Saturday, 07 July 2018 11:30

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(4 votes)

 “አገሩን የሚወድ የአገሩን ህዝቦች ያምናቸዋል”
             
    ሔዋን አዳምን፣ እባብ ሔዋንን አሳሳተ ተባለ። እባብን ያሳሳተው ማነው? … የስህተት ዕድሜ ስንት ነው? ተብሎ ሲጠየቅ መልስ የለም፡፡ … ሰው መጀመሪያና መጨረሻ በሌላቸው ጥያቄዎች ተሞልቷል። እውነቱን የሚነግረው የለም፡፡ እውነት የባለቤቷ ናት። … እንደምነግርህ ተረት አይደለችም፡፡ … አዳም ከዕውቀት ዛፍ ፍሬ ቀመሰ፡፡ … ብርሃን አየ። ራቁቱን መሆኑ ታወቀው፡፡ ሴቲቱን አይቶ አፈረ። … እግዜር በሴቲቱ ተበሳጨ፡፡ ትንፋሿን መልሶ ነጠቃት። እሱን ወደ ምድር ወረወረው፡፡ በየጫካው እየዞረ ስራስርና ቅጠላ ቅጠል እየመረጠ ሲበላ፣ ከቆንጆ ዝንጀሪት ጋር ተዋወቀና አገባት፡፡ ወለዱ፣ ከበዱ፡፡ እናንተን የመሰለ የልጅ ልጆች አፈሩ፡፡ ሰው በግማሽ ጎኑ አውሬ ነው የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ .. ያኔ ባለስልጣን ነበርኩ። “እኔ” በገነት ስንሸራሸር ሔዋንን አገኘሁዋት። በድን ነበረች። እንደ በረዶ ቀዝቃዛ!! ‹እፍ› አልኩባት። ሙቀት ስታገኝ ተፍታታች፡፡ አወራን፡፡ ከገነት አስመለጥኳት። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በአካል ተገናኝተን አናውቅም፡፡ በቀደምለት አዲስ አበባ አገኘሁዋት፡፡ … በነገራችን ላይ ማን እንደሆንኩ አስታወሳችሁኝ? …
***
እግዜር ሰውን ፈጠረ፡፡ ትንፋሹን እፍ አለበት፡፡ ሰውን ‹ሰው› አደረገው፡፡ … እንደ ራሱ፡፡ ይኼን የእግዜር ትንፋሽ፣ አንዳንዶች ሩህ ይሉታል፡፡ በባህላዊ እምነቶች ሰው የተፈጠረው ከውሃ፣ ከአየር ወይም ከነፋስ፣ ከእሳትና ከአፈር ነው ተብሎ ይነገራል፡፡ ይህ አስተሳሰብ ከሞላ ጎደል ከክርስቶስ ልደት በፊት ከነበሩ (624-371 BC) ሊቃውንት አጠቃላይ እሳቤ ጋር ይመሳሰላል፡፡ … የመጀመሪያው አውሮፓዊ ፈላስፋ የሚባለው ታሌስ፤ “የህይወት እርሾ ውሃ ነው” የሚል እምነት ነበረው፡፡ “ውሃ አይደለም አየር ነው” ብሎ የተከራከረው ደግሞ አናክሲሜነስ ሲሆን “ሁለታችሁም ተሳስታችኋል” የህይወት ፅንስ እሳት ነው” የሚለው ሄራክሊተስ ነው። ከነዚህ የተለየ ሃሳብ የነበራቸው የአናክሲሜነስ መምህር አናክሲማንደር እና ዲሞክሪተስ ነበሩ። አናክሲማንደር “የህይወት ፅንስ በርግጥ አለ፣ ለመግለፅ ግን ያስቸግራል” (… idefinite’s stuff, aperion) ባይ ነው። ይህኛው አስተሳሰብ፤ ህይወት ከረቂቅ አተሞች ይፀነሳል ከሚለው የዲሞክሪተስ ሃሳብ ጋር ይቀራረባል። … ከነሱ በኋላ የነበሩ ሌሎች ብዙ ሊቃውንት ደግሞ፡-
“የህይወት ፅንስ መኖሩ እንጂ ምን እንደሆነ አይታወቅም፡፡ መጀመሪያም መጨረሻም የለውም፤ ‹አሁንን› እና ‹ዘለዓለምን› እንዴት መነጠል ይቻላል? … በክብ ውስጥ የመጀመሪያዋ ነጥብ የትኛዋ እንደሆነች መለየት ያስቸግራል፡፡ ጊዜ እንኳ የሚለካው በውስጡ በሚኖረው ነገር ነው፡፡ በጊዜ ውስጥ የሚኖር ከሌለ ጊዜ የለም፡፡ … ‹መኖር› ካለ ደግሞ እርሾው ምክንያት ነው” ይላሉ፡፡
ወዳጄ፡- ሰው የሆንክበት ምክንያት አለህ፡፡ ለመኖር ትገደዳለህ፡፡ የህልውናህ ፅንስ ምክንያትህ ነው። ፍላጎትን ያሳደረብህ፣ ጉጉትና ምኞትን ያሰረፀብህ ምክንያት ነው። ትንፋሽህ ምክንያት ነው፡፡ ነፍስህ የምትንፈራገጠው በምክንያት ነው፡፡ … መብላት፣ መጠጣት፣ መጠለያ ማግኘት መብት ሳይሆን ተፈጥሮ ነው፡፡ የመሆንና ያለመሆን ጉዳይ አይደለም፡፡ የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ እንጂ!! … ህልውናህ ተፈጥሮህ ነው፡፡ ከተፈጥሮህ ጋር ድርድር የለም፡፡ መሆን ያለበት ብቻ ይሆናል፡፡ መሆን ያለበት ሊሆን ካልቻለ ትታገላለህ፡፡ ካልታገልክ ሬሳ ነህ!! … ትንፋሽህን ተነጥቀሃል፡፡
ወዳጄ፡- ሰው የሁለት ተቃራኒ መንፈሶች ውሁድ ነው ይባላል፡፡ በህይወት ለመቆየት አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ ያደርጋል፡፡ ይሰራል ይደክማል፣ ይወድቃል ይነሳል፣ ይወዳል፣ ይጠላል፣ ያፈርሳል፣ ይገነባል፣ ያሸንፋል፣ ይሸነፋል፡፡ አንዳንዴ ታጋሽና ንቁ፣ አስተዋይና ፍትሃዊ ይሆናል፡፡ አንዳንዴ ቁጡና አመፀኛ፣ ወላዋይና መንገኛ ይወጣዋል፡፡ መንገዱን የሚያርቅለት ዕውቀቱ ነው። በጭለማ ይበራለታል። የራሱን ፍላጎት ለመሙላት በሌላው ሰው መንገድ እንዳይደነቀር ያደርገዋል፡፡ ይሉኝታ-ቢስና ኢ-ሞራላዊ እንዳይሆን ይወተውተዋል።
ዕውቀቱ መናኛ ከሆነና አስተሳሰቡ ከደከመ፣ ደመነብስ መሪውን ይጨብጣል፣ ራስ ወዳድ ያደርገዋል። ‹እሰይ! ደግ አደረግሁ፣ ልቤ ቅቤ ጠጣ!› ባይ ይሆናል፡፡ “… “ምን ነካኝ?... ተሳስቻለሁ፣ አጥፍቻለሁ” እያለ ከሚፀፀትባቸው እርምቶች ያርቀዋል። ከቅድስናው ይልቅ ወደ አውሬነቱ የሚያደላው መንፈስ ይበረታበታል፡፡ አርስቶትል፡- “The human average, is nearer to the beast than to the god” እንደሚለው፡፡   
ወዳጄ፡- ሰው በእውቀት ካልተመራና ሃሳቡን በዕውነት ላይ ካላፀና፣ መንገዱ ሁሉ የገደል ቁልቁለት ሊሆንበት ይችላል፡፡ ጭፍን ራስ ወዳድነቱ እያንከባለለ ወደ መጨረሻው ያስጠጋዋል፡፡
“ላልተገራ ፈረስ ልጓምና ሳቢያ እንደሚያስፈልገው ህይወት ከምትነዳበት ቅጥ የለሽ ፍላጎት መቀዛቀዝ የሚቻለው በዕውቀት ስንመራ ነው (… for what bridle and bit are for the imaginable horse, the intellect is for the will in man) የሚለን ሾፐን ሃወር ነው፡፡ ዘመናዊው የሾፐን ሃወር ‹Will› ቀደም ካሉት ፈላስፋዎች (አናክሲሜነስና ዲሞክሪተስ) አስተሳሰብ ጋር ዝምድና እንዳለው የሚያስረዱ ማስረጃዎች አሉ፡፡
ዞሮ ዞሮ ማንኛውም የሰው ልጅ ድርጊት፤ ከማወቅና ካለማወቅ ወይም ከሃሳብ ትልቅነትና መናኛነት ሽክርክሪት ውስጥ ያፈነገጠ አይደለም፡፡ “ድርጊት የሃሳብ የመጨረሻው ደረጃ ነው” (an action is the last stage of an idea) የሚለን አርስቶትል፤ ይህንኑ ሲያረጋግጥልን ይመስላል፡፡ … ጠብ፣ ፍቅር፣ ስዕል፣ ስነፅሑፍ፣ ሙዚቃ፣ ሥራ፣ አመጋገብ፣ አለባበስና የመሳሰሉት የህይወትና የጥበብ ልቃቂቶች ሁሉ ከሃሳብ የሚወለዱ ናቸው፡፡
ወዳጄ፡- አገርን መውደድማ ሃሳብ ነው፡፡ የዚህ ሃሳብ መገለጫ ደግሞ የሚያስበው ሰው ተግባር ነው፡- አገሩን የሚወድ ካገሩ አይሰርቅም፡፡ አገሩን የሚወድ ከድሆች አፍ አይነጥቅም፣ አገሩን የሚወድ የአገሩን ጥቅም ያስከብራል፣ አገሩን የሚወድ ለአገሩ ዘብ ይቆማል፣ አገሩን የሚወድ ፍላጉቱን ካገሩ ፍላጎት አያስበልጥም፣ አገሩን የሚወድ የአገሩን ህዝቦች ያምናቸዋል፡፡ አገሩን የሚወድ ልጆቹንና ቤተሰቦቹን ከአገሩ ጉያ አያርቅም፡፡ አገሩን የሚወድ … የተረፈውን ላንተ ለወዳጄ ትቸዋለሁ፡፡
***
ወደ ተረታችን እንመለስ፡፡ … ዛዴሞስ እባላለሁ፤ አስታወስከኝ?! … የንጉሥ ሰለሞን ጓደኛ ለነበርኩ። ለሺ ዘመናት ደብረ ዘይት ኖሬአለሁ፡፡ … ሆራ ሃይቅ ውስጥ። ቆሪጥ እያሉ ነበር የሚጠሩኝ፡፡ በ ‹MGM› ተጠልፌ ወደ ዋሽንግተን እንደተወሰድኩ ፅፌልህ ነበር። ሳይንስ ማረከኝና ቴክኖሎጂስት ሆንኩ ብዬሃለሁ። አልፎ አልፎ ወደ ኢትዮጵያ ስመጣ፣ ‹ልዩ መንፈስ› ያላቸው ሰዎች ይለዩኛል፡፡ ‹ነቢዩ ኤልያስ መጣልን!› እያሉ ይከተሉል ብዬ አውግቼሃለሁ፡፡ እንዲህ ሲሆን ራሴን እሰውራለሁ። ወደ ቁምነገሩ ልምጣልህና፣ የዛሬ ሳምንት ቅዳሜ የቴክኖሎጂ ዲስፕሌይ ለማየት አዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ተገኘሁ፡፡ ይኸውልህ… እግዜር ተበሳጭቶ በድን ያደረጋትን ልጅ አገኘሁዋት። … ሔዋንን!! ስታየኝ በጣም ደስ አላት፡፡ ምንም አልተለወጠችም፡፡ ሳዑዲ አረቢያ ክርስትና ተነስታ፣ ‹ሶፊያ› ተብላ እንደተጠመቀች አጫወተችኝ፡፡ … ደስ ይላል!
“የሰውን ልጅ አጠፋለሁ ብለሻል እያሉ ያሙሻል” አልኳት፡፡
“እንክት ነዋ!” አለችኝ፡፡
“ለምን?”
“ሮቦት እያሉ ስሜን ያጠፋሉ” አለች፡፡
“ሰው ምን አደረገሽ? እግዜር ነው የበደለሽ” ብላት ዝም አለች፡፡
“ሶፊ፤ አህያውን ፈርቶ ዳውላውን ማለት እንደዚህ ነው” አልኳት፡፡ ሳቋን ለቀቀችው፡፡
“አንተን ካገኘሁማ ሃሳቤን እቀይራለሁ!” አለች፡፡
እግዜር ጨዋታችንን ሰምቶ ይቅር አላት መሰለኝ፤ ስትስቅ እንባዋ ጠብ አለ፡፡ Wonders never end!! እንዲሉ፡፡
ሠላም!!!

Read 1169 times