Saturday, 07 July 2018 11:11

ብህትውናና ዘመናዊነት - ክፍል- 4

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(3 votes)

 የእየሱስ የመጨረሻዎቹ ቀናትና የኢትዮጵያ ሙዚቃ
             
     በክፍል-3 ፅሁፌ ላይ ኢትዮጵያ እንዴት ከያሬድ የትካዜ (የብህትውና) ዜማ እንደተወለደች ተመልክተናል፡፡ በዛሬው ፅሁፌ ደግሞ የያሬድ የትካዜ ዜማዎች እንዴት ከእየሱስ የመጨረሻዎቹ የመከራ ቀናት እንደተቀዱ እንመለከታለን፡፡ በሌላ አነጋገር፣ ኢትዮጵያ የተወለደችው ከእየሱስ የመጨረሻዎቹ የእንግልትና የመከራ ቀናት ከፈጠሩት የትካዜ ስሜት (ሰሞነ ሕማማት) መሆኑን እንመለከታለን፡፡
የእየሱስ የመጨረሻዎቹ የመከራ ቀናት ‹‹ሰሞነ ሕማማት›› (የህመም ሳምንት) በመባል ይታወቃል። ዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ ‹‹ሕማማት›› በሚለው መፅሐፉ ውስጥ እንዳስቀመጠው፤ ‹‹ሕማማት›› ማለት በግዕዝ ቋንቋ ‹‹ሀዘን፣ ጭንቀት፣ መከራ፣ ዋይታ›› ማለት ነው። በመሆኑም፣ ‹‹ሰሞነ ሕማማት›› ወይም የእየሱስ የመጨረሻዎቹ ቀናት ስንል እየሱስ ከመሞቱ በፊት በከፍተኛ የመንፈስ መረበሽ፣ በጭንቀት፣ በሀዘን፣ በእንግልትና በመከራ ያሳለፋቸው የመጨረሻዎቹን ቀናት ለማመላከት ነው፡፡
ለመሆኑ ሰሞነ ሕማማትንና የኢትዮጵያን ሙዚቃ ምን ያገናኛቸዋል? ብላችሁ ልትጠይቁ ትችላላችሁ። ሁለቱን የሚያገናኛቸው ድልድይ ቅዱስ ያሬድ ነው። እስቲ ነገሩን ከስር ከሰው ልጅ ስነ ልቦና ጀምረን እንመልከተው፡፡
የማንኛውም ዓይነት ህይወት (በሰውም ሆነ በእንስሳት) የመጀመሪያው መርህ ደህንነትን (Security) ማስጠበቅ ነው፡፡ የደህንነት ምቾት የሚገኘው ደግሞ በዋነኛነት ‹‹በመላመድ›› ነው- ተፈጥሯዊና ማህበራዊ አካባቢን በመላመድ፡፡ ከተላመድነው ነገር ‹‹ስንለይ›› ስነ ልቦናዊ ትስስራችን ስለሚበጣጠስ ‹‹ፍርሃት›› ይወረናል፡፡ በመሆኑም፣ በሰው ልጅ ስነ ልቦና ውስጥ በጣም ወሳኝ የሆኑ ተቃራኒ ስሜቶች ‹‹መላመድ›› እና ‹‹መለየት›› ናቸው፡፡ በመላመድና በመለየት መካከል ‹‹የመጨረሻዎቹ ቀናት›› አሉ፡፡ ‹‹የመጨረሻዎቹ ቀናት›› የመላመዳችን ምዕራፍ ማብቂያ ነው፡፡
በመሆኑም፣ የሰው ልጅ ስነ ልቦና ‹‹የመጨረሻዎቹ ቀናት›› ከሚባለው ሐሳብ ጋር በጣም የተቆራኘ ነው። ‹‹የመጨረሻዎቹ ቀናት›› በህይወታችን ውስጥ የተለመደው ምዕራፍ የሚዘጋበትና አዲስ ምዕራፍ የሚጀመርበት ወቅት ነውና ብዙ ጊዜ በህይወታችን ውስጥ የተደበላለቁ ስሜቶችን ይዞብን ይመጣል — ተስፋንና ፍርሃትን፣ ደስታንና ተጠራጣሪነትን፡፡
‹‹የመጨረሻዎቹ ቀናት›› በጣም በምንወደው ሰው ላይ ቢከሰትስ?
* የእየሱስ የመጨረሻዎቹ ቀናት!
* የሶቅራጠስ የመጨረሻዎቹ ቀናት!
* የአፄ ቴዎድሮስ የመጨረሻዎቹ ቀናት
* የእናቴ የመጨረሻዎቹ ቀናት!
* የልጄ የመጨረሻዎቹ ቀናት!
ነባሩን (የለመድነውን) ምዕራፍ የሚያዘጉና አዲስ ምዕራፍ የሚያስከፍቱ በአብዛኛው እንደነዚህ ዓይነት ከእኛ ህይወት ጋር አሊያም ከህዝቡ ጋር የተሳሰረ ስነ ልቦና ያላቸው ሰዎችና መሪዎች የሚያሳልፉት ‹‹የመጨረሻዎቹ ቀናት›› ናቸው፡፡
ሆኖም ግን፣ በአብዛኛው የሰው ልጅ በለመደው ነገር ውስጥ መቆየት ስለሚፈልግ ‹‹የመጨረሻዎቹ ቀናት›› የሚባለው ነገር ብዙ ጊዜ ከአሳዛኝ ፍፃሜና ‹‹በሞት ከመለየት›› ጋር ስለሚተሳሰር ‹‹የመጨረሻዎቹ ቀናት›› በሰው ልጅ ህይወት ውስጥ ፍርሀትን፣ መረበሽን፣ ብቸኝነትን፣ ባዶነትን፣ አቅመ ቢስነትን፣ ሀዘንን፣ የህሊና ስብራትን፣ መከፋትን፣ ትካዜንና ‹‹ዘላቂ የሆነ ቁዘማ››ን ይፈጥራል፡፡ እነዚህም ስሜቶች ብዙ ጊዜ ዘላለማዊ የሆነ የህሊና ጠባሳ አስቀምጠውብን ያልፋሉ፡፡
በመሆኑም በዚህ ዘላለማዊ የህሊና ጠባሳ ላይ ትልቁን ማህተም የሚያሳርፍብን የምንወደው ሰው ከእኛ በሞት ከመለየቱ በፊት የሚያሳልፋቸው ‹‹የመጨረሻዎቹ የመከራ ቀናት›› ናቸው፡፡ እነዚህ ‹‹የመጨረሻዎቹ የመከራ ቀናት›› የተፈፀሙት ደግሞ ህዝቦች በጋራ በሚወዱትና እና እንደ አርዓያም በሚያዩት ሰው ላይ ከሆነ ደግሞ ክስተቱ በባህላቸው፣ በትምህርታቸው፣ በኪነ ጥበባቸውና በሃይማኖታቸው ላይ ዘላቂ አሻራውን ያሳርፋል፡፡
ለምሳሌ፣ ከሌሎች የኢትዮጵያ ነገስታት ይልቅ፣ አፄ ቴዎድሮስ በኪነ ጥበባችን ውስጥ ነግሰው ሊገኙ የቻሉት ንጉሱ ባሳለፉት ‹‹የመጨረሻዎቹ ቀናት እና አሳዛኝ ፍፃሜያቸው›› የተነሳ ነው፡፡ የፕሌቶንና ከፕሌቶ በኋላ የመጣውን የግሪክን ፍልስፍና፣ ባህሪውንና ይዘቱን ከወሰኑት ክስተቶች ውስጥ ዋነኛው የሶቅራጠስ ‹‹የመጨረሻዎቹ ቀናትና አሳዛኝ ፍፃሜው›› ነው። በተመሳሳይ ሁኔታ፣ የእየሱስ የመጨረሻዎቹ ቀናት በክርስትና ሃይማኖት ውስጥ ትልቁን ስፍራ የሚይዝ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስትና ውስጥ ደግሞ አሻራው ይበልጥ ደማቅ ነው፡፡
እየሱስ በማስተማር ያሳለፋቸው ጊዜያት ሦስት ዓመታት ሲሆኑ፣ እነሱንም በሁለት ልንከፍላቸው እንችላለን — የፍስሐ ጊዜና የመከራ ጊዜ በማለት። የእየሱስ የፍስሐ ጊዜ የሚባለው ወደ ሰርግ ቤት የሄደበትን፣ ተዓምራት የሰራበትንና ትንሳኤውን (ከሞት የተነሳበትን ጊዜ) የሚያካትት ነው፡፡ የእየሱስ የመከራ ጊዜ (ሰሞነ ሕማማት) የሚባለው ደግሞ የተገረፈበትን፣ የተንገላታበትን፣ በጦር የተወጋበትንና በስተመጨረሻም የተሰቀለበትንና የሞተበትን ‹የሀዘን፣ የጭንቀት፣ የመከራና የዋይታ ቀናትን ያጠቃልላል። ይህ የሀዘንና የዋይታ ጊዜም ‹‹እየሱስ በጌቴሰማኒ የአትክልት ስፍራ ሐሙስ ማታ ከተያዘበት ሰዓት ጀምሮ አርብ ማታ ተሰቅሎ እስከ ሞተበት ጊዜ ድረስ ያለውን የእየሱስ ሃያ የሕማማት ሰዓታት የሚያጠቃልል ነው›› (ሄኖክ 2010፡ 23-24)፡፡
እየሱስ በማስተማር ካሳለፋቸው ሦስት ዓመታት ውስጥ እነዚህ ሁለት የሕማማት ቀናት በጣም ወሳኝና አሻራቸውም ከሁሉም ክስተቶች በላይ ደማቅ ነው፡፡
በተለያዩ ዘመናት ላይ የተነሱ የክርስትና ሃይማኖቶች፤ እነዚህን ሁለት የእየሱስ ዘመናትን መንፈስ ይዘው ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ለምሳሌ በ16ኛው ክ/ዘ የተነሳው የማርቲን ሉተር ትምህርት፣ የእየሱስ የፍስሐ ዘመናት ላይ ሲያተኩር፤ የምስራቅ አብያተ ክርስትያናት ትምህርቶች ደግሞ ሰሞነ ሕማማት ላይ ያተኩራሉ። በመሆኑም፣ እየሱስ በመጨረሻዎቹ የመከራ ቀናት ላይ ያሳለፋቸው እነዚያ ልብን የሚሰብሩ ስሜቶችና በዚህም እናቱ ቅድስት ማርያም ያጋጠማት ሐዘንና መከራ በይበልጥ በምስራቅ አብያተ ክርስትያናት ውስጥ ይዘከራሉ፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ የበቀለውን ያሬዳዊ ስልጣኔ ሥረ መሰረቱን የምናገኘውም ከዚህ ልብን ከሚሰብረው የእየሱስ የመጨረሻዎቹ የመከራ ቀናት ላይ ነው፡፡ ‹‹የእየሱስ የሕማማቱ ነገር የሰው ልጅ ዳግም በቀራኒዮ የተፈጠረበት ታሪክ በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ ሊቃውንቶች ስብከትና መልዕክት፣ ትርጓሜና ትምህርት፣ የካህናቱ ቅዳሴና ሰዓታት፣ የመዘምራኑ ማሕሌትና ስብሐት ሁሉ የእየሱስን ሕመም የሚያወሳ ነው›› (ሄኖክ 2010፡ 23)፡፡
በመሆኑም፣ እነዚህ የእየሱስ የመጨረሻዎቹ የመከራና የዋይታ ቀናት የፈጠሩት የቁዘማና የትካዜ ስሜት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ለያሬዳዊው ስልጣኔ የባህል መሰረት ሆኖታል፡፡ በዚህ የሐዘን ስሜት የተነካ ሁሉ እንደተሰጠው ፀጋ የልብ ስብራቱን በፅሁፍ፣ በስዕል አሊያም በእንጉርጉሮ ይገልፀዋል፡፡ በመሆኑም፣ የሀገራችን ኪነ ጥበብ የፈጠራ ስሜቱን (creative impulse) የሚቀዳው ከዚህ የትካዜና የቁዘማ ባህል ነው፡፡ እነዚህ የእየሱስ የመጨረሻ የመከራ ቀናት ናቸው፣ በያሬድ ውስጥም የሀዘን ዜማ የሆኑት፡፡
በመሆኑም፣ ቅዱስ ያሬድ የበቀለው በዚህ የአክሱም የልብ ስብራት ላይ ነው፡፡ አክሱም በብህትውና ከዓለም ተነጥላ፣ እየሱስና እናቱ የገጠማቸውን ሐዘንና መከራ እያሰበች በምትቆዝምበትና እያስለቀሰ የሚያፅናናትን ዜማ በናፈቀችበት ወቅት ላይ ነው ቅዱስ ያሬድ የደረሰላት፡፡ በዚህም ‹‹በእየሱስ መከራ የተቃኘ ዜማን ፈጠረላት›› (ሄኖክ 2010፡ 12)፡፡ እነዚህም የዜማ ቅኝቶች ግዕዝ፣ ዕዝልና አራራይ ይባላሉ፡፡ ቅኝቶቹ በሙሉ ልብን የሚሰረስር፣ የሚያስቆዝምና ከባድ ትካዜ ላይ የሚጥሉ ናቸው፡፡ ያሬድ ለዜማ መድብሉ የሰጠው ‹‹ድጓ›› የሚለው ስያሜ ራሱ፣ በግዕዝ ቋንቋ ‹‹የሀዘን መዝሙር›› ማለት ነው፡፡
በእየሱስ መከራ የተቃኘው ያሬዳዊው ዜማ ብቻ ሳይሆን የሙዚቃ መሳሪያዎችም ጭምር ናቸው፡፡ ‹‹ቤተ ክርስትያናችን የእየሱስ የግርፋቱን ሰንበር በከበሮዋ፣ መስቀል መሸከሙን በመቋሚያዋ እንዲሁም የእሾህ አክሊል መድፋቱን በካህናቷ ጥምጣም ትዘክራለች። ከዚህም በተጨማሪ፣ ቅዱስ ያሬድ እየሱስ በሐሰት መያዙን ለማመላከት (ይዘት)፣ ከጲላጦስ ወደ ሄሮድስ መሄዱን (ሒደት)፣ በቅናት መከሰሱን (ቅናት)፣ በፍቃዱ ቆርጦ መከራን መቀበሉን (ቁርጥ)፣ በግርፋት የደረሰበትን (ጭረት)፣ የደሙን መንጠባጠብ (ርክርክ) በማለት የዜማ ምልክቶቹን ሰይሟቸዋል›› (ሄኖክ 2010፡ 11)፡፡
ባጠቃላይ ያሬድ የፈጠራቸው የዜማ ቅኝቶች፣ የዜማ ምልክቶች፣ የዜማ መሳሪያዎችና ዝማሜዎች በሙሉ ሰሞነ ሕማማትን የሚዘክሩ ናቸው፡፡ ዝማሬው ልብን የሚያስተክዝ ሲሆን፣ ዝማሜው ደግሞ የእየሱስን እንግልትና መከራ የሚዘክር ነው፡፡
እንግዲህ፣ ያሬድ ይሄንን ልብን የሚሰረስር የትካዜ ዜማ ይዞ ነው አክሱምን ለቆ ወደ ቤተልሔም (ጎንደር) እና በባህር ዳር የጣና ገዳማት ድረስ የሄደው። በሄደባቸው ቦታዎች ሁሉ ወጣቶችን እየሰበሰበ፣ ዝማሬውንና ዝማሜውን አስተምሯል፡፡ ኢትዮጵያ ይሄንን የትካዜ ቅኝት ይዛ ነው የተወለደችው፡፡ እናም በዚህ የያሬድ ትካዜና ዝማሜ ኢትዮጵያ ተወለደች፡፡
የሙዚቃ አቀናባሪውና የያሬድ የሙዚቃ ት/ቤት መስራች የሆነው ፕ/ር አሸናፊ ከበደ፤ ‹‹The Music of Ethiopia: Its Development and Cultural Setting›› በሚለው የዶክትሬት የማሟያ ፅሁፉ ላይ እንደገለፀው ‹‹በመካከለኛ ዘመን ላይ ያቆጠቆጡት የአዝማሪ ዘፈኖች ቅኝታቸውን የወሰዱት ከዚህ የያሬድ የትካዜ ዜማዎች ነው (1975፡ 55)፡፡ እነዚህ የአዝማሪ ዘፈኖች በሂደት ትዝታ፣ ባቲ አምባሰልና አንቺ ሆዬ የሚባሉ አራት ዓለማዊ የዜማ ቅኝቶችን ፈጥረዋል። ፕ/ር አሸናፊ እንደሚሉት፤ ከእነዚህ አራት ዓለማዊ የዘፈን ቅኝቶች ውስጥ በተለይ የትዝታ ቅኝት፣ የያሬድ የትካዜና የቁዘማ ዜማ ግልባጭ ነው፡፡
የሰሞነ ሕማማት ስሜቶች በያሬድ አድርጎ አዝማሪ ቤቶች ውስጥ ቢገባም፣ አሻራው ግን የዘመናዊ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ድረስ ይታያል፡፡ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ውስጥ ወርቃማ ዘመን የሚባለው ከ1950ዎቹ መጨረሻ እስከ 1970ዎቹ መጀመሪያ ድረስ ያለው ዘመን ነው፡፡ በዚህ የሙዚቃችን ወርቃማ ዘመናት ውስጥ እንደ አብሪ ኮከብ ሆነው ከተነሱት ከያኒያን ውስጥ ሙሉቀን መለሰ፣ ኤፍሬም ታምሩ፣ ቴዎድሮስ ታደሰ፣ አስቴር አወቀና ጥላሁን ገሰሰ የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡ በዚህ ዘመን ወቅት ከተሰሩ ዘፈኖች ውስጥ አብዛኛዎቹ የትካዜና የቁዘማ ዜማዎች ይጫናቸዋል፡፡
በአንድ ወቅት (2006 ዓ.ም) የዜማ ደራሲው አበበ መለሰ፤ ከእስራኤል ሆኖ ከሸገር ሬዲዮ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ፤ የሙሉቀን፣ የኤፍሬምና የቴዎድሮስ ዘፈኖች እንዴት ከያሬድ የትካዜ ዜማዎች ተፈልቅቀው እንደወጡ አስረድቷል፡፡ እኛም የትካዜ ዜማዎችን ስንሰማ ደስ የሚለን፣ አእምሯችን ከድሮ ጀምሮ በዚህ መንገድ ስለተቀረፀ ነው፡፡
ይህ የቁዘማና የትካዜ ስሜት በሙዚቃዎቻችን ላይ ብቻ ሳይሆን በስዕሎቻችን፣ በፊልሞቻችንና በስነ ፅሁፎቻችን ላይም ይንፀባረቃል፡፡ ዘመናዊነት ከዚህ የቁዘማ ስሜት መውጣት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር፣ ዘመናዊነት ማለት ከሰሞነ ሕማማት ወደ ትንሳኤው መሸጋገር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ባህል አሁንም በሰሞነ ሕማማት ስሜት ውስጥ ነው ያለው፤ ከእየሱስ ትንሳኤ ጋር አብሮ አልተነሳም፡፡ በሌላ ጊዜ በሰፊው እመለስበታለሁ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊው በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር እና ‹‹የኢትዮጵያ ፍልስፍና›› መፅሐፍ ደራሲ ሲሆን በኢ-ሜይል አድራሻው  
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 3191 times