Saturday, 14 July 2018 11:50

‹‹መንግስት ለድንበር ጉዳዮች በቂ ትኩረት አልሰጠም››

Written by 
Rate this item
(3 votes)

በዓመት አንድ ቢሊየን ብር ገደማ የኮንትሮባንድ ዕቃ ይገባል

    የኢትዮጵያ መንግስት ኢ መደበኛ የጠረፍ ንግድን የሚያበረታታ የህግ ማዕቀፍና ልዝብ የድንበር ፖሊሲ (Soft boarder policy)  ቀርጾ ሊተገብር እንደሚገባ፣ አንድ የአዲስ አበባ ምሁር ሲገልጹ፤  በዓመት በአማካይ አንድ ቢሊየን ብር የሚገመት ኮንትሮባንድ ዕቃ ከውጭ ወደ ሐገር ውስጥ እንደሚገባ የፌዴራል ገቢዎች እና ጉምሩክ ባለስልጣን ባልደረባ አመለከቱ፡፡
‹‹ድንበር የማዕከሉ መስታወት ወይም ነጸብራቅ ነው፡፡ የድንበር ጉዳይ ከጸጥታ ሥራ ጋር ብቻ ተቆራኝቶ መታየት አይኖርበትም›› ያሉት ‹‹የምሥራቅ አፍሪካ የጠረፍ ከተሞች እንቅስቃሴ›› (Borederland Dynamics in East Africa) በሚል ርዕስ የሚካሄድ የጥናት ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶ/ር ፍቃዱ አዱኛ፤ የአፍሪካ የድንበር አካባቢዎች የሚታዩት ታሪካዊና ማህበረሰባዊ ተጨባጭ ሁኔታዎች መንግስታት ‹‹ለዘብ ያለ የድንበር ፖሊሲ›› (Soft boarder policy) እንዲቀርጹ የሚያስገድዱ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
መንግስታት ጥብቅ የሆነ ድንበር ፖሊሲ ሲከተሉ በጠረፍ አካባቢ የሚኖረው ማህበረሰብ እንደሚጎዳ የገለጹትና ህይወቱን ሊያሻሻሽሉ የሚችሉ አካባቢያዊ ምቹ ሁኔታዎችን ወይም በእጁ ያለውን ሐብት መጠቀም እንዳይችል ያደርገዋል ያሉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲው መምህር ዶ/ር ፍቃዱ፤ ጥብቅ የጉምሩክ ህጎች ከጠረፍ ንግድ ሥራ በቀር ሌላ የኑሮ መሠረት የሌላቸውን ዜጎች ህይወት ፈታኝ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
መንግስት ለድንበር ጉዳዮች በቂ ትኩረት አልሰጠም በሚል ወቀሳ የሰነዘሩ የአውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች፤ ከቅኝ ግዛት ጋር ተያይዞ የተፈጠሩና ለመቶ ዓመታት መፍትሔ ሳያገኙ እየተንከባለሉ የመጡ የድንበር ችግሮች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ ችግሩን አቅልለን በማየት ትኩረት ሳንሰጠው የምንቀጥል ከሆነ፣ በጣት በሚቆጠሩ በዓመታት በርካታ ውጥንቅጥ ውስጥ እንደሚከተን መሪዎቻችን እንዲገነዘቡ ማድረግ ይኖርባቸኋል በማለት ለምሁራኑ አደራ ሰጥተዋል፡፡
አውደ ጥናቱ በዓለም አቀፍ ድንበር ላይ ያተኮረ ቢሆንም በውይይቱ በክልሎች መካከል ያሉ የአስተዳደር ወሰን ችግሮችም ይነሱ ነበር፡፡ ‹‹የአስተዳደር ወሰኖችን ድንበር አድርጎ የማየት ዝንባሌ ተበራክቷል፡፡ ግጭት በዝቷል፡፡  እንደ ቀድሞው በድንበርና በአስተዳደር ወሰኖች አካባቢ በሚኖሩ የተለያዩ ብሔረሰቦች መካከል የሚከሰቱ ግጭቶችን በሽማግሌዎች አማካይነት መፍታት የማይቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል›› የሚሉ አስተያየት ሰጪዎችም ተደምጠዋል፡፡
በመንግስት ውሳኔ ያገኙ የአስተዳደር ወሰን ችግሮች ጭምር ተፈጻሚ  ሳይሆኑ ከአስር ዓመታት በላይ መቆየታቸውን በአብነት በመጥቀስ ወቀሳ ያቀረቡ የአውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች፤ በድንበር አካባቢ የሚታዩ አንዳንድ ችግሮች ከመልካም አስተዳደር እጦት ጋር እንደሚያያዙ ጠቅሰው፤ ‹‹መሬታችን ተነጥቆ ለኢንቨስተር ተሰጠብን፤ ካሣ በአግባቡ አላገኘንም›› በሚል ቅሬታ የሚሸፍቱ ሰዎች መኖራቸውን አመልክተዋል፡፡
በሌላ በኩል፤ የቁም ከብት ንግድ ፈቃድ በተወሰኑ ሰዎች መያዙንና እነዚህ ንግድ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች ከብት ሳያረቡ ወይም ሳያደልቡ የቁም ከብት ወደ ውጭ በመውሰድ ለመሸጥ ከሚፈልጉ ፈቃድ የሌላቸው ነጋዴዎች በከብት ሰባት መቶ ብር እያስከፈሉ ያለ ሥራ ገንዘብ የሚሰበስቡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የፌዴራል ገቢዎች እና ጉምሩክ ባለስልጣንን በመወከል በአውደ ጥናቱ የተሳተፉ አንድ ግለሰብ እንደ ገለጹት፤ ከሚደረገው ቁጥጥር ብልሹነት ወይም ደካማነት የተነሳ የሚያልፈው የኮንትሮባንድ ዕቃ ከሚያዘው በብዙ እጥፍ እንደሚበልጥ ጠቅሰው፤ ‹‹በዓመት ከ400 -500 ሚሊየን ብር የኮንትሮባንድ ዕቃ ይያዛል፡፡ ይህም አኃዝ በ2008 ዓ.ም 905 ሚሊየን ብር ደርሶ ነበር። ሆኖም በ2009 እና 2010 ዓ.ም በዓመት ወደ አንድ ቢሊየን ብር ገደማ የሚገመት የኮንትሮባንድ ዕቃ ወደ መሐል ሀገር ገብቷል፡፡ ወደ ሐገር ቤት ከሚገባው የኮንትሮባንድ ዕቃም ውስጥ በብዙ ሚሊየን ብር የሚገመት የጦር መሣሪያ፣ አደንዛዥ ዕጽ እና መድኃኒት ነው›› ብለዋል፡፡
በኮንትሮባንድ ንግድ የተሰማሩት ወገኖች፣ በጣም የረቀቀ ስልት እንደሚጠቀሙና በአሁኑ ሰዓት ከተቆጣጣሪው ይልቅ ኮንትሮባንዲስቱ የረቀቀ የቴክኖሎጂ አቅም እንዳለው ጠቅሰው፤ ነፍስ ባለው ዶሮ ውስጥ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃ በመደበቅ በኮንትሮባንድ ለማስገባት ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡  (ዝርዝሩን በገጽ ……)

Read 2756 times