Tuesday, 10 July 2018 00:00

የናይጀሪያው መሪ ስልጣን አለመልቀቅ ገዢውን ፓርቲ ሰንጥቆታል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የናይጀሪያው ፕሬዚዳንት ሙሃመድ ቡሃሪ በቅርቡ በሚካሄደው ምርጫ ለሁለተኛ የስልጣን ዘመን ለመወዳደር ማሰባቸውና ስልጣን ለመልቀቅ አለመፍቀዳቸውን የተቃወሙ የገዢው ፓርቲ አባላት፤ ባለፈው ረቡዕ አፈንግጠው በመውጣታቸው ፓርቲው ለሁለት መከፈሉን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ኦል ፕሮግረሲቭ ኮንግረስ የተባለው የአገሪቱ ገዢ ፓርቲ አባላት የሆኑ ፖለቲከኞች ባለፈው ረቡዕ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ “ለናይጀሪያውያን መልካም አስተዳደር ለማምጣት የገባውን ቃል ለማክበር ያልቻለ፣ ቀርፋፋና ብቃት የለሽ” በማለት የፕሬዚዳንት ሙሃመድ ቡሃሪን መንግስት ክፉኛ የተቹ ሲሆን፣ የቡሃሪን ለተጨማሪ የስልጣን ዘመን  መወዳደር በጽኑ በመቃወም፣ ከፓርቲው አፈንግጠው በመውጣት፣ ሪፎርምድ ኦል ፕሮግረሲቭ ኮንግረስ የተባለ አዲስ ክንፍ ማቋቋማቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡
የፕሬዚዳንት ቡሃሪ የቀድሞ አጋር እንደሆኑ የሚነገርላቸውና የአዲሱ ክንፍ ብሄራዊ ሊቀመንበር ተደርገው የተሾሙት ቡባ ጋላዲማ፤ በአቡጃ በተካሄደው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፣ አዲሱ ፓርቲ ሪፎርምድ ኦል ፕሮግረሲቭ ኮንግረስ ለህዝብ ታማኝ ተወካዮችን የያዘና ለውጥ የሚያመጣ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡ የገዢው ፓርቲ አባላት አፈንግጠው መውጣታቸውና አዲስ ፓርቲ ማቋቋማቸው የፕሬዚዳንት ቡሃሪን ለተጨማሪ አመታት በስልጣን ላይ የመቆየት ተስፋ ያጨልመዋል መባሉን የዘገበው ቢቢሲ በበኩሉ፤ አዲሱ ፓርቲ የአገሪቱን ከፍተኛ ባለስልጣናት ድጋፍ ያገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጧል፡፡
አዲሱ ፓርቲ ከሌሎች የናይጀሪያ ተቃዋሚ ሃይሎች ጋር ውህደት ፈጥሮ ራሱን በማጠናከር በመጪው የካቲት ወር ላይ በሚደረገው የአገሪቱ ፖሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይ፣ የፕሬዚዳንት ቡሃሪ ቀንደኛ ተቀናቃኝ  ሆኖ ይመጣል ተብሎ እንደሚጠበቅም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

Read 1892 times