Saturday, 07 July 2018 11:28

የቀንዲል ንባቦች

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(5 votes)

መጀመሪያ ያየሁዋት ቀን ልቤ ደነገጠ፡፡ አብሬው የገባሁት ወዳጄ እስኪደነግጥ፣ ዐይኔን ከእርሷ ላይ መንቀል አቃተኝ፡፡ አብሬያት ተንከራተትኩ፡፡ ጨዋታ ጠፋኝ፡፡፡ ሆዴ እጅግ ባባ፡፡ በተለይ ሁለት የከፈለችው ፀጉሯና ድንቡሼ ጉንጮችዋ  ይዞኝ በረረ፡፡
“ምነው ልክ አይደለም ሁኔታህ!”
“አአይ---” አልኩ፤ግን ባለቅስ ደስ ይለኛል፡፡ ስቅስቅ ብዬ -- ወይም ምራቄ ደርሶልኝ ወደ ሰማይ በንዴት ብተፋ - እርካታዬ ወሰን የለውም፡፡
“ምን ልታዘዝ?” ራሷ መጣች፡፡
አንደበቴ ተይዟል፣ ልቤ - ይመታል፡፡
“ለኔ ቡና እንደወረደ” አለ ጢሙን እየፈተለ፡፡
“አዚህስ?”
ድንገት፤ “ጠቆር ያለ ማኪያቶ“
ጂንስ ሱሪዋን ታጥቃ፣ ሞንደል ሞንደል እያለች ወደ ማሽኑ ሄደች፡፡ ካዛንችስ ከሄድኩ ከዚያ ቤት በቀር ማኪያቶ አልጠጣም፡፡ ወደ ባልደራስ የሚሄዱ ታክሲዎች የሚቆሙበትና ጋዜጣ ለማንበብ የሚመች ቦታ ነው፡፡ ያኔ ተማሪ እያለሁ፣ አሰብ---ቀስተደመና ከጓደኞቼ ጋር ድራፍት እጎነጭ ነበር፡፡ አንዳንድ ትዝታዎች አሉኝ፡፡ ደስ የሚሉና የሚያስጠሉ፡፡
ይሁንና ይህቺን ልጅ አይቻት አላውቅም። አልተገጣጠምን ይሁን ወይም ሌላ፣ ዛሬ የመጀመሪያችን ነው፡፡ ወዳጄ ጨዋታውን ቀጥሏል። የሚያወራልኝ ጎረቤቱ ስላለች ሀሜተኛ ሴት ነው፡፡ በተለይ በሩን ዘግቶ ሲቀመጥ፣ ሰው የሌለ እየመሰላት ካገኘችው ሰው ጋር ሆና፣ የሰው ሥጋ እንደምትበላ ያወራኛል፡፡ እኔም ዝም እስካልኩበት ቅፅበት ድረስ የአከራዮቼን ጠባይ ስዘረዝርለት ነበር፡፡ በተለይ ባልና ሚስቱ ከሥራ መልስ ተያይዘው ወጥተው፣ አብረው እንደሚጠጡ ስነግረው፣ በጣም ተደንቆ ነበር፡፡
“Amazing!”
አሁን ግን እኔ መናገርም ማዳመጥም አቅቶኛል።
“በየዕለቱ ቤተ ክርስቲያን የምትሮጥ ሴትዮ፣ እንደዚያ ሀሜተኛ ያደረጋት ነገር አልገባ ብሎኛል” አለና ትንሽ ተነፈሰ፡፡
“ለነገሩ ይሄ ኮንዶሚኒየም የምትለው ካምፕ፣ የብዙ የሕይወት ትርዒቶች የሚታዩበት መድረክ ነው፡፡ አንዳንዶች እንደ ከብት ርቢ፣ ልጆች ለመውለድ ብቻ ውሽሞቻቸው ወይም ሚስቶቻቸው ቀለብ እየሰፈሩ የሚያኖሯቸው ናቸው፡፡”
ልጅቱ ማኪያቶና ቡናውን አምጥታ፣ በየተራ አስቀመጠችልንና፤ “ስኳር ካነሰው እዩና ጨምሩበት” አለችን፡፡ ወዳጄ ተቆጣ፡፡
“ስኳር ለምን ትጨምሩበታላችሁ? ከፈለግን እኛ ራሳችን ለምን አንጨምርም?”
“በቃ - ተዋት! ዝም በላት!” ብዬ ጠበቃ ለመሆን ሞከርኩ፡፡
“ሽማግሌ ነገር ነህ!” አልኩት፡፡
ፈገግ አለና ዝም አለ፡፡ ማኪያቶዬን ፉት እያልኩ፣ እንባዬ ዐይኔን መታከክ ጀመረ፡፡
አልቻልኩም፣ ልጅቷን ጠራኋት፡፡
ወዳጄ ነገሬ አልገባውም፡፡
“ስምሽ ማን ነበር?”
“ቀንዲል!”
“ደስ ሲል!”
“አመሰግናለሁ!”
ቲፕ ደህና አድርጌ ሰጠኋትና፣ ከወዳጄ ጋር ተያይዘን ወጣን፡፡ ውስጤ ይዘፍናል፡፡ “ፍቅሬ ያለሺበት ሀገር አማን ነወይ?”
ይጨንቀኛል ዝምብሎ፣
ይጨንቀኛል፣
አልቻልኩም እኔ፣
እስካይሽ ባይኔ፡፡
ወደ ቤቴ ሄጄ ልረሳት አልቻልኩም፡፡ አላስቻለኝም። ሌላም ቀን ማኪያቶ ፍለጋ ሳይሆን ላያት መጣሁ፡፡ ወደ ቡናው ማሽን አካባቢ  ቆማለች፡፡ አየኋትና አስጠላችኝ፤ ተናደድኩ፡፡ ጠራኋት፡፡ ሁኔታዬን የወደደችው አልመሰለኝም፡፡
“ምንድነው ይሄ ፀጉርሽ?”
“ምን ሆነ?” አለች በድንጋጤ፣
“አያምርም! ያኛውን ዓይነት ለምን አትሰሪም?”
ኮስተር አለችና፤ “እሱ እንኳ የኔ ምርጫ መሰለኝ፡፡”
ብንን እንደማለት አደረገኝና፤ “ይቅርታ እውነትሽን ነው፡፡ እኔ ግን ደስ የምትይኝ ያንን ዓይነት ስትሰሪ ነው-”
 ግራ በመጋባት ትኩር ብላ አየችኝ፡፡
“ለምን እንደሆነ ታውቂያለሽ?”
“አላውቅም ኧረ!”
“ተይው! በቃ!”
“ማለቴ ትልቅ ሰው አይደለህ እንዴ?”
“ታዲያ ትልቅ ሰው አይናፍቅም? … ትልቅ ሰው የፍቅር መስመር የለውም፡፡”
“ሊሆን ይችላል፣ ግን ..”
ሳንግባባ ማኪያቶዬንም ሳልጠጣው ወጣሁ። ቲፕዋን በሚገባ ሰጥቻለሁ፡፡ ቢያንስ እነዚያ ድንቡሼ ጉንጮችዋን እያየሁ፣ መጨከን አልችልም፡፡
“ሚስት የለችህም?” አለችኝ፤ ሌላ ቀን፡፡
“ነበረችኝ!”
“እና ምን ሆነች? ተፋታችሁ?”
“አአይ- ከዳችኝ!”
“ውይ ጨካኝ ናት!”
“ጨካኝማ አይደለችም”
“ሳይህ ገራገር ነገር ነህ፣ እንዴት ብቻህን ተወችህ ብዬ ነዋ!”
ለረዥም ደቂቃዎች አቀርቅሬ፣ቀና ስል፣ ልጅቷ ወደ ሥራዋ ሄዳለች፡፡      
ተመልሳ ስትመጣ፣ ቁርጧን ነገርኳት፡፡ አንዳንድ ሰዎች ተገርመው ያዩኛል፡፡ አንዳንዶቹ ልብም አይሉኝ። ብዙዎቹ ሞባይላቸው ላይ አፍጥጠው፣ የራሳቸው ዐለም ውስጥ ሰጥመዋል፡፡
“አክሊልን ስለምትመስይኝ ነው--”
“አክሊል ማናት?”
“ፍቅረኛዬ!”
“የት ሄደች - አሁን?”
“ተይኝ ባክሽ፤የሰባተኛና ስምንተኛ ክፍል ጓደኛዬ ነበረች፡፡ ወላይታ ሶዶ ስማር፣ ከሊጋባ በየነ ትምህርት ቤት ፊት ለፊት ነበር ቤታቸው--”
“ኧረ እኔ አላውቀውም! ግን የድሮውን እንዴት አትረሳም!”
“እኔጃ ትዝታ ነው!”
ሄድ መጣ እያለች አዳመጠችኝ፡፡ ጨዋታዬ የጣማት መሰለኝ፡፡
“አክሊል ፀጉሯን እንዳንቺ ነበር የምትሰራው፣ እንዳንቺ ሱሪ ባትለብስም፣ የዳሌዋ ቅርፅ ካንቺ ጋር ይመሳሰላል፡፡ ሥትስቂም ራስዋን ትመስያለሽ--”
መገረምም መደሰትም ዓይነት ነገር አየሁባት፡፡ ምን ዐይነት ጅል ነው፣ ሳትለኝም አትቀር!
እንደዚህ ደጋግሜ እየሄድኩ፣ ሳጫውታት በጣም ተላመድን፡፡ ችግሯን ሳይቀር ታወያየኝ ጀመር፡፡ ደስታ ሀዘኗን፣ ፍቅርና ጥላቻዋን፡፡ እኔም ደስ አለኝ፡፡ አክሊልን ያገኘሁ እየመሰለኝ፡፡
አንድ ቀን ግን በቁም ነገር መጥታ አጠገቤ ተቀመጠች፡፡
“እስቲ ንገረኝ---በስንት ዐመተ ምህረት ነበር!...”
ሁሉንም ነገርኳት፡፡
“በኢሕአፓ ዘመን ነው እንዳትለኝ ብቻ!”
“አዎ! በእነ ጌታቸው ማሩ፣ በእነ ብርሃነመስቀል ረዳ ዘመን! ሰው ሰውን አሳልፎ በሚሰጥበት! የፓርቲ ፍቅር፣ ከሰው ፍቅር በበለጠበት! ማርክስ፣ ኤንግልስና ሌኒን - በመለኮት በተመሰሉበት!--”
ልጅቷ የዋዛ አይደለችም፡፡ አንገቷን እየነቀነቀች፣ አንዳንዴም እያወራች፣ ሀሳቤን አደመቀችው፡፡
“እሺ፤ አክሊል ምን ሆና ከዳችህ?”
“ኢሕአፓ በላት! … ገና በልጅነቷ ዋነኛ ሆነችና፣ ወህኒ ቤት ገብታ ሞተች-”
“እርግጠኛ ነህ? … ያንተ ስም ማን ነው?”
“የኔ ስም --- ረድኤት!”
“ጉዴ ፈላ!”
“ነገሩ ቲአትር እንዳይሆን፣ …”
“ፍፁም እውነት እየነገርኩሽ ነው፡፡ ከልቤ ነው---በጣም እወዳት ነበር--”
“የሚገርም ነገር ልንገርህ! … ለእናቴ ታሪክህን አጫውቻት ነበር፡፡ በጣም እየተደነቀች ነው የሰማችኝ--”
“አለቃ ነገር ነበርክ?!”
“ያንድ ክንፍ አስተባባሪ!”
“እንዲያውም ዛሬ መምጣትህን ነግሬያት ነበር። ልትተዋወቅህ ትፈልጋለች፡፡ ያው አባቴም ስለሞተ ሀዘንተኛ ናት---”
“ኦው ሶሪ! አይዞሽ!”
“ዩኒቨርሲቲ ትምህርቴን አቋርጬ ነው እዚህ የምሰራው!”
ሀዘኔ እጥፍ ሆነ፡፡ ምን ላድርጋት? እያልኩ ሳስብ፣ እናቷ ብቅ አለች፡፡
“ጤና ይስጥልኝ!”
“አንተ … አፍንጫህና ጥርስህ ብቻ አልተለወጠም፡፡ ይገርማል! ሞቷል ተብዬ‘ኮ!…”
ተጠምጥማብኝ  ስታለቅስ፣ ጥርሶችዋና ከንፈሮችዋ ታወሱኝ፡፡
“አወቅከኝ--- አክሊል ነኝ!”
ሰው ጉድ እስኪለን ተላቀስን፤ ተከበብን፡፡ ሰዎች ከንፈራቸውን መጠጡ፡፡
“አንቺም ሞተሻል ተብሎ ነበር?!” አልኳት፡፡
ወደ መኖሪያ ቤቷ ወሰደችኝ፡፡ ለጊዜው እንባዬ ቆመ።     

Read 2751 times