Saturday, 07 July 2018 11:35

አርቲስት ዓለምፀሃይ ወዳጆ “ህዝቡ ናፍቆኛል” ትላለች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

  • የጠ/ሚኒስትሩ ተስፋዎች፣ ወደ ተግባር ተለውጠው የማይበት ቀን ሩቅ አይሆንም
   • ህዝባችን ወደ አንድነት፣ ወደ ፍቅር ሲሮጥ ማየቴ፣ ለኔ ትልቅ ዋጋ አለው
   • ልጆቼ ኢትዮጵያ ሲገቡ እንዲያዩ የምፈልገው፣ ህንፃውን አይደለም
   • አሁንም ወደፊትም መፍትሄው፣ በእኩልነት አንድ ሆኖ መኖር ነው
   • በሃገር ቤት እኮ ስሜን መጥራትና መፃፍ እንኳ ወንጀል ሆኖ ነበር

   በፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ሳቢያ ከሃገር ከወጣች 27 ዓመታትን አስቆጥራለች፡፡ በርካቶች በመድረክ ቲያትሮቿ የሚያውቋት ተወዳጅዋ አርቲስት አለምፀሃይ ወዳጆ፤ በጋሽ መሃሙድ አህመድ “ሠላም”፣ በጥላሁን ገሠሠ “እናት ሃገር ኢትዮጵያ”፣ በህፃናት አምባ “እርግቤ ብረሪ” መዝሙርና በሌሎችም የዘፈን ግጥሞቿ ትታወሳለች፡፡ የደርግ መውደቅን ተከትሎ የተተካው ብሔርን መሠረት ያደረገ ፖለቲካ፣ ከሃገሬ ለመሰደድ ምክንያት ሆኖኟል የምትለው አርቲስቷ፤ ከሃገሯ ብትነጠልም ከጥበብ አልተለየችም፡፡ በአሜሪካ አገር፣ ጣይቱ የባህል ማዕከል የተሰኘ በኪነጥበባዊ ጉዳዮች ላይ የሚሠራ ድርጅት አቋቁማ፣ ላለፉት 18 ዓመታት ግጥም፣ ቲያትርና ሌሎች ጥበቦችን በስደት ለሚኖረው ኢትዮጵያዊ መግባለች፡፡ ዘርፈ ብዙ የኪነ ጥበብ ባለሙያዋ አርቲስት ዓለምጸሃይ ወዳጆ፣ ሃገሯ (ህዝቧ) በእጅጉ እንደናፈቃት ትናገራለች፣ የስደት ኑሮ የሚያሳጣውን ነገርም በቁጭት ትገልጻለች፣ ግን ትልቅ ተስፋ ሰንቃለች፡፡ ሁሉንም ለአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ ከዚያው ከአገረ አሜሪካ በስልክ እንዲህ አውግታዋለች፡፡


    መቼ ነው ከሃገር የወጣሽው? ስንት ዓመት ሆነሽ?
እኔ ከሃገሬ የወጣሁት የደርግ መንግስት የተቀየረ ጊዜ ነው፡፡ አሁን 27 አመት ሆኖኛል ማለት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ ሃገሬ ተመልሼ አላውቅም፡፡
ከሃገር ለመውጣት ምክንያትሽ ምን ነበር?
በወቅቱ የሙያ ማህበር ሊቀመንበር ነኝ፤ የብሄራዊ ቲያትር ቤት የፕሮግራምና ፕሮዳክሽን ሃላፊ ነኝ፤ እግዚአብሔር ይመስገንና እጅግ ሠፊ የሆነ ክብር፣ ስም ነበረኝ፡፡ ምንም ችግር አልነበረብኝም፡፡ ነገር ግን በወቅቱ የቲያትር ግብረ ሃይል በማቋቋም፣ ፀሃፊዎችን በማደራጀትና በማስተባበር፣ የኢትዮጵያ አንድነትን በሚመለከት ቅስቀሳዎችን እንሠራ ነበር። ኢትዮጵያ ክልሏ፣ ዳር ድንበሯ እንደተጠበቀ መኖር አለባት ከሚሉት ውስጥ ነበርኩኝ፤ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ባለው የሠላምና የዲሞክራሲ ጥያቄ ላይ ማገዝ፣ የዘር ፖለቲካን የመቃወም እንቅስቃሴ አደርግ ነበር። ከሠላም፣ ከሃገር አንድነት ጋር በርከት ያሉ የጥበብ ስራዎችን ሠርቼያለሁ፡፡ በኋላ ግን አሸናፊው ሃይል ወደ ስልጣን እየተጠጋ ሲመጣ፣ በሠራኋቸው የጥበብ ስራዎች፣ እንደ ጠላት መፈረጄን በራሳቸው ሬድዮ ሠማሁ፡፡ እኔም ደግሞ ያለኝ አቋም፣ ከእንዲህ አይነት የዘር ፖለቲካ የወጣና ኢትዮጵያን ወደ ሌላ የሠላም መንገድ የሚያሸጋግር ሁኔታ እንዲፈጠር ነበር የምታገለው፡፡ ዘረኝነትን እፀየፈዋለሁ፣ ዓላማዬም አልነበረም፡፡ መንግስቱ ኃይለማርያም ማክሰኞ ቀን ነበር ከሃገር ተሠድደው የወጡት፡፡ እኔም ከአለቆቼ ጋር ተነጋግሬ፣ ፕሮሰስ የጀመርኩት በዚያው ቀን ነበር፡፡
ምን ነበር ይበልጥ ስጋት የፈጠረብሽ?
እኔ በወቅቱ ብታሠር ልጆቼ ይሰቃያሉ፡፡ ለምን ለችግር እዳርጋቸዋለሁ ብዬ ነው ከሃገሬ የወጣሁት። በአጠቃላይ የፖለቲካው ሁኔታ ለኔ የተመቸ አልነበረም፡፡
በወቅቱ በጠላትነት አስፈርጀውኝ ነበር ያልሻቸው የጋሽ መሐሙድ “ሠላም”፣ የጥላሁን ገሠሠ “እናት ሃገር ኢትዮጵያ”  ዘፈኖች፣ ዛሬ በድጋሚ የትላልቅ መድረኮች ማጀቢያ ሆነዋል፡፡ ያኔ አንቺ እንዴት ነበር የፃፍሻቸው?
በወቅቱ በኤርትራና በኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት የምንሠራቸው የቅስቀሳ አካል ናቸው፤ ዘፈኖቹ፡፡ ህፃናት አምባ ያሉ ህፃናትንም፣ ስለ ሠላም የፃፍኳቸው መዝሙሮችን ነበር የማዘምረው፤ “እርግቤ ብረሪ ሠላምን አክብሪ” የሚሉ ዓይነት፡፡ እንግዲህ ይህ ነበር በወቅቱ ወንጀል ሆኖ ከሃገሬ እንድሳደድ ያደረገኝ። አሁን የጥላሁን ገሠሠ “ኢትዮጵያ” ዘፈን የሠላማዊ ሠልፍ መክፈቻ፣ የመሪዎቹ መቅረቢያ ሆኖ ሣየው በጣም ያስደስተኛል፡፡ ስሰማው ስሜታዊ ነው የምሆነው፡፡ ህይወታችን ቢያልፍ ኢትዮጵያ ምን ትሆናለች ብለን የምናስብ ብዙዎቻችን፣ ዛሬ ወጣቶች ስለ ሃገራቸው ከፍ አድርገው፣ “ኢትዮጵያ” እያሉ ሲዘምሩ ስናይ፣ ህሊናችን ይረካል፤ እረፍት ያገኛል፡፡ አሁን ደግሞ የበለጠ ህዝባችን ወደ አንድነት፣ ወደ ፍቅር ሲሮጥ ማየቴ፣ ለኔ ትልቅ ዋጋ አለው፡፡
እነዚህን ስራዎች የሰራሽው በሃገር ፍቅር እሣቤ ነው ወይስ በደርግ የሶሻሊስታዊ አመለካከት ውስጥ ሆነሽ ነው?
በደርግ ውስጥም እኮ የመሣሪያ ሃይል ጉዞ እንደማያዛልቅ የሚያምኑ ብዙዎች ነበሩ፡፡ እኔ መሣሪያ ወይም ጦርነት መፍትሄ እንደማይሆን አምን ነበር። እነዚህን የሠላም ጥሪ መዝሙሮች በወቅቱ አዘጋጅ የነበረውም፣ የመሣሪያ ሃይል መፍትሄ እንደማይሆን ለማስገንዘብ ነው፡፡ የሠለጠነው ዓለም እኮ የሚበልጠን እውቀቱን፣ ገንዘቡን፣ ጥበቡን ለአንድነቱ ማጠናከሪያ ማዋሉ ነው፡፡ እኛም ልዩነታችን፤ ጉልበታችን ሊሆን ይገባዋል እንጂ መዳከሚያችን መሆን የለበትም በሚል ነበር፣ “በአንድነት እንሰባሰብ” የሚል ስብከት ስናሰማ የነበረው፡፡ ዛሬ እኛ ተሰደን የምንኖርበት ሃገር (አሜሪካ) ጉልበቱ፣ ከመላው ዓለም የመጡትን አሰባስቦ በአንድነት ማኖሩ ነው፡፡ ጉልበታችን ፍቅርና አንድነት ነው የሚለው ነገር በፊትም የማምንበት ነው። ከዚህ መነሻ ነው መዝሙሮቹን ስፅፋቸው የነበረው፡፡ እነዚህ ብቻ አይደሉም፡፡ ብዙ ስለ አንድነትና ሠላም የሰበክንባቸው መዝሙሮች አሉ፡፡ አሁንም ወደፊትም መፍትሄው፣ በእኩልነት አንድ መሆን፤ በሠላም መኖር ነው - ጉልበት የሚሆነን፡፡
አሁን ደግሞ ወቅቱ ነው፤ ብዙ ስለ ፍቅር፣ ስለ እኩልነት፣ ስለ አንድነት፣ ስለ ኢትዮጵያዊነት እየተሰበከ ነው፡፡ አንቺ በአዲሱ የለውጥ ነፋስ ምን ተሰማሽ?
በእውነቱ በጣም ተደስቼበታለሁ፡፡ የሚኬድበት መስመር ቀናነቱ ይታየኛል፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ነገሮች ከንግግር አልፈው፣ ወደ ህግና ተግባር መለወጥ አለባቸው፡፡ ምንጊዜም ዋስትና የሚሆነው የህግ የበላይነት ነው፡፡ ሠላም ዘላቂ የሚሆነው በህግ የበላይነት ነው፡፡ መዋቅሮች ላይ የሚካሄደው ለውጥ መሠረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ቀና መንገድ ከተጓዝን፣ ሃገሪቱን ቀይደው የያዙና አላሻግር ያሉ ችግሮች የሚቀረፉበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን አምናለሁ፡፡ በተረፈ ግን ኢትዮጵያን፣ ታሪኳን፣ ባህሏን፣ ቀደምት ሃገር መሆኗን---መቀበል የሚችል መሪ ማግኘት መታደል ነው፡፡ እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ በሴቶች እናትነትና እኩልነት የሚያምን መሪ ሳይ  እጅግ ተደስቻለሁ፡፡ እነዚህ ለአንድ መሪ ትልልቅ ብቃቶች ናቸው፡፡ ቀላል አይደለም የታየው ለውጥ፤ እኔ በበኩሌ ደስ ብሎኛል፡፡
ይሄን ሁሉ ዓመት በስደት መኖር ምን ስሜት ይፈጥራል?
እኔ እናቴን፣ አባቴን፣ የምወደውን ባለቤቴን በሞት ያጣሁት በስደት ሆኜ ነው፡፡ ለመቅበር እንኳ አልታደልኩም፡፡ ከልቤ ነው የምነግርህ (እምባና ሣግ እየተናነቃት) እና በአካል ባላያቸውም አስክሬናቸውን እንኳ ማየት ይናፍቀኛል፡፡ በስደት ዓለም ሆነህ የምትቀጣው --- እነዚህ ነገሮች ናቸው፡፡ “ስደት” በሚለው ግጥሜ ላይም ለመግለፅ የሞከርኩት ይሄንኑ ነው፡፡ በስደት ዓለም ስትኖር በሚያንስህ ሰው ተበልጠህ ነው፡፡ የሌላ ሃገር ዜጋ በመሆንህ ብቻ ተዋርደህ ነው የምትኖረው፡፡ እኔ ይኸው ለ27 ዓመት፣ ቤተሰቤንም ወገኔንም አላየሁም፡፡ በሃገር ቤት እኮ ስሜን መጥራትና መፃፍ እንኳ ወንጀል ሆኖ ነበር፡፡ መፅሐፌን ማስመረቅ ይፈራሉ፣ ስሜን መጥራት ይፈራሉ፡፡ የሠራኋቸው ስራዎች፣ ስሜ እየተዘለለ ነበር የሚቀርቡት ወይም የሚነገሩት፡፡ ለምሳሌ የህፃናት ቲያትርን በኢትዮጵያ የጀመረ ሰው ሲባል፣ ስሜን ላለመጥራት ይዘሉታል። የሠራኋቸው በሙሉ እንደሌሉ ተደርገው ነው የሚታለፉት፡፡ ይሄ በጣም ያመኝ ነበር። ዛሬ ደግሞ በአንፃሩ መጥራት የማይቻሉ ነገሮች እየተጠሩ፤ የማይባሉ ነገሮች ተብለው፣ የማናያቸው ነገሮች ታይተው-- ስመለከት ደስታ ይሰማኛል፡፡
ለወደፊት  ምን ተስፋ ይታይሻል?
ሰው ያለወንጀሉ የማይጠየቅባት፣ ሰዎች ወገናቸውን የማያጉላሉባት፣ የማይገረፉባት፣ የማይሠቃዩባት ሃገር እንዲኖረን እመኛለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ብሔረሠቦች በሙሉ ያለምንም የዘር አድልኦ፣ እኩል ሰርተው የሚኖሩባት፣ የነፃነት ምድር እንድትሆን ነው የምፈልገው፡፡ እኔ በለውጡ እርግጠኝነት ነው ያለኝ፡፡ ወደ ኋላ ለመመለስ አዳጋች ነው፡፡ ለምን ከተባለ? ይሄን ቀን ለማምጣት ብዙ ህዝብ ሞቶበታል፣ ብዙ ሰው ተገርፎባታል፤ ተሠዶባታል፡፡ብዙዎቻችን እምባችንን አፍስሰንበታል። ዝም ብሎ የመጣ ለውጥ አይደለም፡፡ እግዚአብሄር ደግሞ በቃችሁ ብሎ የህዝቡን ሃዘንና ሠቆቃ ያዳመጠ ይመስለኛል፡፡ እነዚህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተስፋዎች፣ ወደ ተግባር ተለውጠው፣ የማይበት ቀን እሩቅ አይሆንም፡፡
በዚህ የለውጥ ሂደት ውስጥ ያንቺ ድርሻ፣ እንደ አርቲስት ምን ሊሆን ይችላል?
እኔ እንደሚታወቀው፣ በሰዎች ድጋፍ የተቋቋመ፣ ጣይቱ የባህል ማዕከል የተሠኘ ድርጅት አለኝ፡፡ በዚህ ድርጅቴ በኩል ሁለት ጥያቄዎችን አቅርቤያለሁ፡፡ ለ18 አመት ነው ይህን ትግል ሳደርግ የቆየሁት፡፡ አንደኛው ጥያቄዬ፤ በጣም የምወዳትና የማከብራት፣ የኔ ብቻ ሳትሆን የመላው ኢትዮጵያዊ ኩራት፣ በአፍሪካም ክብር የሆነችውን፣ የእቴጌ ጣይቱን ሃውልት በቆረቆረቻት ከተማ ማቆም ነው፡፡ ይሄን ጥያቄ ለረጅም ጊዜ መንግስትን ስንጠይቀ ነበር፤ አሁን በመጨረሻ ምላሽ ያገኘ ይመስላል፡፡ ቦታ ምረጡ ተብለናል። ይሄ እውን ሆኖ ያየሁ ለታ፣ ስለቴ ሠመረ ማለት ነው። የኔ ትልቁ ምኞት ይህ ነው፡፡ ሌላኛው ህልሜ፣ በዚህ በምኖርበት ዋሺንግተን ዲሲ፣ አንድ ጠንካራ የባህል ማዕከል ማቋቋም ነው፡፡ የባህል ማዕከሉ አስፈላጊነት እንዲህ በቀላሉ የሚነገር አይደለም፡፡ እዚህ የሚወለዱ፣ የሃገራቸውን ታሪክና ባህል አውቀው የሚኮሩባት፣ መነሻ ሃገር እንዳላቸው እንዲያውቁ ማድረግ ማስቻል ነው፡፡ ህፃናት በሃገራቸው ባህል፣ ቋንቋ፣ ታሪክ --- ታንፀው እንዲያድጉ የሚያደርግ ቋሚ ማዕከል አናቋቁማለን፡፡
በ“ጣይቱ የባህል ማዕከል” በኩልም ባህልን፣ ታሪክንና ጥበብን ስታስተዋውቂ ኖረሻል--?
አዎ! ግን ፈተናው ቀላል አልነበረም፡፡ ያሠቃያል፣ ያማል፣ ጤናህን ታጣበታለህም፣ ገንዘብህን ታጠፋበታለህ፣ የልጆችህን ፍቅር ትቀንስበታለህ፣ በቀን 18 ሠዓት መስራት ይጠይቃል፡፡ እረፍት ያሣጣል። ድምፁ፣ አልባሣቱ፣ መድረኩ፣ ተዋንያን ማሠልጠኑ፣ ተመልካች ማግኘቱ ሁሉ ይከብዳል። ግን ያም ሆኖ ከሃምሳ ዘጠኝ በላይ ቲያትሮችን ነው ፕሮዲውስ ያደረግነው፡፡ በየወሩ አርብ ማታ ማታ ያለማቋረጥ፣ የግጥም ምሽት እናካሂዳለን፤ ተዋንያን እናሠለጥናለን። ከአንድ መቶ በላይ አማተር ተዋንያንን በማዕከሉ አሠልጥነንበታል፡፡ የኛን ዓላማ የተከተሉ ብዙ የጥበብ ድርጅቶች አፍርተንበታል፡፡ አውስትራሊያና ካናዳን ጨምሮ በተለያዩ የአለም ክፍሎች ተመሳሳይ ድርጅቶች ተቋቁመዋል፡፡ እኔ እንደ ሌላው ህንፃ አልሠራሁም፤ በሰው አዕምሮ ግን ትልቅ የዘራሁት መልካም ፍሬ አለ። በተለይ ስለ ኢትዮጵያ ህዝብ ባህል፣ ማንነት፣ ታሪክ፡፡
በስደት ላይ ያሉ ኢትዮጵያውያን በለውጡ ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድነት መቆማቸው እየተነገረ ነው። አንቺ ምን ታዘብሽ?
እኔ እንደ ዜጋ የሚሠማኝ አለ፡፡ እንደ ጥበብ ሰውነቴ ደግሞ የህብረተሰቡን ስሜት እሠማለሁ፡፡ አካሉን ብቻ ሳይሆን መንፈሡን ለማዳመጥ እሞክራለሁ፡፡ በዶ/ር አብይ የመጀመሪያ ቀን ንግግር ከተነኩት አንዷ እኔ ነኝ። አንዳንድ የፖለቲካ መሪዎች፣ የፖለቲካ ቋንቋቸውን ሊያሣምሩ ይችላሉ፤ የዶ/ር አብይን ቋንቋ ሣደምጥ ግን ደነገጥኩ፡፡ እሳቸው የሚናገሩት ቋንቋ የማታለያ አልነበረም፡፡ የሰውን ማንነት ቀድሞ ማየት የሚቻለው በእንዲህ ያለ መንገድ ነው፡፡ በወቅቱ የተወሰነ ሃይል ጥርጣሬ ላይ ነበር፡፡ እኔ ግን በጣም ሰውኛ መሪ ነው፣ የሠው ባህሪ የተላበሠ መሪ ነው ብዬ ነበር፡፡ ስለ እግዚአብሄር፣ ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ፣ ስለ ልጆቹ፣ ስለ እናቱ፣ ስለ ሚስቱ---የሚናገር መሪ መስማት አዲስ ነገር ነበር፡፡ ስሜት ይሠጣል፡፡ እንደሚታወቀው ስደተኛው ስለ ሃገሩ ሲጮህ ነው የኖረው፡፡ ሃገር ቤት ያሉ ወንድም እህቶቹን፤ እንደኔ ደግሞ አባት እናቱን ያልቀበረ፣ አይናቸውን እንኳ ለማየት ያልታደለ፣ ሃገር ውስጥ መግባት የተከለከለ --- ለሃገሩ ምድር፣ ለህዝቡ ነፃነት በየቀኑ መስዋዕትነት ሲከፍል ነው የኖረው፡፡ ሃገር ቤት እንዳሉት አልታሠርንም አልተገረፍንም እንጂ እዚህ ያለነውም የህሊና እስረኞች ነን፡፡
ለአንድ ቀን እንኳን ሃገራችን ከውስጣችን ወጥታ አታውቅም፡፡ በሌላ ሃገር ስደተኛና በኛ መካከል ያለው ልዩነት በጣም ሰፊ ነው፡፡ ሌላው ስደተኛ አሜሪካ ሲኖር፣ ጣጣውን ጨርሶ፣ ተደላድሎ ነው፤ የኛ ህዝብ ግን እዚህች ሃገር ላይ ከልቡ ኖሮ አያውቅም፡፡ አሁን ነገሮች እየተለወጡ ሲመጡ የተሰማውን ደስታ መግለፅ ያዳግታል፡፡ ከመቼ ወዲህ ነው የኢትዮጵያ ህዝብ፣ የመሪውን ፎቶግራፍ፣ በራሱ ፍቃድ፣ በቲ-ሸርት አሠርቶ፣ ስም እያወደሰ፣ ሰልፍ የሚወጣው? ይሄኮ አዲስ ነገር ነው፡፡ ዶ/ር አቢይም ቢሆን ዕድለኛ ሰው ነው፡፡ እንዲህ አይነት ነገር እንኳን በኢትዮጵያ በአፍሪካ ማግኘት ከባድ ነው፡፡ አልተለመደም፡፡ እንደ ህብረተሰብ፣ እኛ ሃገር፣ ይህን ነገር አይተን አናውቅም። ህዝቡ በመሪ ይምል የነበረው፣ በእምዬ ምኒልክ ጊዜ ነው፡፡ ምኒልክ ይሙት ካለ… አበቃ፡፡ ዛሬ ያንን እያየን ነው፡፡ ፍቅርን በአንደበት እንጂ በጦር አስገድደህ የምታገኘው ነገር አይደለም፡፡ ስለ ፍቅር የሚሰብክ መሪ ሲያገኙ፣ ኢትዮጵያውያንም ፍቅር መመለሳቸው ተገቢ ነው፡፡ እዚህ ያለው ሁኔታ በጣም ነው የሚደንቀው። ወጣቱ፣ አዛውንቱ፣ ልጆች ሣይቀሩ የተለየ መንፈስ ነው ያላቸው፡፡ ያለፈው ጊዜ ጉዳቱ ብዙ ነው፡፡ በጥበብ ስራዎች ውስጥ ይታያል፣ በንግዱ ላይ ይታያል፡፡ እነዚህን ችግሮች የሚቀርፍ መንገድ ነው የያዝነው ማለት ይቻላል፡፡
በ27 ዓመት የስደት ኑሮ፣ ከሃገርሽ በተለየ  የሚናፍቅሽ ነገር ምንድን ነው?
መድረክ ነው የሚናፍቀኝ፤ ህዝቡ ነው የሚናፍቀኝ። አብሮኝ መድረክ ላይ ሲሆን የሚጮኸው፡፡ ሣለቅስ የሚያለቅሠው፣ ስስቅ የሚስቀው - ተመልካቼ ይናፍቀኛል፡፡ የጥበብ ሰው--- ሠዓሊ በለው፣ ሙዚቀኛ በለው፣ ተዋናይ በለው---የህዝብ አይንና እጅ ሆኖ፣ ስለ ህዝብ ስሜት ነው የሚሰራው፡፡ ያ ተመልካች እንዴት እንደሚናፍቀኝ ለመግለፅ አልችልም፡፡ በመላው ኢትዮጵያ የሰራኋቸው መድረኮች በሙሉ ይናፍቁኛል። አሶሳ መድረክ በሌለበት፣ መኪና ላይ መድረክ ሠርተናል፡፡ ውሽውሽ ሻይ ልማት፣ በበቃ ቡና ልማት እርሻ ውስጥ ትያትር ሰርተናል፡፡ ከእነ ወጋየሁ ንጋቱ ጋር ማሾ እያበራን ትያትር ሰርቻለሁ፡፡ የዚያን ህዝብ ፍቅርና ስሜት ነው ተሸክሜ የወጣሁት፡፡ መቼም አልረሳውም። ልጆቼንም ኢትዮጵያ ሲገቡ ልብ ብለው እንዲያዩ የምፈልገው፣ ህንፃውን አይደለም፤ የህዝቡን ፍቅር፣ የህዝቡን ትህትና፣ የህዝቡን ትልቅነት እንዲያስተውሉ ነው የምመክራቸው፡፡ ይህ ለራሱ ከመብላቱ በፊት ለሌላው የሚያጎርስ ህዝብ ያልናፈቀኝ፣ ማን ይናፍቀኛል ብለህ ነው፡፡ በጣም የናፈቀኝ ህዝቡ ነው፡፡
ወደ ሃገር ቤት መቼ ትመለሻለሽ?
የመምጣት ሃሳብ አለኝ፡፡ አሁን ካስቀመጥኩት ዓላማ ጋር የተሣሠረ ትንሽ ነገር ባገኝ ደስ ይለኛል። መድረኬ ላይ የማቀርበው ነገር ኖሮኝ፣ ከህዝቤ ጋር በመድረኬ ነው መገናኘት የምፈልገው፡፡ እኔ የመድረክ ሰው ነኝ፡፡ በስደትም ቢሆን በግጥሞቼ፣ በፅሁፎቼ ነው ህዝቤን ሳገኝ የነበረው፡፡ አሁንም በመድረክ ህዝቤን ማግኘት ይናፍቀኛል፡፡ እግዚአብሔር ይጨመርበትና ተስፋ አለኝ፤ በቅርቡ ልመጣ እችላለሁ፡፡ የጥበብ ሰውና የሚዲያ ሰው ሃላፊነት ከባድ ነው፡፡ ህብረተሰብን መቅረፅ፣ ለህብረተሰብ እኩልነትና ነፃነት መቆም፣ አንደበት መሆንን ማቋረጥ የለብንም፡፡ አንድን ነገር የሚለውጠው፣ የመንግስት የፖለቲካ ስርአት ለውጥ ሳይሆን የህብረተሰብ አስተሳሰብ ለውጥ ነው፡፡ አሁን አሜሪካ ዲሞክራሲ አለ ተብሎ ቢነገርም፣ በደሎች የማይበዙት፣ ህዝቡ እምቢ ስለሚል ነው፡፡ አስተሣሠቡ የተለወጠ ህብረተሰብ ስለሆነ፣ ራሱ ዲሞክራሲውን ይኖረዋል፡፡ እኛም ህዝባችንን ወደዚህ መለወጥ አለብን። ይሄ የጥበብና የሚዲያ ሰዎች ትልቅ ሃላፊነት ነው፡፡
ለናፈቀሽ ህዝብ የምታስተላልፊው መልዕክት አለሽ?
በመጀመሪያ፤ ይሄ ሠላምና ፍቅር የናፈቀው ህዝብ፤ የናፈቀውን እያየ በመምጣቱ፣ እንኳን ደስ አለን እላለሁ፡፡ ይህን ሁኔታ ለማምጣት ህይወታቸው ያለፈ፣ አካላቸው የተጎዳ፣--- ልጆቻቸውን ያጡ እግዚአብሄር ያጽናቸው። “ልጆቻችሁ ለህዝብ የብርሃን ቀን ለማምጣት ነው ዋጋ የከፈሉት” ብዬ ላፅናናቸው እፈልጋለሁ፡፡ ግን ይሄን ሁኔታ ለማምጣት ያለፉት ሁኔታዎችን መቼውንም መርሳት የለብንም። የተጀመረው ለውጥ ወደ ትልቅ ደረጃ እንዲሸጋገር፣ እያንዳንዱ ባለው ሁሉ እንዲሠራ እጠይቃለሁ፡፡ በእኩልነት፣ በነፃነት አንድ ላይ የምንኖርበትን ሃገር እንድንመሰርት ጥሪዬን አቀርባለሁ። የጥበብ ሰዎች የሚዲያ ባለሙያዎች ---- ቀሪ ነገሮች እንዲሟሉ፣ ያለማወላወል እየጠየቁ፣ የህብረተሰቡ አይንና ጆሮ ሆነው እንዲሠሩ አደራ እላለሁ፡፡ በተረፈ ሙሉ ሃገር ናት ያለችን፤ በጣም ቆንጆ አለም፣ የሚቀናበት ባህልና ታሪክ ነው ያለን፡፡ ያንን ደግሞ በአዲስ የተሻለ ታሪክ እንድንቀይረው እንትጋ እላለሁ፡፡

Read 2663 times