደረሳቸው በመጥቀስ አስተያየት ሰጥተዋል።
‹‹የድንበር ጉዳይን ከማዕከል ለይቶ ማየት ተገቢ አይደለም፡፡ ድንበር የማዕከሉ መስታወት ወይም ነጸብራቅ ነው፡፡ የድንበር ጉዳይ ከጸጥታ ሥራ ጋር ብቻ ተቆራኝቶ መታየት አይኖርበትም›› ያሉት ዶ/ር ፍቃዱ፤ የአፍሪካ የድንበር አካባቢዎች ታሪካዊ እና ማህበረሰባዊ ተጨባጭ ሁኔታዎች መንግስታት ‹‹ለዘብ ያለ የድንበር ፖሊሲ›› (Soft boarder policy) እንዲቀርጹ የሚያስገድዱ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ‹‹ድንበርን የሚጠብቀው ወታደር ሳይሆን ህዝብ ነው›› ብለዋል። መንግስታት ጥብቅ የሆነ ድንበር ፖሊሲ ሲከተሉ በጠረፍ አካባቢ የሚኖረው ማህበረሰብ እንደሚጎዳ የገለጹት እና ህይወቱን ማሻሻል የሚችሉ አካባቢያዊ ምቹ ሁኔታዎችን ወይም በእጁ ያለውን ሐብት መጠቀም እንዳይችል ያደርገዋል ያሉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲው መምህር ዶ/ር ፍቃዱ፤ በአብነት ጥብቅ የጉምሩክ ህጎች ከጠረፍ ንግድ ሥራ በቀር ሌላ የኑሮ መሠረት የሌላቸውን ዜጎች ህይወት ፈታኝ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
በድንበር አካባቢ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ኢንቨስትመንቶች አለመኖራቸውን በመጥቀስ የጠረፍ ንግድ ሥራን የሚያበረታታ ሁኔታ መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን በማስታወስ፤ የጠረፍ ንግድ ሥራን ‹‹ኮንትሮባንድ›› በሚል አስደንጋጭ ቃል መጥቀሱን አቁመን፤ ‹‹ኢ-መደበኛ ድንበር ተሻጋሪ ንግድ›› የሚል ለዘብ ያለ ስያሜ በመስጠት፤ የጠረፍ አካባቢ ህዝብ ኑሮውን ለመደገፍ በሚያስችል የንግድ ሥራ እንዲሰማራ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ዶ/ር ፍቃዱ አዱኛ ተናግረዋል፡፡
ይህን ሐሳብ መነሻ በማድረግ አስተያየት የሰጡ አንድ የሥራ ኃላፊ፤ ከድንበር ጋር ተያያዥ የሆኑ ችግሮችን ለማስወገድ የኢኮኖሚ ውህደት መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአሁኑ ጊዜ ድንበርን ሙሉ በሙሉ ለማስከበር የሚያስችል ቁመና እንደሌለን እና ድንበርን ላላ የማድረጉ ሐሳብ አሁን ሥልጣን ላይ ያለው አመራር ከሚያራምደው አቋም አንጻር የተቃኘ እንዲሆን ከተደረገ ‹‹ልዝብ ድንበር›› የመፍጠሩ ምክረ ሐሳብ ተደማጭነት እንደሚያገኝ እና የኢኮኖሚ ውህደት የመፍጠር ጉዳይም የበርካታ የአፍሪካ ሐገራት አቋም እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
የጉባዔው ተሳታፊዎች የተለያዩ የድንበር አካባቢ ችግሮችን እየጠቀሱ ሰፊ ውይይት ያደረጉ ሲሆን፤ ከኢሚግሬሽ የተወከሉ አንድ ተሳታፊ በበኩላቸው፤ በድንበር አካባቢ ነጻ ቀጣና (በፈር ዞን) አለመኖሩን እንደ ችግር ጠቅሰው፤ አብዛኞቹ የጠረፍ ከተሞች ቀደም ሲል የድንበር ኬላዎች የነበሩ እና ከተሞቹ ከድንበሩ ሥር ተጠግተው የተቆረቆሩ፤ እንዲሁም  በዕቅድ ያልተገነቡ ከተሞች በመሆናቸው የተሟላ ማዘጋጀቤታዊ አግልግሎት እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡
ይህ የድንበር ከተሞች አመሰራረት ያለውን ችግሩን ውስብስብ አድርጎታል ያሉት የሥራ ኃላፊ፤ በጅቡቲ - በሱማሊያ - በሱዳን እና በኢትዮጵያ መካከል ባለው ድንበር አካባቢ ያሉት እንደ ቀብሪበያህ እና ተፈሪ በር የመሳሰሉ የጠረፍ ከተሞች ኬላ እንደነበሩ ጠቅሰው፤ ዛሬ የእነዚህን ከተሞች ማዘጋጃቤታዊ አገልግሎት ለማሻሻል የሚያስችል የማስተር ፕላን ዝግጅት ብንጀምር፤ የጎረቤት ሐገራት ይህን እንቅስቃሴአችንን በበጎ እንደማይመለከቱት እና ይህም ችግሩን ይበልጥ ውስብስብ እንደሚያደርገው ገልጸዋል፡፡
‹‹መንግስት ግልጽ የድንበር አስተዳደር ፖሊሲ ሊኖረው ይገባል›› ያሉት የኢሚግሬሽኑ ተወካይ፤ ባለፉት ዓመታት እንደታየው ችግሩን አሳንሰን ከተመለከትነው በድንበር አካባቢ መስራት ያለብን ሥራ ለሌላ መቶ ዓመት ተወዝፎ ይቀመጣል የሚል ስጋት እንዳላቸው እና ለጉዳዩ በቂ ትኩረት ካልተሰጠው በመጪዎቹ ጥቂት ዓመታት ችግሩ ለመፍታት በሚያስቸግር ደረጃ ውስብስብ እንደሚሆን እና ትልቅ እሣት የሚጭር ችግር ይሆናል የሚል ሥጋታቸውን አንጸባርቀዋል፡፡
በቅርቡ ከኤርትራ ጋር ያለውን የድንበር ችግር ለመፍታት ሐገራችን የወሰደችው እርምጃ የሚደነቅ መሆኑን የጠቀሱት አስተያየት ሰጪ፤ ‹‹አሁን ትኩረታችን የተሳበው በውስጥ ጉዳዮች ነው፡፡ የአስተዳደር ወሰንን እንደ ድንበር የመቁጠር አዝማሚያም እየተበራከተ ነው፡፡ ከጎረቤት ሐገራት ጋር ካለው ድንበር ይልቅ በክልሎች መካከል ያለው የአስተዳደር ወሰን ትልቅ አጀንዳ ሆኗል›› ብለዋል፡፡
ለሁለት ቀናት በቆየው በዚህ አውደ ጥናት የሞያሌ እና የመተማ አካባቢ ድንበር ጉዳዮች የተዳሰሱ ሲሆን፤ የቀቡት ጥናቶችም የድንበር አካባቢ ጉዳዮች ውስብስብ እና የመንግስትን ትኩረት የሚሹ መሆናቸውን የሚያስገነዝቡ ናቸው፡፡ በድንበር አካባቢ በሚኖሩት ማህበረሰቦች መካከል የሚታየው ግንኙነት ጥብቅ ትስስርን የሚያንጸባርቅ እና አልፎ አልፎም ግጭት የሚያስተናግድ ነወ፡፡ ለምሣሌ በኢትዮጵያ እና በሱዳን ህዝቦች መካከል ለረጅም ዘመናት የዘለቀ የወንድማማችነት መንፈስ የሚንጸባረቅበት ሰላማዊ ግንኙነት መኖሩን የገለጹት ከመተማ የመጡ አንድ አባት፤ አልፎ አልፎ ከእርሻ መሬት ጋር በተያያዘ ድንገት ግጭት እንደሚፈጠር ለታዳሚው አስረድተዋል፡፡
ሰኔ 23-24 የተካሄደው አውደ ጥናት እንደ ተጠናቀቀ በመተማ ግጭት መከሰቱን ባለፈው ሣምንት መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፤ ሱዳንን ከኢትዮጵያ በሚያዋስነው የምዕራብ ጎንደር ዞን፣ መተማ አካባቢ በሚገኝ የእርሻ መሬት ይገባኛል ጥያቄ ምክንያት የተቀሰቀሰው ግጭት 13 ሰዎችን ለህይወት መጥፋት እና ለአካል ጉዳት የዳረገ ነበር፡፡ ከመተማ ከተማ የሚጡ አንድ አዛውንት እንደ ገለፁት፤ በከተማ ነዋሪዎች መካካል የሚታይ ግጭት የለም፡፡ በሱዳን ጋላባት እና በኢትዮጵያ መተማ ከተማ ነዋሪዎች መካከል ያለው ግንኙነት በጣም የሚያስደስት ሆኖ ሳለ በአርሦ አደሮች በኩል ግን አሳዛኝ ግጭት ይታያል ብለዋል፡፡
‹‹እኛ እና ሱዳን ሰላም ነነ፤ እኛ እና ሱዳን ጠቦች ነነ የሚለው ሁለት አፍ ሆነ›› ተብሏል በሚል አስተያየት መስጠት የጀመሩት አዛውንት፤ ‹‹አዎ፤ የሱዳን ጋላባት ከተማ እና የሐበሻ መተማ ከተማ ነዋሪዎች በመካከላችን ድንበር ሆኖ የሚገኘው አንድ ድልድይ ነው፡፡ እኛ ሰላም ነነ፤ ተቃቅፋን፣ ተዋደን እንኖራለን። ቋንቋም እንወራረሳለን፡፡ አሁን የእኛ ችግር የእርሻ መሬት ላይ ነው፡፡ ድንበሩ ከዚህ እስከዚህ የሱዳን ነው። ከእዚህ እስከ እዚህ የሐበሻ ነው ተብሎ የተከለለ መሬት የለም፡፡ ከዚህ ቀደም በመፈራራት እንኖር ነበር። አሁን በመደፋፈር ነው፡፡ መጥተው ክምር ያቃጥላሉ፡፡ አሁን ሰኔ የሰሊጥ ወቅት ነው፡፡ እነሱ 75 በሬ ነድተው ወስደዋል›› በማለት ያለውን ችግር አብራርተዋል፡፡
ከፌዴራል ገቢዎች እና ጉምሩክ ባለስልጣን የተወከሉት የጉባዔው ተሳታፊ፤ በድንበር ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሰፊ ጥናት ለመጀመሪያ ጊዜ መደረጉን በማድነቅ፤ የፕሮጀክቱን አስተባባሪዎች ካመሰገኑ በኋላ መደበኛ (ህጋዊ) ያልሆነ የድንበር ንግድ እንዲኖር መፍቀድ ያስፈልጋል በሚል በጉባዔው የተነሳውን ሐሳብ ተንተርሰው ባነሱት ጥያቄ፤ ‹‹ለመሆኑ  ኢ-መደበኛ ድንበር ተሻጋሪ ንግድ›› ሲባል ምን ማለት ነው? እንዲህ ያለ ንግድ እንዲኖር መፍቀድ የሚጠቅመው ማንን ነው? የሚጎዳውስ ማንን ነው? ሐገራዊ አንድምታውስ ምንድነው?›› ብለዋል፡፡
አንዳንድ ያደጉ ሐገራት ‹‹ኢ-መደበኛ ድንበር ተሻጋሪ የንግድ ሥራ›› ምንድነው የሚለውን በህግ ደንግገው ማስቀመጣቸውን የገለጹት የፌዴራል ገቢዎች እና ጉምሩክ ባለስልጣን ተወካይ፤ ‹‹ኢ-መደበኛ ድንበር ተሻጋሪ ንግድ ሲሉ፤ የህግ ገደብ ያልተደረገባቸውን ቀረጥ እና ታክስ ያልተከፈለባቸውን ሸቀጣሸቀጥ ወይም ዕቃዎች ግብይትን ለመጥቀስ ሲሆን፤ በተቃራኒው ኮንትሮባንድ ሲባል፤ የሕግ ገደብ እና ክልከላ የተደረገባቸውን እንደ ጦር መሣሪያ፣ አደንዛዥ ዕጽ እና መድኃኒት ያሉ ሸቀጦችን ለማመልከት ነው›› ብለዋል፡፡
የተጠቀሱት ሐገራት ‹‹ኢ-መደበኛ ድንበር ተሻጋሪ ንግድ›› የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ጠቃሚ መሆኑን እንደሚቀበሉ እና ኮንትሮባድን ደግሞ በጥብቅ እንደሚከላከሉ የገለጹት የጉምሩኩ ተወካይ፤ ከራሳቸው ሁኔታ ጋር የተጣጣመ ህግ አውጥተው እንደሚሰሩ እና የጠረፍ ንግድን የሚቆጣጠሩበት በቴክኖሎጂ የታገዘ ጠንካራ የቁጥጥር ስርዓት እንዳላቸውም አመልክተዋል፡፡
አያይዘውም፤ በኢትዮጵያ የጉምሩክ አዋጅ ድንጋጌ፤ ኮንትሮባንድ ‹‹የተከለከለ፣ ገደብ የተደረገበት፣ ቀረጥ እና ታክስ ያልተከፈለበት ዕቃ›› መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህ መሠረት በኢትዮጵያ ኮንትሮባንድ የሚለው ጽንሰ ሐሳብ ኢ-መደበኛ ድንበር ተሻጋሪ ንግድን ያጠቃልላል›› ብለዋል፡፡
በመሆኑም ሌሎች ሐገራት ‹‹ኢ-መደበኛ ድንበር ተሻጋሪ ንግድ›› የሚሉት የንግድ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ኮንትሮባንድ እንደሚባል የተናገሩት የጉባዔው ተሳታፊ፤ ሆኖም ጉዳዩ በተወሰነ የድንበር አካባቢ ከሚኖሩ ሰዎች አንጻር ብቻ ሳይሆን በሐገር አቀፍ ደረጃ ካለው አንድምታ አንጻር መታየት አለበት ብለዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በጉምሩክ የቁጥጥር ስርዓት በጣም ከፍተኛ ችግሮች መኖራቸውን እና በጠረፍ አካባቢ ያለው ህብረተሰብ ኑሮውን በንግድ ሥራ ለመደገፍ የሚችልበት ዕድል ባለማግኘቱ ከፍተኛ ችግር እንደሚገጥመው እናውቃለን ካሉ በኋላ፤ ‹‹ኢ-መደበኛ ድንበር ተሻጋሪ ንግድን›› መፍቀድ በድንበር አካባቢ ለሚኖረው ህብረተሰብ ችግር ማቃለያ ይሆናል ስንል፤ መፍትሔው ዘላቂ ነው ወይ የሚለውን ከግምት ማስገባት ይኖርብናል በማለት ጥናቱ ትንሽ ጠለቅ ብሎ ሊመለከታቸው የሚገቡ ነገሮች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡
አያይዘውም፤ ‹‹እስከ 2008 ዓ.ም ድረስ በየዓመቱ በአማካይ ከ200 እስከ 300 ሚሊየን ብር የሚገመት የበኮንትሮባንድ ዕቃ ይያዛል›› ያሉት የጉምሩኩ ተወካይ፤ ይህ አኃዝ ባለው የጉምሩክ ቁጥጥር ስርዓት ብልሹነት እና ድክመት የተነሳ የሚያልፈውን የኮንትሮባንድ ዕቃ እንደማይጨምር ተናግረዋል፡፡
ይህ አኃዝ በ2008 ዓ.ም 905 ሚሊየን ብር እንደ ነበር እና በ2009 እና 2010 ዓ.ም ደግሞ በዓመት አንድ ቢሊየን ብር እንደደረሰ ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህ ህገ ወጥ እንቅስቃሴም ተጠቃሚ የሚሆኑት የጠረፍ አካባቢ ነዋሪዎች አይደሉም ብለዋል፡፡
ከዚህ እንቅስቃሴ ተጠቃሚ የሚሆኑት ዕቃውን ወደ መሀል ሐገር የሚያስገቡት ኮንትሮባንዲስቶች ናቸው፡፡ ከዚህ ኮንትሮባንድ ተጠቃሚ የሆኑት በጠፈር አካባቢ ያሉት አነስተኛ ነጋዴዎች አይደሉም። በጠፈር አካባቢ ያሉት አነስተኛ ነጋዴዎች ከአንድ የሸቀጥ ልውውጥ መቶ ወይም ሁለት መቶ ብር ለማግኘት እንደሚሰሩ እና በዝቅተኛ ዋጋ የሚቀርበው ይህን ያህል ዕቃ ወደ መሐል ሐገር ሲገባ፤ ሐገር በቀል ኢንዱስትሪውን ገበያ በማሳጣት ዘርፉን እንደሚጎዳው አስረድተዋል፡፡
ይህ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ በማህበራዊ እና በሐገር ደህንነት ላይ የሚያስከትለው አደጋ ከፍተኛ ነው ያሉት የጉምሩክ ተወካይ፤ ወደ ሐገር ቤት ከሚገባው የኮንትሮባንድ ዕቃ ውስጥ በብዙ ሚሊየን ብር የሚገመት የጦር መሣሪያ፣ አደንዛዥ ዕጽ እና መድኃኒት መሆኑን ያለው መረጃ ያመለክታል በማለት ‹‹ኢ-መደበኛ ድንበር ተሻጋሪ ንግድ›› በጠረፍ አካባቢ ላለው ህብረተሰብ ይጠቅማል ወይ የሚለው ጉዳይ በደንብ መፈተሽ እንደሚኖርበት ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት ከተቆጣጣሪው ይልቅ ኮንትሮባንዲስቱ የረቀቀ የቴክኖሎጂ አቅም እንዳለው እና ነፍስ ያለው ዶሮ ውስጥ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃ በመደበቅ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን ለማስገባት ሲጥሩ ይታያል ብለዋል፡፡
የድንበር ጉዳይ በተለያየ ጊዜ የተለያየ አመለካከት የሚንጸባረቅበት መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ፍቃዱ አዱኛ፤ የድንበር ጉዳይ አንዳንድ ጊዜ የመጥበቅ ሌላ ጊዜ የመላላት ሁኔታ እንደሚታይበት እና በአሁኑ ወቅት ምዕራባዊ መንግስታት ድንበር ማጥበቅ መጀመራቸውን ከጠቀሱ በኋላ፤ ‹‹የድንበር ጥበቃ ጉዳይ ከሉዓላዊነት ጋር የተያያዘ በመሆኑ ጥበቃ የማይቀር ቢሆንም፤ እኛ እንደ ፖሊሲ ምክረ ሐሳብ የምናቀርበው ለዘብ ያለ የድንበር ፖሊሲን ነው›› ብለዋል፡፡
‹‹እኛ እንደ ማንኛውም ሰው ኮንትሮባንድን እንቃወማለን፡፡ ኮንትሮባንዲስቶች በሚሊዮን ሲነግዱ እንቃወማለን፡፡ ሆኖም መታየት ያለባቸው ሌሎች ጉዳዮችም አሉ፡፡ ለምሣሌ፤ የኢትዮጵያ ሞያሌ ነዋሪዎችን ብንወስድ ከድንበር ባሻገር ካሉት ህዝቦች ጋር በአመጋገብ፣ በአለባበስ ባህል እና በአኗኗር ዘዬ ተመሳሳይ በመሆናቸው ከድንበር ማዶ ካለችው ኬንያ ሞያሌ የሚፈልጉትን ብዙ ነገር ያገኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሞያሌ ከአዲስ አበባ 800 ኪሜ ይርቃል፡፡ ነገር ግን ከኬንያ ሞያሌ ያለው ርቀት 200 ኪሜ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ አካባቢ የኢትዮጵያ ሞያሌ ነዋሪ የሚፈልገው ሩዝ ይገኛል፡፡ አንድ ኪሎ ሩዝ ከኬንያ ሞያሌ ሲመጣ ዋጋው 10 ብር ሊሆን ይችላል፡፡ ከአዲስ አበባ ሲመጣ ዋጋው ይጨምራል፡፡
‹‹በተመሳሳይ በኢትዮጵያ- ሱዳን ድንበር ባለችው ኩርሙክ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አለባበሳቸው ከሱዳን ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ሁለቱ ህዝቦች ተመሳሳይ የአለባበስ ባህል ያላቸው በመሆኑ፣ ልብሱም ከአካባቢው የአየር ጸባይ ጋር ተስማሚ በመሆኑ የሚፈልጉትን ልብስ በዝቅተኛ ዋጋ ከሱዳን መግዛት ይችላሉ፡፡ ይህን ሁኔታ በመረዳት የኢጋድ አባል ሐገር መንግስታት የድንበር ንግድ እንዲኖር ውሳኔ አሳልፈዋል። በዚህ ስምምነት እስከ 1 ሺህ ዶላር ድረስ የድንበር ንግድ እንዲኖር መፍቀዳቸው ይታወቃል፡፡ በመሆኑም በወር ሁለት ጊዜ ተዘርዝሮ የተፈቀደላቸውን ዕቃ ብቻ ይገዛሉ፡፡ ሆኖም አንዳንዶቹ ዕቃዎች በአካባቢው ተፈላጊ ያልሆኑ እና የተፈቀደው ገንዘብም ትንሽ ነው፡፡ ሆኖም በዚህ ንግድ ግብር ይከፍላሉ፡፡ ከተፈቀደው ብር መጠን በላይ እንዳይሄዱም ክትትል ይደረግባቸዋል፡፡ ይህን ውሳኔ ተከትሎ በሞያሌ ወደ 40 ሰዎች ፈቃድ አወጡ፡፡ እነዚህ ሰዎች ግብር ሲከፍሉ፤ ሌሎች በህገ ወጥ ንግዱ ቀጥለዋል፡፡ ስለዚህ ፈቃድ የወሰዱ ሰዎች በዓመቱ መለሱ፡፡ እንዲህ ዓይነት ችግር አለ›› ብለዋል፡፡
በመጨረሻም፤ ዶ/ር ፍቃዱ ከተሳታፊዎች የቀረቡት አስተያየቶች ለፖሊሲ ምክረ ሐሳቡ ዝግጅት ግብአት እንደሚሆን በመግለጽ፤  የሶሻል አንትሮፖሎጂ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ዶ/ር ተሾመ ኢማና የመዝጊያ ንግግር እንዲያደርጉ ጋብዘዋል፡፡ ዶ/ር ተሸመም ፕሮጀክቱን በተለያየ አግባብ የደገፉ ወገኖችን እና አውደ ጥናቱን ተሳታፊዎች በማመስገን ለሁለት ቀናት የዘለቀው ጉባዔ መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡

Read 1463 times