Saturday, 14 July 2018 11:55

ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ዛሬ አዲስ አበባ ይገባሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

 አሊ ቢራ፣ መሃሙድ አህመድ፣ ሃጫሉ ሁንዴሳ… በሚሊኒየም አዳራሽ ያዜማሉ

    የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሣያስ አፈወርቂ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባደረጉላቸው ግብዣ መሰረት  ዛሬ ረፋድ ላይ ለይፋዊ ጉብኝት አዲስ አበባ የሚገቡ ሲሆን ከቦሌ ዓለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጀምሮ እስከ ቤተመንግስት ድረስ ደማቅ ህዝባዊ አቀባበል እንደሚደረግላቸው ታውቋል፡፡
ከ20 ዓመታት በኋላ ወደ አዲስ አበባ የሚመጡት ፕሬዚዳንት ኢሣያስ አፈወርቂ፤ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ ከፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ እና ከአፍሪካ ህብረት ዋና ፀሃፊ ሙሣ ፋኪ ጋር ይወያያሉ ተብሏል፡፡
በሚሊኒየም አዳራሽ ነገ እሁድ ምሽት ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በሚደረገው የእራት ግብዣ ላይ በርካታ ታዋቂ ድምጻውያን የኪነ ጥበብ ሥራዎቻቸውን የሚያቀርቡ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ አንጋፋው ድምፃዊ አሊ ቢራ፣ መሃመድ አህመድ፣ ጃኪ ጎሲ፣ ሃጫሉ ሁንዴሳ እና ሌሎችም ያቀነቅናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በኢትዮጵያ የ3 ቀናት ጉብኝት የሚያደርጉ ሲሆን የአዋሳውን የኢንዱትሪፓርክ ይጎበኟቸዋል ከተባሉት ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡
ስታዲየም አካባቢ የሚገኘውና ቀድሞ የኤርትራ ኢምባሲ የነበረው ቢሮም በነገው እለት በይፋ “በኢትዮጵያ የኤርትራ ኢምባሲ” ሆኖ ስራውን ይጀምራል ተብሏል፡፡
ባለፈው ሣምንት እሁድ ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ በአስመራ እጅግ ደማቅና አስደማሚ አቀባበል የተደረገላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ በሁለቱ ሃገራት መካከል ይፋዊ እርቅ የሚፈጥር ባለ አምስት ነጥብ ስምምነት ከኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ተፈራርመው መመለሳቸው ይታወቃል፡፡
ኤርትራ በ1983 ነፃነቷን ማግኘቷን ተከትሎ፣ ላለፉት 27 ዓመታት አገሪቷን በፕሬዚዳንትነት እየመሩ የሚገኙት የ72 አመቱ ፕሬዚዳንት ኢሣያስ አፈወርቂ፤ የሁለቱን ሃገራት ህዝቦች ለማቀራረብ ተከታታይ ስራዎችን እንደሚሠሩ ለሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ  አስታውቀዋል፡፡
በአጭር ጊዜ ውስጥ በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል የፈነጠቀውን የሰላምና የተስፋ ብርሃን በተመለከተ የታሪክ ምሁሩ ፕ/ር ገብሩ ታረቀ ለአዲስ አድማስ በሰጡት አስተያየት፤ “በአግራሞትና በመደነቅ ነው ያየሁት፡፡ ምክንያቱም ሂደቱ በጣም ፈጣን ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አስመራ ሄደው ባለ አምስት ነጥብ ስምምነት መፈራረም ያልተጠበቀና አስገራሚ፣ አንዳንዴም አስደንጋጭ ሆኖ አገኘዋለሁ፡፡ ይህ የሠላም ስምምነት የቀጠናውን ሁኔታ ይቀይረዋል የሚል ግምት አለኝ፡፡” ብለዋል፡፡
በኤርትራ አስመራ ልዩ ስሙ አባሻውል በተባለ ስፍራ የተወለዱት ኢሣያስ አፈወርቂ፤ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአስመራ በሚገኘው ልኡል መኮንን ት/ቤት  ከተማሩ በኋላ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ አዲስ አበባ መጥተው፣ የቀድሞው የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርሲቲን የተቀላቀሉ ሲሆን የኢንጂነሪንግ ተማሪ እንደነበሩም ይታወቃል፡፡ እ.ኤ.አ በ1966 የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን በማቋረጥ በሱዳን በኩል ይንቀሳቀስ የነበረውን ኤርትራ ነፃነት ግንባርን እንደተቀላቀሉ ግለ ታሪካቸው ያመለክታል፡፡ በወጣትነታቸው በቻይና ከፍተኛ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ስልጠና ለሁለት አመታት የወሰዱት ኢሳያስ አፈወርቂ፤ 30 አመት የፈጀውን የኤርትራ የነፃነት ትግልን ከጓዶቻቸው ጋር እንደመሩ ይነገራል፡፡ ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ገደማም ኤርትራን በፕሬዚዳንትነት በመምራት ላይ ይገኛሉ፡፡

Read 9776 times