Monday, 09 July 2018 00:00

ማዕከላዊን በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ማዕከላዊ፤ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ፣ ከአራዳ ጊዮርጊስ ወደ ሰሜን ሆቴል በሚወስደው መንገድ የሚገኝ ግቢ ነው፡፡ ብዙ ሰው ላያውቀው ይችላል፤ ቢያውቀውም ብዙ ትኩረት አይሰጠውም። ስለ ማዕከላዊ ሳስብ የሚያሳዝነኝ አንድ ጉዳይ አለ። ማዕከላዊ ፊት ለፊት  በተለምዶ “ዳትሰን” የሚባል ሲደለቅበት የሚያድር ሰፈር አለ፡፡ በርካታ ወጣቶችም በአንድ ቤት ውስጥ ታጭቀውና ራሳቸውን ረስተው የሚዘሉበት ሰፈር ነው፡፡ ፊት ለፊቱ ደግሞ፣ ወጣቶች በበርካታ መርማሪ ተከበው፣ ሲገረፉ የሚያድሩበት ማዕከላዊ አለ፡፡
ከአንድ ኪሎ ሜትር በላይ በማይሆን ርቀት ውስጥ እጅግ የተለያየ ተግባር ሲፈጸምባቸው ያድራል፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ታዲያ፣ ከሚዝናኑት አብዛኞቹ ይህን ማዕከላዊ ተብሎ የሚጠራውን ቦታ የሚያውቁት አለመምሰላቸው፣ ቢያውቁት ኖሮ፣ እነዛ ጭፈራ ቤቶች፣ አንድም ወጣት ባልገባባቸው ነበር። በርካቶች፣ ማዕከላዊ የሚባለውን ቤት እንደ ተራ መስርያ ቤት ብቻ አስበው በጥጉ ያልፋሉ፡፡ ማዕከላዊ ግን፣ መስርያ ቤት ይደለም፡፡ በማዕከላዊ የስቃይ ሕይወት ያሳለፉት የዋልድባው ገዳም መነኩሴ፣ አባ ገ/ኢየሱስ ኪ/ማርያም፤ “ማዕከላዊ የሚባል ቤት” እያልኩ ሳወራ፣ “ልጄ፣ ማዕከላዊ ቤት አይደለም” ብለው አርመውኛል፡፡ እውነት ነው፣ ማዕከላዊ ቤት አይደለም! አባ ወ/ኃይማኖት፣ ስለ ማዕከላዊ ጠይቄያቸው፤ “የማዕከላዊን ነገር አታንሳው” ብለውኛል፡፡ መነኮሳቱ በማዕከላዊ ተገርፈዋል፡፡ ለምሳሌ፣ አባ ገ/ስላሴ ወ/ኃይማኖት፤ ሰውነታቸውን በሚስማር እንደበሳሷቸው አጫውተውኛል፡፡ የዛን ነውረኛ “ቤት” ጉዳይ ስለማውቅ፣ “ልብስዎን አስወለቁዎት” ብዬ ጠይቄያቸው፣ “ብዙ ጊዜ አውልቁ ይሉናል፡፡ ሁለት ቀን ከአቅሜ በላይ ሆኖብኝ፣ አውልቀውብኛል” ብለው አዝነው ነግረውኛል። ማዕከላዊ፣ የመነኮሳትን አይደለም፣ የእግዚአብሔርን ክብር የሚያዋርድ “ቤት” ነው፡፡
ሳይቤርያ
ታሳሪዎቹ ብዙ ጊዜ የመጀመርያ መቆያቸው ከሳይቤርያ ይጀምራል፡፡ ሳይቤርያ የሚለው ቤት፣ በሩሲያው ሀገር ውስጥ፣ ቀን ቀን ሞቃት፣ ሌሊት ሌሊት ደግሞ፣ በጣም ቀዝቃዛ በሆነው ግዛት ስም የተሰየመ ነው፡፡ ሰማይ እንዲመስል ጣራው ሰማያዊ ቀለም ተቀብቷል፡፡ ሳይቤርያ በምርመራ ላይ ያለ እስረኛ የሚታሰርበት ሲሆን 2፣3፣4፣5፣6፣7፣8፣9 እና 10 የተባሉ ቁጥር የተሰጣቸው ቤቶች አሉት፡፡ 1 ቁጥር ዝግ ነው፡፡ ከ8 ቁጥር ውጭ ያሉ እስከ 25 እስረኞች የሚታሰሩበት ሲሆን ከ6፣7 እና 8 ውጭ ያሉ ክፍሎች ስፋታቸው በግምት፣ 3 ነጥብ 8 ሜትር በ4 ሜትር ቢሆን ነው። 6 እና 7 ቁጥር ከእነዚህ ክፍሎች በአንፃራዊነት ስፋት አላቸው። አራት በአራት የማይሆን ክፍል ውስጥ እስከ 20 የሚደርሱ እስረኞች እቃ ይቀመጣል፡፡ ሽንት ቤት፣ በቀን ከሁለት ጊዜ ውጭ ስለማይፈቀድ፣ የሽንት ማስቀመጫ ፕላስቲክ ኮዳዎች ይቀመጣሉ። የሚያሳዝነው፣ ከቦታ ጥበት የተነሳ፣ የውሃ ፕላስቲክ ኮዳዎች እና ምግብ የሚቀመጠው አንድ ላይ ነው፡፡
ክፍሉ ለመኝታ ስለማይበቃ፣ ቀን ቀን የተወሰኑ እስረኞች ሲተኙ ቀሪው ቁጭ ይላል፡፡ ሌሊት ራስና እግር እየሆነ (አንደኛው ራሱን ከጎኑ ወደተኛው እስረኛ እግር አድርጎ)፣ በአንድ ጎን ብቻ እስኪነጋ ይተኛል። የሁሉም ክፍል ዝግ ስለሆኑ እስረኛ ሲበዛ ከመጠን በላይ ይሞቃሉ፡፡ መስኮታቸው ከሁለት ሜትር የሚርቅ ሲሆን መብራት የሚገባው በመስኮቱ በኩል ነው። በዚህም ምክንያት ጨለማ ቤት ተብለው ይጠራሉ። የአንድ ክፍል እስረኛ ከሌላኛው ክፍል እስረኛ ጋር መረጃ እንዳይለዋወጥ በሮቹ ይዘጋሉ፡፡ በተመሳሳይ ጉዳይ ተጠርጥረው የገቡ እስረኞችን፣ አንደኛውን በሌላኛው ላይ ለማውጣጣት ሲባል፣ ወይም መረጃ እየተለዋወጡ ለምርመራ እንዳያስቸግሩ ለማድረግ፣ አንደኛው ክፍል የታሰረ ከሌላኛው ክፍል ከታሰረው ጋር እንዳይገናኝ ብርቱ ጥንቃቄ ያደርጋሉ፡፡ ሲያወራ የተገኘም ቅጣት ይጠብቀዋል፡፡ አየር ለማግኘት እንኳ በሮቹ የሚከፈቱት በልመና ነው፡፡
ሳይቤርያ የታሰረ እስረኛ በአንድ ቀን ውስጥ ሁለት ጊዜ ብቻ ሽንት ቤት እንዲወጣ ይፈቀድለታል፡፡ ሌሊት 11 ሰአት የየክፍሉ እስረኛ በተራ ሽንት ቤት ይጠቀማል። ክፍሎቹ በየተራ እየተከፈቱ ከ10 እስከ 15 ባለ ደቂቃ፣ 20 እና ከዛ በላይ እስረኛ ሽንት ቤት ተጠቅሞ ይገባል። በቀን አንድ ጊዜ ለ10 ደቂቃ ፀሐይ መሞቅ ይፈቀዳል። ጨለማ ቤት ባደከመው አይኑም በዛች ትንሽ ደቂቃ የተከለከለው ሰማይ ላይ የተለየ ነገር ይፈልጋል፡፡ ደመና የተለየ ነው። ጨረቃ አትገኝም፡፡ ኮከብ ብርቅ ነው፡፡ አሞራ እንደ ብርቅ ነገር ይታያል፡፡ ሰማይ ይናፍቃል!
በሳምንት አንድ ቀን፣ ቤቶቹ በየተራ እየተከፈቱ፣ እስረኞች ልብስ እንዲያጥቡ ይደረጋል፡፡ ምንም አይን ከለላ የሌለው ቦታ ላይ፣ ህጻናት ወንዝ ወርደው እንደሚታጠቡት፣ እየተጋፉ “ሻወር” ይወስዳሉ፡፡ ከአንድ የዛገ ብረት የሚወርደውን ውሃ “ጠፋ! መጣ!” እያሉ እየተጋፉ፣ ሳምንት ጠብቀው ያገኙትን “ሻወር” ይወስዳሉ፡፡ ሽንት ቤቶቹ ከለላ የላቸውም፡፡ አንዱ ሲጠቀም ሌሎች እስረኞች በር ድረስ ተኮልኩለው ተራ ይጠብቃሉ፡፡ በዚህ መሃል ፖሊስ ከሽንት ቤቶቹ ውጭ ያለውን ዋናውን በር በዱላ እየነረተ፣ እስረኛው ወደ ክፍሉ እንዲገባ ያዝዘዋል፡፡ ሌላ ቤት ተከፍቶ ተረኛ ይጠቀማል፡፡ ቤቱ እንደተከፈተ የተረኛው ክፍል እስረኞች፣ በእጃቸው በሀይላንድ ቤት ውስጥ የዋለውን ሽንት ሳይሳቀቁ ተሸክመው፣ ወደ ሽንት ቤት ያመራሉ፡፡
“8” ቁጥር
ማዕከላዊ ውስጥ ካሉት የሚታወቁት ጨለማ ቤቶች አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ አንዱ ክፍል ለ4 ተከፍሎ 1፣2፣3፣4 የሚባሉ ንዑስ ክፍሎች አሉት፡፡ ክፍሎቹ ኮሪደር መሃል ካለው መብራት ውጭ ሙሉ በሙሉ ጨለማ ሲሆኑ እያንዳንዱ ክፍል አንድ ሰው ብቻ ይታሰርበታል፡፡ በእነዚህ ክፍሎች የሚታሰሩ እስረኞች ከፍተኛ በደል የሚደርስባቸው፣ ሁሉም ሌሊት እየተጠሩ የሚደበደቡና ስቃይ የሚደርስባቸው ናቸው፡፡ በምርመራ ወቅት አናምንም ያሉ እስረኞች ለወርና ለሁለት ወር ያህል በእነዚህ ጠባብ ክፍሎች ይታሰራሉ፡፡ ሽንት ቤት የሚሄዱት፣ ፀሃይ የሚሞቁት ብቻቸውን ነው፡፡ ከሳይቤርያ ታሳሪዎች ሁሉ ከፍተኛ የአካልና የስነ ልቦና ጥቃት ይደርስባቸዋል፡፡ ያመነ እስረኛ ወደ ሳይቤርያ ሌሎች ክፍሎች፣ ወይ ደግሞ ወደ “ሸራተን” ይዛወራል፡፡
መርማሪዎች ፈፅማችኋል ያሏቸውን እንዲያምኑ 8 ቁጥር ከሚገቡት በተጨማሪ፣ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ሆነው በሌሎች ተጠርጣሪዎች ላይ ቃላቸውን እንዲሰጡ የሚፈለጉ ተጠርጣሪዎችም በዚህ ክፍል ይታሰራሉ፡፡ ሰዎች መጀመርያ በወንጀል ተጠርጥረው ገብተው መረጃ ሲጠፋ፣ በሌላ ሰው ላይ በሀሰት እንዲመሰክሩ ሲጠየቁ፣ ካልተስማሙ 8 ቁጥር ይታሰራሉ። እንመሰክራለን ካሉ ግን ወደ ጣውላ ቤት ይዛወራሉ፡፡ 8 ቁጥር ከሳይቤርያ ቀሪ ክፍሎችም የባሰ ነው፡፡ በዚህኛው ክፍል ደግሞ ከሰው ጋር መብላት፣ የሰው ድምፅ መስማትም ይናፍቃል፡፡
ምርመራውን የጨረሰ፣ ቃል ሰጥቶ የፈረመ እስረኛ የሚታሰርበት የእስር ቤት ክፍል ነው፡፡ 12 ክፍሎች ያሉት ጠባብ ክፍል ሲሆን ቤቶቹ ክፍት ሆነው ይውላሉ፡፡ እስረኞች ወደ ሌሎች ክፍሎች እየተዘወዋወሩ መጫወት ይችላሉ፡፡ ቤቶቹ በር ላይ ሆኖ ፀሀይ መሞቅ ይቻላል፡፡ ይህም ከሳይቤሪያ ጋር ሲነፃፀር ሸራተን የሚል ስያሜ  አሰጥቶታል፡፡ ይህ እስር ቤት፣ በቤቶች መካከል የተወሰነ የሰማይ ክፍልን ያሳያል፡፡ በር ላይ ቁጭ ብሎ ፀሀይ መሞቅ፣ አየር ማግኘት ይቻላል፡፡ እስረኛው እንደ ሳይቤሪያ በፖሊስ እየተጠበቀና “ጨርስ” እየተባለ ሳይሆን በፈለገው ሰዓት ወደ መፀዳጃ ቤት መሄድ ይችላል፡፡ ወደ ሌላ ክፍል ገብቶ ከጓደኞቹ ጋር መጫወት ይችላል። አንድ እስረኛ ተጨማሪ መረጃ ከተገኘበት ወይም በሌላ ሰው እንዲመሰክር ተጠይቆ አልመሰክርም ካለ ከሸራተን ወደ ሳይቤርያ፣ ብሎም ወደ 8 ቁጥር ይመለሳል፡፡
ጣውላ ቤት
ከወንጀል ምርመራ ቢሮዎች ስር የሚገኙ ክፍሎች ናቸው። ሴቶችና ምስክሮች የሚታሰሩበት ሲሆን አራት ክፍሎች አሉት። ሁለቱ የሴቶች፣ ሁለቱ የምስክሮች ሲሆኑ ክፍሎቹ ተከፍተው ስለሚውሉ አየር ያገኛሉ፡፡ በር ላይ ቁጭ ብለው ፀሀይ መሞቅ ይችላሉ፡፡
  ምርመራ
ማዕከላዊ 24 ሰዓት ምርመራ የሚደረግበት እስር ቤት ነው፡፡ ድብደባ የሚፈፀመው በአብዛኛው ሌሊት ነው፡፡ ይህም የሚደረገው ጩኽት እንዳይሰማና ድብደባ ሲፈፅሙ ብዙ እስረኛ እንዳያይና እንዳይሰማ ነው፡፡ አንድ እስረኛ እስከ 6 በሚደርሱ መርማሪዎች ሊመረመር ይችላል፡፡ ሁሉም ያዋክቡታል፡፡ ፊት ለፊት ካለው ጋር እየተነጋገረ፣ ከኋላም መጥተው ይደበድቡታል፡፡
ግድግዳ ላይ መስቀል፣ ከአቅም በላይ ስፖርት በማሰራት እስረኛው ተዝለፍልፎ እንዲወድቅና እንዲሰቃይ ማድረግ፣ ስፖርት በሚሰራበት ወቅት ሳያስበው መትቶ መጣል፣ በገመድ መግረፍ፣ ሁለት ጠረጴዛዎች ላይ “ወፌ ላላ” መስቀል (መገልበጥ)፣ በእንጨት፣ በጥፊ፣ በእርግጫ መደብደብ፣ ስድብና ዛቻ የተለመዱ ናቸው፡፡ የኤሌክትሪክ ንዝረት፣ ጥፍር መንቀል፣ ርቃን መመርመር፣ ብልትን በሴቶች እያስነኩ ማሸማቀቅ፣ የውሃ ኮዳ ማንጠልጠል፣ በሽጉጥ ማስፈራራት፣…ፀያፍ ነገር ማስፈራሪያ ማድረግና የመሳሰሉት የተለመዱ የምርመራ ክፍሎቹ መገለጫዎች ናቸው፡፡
(በጌታቸው ሺፈራው “የሰቆቃ ድምጾች”፤ ሰኔ 2010 ዓ.ም)

Read 1058 times