Sunday, 06 May 2012 15:27

አንባቢ ትውልድ ለመፍጠር ምን ተደረገ?

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(0 votes)

“አጤ ምኒልክ” በሚል ርዕስ በጳውሎስ ኞኞ በተዘጋጀው መጽሐፍ ውስጥ እንደተጠቆመው፤ በ1889 ዓ.ም የጽሕፈት ማተሚያ ማሽን ወደ ኢትዮጵያ በማስገባት የፈረንሳይ ዜግነት የነበረው ነጋዴ ቀዳሚ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ማሽኑ አገልግሎት መስጠት አልቻለም ነበር፡፡በ1898 ዓ.ም ግን ኢዲልቢ የሚባል ሶርያዊ ነጋዴ፤ የጽሕፈት ማሽን ወደ አዲስ አበባ አስመጥቶ የሕትመት ሥራ ጀማሪ ለመሆን ችሏል፡፡ የሕትመት ዘርፍ እንዲጀመርና ለዕድገቱም የውጭ አገር ዜጎች ብቻ ሳይሆኑ በተለያዩ ዘመናት የነበሩ መንግስታት፣ የሃይማኖት ተቋማትና ድርጅቶች ቀላል የማይባል አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ሶርያዊው ኢዲልቢ ፈረንሳዊው ነጋዴ ሞክሮ ወደ አልተሳካለት የሕትመት ዘርፍ ሲገባ ዓላማውን ከግብ ያደረሰው አፄ ምኒልክ ባደረጉለት ትብብር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከግዕዝ በተሻለ በአማርኛ ቋንቋ የታተሙ መፃሕፍት ቁጥር እንዲበረክቱ ሚሲዮናውያን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸው ይነገርላቸዋል፡፡ አብዛኛው የአገሪቱ ሕዝብ ለንግግር በሚጠቀምበት አማርኛ ቋንቋ የሃይማኖት መፃሕፍትን በብዛት ማተም ዓላማቸውን እንደሚያሳካላቸው የተረዱ ሚሲዮናዊያን፤ ለአገራችን የሕትመት ኢንዱስትሪ ዕድገት ቀላል የማይባል አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ በአገራችን የመጀመሪያው ጋዜጣ እንደሆነ የሚነገርለት “አዕምሮ” ጋዜጣ ይታተምበት የነበረው መርሀ ጥበብ እና በ1914 ዓ.ም ሥራ የጀመረው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤቶችን በማቋቋም አፄ ምኒልክና አፄ ኃይለሥላሴ በአገር ውስጥ ፈር ቀዳጆች ሲሆኑ ከውጭ ሶሪያዊው ኢዲልቢ ይጠቀሳል፡፡ የጽሕፈት መኪናን በመጠቀም መፃሕፍት በማተሙ ሥራ ብቻ ሳይሆን በአዲስ አበባ ከተማ ቀዳሚውን የመጽሐፍ መሸጫ መደብር በመክፈትም ፈር ቀዳጆቹ የውጭ አገር ዜጎች ናቸው፡፡ ፒያሳ የሚገኘውና ለ60 ዓመታት ያህል አገልግሎት እንደሰጠ የሚነገርለት “አፍሪካዊያን የመፃሕፍት መደብር” የመጀመሪያው ባለቤቶች የውጭ አገር ዜጎች ነበሩ ይባላል፡፡ በአገራችን በየዘርፉ እንደሚታየው የምሥረታ ዕድሜያቸው ረዘም ያለ ሆኖ ያስመዘገቡት ዕድገት አዝጋሚ ነው ከሚባሉት ጋር የሚመደበው የሕትመት ሥራና ተያያዥ እንቅስቃሴዎቹም አዝጋሚ ሆነዋል፡፡ “Discovering Ethiopia” በሚል ርዕስ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ኮሚሽን በ1980 ዓ.ም ያሳተመው መጽሐፍ፤ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙና በተለይ ቱሪስቶች ሊጎበኙዋቸው የሚችሉ የመፃሕፍት መደብሮች ሦስት ብቻ እንደነበሩ ያመለክታል፡፡ አንደኛው አሁን “ሜጋ” በሚል የሚጠራውና ቀድሞ “ኩራዝ” ይባል የነበረው የመፃሕፍት መደብር ነው፡፡ ሁለተኛው ቅርንጫፎቹ በሙሉ ተዘግተው አገልግሎት መስጠት ያቆመው “ኢትዮጵያ መፃሕፍት

መደብር” ሲሆን ሦስተኛው በግሪካዊያን እንደተቋቋመ የሚነገርለት “አፍሪካዊያን የመፃህፍት መደብር”ን ነው “Discovering Ethiopia” ለቱሪስቶች ለያስተዋውቅ የሞከረው፡፡የሕትመቱ ዘርፍና ተያያዥ አገልግሎቶቹ በፍጥነት አለማደጉ መፃሕፍት፣ ደራሲና ተደራሲያን እንዳይገናኙ እንቅፋት መሆኑን በቅድሚያ የተረዱ የሚመስሉት አፄ ኃይለሥላሴ፤ ደራሲያንን ለማበረታትና የድርሰት ሥራዎች ለአንባቢያን እንዲደርሱ የመፃሕፍትን ሙሉ የማሳተሚያ ወጪ እየሸፈኑ መፃሕፍትን ለተለያዩ ትምህርት ቤቶች እንዲደርሱ ማድረጋቸው ይነገርላቸዋል፡፡ የግል ማተሚያ ቤቶችን ወርሶ የመንግሥት ያደረገው ደርግ፤ በዘርፉ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ያስችላል ብሎ ካቋቋመው ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ጋር የመፃሕፍት መሸጫ መደብሮችን ማደራጀቱ በበጐነቱ ተጠቃሽ ነው፡፡ ደርግ ኩራዝ አሳታሚ ድርጅትን በማቋቋም ብቻ ሳይሆን ርዕዮተ ዓለሙን ለማስፋፋት በየመስሪያ ቤቱ የውይይትና የንባብ ክበብ እንዲቋቋም ማድረጉም ወደ ኋላ ላይ አሰልቺ እየሆነ ቢመጣም ጥሎ ያለፈው መልካም ነገርም ነበር፡፡ አሁን ከፓርላማ ጀምሮ፣ በየሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ በተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት፣ በከተሞች፣ በክፍለ ከተሞች፣ በወረዳና በቀበሌ ደረጃ በርካታ ቤተ መፃሕፍት ማቋቋም የተቻለው አንድም ከደርግ ዘመን የንባብ ክበባት ተሞክሮ ተወስዶ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ብዙም ባያተርፍ ለኪሳራ አይዳርግም የሚባለው የሕትመት ሥራ፤ በአገራችን ከ1983 ዓ.ም በኋላ እየተስፋፋ መጥቷል፡፡ እየታተሙ በመሰራጨት ላይ ያሉ መፃሕፍት ቁጥር ጨምሯል፡፡ ኢምፐርቴክ ኢትዮጵያ ቢዝነስ ሶሳይቲ “የብልፅግና ቁልፍ ቁጥር 5” በሚል ርዕስ በ2004 ዓ.ም ባሳተመው መጽሐፍ ውስጥ አንድ ሰው በዚህ ርዕሰ ጉዳይ በሰጡት ምስክርነት “በሚያዝያ ወር 2003 ዓ.ም ብቻ በአገራችን ኢትዮጵያ 89 መፃሕፍት ታትመው ለአንባቢያን ተሰራጭተዋል” ይላሉ፡፡ የሕትመቱ ዘርፍ እንዲህ እያደገ የመጣ ቢመስልም ዛሬም ቢሆን የሕትመት ውጤቶች ከአንባቢያን ጋር በቅጡ አልተገናኙም ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህ አባባሌ መነሻ የሆነኝን ገጠመኝ ከማቅረቤ በፊት የደርግ መውደቅን ተከትሎ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በክልል ከተሞች ቅርንጫፎችን መክፈት የቻሉና ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደጉ የመጡት የግል መፃሕፍት መሸጫ መደብሮች መነሻቸው አሮጌ መፃሕፍት የመሸጥ ሥራን መተዳደሪያ ያደረጉ ሰዎች ነበሩ፡፡ ለዚህ መነሻ በመሆንም የመርካቶው አሮጌ መጽሐፍ ተራ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል፡፡ አሁን በኮልፌ፣ በአውቶቢስ ተራ፣ በፒያሳ፣ በመገናኛ፣ በጊዮርጊስ፣ በለገሀር፣ በብሔራዊ ቴአትር አካባቢዎች ከምናገኛቸው መጽሐፍ ነጋዴዎችና ባለመደብሮች ጥቂት የማይባሉት ከመርካቶው አሮጌ መጽሐፍ ተራ ጋር የተያያዘ ታሪክ ያላቸው ናቸው፡፡ የመርካቶ አሮጌ መጽሐፍ ተራ ዛሬም ቢሆን በረንዳዎችን ተጠልሎ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ በብዙ አሰራር፣ አስተሳሰብ፣ አካሄዳችን ውስጥ አሮጌና አዲሱ፣ ባህላዊና ዘመናዊው፣ ነባሩና መጤው፣ ፈጣንና ኋላቀሩ…እየተቀላቀሉ የቱን መያዝ የቱን መተው፣ የቱ ጥሩ የቱ መጥፎ፣ ምኑ ጠቃሚ፣ ማንኛውም ጐጂ…መሆናቸውን ለመምረጥ ስንቸገር እንደምንታየው ሁሉ፤ ከሕትመት ሥራና በተያያዥ አገልግሎቶቹ ውስጥም ዕድገትና ችግሩ ተቀላቅለው ወይም ዕድገቱ ችግሩን በበቂ ሁኔታ መቅረፍ አለመቻሉ ይታያል፡፡ ባለፈው ሳምንት ሚያዝያ 18 ቀን 2004 ዓ.ም ኮልፌ በሚኘው “ሜሊኒየም 2ኛ ደረጃ የመሰናዶ ትምህርት ቤት” ለ3ተኛ ጊዜ የተሰናዳ የመፃሕፍት ቀን በዓል ዝግጅት ነበር፡፡ በዕለቱ ከኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ተጋብዘው የተገኙት አቶ አፈወርቅ በቀለ፤ የትምህር ቤቱን ቤተ መፃሕፍት ከጐበኙ በኋላ ቤተመፃህፍቱ በአማርኛ መፃሕፍት ድርቅ እንደተመታ ገልፀው ነበር፡፡ ቤተ መፃህፍቱ ካሉት 3556 መፃሕፍት ውስጥ የአማርኛ መፃሕፍት ቁጥር 321 ብቻ ነው፡፡ 164 የተማሪ መርጃ፣ 157ቱ ደግሞ የልቦለድ መፃሕፍት፡፡ በሕትመት ዘርፉ ዕድገት ካለ፤ በየወሩ በ80 የሚቆጠሩ መፃሕፍት የሚታተሙ ከሆነ፤ መፃሕፍቱን ማግኘት ያለባቸው ተማሪዎች ጋ ለምን አልደረሰም? ኢትዮጵያዊያን ደራሲያንና ኢትዮጵያዊያን ተማሪዎች እንዳይገናኙ እንቅፋት የሆነባቸው ማን ነው? ምንድን ነው? የአገሪቱን ምሁራን ዕውቀት ካገሪቱ ተማሪዎች ጋር በመፃሕፍት በኩል ለማገናኘት የሞከሩት የአፄ ኃይለሥላሴ ተግባር አርቆ ከማሰብ የመነጨ መሆኑን ምስክርነት ለመስጠት ግድ የሚለው ለዚህ ነው፡፡ በንጉሱ ዘመን የተጀመረው መፃሕፍትን ለትምህርት ቤቶች የመለገስ ተግባር እስከ ኢሕአዴግ ዘመንም ዘልቆ ታይቷል፡፡ አሁን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ስር ለሚገኘው የስነ ጥበብ ትምህርት ቤት ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ በ1995 ዓ.ም የተለያዩ መፃሕፍትን አበርክተው ነበር፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሚዩዚክ ሜይዴይ ለተመሳሳይ ዓላማ መንቀሳቀስ መጀመሩ ይታወቃል፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በፊትም በብሔራዊ ቴአትር በተሰናዳ ፕሮግራም፤ ለአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት ቤተመፃሕፍት የሚሰጡ በሺ የሚቆጠሩ መፃሕፍት ተሰባስበው ነበር፡፡ ተማሪዎች የማንበብ ባህልን እንዲያዳብሩና በእውቀትና በመረጃ እየበለፀጉ እንዲያድጉ ከተፈለገ ተቋማት፣ ታዋቂ ግለሰቦችና ሌሎችም መፃህፍት ለት/ቤቶች ይደርሱ ዘንድ የድርሻውን ሊያበረክቱ ይገባል፡፡ ለምሳሌ “አለኝ የምለው ሀብት መፃሕፍቶቼ ናቸው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፤ ከሀብታቸው ጥቂቱን ቆንጥረው ለአንዱ ትምህርት ቤት ቢለግሱ ለብዙዎች አርአያ ሊሆኑ ሊያነሳሱ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል፡፡

 

 

Read 15432 times Last modified on Sunday, 06 May 2012 16:06