Saturday, 07 July 2018 11:22

ይቅርታንና ፍቅርን፤ ከባነር ወደ ተግባር

Written by  በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ አንለይ
Rate this item
(7 votes)

“የይቅርታን፣ የዕርቅንና የመደመርን ባነር አንግበን፣ በጥላቻ ጎዳና ከመጓዝ እንመለስ”
     በሀገራችን ያለው ሁኔታ ከቀደሙት ጊዜዎች ባልተናነሰ አሁንም አሳሳቢ ነው ማለት ይቻላል። የሚታዩት ግጭቶች፣ ዘውግ ተኮር ጥቃቶችና የመሳሰሉት ሁሉ በየሰው ልብ ውስጥ ላለው ወይም ለተረገዘው ጥላቻ፣ ቂምና ቁርሾ ማሳያዎች ናቸው። በግጭት ወይም በሌላ መሰል ክስተት ያልተገለጹ፣ በየሰው ልብ ግን የተቋጠሩና ምቹ ሁኔታዎችን የሚጠብቁ ቁርሾዎች መኖራቸውንም የሚጠቁሙ ናቸው እንጂ ብቸኛ ችግሮች አይደሉም ለማለት ያስደፍራል፡፡ ይህም የሚያስደነቅ ሊሆን አይችልም፡፡
በንጉሡ ዘመን ከተቀነቀነው ዘውጌ ተኮር አብዮት ጀምሮ ከስድሳ ዐመታት ለሚበልጥ ጊዜ ማፍረስና ማፈራረስ ሲፈጸምበት የኖረው ኢትዮጵያዊ ጨዋነት፤ እርሾው ቀርቶለት ካልሆነ በቀር ብዙ ነገሩ አለ ለማለት ያስቸግራል፡፡ ከዚህም ሁሉ ጋር ባለፉት ዐርባና ሃምሳ ዐመታት በአብዮት፣ በውትድርናና በመንግሥት ለውጥ ምክንያት ከቅርብ ቤተሰቡ ቢያንስ፣ አንድ ሰው ያላጣ ቤተሰብ መኖሩ አጠራጣሪ ነው፡፡ ከዚህም ሁሉ ጋር ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል ነገሮችን፣ ክስተቶችንና ታሪኮችን ከዐውዳቸው አውጥቶ ቆርጦና ቀጣጥሎ የተለየ ትርጉም ሰጥቶ፣ ጥላቻን ሲዘራ የኖረ ሁሉ፣ እንደ ታጋይና አታጋይ፣ እንደ አርበኛና የዘውግ መሲሕ ሲታይ ሲከበር እና ሲዘመርለት የመጣንበት ዘመን ነው፤ አሁንም እንኳ ገና ከዚያ ቅኝት የወጣን አይመስልም። ስለዚህ ባሳለፍናቸው በርከት ያሉ ዐሥርት ዐመታት በአንድም ሆነ በሌላ የዘራናቸው ከሌሎች ሀገር ዜጎች ፖለቲከኞች የገዛናቸውም ሆኑ ከራሳችን ያመነጨናቸው  የፖለቲካ በሽታ አምጭ ተውሳኮችን፣ ከአስተሳሰብ ደማችን የሚጠርግ፣ በቂ ሕክምና ባላገኘንበት ሁኔታ፣ ግጭቶችና በቀሎች በአጭር ጊዜ ይጠፋሉ ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡
ሆኖም አንድ በጽኑ በሽታ የተያዘ ሰው ጥርሱን ነክሶ፣ ስቃዩን ችሎ መታከሙ፣ ለነገ ጤንነቱ እንደሚጠቅመው ሁሉ፣ እኛም ጥርሳችንን ነክሰን የውስጥ ስቃያችንን፣ ቅሬታችንን፣ የበቀልና የጸብ ስሜቶቻችን ገትተን፣ ወደ ይቅርታና ዕርቅ ከማምራት ውጭ ምንም አማራጭ የለንም፡፡ ከዚህ በኋላ የምትፈጠረው እያንዳንዷ ትንሽ ነገር ከፍተኛ ዋጋ እንደምታስከፍል፣ ዛሬ መገንዘብ ካልቻልንና ድርጊቶቻችን በሙሉ በርጋታና በጤናማ አስተሳሰቦች ላይ ካልተመሠረቱ፣ አሁንም የችግሩን አዙሪት እናሰፋው፣ ጥልቀቱንም እናርቀው ካልሆነ በቀር፣ ተስፋችን ዝናብ የሌለው ባዶ ደመና ከመሆን አይድንም፡፡ ስለዚህ በእውነት ይቅርታና ዕርቅን የምንፈልጋቸው ከሆነ ይዘናቸው ከምንወጣቸው የሰልፍ የመፍክር ባነሮች ላይ አንሥተን፣ ወደ ትክክለኛ ቦታቸው፣ ወደ ልባችንና ወደ አስተሳሰባችን ማስገባት ይኖርብናል፡፡
ሰሞኑን በተለይ በመስቀል አደባባይ  ከተደረገው ታላቅ የድጋፍ ሰልፍ በኋላ፣ በማኅበራዊ ሚዲያው ላይ የሚሽከረከሩ ግምቶች፣ ፍረጃዎችና ለፍቅር በመቆም ስም የሚቀነቀኑ ጥላቻዎች፣ እውነተኛ መረጃዎችን ሊደብቁ ከመቻላቸው አልፎ ለተጨማሪ ችግሮችና የምናቀነቅንለትንና እንወደዋለን የምንለውን ዐላማ በአጭር ከማስቀረት የዘለለ ፋይዳ የሚኖራቸውም አይመስለኝም፡፡ እኔም በዚህ ጽሑፍ ለዐመታት ከሰለጠነብንና አሁንም ካልተላቀቅነው ከንቱ ፍረጃና ጥላቻ ለመውጣት ሊረዱን ይችላሉ ብዬ በማስባቸው ጉዳዮች ላይ መጠነኛ ሀሳብ ላቅርብ፡፡ በመሆኑም ለዚህ ችግር መፈጠር ምክንያት ከሚሆኑት ጥቂቶቹን እንኳ በመመርመር ወደፊት ለምናደርገው ሰላማዊ የፍቅርና የአንድነት ጉዞ ሊጠቅሙ ይችላሉ ብዬ ያመንኩባቸውን ችግሮች ከማስቀደም ልጀምር፡፡  
ስምዐ አድሎ (Confirmation bias)
አሁን ያለው የእኛ ማኅበረሰብ ቀርቶ በየትኛውም ሀገርና ዘመን የሚኖር ሕዝብ ሁሉ፣ በትንሹም ቢሆን በዕውቀትና በማስረጃ ያልተደገፈ እምነት አለው። ቀደም ብሎ እንደተጠቀሰው ደግሞ በተለይ በመማራችን ብቻ እናውቃለን ብለን የምናስብ ሰዎች ችግሩ ጎላ ብሎ ሊታይብን ይችላል፡፡ ይልቁንም ደግሞ አሁን ባለው ሀገራዊ ክስተት ውስጥ ንቁ ተሳታፊ የሆንነው ሁሉ፣ አንዱ ስለ ሌላው የሚያምነው እምነት ከፍተኛ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል በአሁኑ ወቅት ከሌላ ዘውግ (ብሔር) ራሱን ከሚመድበው አብዛኛው ትግሬ ስለሆነ፣ ሰው ሁሉ የተለያየም ቢሆን የየራሱ እምነት አለው፡፡ ከትግራይ የሆኑት ደግሞ ስለ አማራና ስለ ኦሮሞ ብዙዎች አሁንም የራሳቸው እምነት አላቸው፡፡ እንዲያውም ይህ ወቅት በሌላው ጊዜ ነጻ አመለካከት የነበራቸው ሁሉ፣ ከዚህ በፊት |በሌሎች አይተው የተጸየፉትን እምነት ራሳቸው የሚገዙበት ወይም በባለቤትነት ይዘው እስካሁን መታለላቸውን የሚናገሩበት ወቅትም ሊሆን ይችላል፡፡ ታዲያ ይህን እምነት ከያዝን በኋላ፣ ለመግባባትና ወደ አንድነት ለመምጣት በጣም አዳጋች ይሆናል፡፡
ምክንያቱ ምን ቢነገር ቢጻፍ ቢታወጅም፣ አእምሮአችን ሁለት ችግሮች ይገጥሙታል፡፡ እንደ ማንኛውም እምነት ሁሉ አእምሮአችን የሚፈልገው የሚያምነውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ እንጂ የቀረበውን ማስረጃ መርምሮ አቋም ማስተካከል ይሳነዋል፡፡ ስለዚህ ጸሐፊዎች፣ ሞጋቾች ወይም ተከራካሪዎች ሳይቀር ብዙ ጊዜያቸውን የሚያባክኑት፣ የሚያምኑበትን ያረጋግጡልናል ብለው የሚያስቧቸውን ብጥስጣሽ ክስተቶች እየቀጣጠሉ፣ በሚያምኑት አስተሳሰብ የተቃኘ ትርጉም ይፈጥሩና በማስረጃ የተደገፈ ዕውቀት ወይም ትንታኔ አስመስለው (ለራሳቸው እንኳ እውነት ነው) ለሕዝብ ያሰራጩታል፡፡ ከሕዝቡ መካከል የእነርሱ እምነት ያለው ደግሞ እምነቱን የሚያረጋግጥ ነገር በማግኘቱ እየተደሰተና እየተደነቀ፣ በቀደመ የተሳሳተ እምነቱ እርግጠኝነት እየያዘ ይሔዳል፡፡ በርግጥ አሜሪካዊው ተመራማሪ ኒኮላስ ቶም እንደሚለው፤ ሁኔታው የሚያድገው ተፈጥሮአዊ ሊባል ከሚችለው፣የምናምነውን የማረጋገጥ ዝንባሌ ነው፡፡ ኒኮላስ እንዲህ ይላል፡-   “We all have an inherent and natural tendency to search for evidence that already meshes with our beliefs” - ‘ ሁላችንም እምነት አድረገን የያዝነውን ነገር የሚያረጋግጥል ማስረጃ የመፈለግ ተፈጥሮአዊ የሆነ ዝንባሌ አለን’ (Tom Nicholas, The Death of Expertise, P.41)
ከዚህ የተነሣ ደግሞ አእምሮአችን ሳይታወቀን የሚሰማውም ሆነ የሚያስታውሰው፣ ከምናምነው እምነት ጋር የሚሔደውን ብቻ እየለየ መሆን ይጀምራል። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው፣ በኮሎምቦስ ኦሐዮ ይኖር የነበረ አንድ ሰው ነው፡፡ ይህ ሰው በአውሮፕላን ተሳፍሮ መሔድ የሚፈራ ሰው ነበር፡፡ ከፍርሃቱ የተነሣም ነፍስ ካወቀበት ጊዜ አንሥቶ በአውሮፕላን ተሳፍሮ አያውቅም፡፡ ቀስ እያለ ደግሞ ውሳኔው ትክክል መሆኑን ለማሳየት በዐለም ላይ ስላጋጠሙ የአውሮፕላን መከስከሶች መረጃ መሰብሰብ ጀመረ፡፡ ከዚያም በዐለም ላይ ስላጋጠሙት የአውሮፕላን አደጋዎች በሙሉ ከእነ ዝርዝር መረጃቸው ዐወቀ፡፡ ከዚያ በኋላ አእምሮው ውስጥ የሚያቃጭለው የአውሮፕላን አደጋ ብቻ ሆነ። በዐለም ላይ በየዕለቱ ስለሚከናወኑ ሰላማዊ በረራዎች ስለ አንዱም አያውቅም፡፡ በዐለም ላይ የአውሮፕላን አደጋ ሲፈጠር ግን በከፍተኛ ደረጃ እያንዳንዷን ሂደት በንቃት ይከታተላል፤ ስለ ሁሉም ነገርም ያውቃል፡፡ አደጋው በተፈጠረበት ዕለት ስለነበሩ ሌሎች ሰላማዊ በረራዎች ግን ቢነገረውም አይሰማም፡፡ አንድ ጊዜ አእምሮው አደጋውን ብቻ መርጦ የሚሰማ ሆኗልና። ከጊዜ በኋላ ይህ ሰው ከኦሃዮ (ምሥራቅ አሜሪካ) ወደ ካሊፎርኒያ (ምዕራብ አሜሪካ) የግድ የሚያስኬድ መንገድ ገጠመው፡፡ ይህ ጉዞ በአውሮፕላን ከ5፡30 ያላነሠ በረራ የሚያስፈልገው ነበር፡፡ አብሮት የሚሔደው ወንድሙ በአውሮፕላን እንዲሔዱ ትኬት ሊቆርጥ ሲል አይደረግም አለ፡፡ ወንድሙ ለርቀቱ ብቻ ሳይሆን ለደኅንነቱም በአውሮፕላን መጓዝ ምን ያህል የተሻለ እንደሆነ ለማስረዳት ጥረት ቢያደርግም፣ ይህ ሰው አእምሮው ስለመዘገበው አደጋ ብቻ እያብራራ አሻፈረኝ አለ፡፡ ስለ ሚሊየኖች ሰላማዊ በረራዎች ቢነገረውም፣ የእርሱ አእምሮ ውስጥ ያለው አደጋው ብቻ ስለሆነ ሀሳቡን ሳይቀበል ቀረ፡፡ በዚህ ምክንያትም ቀናት ከመውሰዱ በላይ በመካከሉ ካለው አስቸጋሪነት የተነሣ እጅግ አስፈሪነት ያለውን የመኪና ጉዞ መርጦ፣ የበለጠ ለአደጋ በተጋለጠ ሁኔታ መጓዝን መምረጡ በታሪክ ይታወቃል፡፡ ስምዐ አድሎ (Confirmation bias) የሚባለውም ይህ ነው፡፡ አእምሮአችን ሲሰማ የሚመዘግባቸው፣ ስንጠየቅ የምናቀርባቸው ማስረጃዎች በሙሉ፣ እንደዚህ ልክ፣ አድሎአችንን የሚያረጋግጡትን ብቻ ይሆናል፡፡
ይህ በሽታ በሀገራችን ብዙ ሰዎችን እየበከለና እያደረሰ የመጣው ደግሞ  የሶሻሊዝም ርእዮተ ዐለም መስፋፋት ጋር ተያይዞ ነው፡፡ አንዳንድ ምሁራን፣ ድርጊቱ ቅኝ ገዢዎች ሀገሪቱን ለመከፋፈል የቀመሙልን መሆኑን ቢጠቁሙም፣ ሀሳባቸው ከምርምር ጽሑፍነት ወጥቶ ለሕዝብ በተገቢው መንገድ ባለመድረሱ ይመስለኛል፣ ከዚህ ክፉ የመከፋፈያ መንፈስ እስካሁን ልንወጣ አልቻልንም፡፡ የሚያሳዝነው ደግሞ አዲሱ የእኛ ትውልድም፣ የዚሁ ክፉ በሽታ ከፍተኛ ሰለባ እየሆነ መምጣቱ ነው፡፡
የእኛ ሀገር የዘውግ ወይም የቋንቋ ፖለቲካም በብዙዎቹ አቀንቃኞቹ ዘንድ እዚህ ደረጃ የደረሰ ይመስለኛል፡፡ በሆነ ዕድሜያችን እንድናምንበት የተደረገ አስተሳሰብ ወይም አመለካከት አለ፡፡ ከዚያ በኋላ እንድንጠላው ስለተደረገው ብሔረሰብም ሆነ ግለሰብ አእምሮአችን የሚመዘግበው፣ መርጦ ክፉውን ብቻ ይሆናል፡፡ ስለምንወድደውና የእኛ ስለምንለው ደግሞ አእምሮአችን የሚቀበለው፣ በጎውንና እኛን ደስ የሚያሰኘን ብቻ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ያህል በአብዛኛው የእኛ ማኅበረሰብ ዘንድ ከዘመነ መሳፍንት በኋላ ስለተነሡት ሦስት ነገሥታት የምንሰማቸውን ውርክቦች ማየት ይቻላል፡፡ ጭፍን አፍቃሬ አማራ የሆኑት በሙሉ፣ ከዐፄ ዮሐንስ ምንም ጠንካራ ጎን አይታያቸውም፡፡ በአንጻሩ ጭፍን አፍቃርያን ትግራዮች ደግሞ ስለ ቴዎድሮስና ምኒልክ በጎ ነገር አይሰማቸውም፡፡ ስለ አማራ እንቆረቆራለን ከሚሉት ለአንዳንዶች፣ የዮሐንስ ቴዎድሮስን ማስገደሉ ብቻ ይታወሳቸዋል፡፡ ስለ ትግራይ ተቆረቆርን የሚሉትም፣ የምኒልክ ዮሐንስን አስገድሏል የሚለው ሐቲት ብቻ ትዝ ይላቸዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች የነጋሢነት ዘር ሀረጋቸው፣ ከአንድ የሚቀዳ ነው ቢባሉ አያምኑም፡፡ እንኳን እንደዚህ በምንናገረው መጠን ተራርቆ ቀርቶ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ፣ ዳዊትን ልጁ አቤሶሎም ገድሎ ሊነግሥ ወግቶታል፤ ኢትዮጵያዊውን ንጉሥ ኢያሱ አድያም ሰገድን ለተልእኮ በወጣበት፣ ልጁ ተክለ ሃይማኖት መንበሩን ይዞ አባቱን አባርሮታል፤ እያልን ሥልጣን አባትና ልጅን፣ ታላቅና ታናሽን ያገዳደሉ ታሪኮች ብንነግራቸው አይቀበሉም፡፡ የእነርሱ አእምሮ ሊመዘግበው የሚችለው፣ ለትግሬዎቹ  በትግሬው ላይ አማራው አደረገው የሚባለው፣ ክፉ ክፉው ብቻ ሲሆን ለአማራውም  በአማራው ላይ ትግሬው አደረገው የሚባለው ክፉ ክፉው ብቻ ይሆናል፡፡
ልክ እንደዚሁ አማራውን ከሌላው ብሔር፣ ኦሮሞውንም ከሌላው ጋር የሚለያዩና ደማቸው እየተንተከተከ የሚናገሩ፣ የሚጽፉና ራሳቸውን ያለ ተንኮል እውነተኛ አድርገው የሚቆጥሩ ሰዎች፤ በዚህ በስምዐ አድሎው፣ የአእምሮ ወይም የአስተሳሰብ በሽታ የተለከፉ ሰዎች ናቸው፡፡ ምክንያቱም አንድ ላይ በሚኖርና በታሪክ ብዙ ውጣ ውረድ ባሳለፈ ሕዝብ መካከል ቀርቶ፣ በአንድ ቤተሰብ መካከል እንኳ አነሰም አደገም ያለ ግጭትና ያለ ስሕተት መኖረ የቻለ የለም፤ ሊኖርም አይችልምና፡፡ ይሁን እንጂ እንደ ክፉዎቹ የታሪክ አጋጣማዎች ሁሉ፣ ብዙ መልካም የታሪክ አጋጣሚዎችም ነበሩ፡፡ ስምዐ አድሎ ያሳመመው ግን በጎውን ለፍቅር፣ ክፉውን ለታሪክ ከመያዝ ይልቅ፣ ክፉውን ብቻ አጋንኖ ለጸብና ለበቀል ያስይዛቸዋል፡፡ ትልቅ ሕክምና የሚሻ፣ ያልተነገረለት ክፉ በሽታ፤ ስምዐ አድሎ፡፡
ድንቁርና የሚያገረሽ በሽታ
ይህ መሠረታዊ ችግር ደግሞ በአብዛኛው የሚከሰተው፣ ተማርኩ በሚለው ማኅበረሰብ ውስጥ ነው፡፡ ለእርሱ እያወቀ እየነቃ፣ እየተገነዘበ ይመስለዋል። ነገር ግን ለሚሠራው ሥራ በሚገባ መጠን ቀርቶ ሌሎች በሚገምቱት መጠን እንኳ ላይገኝ ይችላል፡፡ ችግር እንዲፈጥር የሚያስደርገውም፣ ይህ በዲግሪዎችና በሰርትፍኬቶች የተጠለለ፣ ከዕውቀት መሰል የድንቁርና ተውሳክ የሚከሰተው አደገኛ በሽታ ነው፡፡ ሰዎችን ለእነርሱ ዕውቀት በሚመስላቸው፣ ነገር ግን ለራሳቸውም ሆነ ለማኅበረሰብ፣ እንደተቀመጡበት የኃላፊነት ቦታ ደግሞ ለሀገርም ችግር እንዲሆኑ የሚያደርጋቸው ጽኑ ድንቁርና፣ እንዴት ሊከሰት ይችላል የሚለው ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም ብዙ ሰዎች እጅግ ሊደረጉ ቀርቶ ሊታሰቡ የማይገባቸውን ድርጊቶች የሚፈጽሙት፣ በተንኮል ብቻ ነው ብሎ ማሰብ፣ ራሱ ሌላ ደካማነት ነው፡፡ እነዚያ አካላት ያሉበትን የአስተሳሰብ ሁኔታና መሠረታዊ ምክንያት ከሳትነው፣ ችግሩን እናሰፋዋለን እንጂ ልናስተካክለው አንችልም፡፡ ሰዎቹም የማይጸጸቱት፣ ኅሊናቸው፣ ድርጊታቸው ትክክል እንደሆነ ስለሚነግራቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ለእነርሱ ደግሞ ተንኮለኛውና ችግር ያለበት ሰው፣ እነርሱን የሚቃወማቸው የሚመስላቸው ለዚህ ነውና፡፡ በውጥረት ውስጥ ካለ ማኅበረሰብ፣ ከሁለቱም አቅጣጫ ይህ ከታየ፣ ሁላችንም በጽኑ ድንቁርና ተይዘናል ማለት ነው፡፡ የጽኑ ድንቁርና አንዱ ምልክቱም ይኸው ነውና፡፡
በአዲስ አበባ የኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት በምማርበት ጊዜ ፕሮፌሰር ባዬ ይማም እያስተማሩን እያለ፣ ድንገት አንድ ጥያቄ ተነሣ፡፡ ጥያቄውም (ቃል በቃል መሆኑን ርግጠኛ አይደለሁም) እንዲያው ለመሆኑ ዘመናዊ ትምህርት ኢትዮጵያ ውስጥ በመምጣቱ ኢትዮጵያ ያተረፈችው ምንድን ነው? የሚል ነበር፡፡ ፕሮፌሰር ባዬም  የሚናገሩትን እያሰቡ መሆኑን በሚያመለክት ሁኔታ፤ ክፍል ውስጥ ትንሽ ዘወር ዘወር ካሉ በኋላ፣ ምን አልባት ተማረ የተባለውን ሰው የተሻለ ደመወዝ አስገኝቶ ካልሆነ በቀር ለእኔም የተለየ ጥቅሙ አልታየኝም አሉን፡፡ ከዚያ ደግሞ ለምን እንዲህ ሊሆን ቻለ የሚል ጥያቄ አስከተልን፡፡ ፕሮፌሰሩ ቀጠሉ፡፡ እንደ ድንቁርና የሚያገረሽ በሽታ የለም፡፡ አንድ ሰው ወደ ትምህርት ቤት ገብቶ የሚማረው፣ ከድንቁርና ለመላቀቅ ነበር፡፡ በርግጥም ድንቁርና ከትምህርት በሚገኝ ዕውቀት ሊጠፋ ይችላል፡፡ ነገር ግን የሚማረው ሰው፤ የተማረው ትምህርት ብቻውን ድንቁርናን ሊያጠፋለት አይችልም፡፡ ድንቁርና የሚጠፋው አንድ ሰው በተማረበት ሙያና ለተቀመጠለት ኃላፊነት ብቃት እንዲኖረው የሚያደርግ ብቻ ሳይሆን ሁለንተናዊ ግንዛቤውን የሚያሳድግ ሰፋ ያለ ንባብ ያስፈልገዋል። ማንበቡ በራሱ ደግሞ ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ ያነበበውን ይዞና ባለው ዕውቀት ላይ ተመሥርቶ፣ ልክ ለንባቡ ጊዜ እንደሰጠው ጊዜ ወስዶ ማሰላሰልና ማሰብ አለበት፡፡ ነቂስ ንባብና ጥልቅ ሀሳብ ከተገናኙ ዕውቀት ይወለዳል፤ ይዳብራል፡፡ ከዚያ ዕውቀት የሥራ ዕቅድ፣ አዲስ ትልም ፈጠራና የመሳሰሉት ሲገኙ፣ ትምህርት ሀገርን ይለውጣል፤ ያሳድጋል፡፡ አንዴ ትምህርት ስለተማረና እስከ ሦስተኛ ዲግሪም ስለያዘ ብቻ ግን መሥራትና መለወጥ አይችልም፡፡ እንዲያውም አንድ ሰው የማስተርስና የፒኤችዲ ዲግሪ ይዞ የማያነብ ከሆነ፣ ሲማር ትንሽ ታግሦለት የነበረው ድንቁርና፣ እንደገና መመለስ ይጀምራል፤ እየሰነበተ በሔደ ቁጥር ደግሞ ያን የተማረውን እንኳ  ፈጽሞ ይረሳውና ድንቁርናው ያገረሽበታል፡፡ ከዚያም ባለ ዲግሪ ደንቆሮ ይሆናል፡፡ በዚሁ ሂደት የሌሎች ሰዎች ሀሳብ የማይገባው፣ ያለ ራሱ የማያዳምጥ ይሆንና በመጨረሻ የድንቁርና ብቃት ላይ ይደርሳል  አሉን ፤ፕሮፌሰሩ፡፡ ቃል በቃልም ባይሆን ምንም ሀሳብ እንዳልጨመርኩም እንዳልቀነስኩም ግን ይሰማኛል፡፡ ያን ዕለት፣ አሁንም ሳስበው፣ ዛሬ የነገሩኝ ያህል፣ ከእነ እንቅስቃሴያቸው በኅሊናዬ ተቀርጾ ይኖራል፡፡  
በርግጥም በአሁኑ ዘመን ከተማርነው ትምህርት ብቻ የተነሣ የተሻለ የምናውቅና የምናስብ የሚመስለን ሰዎች፣ ቁጥራችን ቀላል አይደለም፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ አንዳንድ ሰዎች፣ ለራሳቸው ዕውቀት በመሰላቸው ጉዳይ ላይ ከፍተኛ እርግጠኝነት የሚሰማቸው መሆኑ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የድንቁርና ጥግ ወይም ፕሮፌሰር ባዬ እንዳሉት፤ የድንቁርና ብቃት ከመሆን የሚያልፍ አይደለም፡፡ ዴቪድ ደኒን እና ጀስቲን ክሩገር የተባሉ የሥነ ልቡና ሳይንቲስቶች እንደሚሉት፤ ለራሳቸው እንደዚህ ያለ ግንዛቤ ያላቸው ሰዎች፣ ከዚህ ለመውጣት ያላቸው ዕድልም ዝቅተኛ ሳይሆን አይቀርም፡፡  ሳይንቲስቶቹ ሁኔታውን ሲያስረዱ፤ “the least competent people were the least likely to know they were wrong or to know that others were right, the most likely to try to fake it, and the least able to learn anything” - ‘የመጨረሻው ዝቅተኛ የአስተሳሰብ ደረጃ ላይ ያሉ ሰዎች፣ እነርሱ የተሳሳቱ መሆናቸውን ወይም ሌሎች ትክክል የነበሩ መሆናቸውንም፣ የመረዳት ዕድላቸውም፣ በጣም ዝቅተኛ እና ነገሩን ሐሰት አድርገው የማቅረብ አቅማቸው ደግሞ ከፍተኛ ነው፡፡ ምንም ነገር የመማር አቅምም የሌላቸው ናቸው’ ይላሉ፡፡ ይህ በቤተ ሙከራ ጥናት የታገዘ ግኝታቸው በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነትም ስላገኘ፣ ይህ ጠባይ ያላቸው ሰዎች ሁሉ፣ የክሩገር ተጽእኖ ያለባቸው እየተባሉ የሚጠሩ ሆነዋል፡፡ በጣም የሚገርመው ደግሞ እጅግ በጣም ዘገምተኛ የሆነ ሰው፣ እርሱ የአስተሳሰብ ዝግመት እንደሌለበት በጣም በእርግጠኛነት የሚናገር መሆኑ ነው፡፡
እንግዲህ ይህ ነገር በሌሎቹ የሚኖር ከሆነ፣ በእኛ ሀገርም የለም ልንለው አንችልም፡፡ አሳዛኙ ገጽታው ደግሞ እንደተገለጸው የሆነው፣ ራሳችን ደኅና አድርገን መውሰዳችን ብቻ ሳይሆን በእኛ ሀገር ሁልጊዜም ሰለባ ሆነው የሚታዩን ሌሎች ሰዎች ብቻ መሆናቸው ነው። በርግጥ ብንፈልግ ይህን የመሰለ ችግር ሰለባዎች መሆናችንን የሚያረጋግጡ፣ በሚዲያ ላይ ከሚቀርቡ ሰዎች እንኳ ልናጣ አንችልም፡፡ እንዲያውም እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ሁሉንም የተማረ ኢትዮጵያዊ ሊያካትት አለመቻሉ የታወቀ ቢሆንም፣ ሀገሪቱን በችግር እሽክርክሪት የከታት ትውልድ ግን በዚህ ውስጥ ሊካተት የሚችለው ትውልድ ለመሆኑ ነጋሪ አያሻም፡፡ በአሁኑ ወቅት አሳሳቢ ያደረገው ደግሞ ይህ ችግር ብሔራዊ ቅርጽ ሊይዝ እየተንደረደረ ያለ መምሰሉ ነው፡፡ ቢያንስ ለእኔ የሚያስፈሩ እንዲህ ዐይነት ነገሮች ይታዩኛል፡፡ ስለዚህ የሚሻለን ቆም ብለን የምንወቅሳቸው አካላት የሚያደርጉትን ብቻ ሳይሆን ወቃሾቹ የምናደርገውንም በቀናነት መመርመር ነው፡፡  የሀገር ፍቅርና ለወገን በጎ ማሰብ ብቻቸውን ድንቁርናንና እንደዚህ ያለ ሀገር የሚያጠፋ ዘገምተኝነትን አያሸንፉትምና፡፡ በተለያየ መጠን ቢሆንም በሽታው በሁላችንም በኩል የሚታይ ስለሆነ፣ አንዱ የሰሐራ በታች ወረርሽኝ አድርገን እንድዘምትበት የሚሻ ይመስለኛል፡፡ ወደ ዘላቂ ሰላምና ብልጽግና እንሸጋገር ዘንድ ከምር የምንፈልግ ከሆነ፣ ነገሩን በጥሞና መመርምርና ሀሳብንና አስተያየቶችንም ስናጋራ፣ ይህን ታሳቢ ያደረገ መሆን የሚያስፈልገው ይመስለኛል፡፡ አበጀን ብለን እንዳናበላሽ፣ ገነባንም ብለን እንዳናፈርስ፣ ፍቅርንም ለመጨመር ስንተጋ ጥላቻን እንዳናሳድግ፣ ድርጊታችንን መመርመር በርግጥም በዕውቀት ላይ ተመሥርቶ ማድረግ፣ ከሁላችንም የሚጠበቅ የውዴታ ግዴታ መሆን ይገባዋልና፡፡
ምክንያቱም ዲሞክራሴያዊ አስተሳሰብ ይልቁንም የመናገር ነጻነት የሚሰጥበት መሠረታዊ ምክንያቱም እንዲህ ያለውን ችግር እንኳን እንደ ኢትዮጵያ ካለ ኋላ ቀር ሀገር ቀርቶ፣ ከሌላውም ማጥፋት ስለማይቻል ነው። ሊደረግ የሚችለው እንደዚህ ያለ ነገር በምናይበት ጊዜ ያ ሰው በዚህ በሽታ የተለከፈ መሆኑን ተረድቶ፣ መተው ብቻ ነው፡፡ ያንን እንደ ጤነኛ ሰው አይቶ፣ ንግግሩን ወይም ጽሑፉን እየተቀባበሉ፣ እየተረጎሙና እያስፋፉ መሔድ፣ በሽታውን ወደ ራስ ማጋባትና ጥላቻንና ጸብን ተምረዋል ብሎ ወደሚቀበለን ወደ የዋሁ ሕዝብ በማሰራጨት፣ ሀገር ከማጥፋት፣ ሕዝብን በሕዝብ ላይ ከማስነሣት የሚያልፍ ምንም ፋይዳ የለውም፡፡ ያውቁልኛል ብሎ አምኖ የተቀበላቸውን ሰዎች ሰምቶ፣ አሁን በሀገራችን አልፎ አልፎ እንደሚታየው፣ አንዱ በአንዱ ላይ ቢነሣም፣ ሕዝብ የበሽታው አመንጭና ተጠያቂ ሳይሆን በውል በማያውቀው ነገር ሌሎቹን ጠልቶ እንዲዘምት የተደረገ፣ የመጀመሪያው የኅሊና ጉዳት የደረሰበት ተበዳይ ነው፡፡ ስለዚህ ሕዝብን አጠቃልሎ መውቀስም እዚያው የዘገምተኝነት አዙሪት ውስጥ ከመግባት የተለየ ጥቅምና ፋይዳ የለውም፡፡ ዕውቀት መሰል ጽኑ ድንቁርና ማለትም ይኸን መሰሉ፣ የተማሩ ሰዎች የሚንገላቱበት፣ ጽኑ በሽታ መሆኑን አውቀን፣ ራሳችንን ካስተኛንበት የዐውቂያለሁ በሽታ ለመዳን ብንታገል፣ በርግጥም ጉዞአችን ወደ እውነተኛ ይቅርታና ዕርቅ፣ ከዚያም ወደ ነጻነት፣ ሰላምና ብልጽግና ሊሆን ይችላል፡፡ ካለበለዚያ ሂደታችን ወቅታዊና ደርግ “ኢትዮጵያ ትቅደም ያለምንም ደም” የሚል መፈክር እያስነገረ ከቆየ በኋላ ሀገሪቱን ደም በደም እንዳደረጋትና በኢኮኖሚውም ከመጨረሻዎቹ ተርታ እንዳሰለፋት፣ የእኛም መፈክር ጊዚያዊና የቀደመውን በማውገዝ ላይ ብቻ የተገኘ፣ የቀበሮ ደስታ እንዳይሆን ያሰጋል፡፡
ዘመነ ብዝኀ  ነገር (ነገር የበዛበት ዘመን)
በልማድ ይሁን በዕውቀት እንደተደረገ ባላውቅም፣ ይህ ዘመን ከሚጠራባቸው ስያሜዎች አንዱ የመረጃ ዘመን የሚለው ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የመረጃ ዘመን ከምንለው ይልቅ የማሳሳቻ ዘመን (Age of misinformation) ብንለው የሚሻል ይመስለኛል፡፡ በርግጥም ደግሞ እንደዚያ ነው፡፡ የሳንዲያጎ ኮምፒዩተር ሴንተር ተመራማሪዎች፣ በፈረንጆች በ2015 ባካሔዱት ጥናት፤ አንድ የእኛ ዘመን ሰው በቀን እስከ ዘጠኝ ዲቪዲ መረጃ ይወስዳል፡፡ እንደ ተቋሙ ጥናት፤ከዚህ ውስጥ አብዛኛው መረጃ የተዛባ፣ የተሳሳተ፣ የስሕተት፣ ወጥነት የሚጎድለው፣ የተቆራረጠና እውነትነት በእጅጉ የሚጎድለው ነው፡፡ በተለይ በበይነ መረብ (Internet) የሚሰራጩትን ብዙዎችን መረጃዎች ቀርቶ ለትምህርትና ለዕውቀትም ሳያጠራ የሚያግበሰብስ ሰው፤አገኘሁት በሚለው ዕውቀት ከሚኖር ምንም ዐይነት ትምህርት ሳይማር ቢኖር ይሻለው ነበር እስከ ማለት ደርሰዋል፡፡ ቶም ኒኮላስም የሚከተለውን ብሏል፡-”Accessing the Internet can actually make people dumber than if they had never engaged a subject at all. The very act of searching for information makes people think they have learned when in fact they are more likely to be immersed in more data they do not understand” - ‘በመሠረቱ ኢንተርኔትን መጠቀም ሰዎቹ ራሳቸው ምንም ዐይነት ትምህርት ሳይማሩ ቢኖሩ ከሚገጥማቸው ይልቅ ዘገምተኞች ያደርጋቸዋል። በኢንተርኔት መረጃ መሰብሰብ ሰዎችን ትምህርት የወሰዱ እንዲመስላቸው ቢያደርግም እውነታው ግን በአግባቡ ሊረዱት በማይችሉት የጥናት መረጃ ውስጥ እንዲዘፈቁ ከማድረግ ያለፈ አይፈይድላቸውም’ /ዝኒ ከማሁ፣ ገጽ 119)፡፡ የያሌ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልቡና መምህራንም፤ “people thinking they are smart because they searched the Internet is like thinking they are good swimmers because they got wet walking through a rain storm” -  ‘ኢንተርኔትን መጠቀም መሠልጠን የሚመስላቸው ሰዎች፣ ልክ በዶፍ ዝናብ ወስጥ እየሄዱ በመበስበሳቸው ጥሩ ዋነተኛ እንደሆኑ እንደሚቆጥሩ ያሉ ሰዎች ናቸው’ ብለዋል፡፡ በርግጥም የእኛ ዘመን እንደዚህ ይመስላል። ኢንተርኔትን በአግባቡና በተገቢው መንገድ የሚጠቀሙት፣ በዚያ ከምንጎዳው አንጻር በጣም ጥቂቶች ናቸውና፡፡
ይልቁንም በማኅበራዊ ሚዲያ ሲሆን ደግሞ ጉዳቱ ይጨምራል፡፡ የዚህ መሠረታዊ ምክንያቶች ብዙዎች ሊሆኑ ቢችሉም፣ ለዛሬው ሦስት ያህሉን ላንሣ፡፡ የመጀመሪያ የማኅበራዊ ሚዲያ ተፈጥሮው፣ በአኗኗር ዘዴ እየጠፋ የነበረውን ማኅበራዊነት፣ ግንኙነት ማሳለጥ ማገናኘትና አንዱ ከሌላው እንዲካፈልና እንዲያካፍል ስለሆነ፣ ላይክና ሼር ማድረጊያ አላባዎች እንዲኖራቸው ተደርጓል፡፡ ብዙዎቻችን ላይክና ሼር የምናደርገው ደግሞ ለምንወድደውና ለምንስማማበት ጽሑፍ ወይም ምሰል ወድምፅ ብቻ ይሆናል፤ ከላይ በስምዐ አድሎ ላይ እንደተገለጸው፣ ለላይክና ለሼር እንመርጣለን ማለት የምንመርጣቸው በእውነተኝነታቸውና በጠቀሜታቸው ሳይሆን ከእኛ ሀሳብ ጋር በመስማማታቸው፣ በመግጠማቸው፣ የምንጠላውን የሚጠሉ፣ የምንወድደውን የሚወድዱና በአጠቃላይ የራሳችንን ሀሳብ በመግለጣቸው ነው እንጂ በእውነትና በጠቀሜታቸው መሆኑ ይቀራል። ይህ ደግሞ እየተደጋገመ በሆነ ቁጥር ምንም ያህል ጠቃሚ ቢሆን ከእኛ ሀሳብ የተለየውን እንድንጠላውና እንድንሰድበው እንጂ ታግሠን፣ አንብበን፣ እየለበለበንም ቢሆን እውነቱንና የሚጠቅመንን የመውሰድ አቅማችንን ከውስጣችን አሟጥጦ ያጠፈዋል፡፡ እንዲያውም አንዳንድ ምሁራን እንደሚሉት፤ አብዛኛው የእነዚህ ሚዲያዎች ተጠቃሚ ሰው ነቅቶና ተጠንቅቆ ካላደረገው በቀር በተለይ ራሱን የሚተች ሀሳብንና አመለካከትን ትንሽም ቢሆን እንኳ መታገስ እንዲያቅተው ያደርገዋል፡፡ ትዕግሥት ማጣቱን ደግሞ በብሎክና በመሳሰለው ድርጊት የምናየው ነው። ዋሽንግተን ፖስት፤ በሪፐብሊካንና በዲሞክራቶች ላይ ባካሔደው ጥናት፤ ብዙ ጊዜ ጓደኞቻቸውን በማኅበራዊ ሚዲያ ብሎክ የሚያደርጉት ዴሞክራቶች ናቸው ብሏል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሪፐብሊካኖች ሲጎዳኙ መወሰናቸው ሲሆን በአንጻሩ ዴሞክራቶች ደግሞ ነጻና ሁሉን ማስተናገድ የሚችሉ መስሏቸው ቢጀምሩትም በኋላ ግን ራሱ የሚዲያው ጠባይ፣ትዕግሥትን ስለሚያጠፋ፣ ብሎክ ወደ ማድረግ ይሸጋገራሉ ይላል፡፡
 ይህ እያደገ ሔዶ፣ የማታ ማታ፣ ሌሎችን የመስማት ፍላጎታችን ጨርሶ ሊጠፋ ይችላል፡፡ በመጨረሻም ሌሎችን ፈጽሞ ወዳለመስማት ይወስደንና ማኅበራዊ ዝምድናን ለመጨመር የተፈጠረው ሚዲያን፣ ከተፈጠረበት ዓላማ በተቃራኒ በመጠቀም፣ ማኅበራዊ ችግሮችን አሸክሞን ይሔዳል ማለት ነው፡፡ አሁንም ከቶም ኒኮላስ ልዋስ፡- “The unwillingness to hear out others not only makes us all more unpleasant with each other in general, but also makes us less able to think, to argue persuasively, and to accept correction when we are wrong. When we are incapable of sustaining a chain of reasoning past a few mouse clicks, we cannot tolerate even the smallest challenge to our beliefs or ideas. This is dangerous because it both undermines the role of knowledge and expertise in a modern society.”- ‘ሌሎችን የመስማት ፈቃደኝነታችን መጥፋቱ አንዲያው በደምሳሳው ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ደስተኞች ባለማድረግ ብቻ የሚቆም ሳይሆን ይልቁንም የማሰብ ችሎታችንን፣ አሳማኝ ሆኖ የመወያየት አቅማችንንና በተሳሳትን ጊዜ ማስተካከያ የመቀበል ችሎታችን ሁሉ ዝቅተኛ ያደርገዋል፡፡ በምናነበው ጽሑፍ ተከታታይ መከራካሪያዎችን አንድ በአንድ በትዕግሥት ለማንበብ ከተሳነን፣ የእኛን እምነት ወይም ሀሳብ በትንሹም የሚሞግትን ነገር መታገስ ያቅተናል፡፡ ይህ ደግሞ የዘመናዊውን ትውልድ፣ የዕውቀትና የሙያ አስተዋጽኦ የሚያሳንስ በመሆኑ አደገኛ ነገር ነው’፡፡   
ማኅበራዊ ሚዲያው ከዚህም ባሻገር ሁለት አባባሽ ነገሮች አሉት፡፡ የቦታ ርቀትና ስም ለውጦ መጠቀም። የቦታ ርቀት በተፈጥሮው ልክ እንደ ሐሜት በአካል ብንገናኝ ልንለው የማንችለውን በማኅበራዊ ሚዲያ ግን ድፍረት አግኝተን ያልተጣራም ቢሆን እስካመንነበት ድረስ የፈለግነውን የማለት ዕድል ይሰጣል፡፡ ስምንም ደብቆ ማንነትን በቀላሉ ሊያሳውቅ በማይችል ስም የመቅረብ ዕድል መፍጠሩ ደግሞ ከሽፍታ እንኳ ያነሰ ሰብእናን እንድንጎናጸፍ ያለማምደናል፡፡ ይልቁንም በክርክርና በውይይት ቀርቶ በጦርነትም ፊት ለፊት ወይም ግንባር ለግንባር በመግጠም ይታወቅ ከነበረው ቀድሞ ሥልጣኔ ከነበረው የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ተገኝቶ፣ የሳይበር ጫካውን ተጠቅሞ ለፍትህ ሳይሆን ፍርሃትና ጭካኔ በፈጠሩት ውዳቂ ሰብእና ምክንያት የተደበቀ ሰው ምን ያህል ኃላፊነት ሊጎድለው እንደሚችል መገመት የሚያስቸግር አይመስለኝም፡፡ ከፋም በጀም በግልጽ ማንነታቸውን አሳውቀው የሚያደርጉ ሰዎች ቢሳሳቱም እንኳ ለሀሳባቸው ሓላፊነትን ስለወሰዱ ምስጋና ይገባቸዋል፡፡ እንግዲህ በእኛ ማኅበረሰብ ውስጥ ጥላቻንና በቀልን ለማስተላለፍ ከሚያግዙት ውስጥ አንዱ ይኸው በየሚዲያው ከመጠን በላይ የሚለቀቀው ዳታ ስለሆነ፣ በአግባቡ የመጠቀም ሓላፊነት የሁላችን ግዴታ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባውም፡፡
ከባነር ወደ ተግባር
በአሁኑ ወቅት በአባዛኛው ሰው የሚቀነቀነው ከጠቅላይ ሚኒስትራችን የሚሰማው የይቅርታ፣ የዕርቅና የመደመር ነገር ነው፡፡ ፎቶ ግራፎች፣ ካኔቴራዎች፣ ባነሮች ሀሉ የሚያውጁት እነዚህን ነው። ሆኖም እነዚህን ከመጠቀም ጋር አንዳንድ ሰዎች የሚያስፋፏቸው ጉዳዮች ከመፈክሮቹ የሚቃርኑ እንደሆኑ ይታያል፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ምንአልባትም ጠቅላይ ሚንስትሩ፣ እኛ የምንጠላቸውን ሁሉ የሚጠሉ ስለመሰለንና  ችግር በመፍጠር ላይ ናቸው ብለን የምናስባቸውንም፣ የምናሸንፍ ስለመሰለን ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም የመደመር ካኔቴራ ለብሶ በሌሎች ላይ ጥርስን ማፋጨት፣ የይቅርታን መፈክር አንግቦ፣ ለበቀል መዛትና ስለ ዕርቅ እየዘመሩ  ጸብንና ግጭትን ሊያባብሱ የሚችሉ ነገሮችን መወርወር ከላይ ከጠቀስኳቸው ችግሮች ቢያንስ በአንዱ መያዛችንን ከማመልከት ያለፈ ነገር አይኖራቸውም፡፡
ስለዚህ በርግጥ ይቅርታና ዕርቁን እንዲሁም መደመሩን ከልብ የምንፈልገው ከሆነ፣ በመፈለጋችን ብቻ ሊሳካ እንደማይችል ከመገንዘብ መጀመር ይኖርብናል፡፡ እንዲያውም ከእያንዳንዳችንም የሚፈልገው መሥዋዕትነት አለ፡፡ ይቅርታ ለአጥፊ ሰው የሚደረግ እንደ መሆኑ መጠን የምንወቅሳቸው ሰዎች ለይቅርታ የተዘጋጁ እንኳ ባይሆኑ ከምንፈልገው ሰዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በተግባር ሊታይ የሚገባው ነገር ነው፡፡ ምን አልባትም በየቤተሰባችን የገጠሙን አሰቃቂ ፈተናዎች ሊኖሩ ይችላሉ፤ ደግሞም ሞልተዋል፡፡ ይቅርታ ያስፈለገውም በእነዚህ ቁርሾዎች ወደፊት ሊመጣ የሚችለውን አደጋ ለመከላከል ነውና እያዘንንና እያመመንም ቢሆን የግድ መተው አለብን። ይህን ማድረግ ከሞቱትና ከተሰቃዩት የሚጠጋ ትልቅ መሥዋዕትነት ነው፡፡ በርግጥም ሀገርና ሕዝብ ሊድን የሚችለው እንዲህ ባለ እውነተኛና ተግባራዊ ይቅርታ ነው፡፡ ካለበለዚያ መሰለፋችን፤ መዘመራችን፣ ሌላም ሌላም ማለታችን፣ ብዙም ጥቅም ሊኖረው አይችልም፡፡ ስለዚህ በእውነት መንገዱ የመደመር እንዲሆን ከፈለግን፣ ሰዎችን ሳንለያይ ይቅር ማለት አለብን፡፡ ሁሉም የፖለቲካ እሥረኞች እንዲሁም ሞት የተፈረደባቸውም ጭምር በመፈታታቸው ደስ ካለንና በዚህ የምናምን ከሆነ፣ እኛም ሁሉንም ይቅር በማለት ከልብ ማመን አለብን፡፡ ሌሎቹን በማታለልና በማስመሰል ስናወግዝ ከርመን፣ እኛ ጋ ሲደርስ እንዴት ትክክል ሊሆን ይችላል? ሌሎቹ በወገኖቻችን ላይ ስም እየሰጡና እየፈረጁ፣ እሥራትና ግርፋት መፈጸማቸውን ከተቃወምነው፣ እኛም ሌሎችን በችኮላ፣ በቂና የተረጋገጠ መረጃ ሳይኖር፣ መፈረጃችንን ማቆም አለብን፡፡ ከፍለን ይቅር የምንል፣ በአንዳንዶች ላይ የተለየ ጥላቻ የምናራምድ ከሆነ፣ የአድሎና የግፍ ዱላውን ከእነርሱ ተቀብለን፣ ሩጫቸውን እየተወዳደርንላቸው ከመሆኑ በቀር የተፈጠረ የአስተሳሰብ ለውጥ የለም ማለት ነው፡፡ መንግሥትንና ሹማምንቱን “ተለወጡ፣ አስተካክሉ፣ ይህ ይቀራችኋል” ስንል ከነበርን፣ እኛም መለወጥ መስተካከል፣ መፈክራችንንም ከተሸከምነው ባነር፣ ወደ ልቡናችንና ወደ ተግባር ማሸጋገር ግዴታችን ይሆናል፡፡
በሌላ ቋንቋ ደግሞ የምንጠላቸውና የምናወግዛቸው አካላት ችግር፣ የእኛም ችግር ሆኗል ማለት ነው፡፡ ከላይ ያሉትን ሦስት መሠረታዊ ችግሮች ያነሣሁትም፣ አይታወቀንም እንጂ ሁላችንም ተመሳሳይ ሰብእና እየያዝን ነው፡፡ አይታወቀንም እንጂ ሁላችንም በሁሉም ችግሮች ተይዘናል፡፡ አይታወቀንም እንጂ ይጠሉናል በምንለው መጠን ሌሎቹን እንጠላለን፡፡ አይታወቀንም እንጂ የእኛም ድርጊት ሀገር ለሚገነቡት ሳይሆን ለሚያፈርሱት አስተዋጽኦ የሚያደርግ ነው፡፡ አይታወቀንም እንጂ እኛም ውስጥ አልህና ደንዳናነት አለ፡፡ ስለዚህ ወደ ራስ ማየትም ያስፈልጋል፡፡ በሌሎች የምናወግዛቸውን ድርጊቶች ሁሉ ቀድመን ከራሳችን ማስወገድ ይጠይቃል፡፡ መንሥኤዎቹን መረዳት ደግሞ ራሳችንን ከችግሮቹ እንድናጸዳ ብቻ ሳይሆን ሌሎቹም በዚህ የሕይወት አዙሪት ውስጥ የወደቁት ሳያውቁ መሆኑንና አሁንም ሙጭጭ ያሉት የሚጠቅም መስሏቸው መሆኑን መገመት ያስፈልጋል፡፡ ከዚያም ሲሆን ካሉበት አስተሳሰብ እንዲወጡና ባለውለታቸው እንድንሆን፣ ያ መሆን ካልቻለ እንኳ፣ በሚገጥማቸው ችግር እኛም ተጠያቂዎች እንዳንሆን፣ ተገቢውን ኃላፊነት መውሰድ ለነገ የማይባል ነው፡፡ እንግዲያውስ የይቅርታንና የዕርቅን እንዲሁም የመደመርን ባነር አንግበን፣ በጥላቻው አውራ ጎዳና ላይ ከመጓዝ እንመለስ፡፡ ቃላቱም  ከባነሩ ወርደው፣ ወደ ልቡናችን ሰሌዳ፣ ከመፈክርነትም ወደ ተግባራዊ ሕይወትነት ይለወጡ፡፡

Read 3596 times