Saturday, 07 July 2018 11:33

‹‹…Prostate …. የወንዶች የስነተዋልዶ ጤና ችግር…››

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

 ….የተወደዳችሁ የላንቺና ላንተ አምድ ጸሐፊዎች፡፡ እኔ አንድ የጤና ጥያቄ አለኝ፡፡ በእርግጥ ከአሁን በፊት አልተዳሰሰም ብዬ አይደለም፡፡ ከተወሰኑ አመታት በፊት በአምዳችሁ ላይ የነበረ ቢሆንም እኔ ግን ችግሩ የገጠመኝ ከአንድ አመት ወዲህ በመሆኑ ነው፡፡ ምን መሰላችሁ? እድሜዬ ወደ 58 አመት ገብቶአል፡፡ ታዲያ አሁን አሁን የገጠመኝ ነገር ጠዋት… ጠዋት ሽንቴን ለመሽናት እጅግ በጣም ትግል ሆኖአል፡፡ በጣም ትንሽ ትንሽ በመሆን ሽንቴ ሲወጣ በጣም ያሰቃየኛል፡፡ ያስምጠኛል። ቀን ደግሞ አሁንም አሁንም ሽንት መጣሁ ይለኛል፡፡ ነገር ግን በእርካታ አልሸናም፡፡ በዚህም ምክንያት በሀሳቤ ለባለቤቴም ችግር እፈጥር ይሆን በማለት እጨነቃለሁ፡፡ እሱዋ ግን ምንም ያወቀችው ነገር የለም፡፡ ምናልባትም የሰማች እንደሆነ ከእኔ በላይ ትጨነቃለች ብዬ ስለማስብ እንዲያው ችግሩን ለእራሴ አምቄ ይዤዋለሁ፡፡ እንደቀድሞ ውም ባይሆን እንኩዋን አለፍ አለፍ ብዬ የወሲብ ግንኙነት ስፈጽም እንደቀድሞው ነጻነት ስለማይሰማኝ እየፈራሁ እንጂ እየተደሰትኩ አይደለም፡፡ እስቲ ስለወንዶች የስነተዋልዶ ጤና ሊያናግሩአችሁ የሚችሉ ባለሙያዎችን ስለ (prostate) ፕሮስቴት አናግሩልኝ፡፡ በእርግጥ ይህ ችግር የእኔ ብቻ እንደማይሆን እርግጠኛ ባልሆንም እንኩዋን ሌሎችም እንደሚኖሩ እገምታለሁ፡፡
ታመነ ኃይሌ …ከለቡ
ከላይ ያስነበብናችሁ በእድሜያቸው ወደ ስድሳው እየተጠጉ ያሉ አንድ አዛውንት ያደረሱን መልእክት ነው፡፡ በእርግጥም እሳቸው እንዳሉት ይህ የprostate ጉዳይ የአንድ ወይንም የሁለት ሰው ሳይሆን የብዙዎች የጤና ችግር ነው ከሚል የተለያዩ የጥናት ስራዎችን እንዲሁም የባለሙያዎ ችን እምነት ለአንባቢዎች ይደርስ ዘንድ እነሆ ብለናል፡፡ በተከታይ የምትመለከቱት የወንዶች የስነተዋልዶ አካልና የሽንት ማጠራቀሚያ እንዲሁም (prostate) ፕሮስቴት የተባለውን እጢ እና ሌሎችንም ነው፡፡
የወንዶች የ prostate እጢ ሕመም የሚገጥመው በአብዛኛው በእድሜ ከ50 በላይ ሲሆኑ መሆኑን ምርምሮች ይገልጻሉ። በቅድሚያ ግን ጠያቂው እንዳሉት በተለይም ጠዋት ጠዋት ሽንት የመሽናት ችግር እንደሚገጥማቸውና በቀኑ ውሎአቸውም በትንሽ በትንሹ ነገር ግን ቶሎ ቶሎ ሽንት ቤት መሄድ እንዳለባቸው የሚያመላክት ነው፡፡ አስቀድሞ ግንኙነቱን መፈተሸ ያስፈልጋል፡፡
እንደእውነቱ ከሆነ የወንድም ሆነ የሴት ሽንት የሚፈጠረው ኩላሊት ውስጥ ነው፡፡ ኩላሊቶ ቻችን የሚገኙት ደግሞ ከሆዳችን ውስጥ ከወገባችን ትንሽ ከፍ ብሎ ከአከርካረ አጥንታችን ጎን በግራና በቀኝ በኩል ነው፡፡ በእነዚህ ኩላሊቶቻችን ውስጥ ሽንት ከተፈጠረ በኋላ ሽንቱ (urethras) በሚባሉ ቱቦዎች ወደ ፊኛ (Bladder) ይገባል፡፡ ከፊኛ ቀጥሎ ደግሞ urethra የሚባል ሌላ ቱቦ አለ ፡፡ በዚህ ቱቦ በኩል በማድረግ በብልት በኩል ሽንት ከሰውነት ይወጣል ማለት ነው፡፡
የሽንት ፊኛ(Bladder) ውስጥ ከተጠራቀመ በኋላ በመውጫው በኩል urethra ላይ ፕሮስቴት (prostate) የሚባል ዕጢ አለ፡፡ በተጨማሪም ከፕሮስቴት ዕጢ መሃል ሰንጥቆ የሚወጣ urethra የሚባል ሽንት የሚወጣበት ቱቦ አለ፡፡ይህ በውጭ በኩል ያለው external ወይም ደግሞ penile urethra ይባላል፡፡ በውስጥ በኩል ደግሞ ከፊኛ ቀጥሎ ያለው በ prostate መሃል የሚያልፈው ቱቦ  internal urethra ወይም ደግሞ (prostate Urethra) ይባላል፡፡ይህ prostate የተባለው ዕጢ ሽንት ከፊኛ ሲወጣ አቅፎ የሚይዝ ነው ፡፡ ወንዶች በዚህ ጉዳይ ሐኪሞቻቸውን የሚጎበኙት ይኼ ፕሮስቴት (prostate) የሚባለው እጢ በሚያብጥበት ጊዜ የሽንት መሽናት ችግር ስለሚፈጥር ነው፡፡
አንድ ሰው የሽንት መሽናት ሁኔታው ጤነኛ ነው የሚያሰኘው፡-
ሽንቱን ሲሸና ምንም ህመም ሳይሰማው እንዲያውም ሽንቱን በመሽናቱ ምክንያት እርካታ የሚሰማው ከሆነ ፤
የሸንት መጠኑ በቂ ከሆነ ፤ አንድ ሰው በአማካኝ ከ800 (ስምንት መቶ) ሲሲ ያላነሰ ሽንት በሃያ አራት (24) ሰአት ጊዜ ውስጥ መሽናት ይጠበቅበታል፡፡
በእርግጥ አንዳንድ ጊዜ የሽንት መጠኑ በ800 ሲሲ ብቻ ሳወሰን ከዚያም በላይ ሊሆን እንደሚችል መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከዚህም በተጨማሪ አንድ ሰው የሽንት አሸናኑ ጤነኛ አይደለም የሚባለው፡-
ሽንት ሲሸና የማጣደፍ ሁኔታ ሲኖር፣
ሽንት በሰላማዊ መንገድ ወይንም ካለምንም ግፊት ተፈጥሮ በሚፈቅደው መንገድ ካልተወገደ፤
የሽንት መቅላት ወይንም እንደደም መምሰል ሲከሰት፣
እንዲሁም መጠኑ ተገቢውን የማያክል ከሆነ ጤነኛ ያልሆነ የሽንት አሸናን አለ ያሰኛል፡፡  
አንድ ሰው የሽንት መሽናት ችግር የሚገጥመው በግድ (prostate) በፕሮስቴት እጢ እብጠት ምክንያት ነው ለማለትም አያስደፍርም፡፡ የሽንት መሽናት ችግር የሚፈጠረው በሁለት አጋጣሚዎች ሊሆን ይችላል፡፡
አንደኛው በማንኛውም ጊዜ የሚከሰት ችግር ሲኖር፣ ለምሳሌ (infection) መመረዝ ሲኖር፣ የፊኛ ውስጥ ወይም ኩላሊት ውስጥ ጠጠር ሲኖር፤
ሁለተኛው ደግሞ የፕሮስቴት (prostate) እጢ ላይ ኢንፌክሽን (infection) ወይም ካንሰር ሰፈጠር ፤ወይም ደግሞ ፕሮስቴት እጢ ላይ ካንሰር ያልሆን እብጠት ሲኖር የሽንት መሽናት ችግር ይከሰታል ማለት ነው፡፡
የ(prostate) ፕሮስቴት እጢ እብጠት መንስኤ እስከአሁን በትክክል አልታወቀም ፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ እንደ መንስዔ ከሚጠቀሱ መካከል ለምሳሌ በዘር (በቤተሰብ) የሚተላለፍ ነው ተብሎ ይታሰባል ፣የአመጋገብ ሁኔታም ለዚህ ችግር ሊያጋልጥ ይችላል፣ የአካል እንቅስቃሴ አዘውትረው በማያደርጉ ወንዶች ላይ ሊከሰት ይችላል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ፍራፍሬ ቅጠላቅጠል በሚመገቡ እንቅስቃሴ በሚያደርጉ ወንዶች ላይ ችግሩ እጅግ ባነሰ መልኩ ሊከሰት ይችላል ተብሎ ይገመታል፡፡
የፕሮስቴት (prostate) እጢ እብጠት በእንግሊዘኛው ባጭሩ (BPH) (benign prostatic hyperplasia) ይባላል። የፕሮስቴት እብጠት በተለይ የሚከሰተው እድሜ ወደ ሃምሳ/50/ ዓመት ሲደርስ እና  ከዛ በላይ ሲሆን ነው፡፡ ይህ prostate እጢ ሽፋን ያለው ሲሆን በሚያ ብጥበት ጊዜ ይህ ሽፋን ስለማይለጠጥ የሽንት መሽኛው ወይንም መተላለፊያው መንገዱ ይጠበዋል። የሽንት መተላለፊያው በሚጠብበት ጊዜ የመሽናት ችግር ይፈጠራል፡፡
የሽንት መሽናት ችግር ተከሰተ ከሚያሰኘው ምልክቶች አንዱ የሽንት ቶሎቶሎ መምጣት ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ መተላለፊያው ስለጠበበ የመጣው ሽንት በአንድ ጊዜ ተጨርሶ ስለማይሸና ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሚከተሉት የጤና መጉዋደል ምልክቶች ይስተዋላሉ፡፡
አንድ ሰው  ከተኛ በኋላ  ብዙ ጊዜ ወደ ሽንት ቤት ተመላልሶ የሽንት መሽናት እንዲያደርግ የሚያስገድደው ስሜት ይፈጥርበታል፡፡
ሌላው ደግሞ ሽንት ሲሸና ሽንቱ ቀጭን ሆኖ እየተቆራረጠ ነው የሚወጣው ፡፡
በእርግጥ እንደዚህ ያለው ሁኔታ ሲከሰት ሁል ጊዜ የፕሮስቴት እጢ አብጦ ነው ለማለት አያስደፍርም ፡፡ ለማንኛውም ግን እንደዚህ አይነት ችግር ሲከሰት ሀኪሞችን ማማከር ተገቢ ይሆናል ፡፡
(prostate) እና ወሲብ ምን ያህል ይገናኛሉ? በቀጣዩ ሕትመት እናስነብባችሁዋለን፡፡

Read 4778 times