Saturday, 14 July 2018 11:51

ቤተ ክርስቲያኒቱ፡ ሙስናንና ዘረኝነትን ማጥፋት ዋነኛ አጀንዳዬ ይኾናል አለች የቀድሞው ፓትርያርክና የተሰደዱ ጳጳሳት ወደ አገር ይመለሳሉ

Written by 
Rate this item
(9 votes)

 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ሙስናንና ዘረኝነትን ከቤተ ክርስቲያኒቱ ማጥፋትን ዋነኛ አጀንዳው አድርጎ እንደሚንቀሳቀስ አስታወቀ፡፡
የሙስና እና ጠባብነት መስፋፋት እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ዕጦት ቤተ ክርስቲያኒቱን ለከፍተኛ ክስና ወቀሳ እያጋለጣት እንደኾነ የተወያየው ቅዱስ ሲኖዶሱ፤ ችግሩን ለመፍታት ያስችላል ያለውን መሪ ዕቅድና የተለያዩ ጥናቶች ተግባራዊነት ዋነኛ አጀንዳው እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ ሐምሌ 3 ቀን 2010 ዓ.ም ያካሔደውን አስቸኳይ ስብሰባ ሲያጠናቅቅ፣ ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ እንደተናገሩት፤ መልካም አስተዳደርን በቤተ ክርስቲያኒቱ የበለጠ ለማስፈን በባለሞያዎች የተዘጋጀው መሪ ዕቅድና ከአሁን በፊት የተጠኑ የመዋቅር፣ የአደረጃጀትና የአሠራር ለውጥ ጥናቶች በቀጣዩ ዓመት ጥቅምት የቅዱስ ሲኖዶሱ ምልዓተ ጉባኤ፣ ዋነኛ የመነጋገሪያ አጀንዳ ኾነው እንዲቀርቡ መወሰኑን ገልጸዋል፡፡ በዋና አጀንዳነት የሚቀርበው መሪ ዕቅዱ፣ ወቅቱንና ዘመኑን በዋጀ መልኩ የቤተ ክርስቲያኒቱን የመልካም አስተዳደርና ሙስና ችግሮች ለመፍታት ያስችላል፤ ተብሏል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶሱ በአስቸኳይ ስብሰባው፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ወቅታዊና ዐበይት ችግሮች አጥንቶ ከመፍትሔዎቻቸው ጋር እንዲያቀርቡ የሠየመው ስድስት አባላት ያሉት የሊቃነ ጳጳሳት ኮሚቴ ያዘጋጀውን ጥናታዊ ጽሑፍ መነሻ በማድረግ በስፋት ተነጋግሯል፡፡
ለምልአተ ጉባኤው በቀረበው ፅሁፍ፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር በተለይ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፣ ከቅጥር፣ ዕድገትና ዝውውር ጋራ ተያይዞ መልካም አስተዳደር ማስፈን አዳጋች መሆኑን፤ በአድባራትና ገዳማት ያለው የመሬት ወረራና በኪራይ ስም የሚፈፀም ሙስና መበራከቱን እንዲሁም ዘረኝነትንና ጎሠኝነትን መከላከል እንዳልተቻለ ተመልክቷል፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቱ ያለባትን አጠቃላይ አስተዳደራዊ ችግር በጊዜ ባለመፍታቷ፣ የሚሰጠውን እርምትና ማስተካከያም ለመቀበል በጎ ፈቃድ ባለማሳየቷ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት፣ በፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር፣ በሰብአዊ መብት ኮሚሽንና በሰራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት በኩል በተደጋጋሚ ለክስና ወቀሳ መጋለጧም ተጠቁሟል፡፡
ለሰብአዊ መብት መከበር ግንባር ቀደም ሆና መቆም የሚገባት ቤተ ክርስቲያኒቱ፣ በሰብአዊ መብት ጥሰት በቁጥር አንድ ደረጃ መቀመጧም አሳሳቢ ነው፤ ብሏል - ሪፖርቱ፡፡
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሥራ ኃላፊዎችና የአድባራትና ገዳማት ሰራተኞች፣ ምንጩ የማይታወቅ ሃብት ባለቤት መሆናቸውን ያተተው ጽሑፉ፤ በግልና በተደራጀ የቡድን ዝርፊያም ሠራተኞቹ ይታማሉ፤ ይህም ቤተ ክርስቲያኒቱን ለነቀፋና ትችት ዳርጓታል - ብሏል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶሱ በጥናታዊ ጽሑፉ የተጠቆሙ ዐበይት ወቅታዊ ችግሮችን ከተነጋገረባቸው በኋላ፣ ሦስት የመፍትሄ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡ እነዚህም፣ ችግሮቹ ገዝፈው የሚታዩበትን የአዲስ አበባ ሃገረ ስብከትን እንደገና ማዋቀርና ማደራጀት፤ በነበረው የአስተዳደርና የአሠራር ብልሽት ያለአግባብ ከሥራቸው የተፈናቀሉ ሠራተኞች ከሃይማኖት ሕጸጽና ከሙስና ነጻ መኾናቸው እየተገመገመ ወደ ሥራ እንዲመለሱ፤ በአጠቃላይ ከአዲስ አበባም ኾነ ክፍተት ካለባቸው አህጉረ ስብከት ሙስናንና ዘረኝነትን ለማጥፋት፣ ከዚህ በፊት በባለሞያዎች ተጠንቶ የተዘጋጀው መሪ ዕቅድ ተግባራዊ እንዲኾን በጥናታዊ ጽሑፉ የቀረበውን የመፍትሔ ሐሳብ ተቀብሎታል፡፡ በቀጣዩ የጥቅምት 2011 ምልዓተ ጉባኤም፣ ዋና የመነጋገሪያ አጀንዳ ኾኖ እንዲቀርብለት ወስኗል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶሱ በዚሁ አስቸኳይ ስብሰባው፣ ላለፉት 26 ዓመታት በአሜሪካ በስደት ከሚገኙ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች ጋር የተፈጠረው አለመግባባት ተጀምሮ በቆየው ዕርቀ ሰላም እንዲያበቃ ሦስት ሊቃነ ጳጳሳትን በልዑክነት መሠየሙን አስታውቋል፡፡
ከመጪው ሐምሌ 11 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ፣ በዋሽንግተን ዲሲ የሚከናወነው የዕርቀ ሰላም ሂደት፣ 4ኛውን ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስን ጨምሮ በውጭ አገር የሚገኙ አባቶች ወደ አገር ውስጥ የሚገቡበትና ፍጹም የቤተ ክርስቲያን አንድነት የሚመለስበት ይኾናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ሐምሌ 21 እና 22 ቀን በዋሽንግተን ዲሲ እና በሎሳንጀለስ ከተሞች ከኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር የሚወያዩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ በመርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው ለዕርቀ ሰላሙ ድጋፍ እንደሚሰጡም ታውቋል፡፡    

Read 7328 times