Saturday, 07 July 2018 10:54

የቄሮ እና ፋኖ ትግል በዳይሌክቲካዊ አተያይ

Written by  አሸናፊ ትርፌ (በአ.አ.ዩ የሶስዮሎጅ የዶክትሬት ተማሪ)
Rate this item
(1 Vote)


    የሳይንሱ አለም በአጠቃላይ አንድን ነገር ለመግለጽ ወይም ደግሞ ለማጥናት የሚጠቀምበት የጋራ የሆነ አካሄድ፣ መርህና ህግጋት ሲኖሩት፣ ከእነዚህ የጋራ ከሆኑት በተጨማሪ አንዱ የሳይንስ ዘርፍ ከሌላው የሚለይበት የራሱ የሆነ፣ የማጥኛና ነገሮችን መግለጫ ዘዴ አለው፡፡
በማህበራዊው ዘርፍ ባሉ የሳይንስ መስኮች ውስጥ ነገሮችን ለመግለጽም ሆነ ለማጥናት በስፋት ከሚያገለግሉት ዘዴዎች አንዱ ዳይሌክቲካዊ አስተሳሰብ ነው፡፡ ዳይሌክቲክስ የሚለው ቃል የተገኘው ከግሪክ ሲሆን ጥሬ ትርጉሙም፤ ሙግትን ወይም መፋለምን ይገልጻል፡፡  ይህን መነሻ በማድረግም የዳይሌክቲካዊ አተያይ መሰረቱና መነሻው ከጥንታዊው የግሪክ ፈላስፋ ሶቅራጠስ ጋር ይገናኛል የሚሉ ጥቂት ምሁራን አሉ፡፡
የዚህ ሀሳብ አራማጆች ሶቅራጠስ ሀሳቡን ለመግለጽ ሲጠቀምበት የነበረውን የሙግትና የውይይት አካሄድ (dialogue) ዳይሌክቲካዊ ነው በማለት ለሀሳባቸው  ማስረጃ ያቀርባሉ፡፡ ከዚህ በተለየ ለአብዛኛው የማህበራዊ ሳይንስ ምሁራን፣ አሁን ያለውን ትርጉምና ጥቅም በያዘ መልኩ የዳይሌክቲካዊ አስተሳሰብን (dialectical thinking) ለሳይንሱ አለም ያስተዋወቀው፤ ጀርመናዊው ፈላስፋ ጆርጅ ሄግል ነው።
ለዚህ ጀርመናዊ ፈላስፋ፤ ሰዎች ለነገሮች ባላቸው አተያይ፣ ልዩነት ያላቸው ሲሆን ይህን ያላቸውን የሀሳብ ልዩነት ሲፈቱ ሌላ ልዩነት ይወለዳል፤ ያም ሲፈታ ሌላ ቅራኔ ይጀምራሉ፡፡  ዳይሌክቲካዊ አስተሳሰብም ይህን የሀሳብ ግጭትና የግጭቱ ውጤት የሆነውን የታሪክ እድገት የሚገልጽና የሚያስረዳ መሳርያ ነው፡፡  የሄግል ተከታይ የነበረው ሉድዌግ ፌርባህ፤ ይህን ሀሳባዊነት፣ ቁሳካላዊነት ገጽታ(Dialectical Materialism) እንዲላበስ አደረገው፡፡ እንደ ፌርባህ አተያይ፤ ዳይሌክቲክስ በሃሳብ ቅራኔዎች ብቻ የሚገታ ሳይሆን በአለም ላይ የምናያቸውን ነገሮች፣ ተፈጥሮንና ክስተቶችን ጨምሮ የምንገልጽበትና የምናጠናበት ዘዴ ነው፡፡
ከሁለቱ ሊቃውንት በኋላ የመጣው እውቁ ካርል ማርክስ፤ የሁለቱን ሰዎች ሀሳብ ቀላቅሎ፣ ታሪክን ለማጥናትና በዘመኑ የነበረውን የወዛደሩንና የቡርዣውን ግጭት ለመግለጽ ተጠቀመበት፡፡
በአጠቃላይ በዲያሌክቲካዊ አተያይ፤ በአለም ላይ በተቃራኒዎች የማይከፋፈል ነገር ወይም ክስተት የለም፡፡ አንድ ነገር የነባሪነትን ህላዌ የሚያገኘው፣ በውስጣዊና ውጫዊ ቅራኔዎቹ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር፤ እያንዳንዱ ነገር  እና ክስተቶች በውስጣቸው ተቃራኒ መልኮች አሏቸው፡፡ የአንድ ዛፍ ሁለት ቅጠሎች እንደማይመሳሰሉት ሁሉ፣ የሰው ልጅ የእጆቹ መዳፍ አሻራዎች ልዩነት አላቸው፡፡ አንዱን የምንረዳው፣ ከሌላው ጋር ባለው ግንኙነት ነው፡፡
በዳይሌክቲክስ መርህ ደግሞ ውስጣዊ ቅራኔዎች፣ ዋነኞቹ የእንቅስቃሴና የለውጥ ምንጭ ናቸው፡፡ ይህን እውነት ኢሊቲስካያ የተባለው ተርጓሚ፣ ከራሽያ ወደ እንግሊዝኛ በተረጎመው “ABC of Dialectical and Historical Materialism” በተባለው መፅሐፉ እንደሚከተለው አስቀምጦታል፤
“Every material or spiritual phenomenon or process is a unity of opposites which inherently belong to it and inseparable. The sources of any object’s movement lies in the interaction (conflict) of opposites which are inherent in it. Therefore, movement is self-movement” (Ilitiskaya, 1978:183).
በተጨማሪም በዳይሌክቲካዊ አጠናን ቀድሞ የተከሰተ ነገር በኋላ ለሚከሰተው ነገር አስተዋፅዖ እንደሚያደርገው ሁሉ፣ በኋላ የመጣውም ለፊተኛው ተመሳሳይ ውለታ ይውላል፡፡ (For dialectical thinker, the causal relationship of phenomena never flows in a single direction. They have a reciprocal relationship than a cause and effect relationship. An antecedent may have effect on the consequent, but the consequent has also effect on the antecedent).
ይህን መነሻ ካደረግን፣ የኢህአዴግ ግንባር ፓርቲዎች፣ የህወሓትን ሀሳብ ያለ ልዩነት ሲያራምዱ የነበሩበት ዘመን፣ ዳይሌክቲካዊ የሆነውን የተፈጥሮ ህግ የሚቃረን ነበር፡፡ ከውጫዊ ቅራኔ ሌላ ውስጣዊ ቅራኔ ያልነበረው ኢህአዴግ፤ ነፍስ የዘራውም ሆነ የነባራዊ ሁናቴ ያገኘው በቅርቡ በውስጡ ያሉት የግንባሩ አባላት (ህወሓት፣ ኦህዴድ፣ ብአዴን እና ደህዴን) ቅራኔ ማሳየት በጀመሩበት ወቅት ነው፡፡ ይህ ውስጣዊ ቅራኔ እንዲፈጠርና ኢህአዴግ ወደ ተፈጥሮ ህግ እንዲመለስ ያደረገው ደግሞ ከቄሮና ፋኖ ጋር የፈጠረው ውጫዊ ቅራኔ ነው፡፡ ማለትም የኢህዴግ አምባገነናዊ አገዛዝና መብት ረገጣ፣  ቄሮንና ፋኖዎችን ፈጠረ፡፡  በግፋዊ አገዛዙ የተፈጠሩት ቄሮና ፋኖዎችም ከብዙ መስዋዕትነት በኋላ፣ በጊዜ ሂደት በኢህአዴግ ላይ ተፅዕኖ ፈጠሩ፡፡ ( An antecedent may have effect on the consequent, but the consequent has also effect on the antecedent)  
በዚህ አተያይ ቄሮና ፋኖ ለኢህአዴግም ባለውለታ ናቸው፡፡ በግምባሩ ውስጥ የሀሳብ ልዩነት እንዲፈጠርና የተፈጠረውም የሃሳብ ልዩነት ወደለየለት መሬት የወረደ ግጭት እንዲገቡ ያደረገ ነው፡፡ በተጨማሪም አሁን  እየታዩ ያሉት ለውጦችና ተስፋዎች መሰረታቸው የተጣለው፣ በቄሮና ፋኖዎች ጥቁር ደም ጠብታ ነው። (እና ክብር ይገባቸዋል)
በዳይሌክቲክሳዊ  መርህ፤  እውነተኛ ለውጥ ከተፈለገ፣ ቅራኔዎች በአንደኛው ወገን አሸናፊነት መደምደም አለባቸው፡፡ የሀይል ሚዛኑን መጠበቅና (equilibrium) ማቆየትም የለውጡን ጊዜ ከማዘግየት ባሻገር ወደ ኋላ ሊመልሰው ይችላል፡፡ ሲጀምር፤ በተቃራኒዎች መካከል የሀይል ተመጣጣኝነት (ጉልቤነት) ካለ፣ ሰላምም ሆነ ለውጥ የለም፡፡ ስለዚህ ተመጣጣኝነት የሚኖረው ለአጭር ጊዜ ነው፡፡ አንዱ መሸነፍና ማሳመን አለበት፡፡ “Opposites can attain only partial, relative equilibrium, and that only for a time; they can never become balanced completely” (Ilituskaya, 1978:183).
በመሆኑም አሁን ባለንበት ሰዓት፣ የኦህዴድ (ብአዴን በቲፎዞነት ያለው ሚና ሳይረሳ) ሀይሉ ጨምሮ፣ የህወሓት ደግሞ ቁልቁል ወርዷል፡፡ ነገር ግን “አሁንም ሀገሪቱ በእኔ እጅ ነች፤ የምመራትም እኔው ነኝ” ለማለት የሚደረጉ ነገሮች አሉ፡፡ በሌላ አነጋገር፤ ህወሓት እና ኦህዴድ (ከእነ ደጋፊዎቹ) በቅራኔ ተፋጠዋል፡፡  በመሃላቸው ያለው ቅራኔ ደግሞ ተመሳሳይ ዕይታ ባላቸው ወዳጃዊ ፓርቲዎች /የአንድ ግምባር አባላት/ ላይ የሚታይ ቅራኔ አይደለም፡፡ በጓዳዊ ትችትና መተራረም የማይመለስ ነው፡፡
የተጀመሩት ለውጦች ቀጣይነት እንዲኖራቸው፣ ተስፋችንም ድርግም እንዳይልና ለራሱም ቀጣይ ህልውና ሲል፣ ኢህአዴግ በውስጡ የተፈጠረውን ቅራኔ በኦህዴድ እና ቲፎዞዎቹ የበላይነት ማጠናቀቅ አለበት፡፡ ኦህዴድ ህወሓትን መዘረርና ማሳመን አለበት፡፡ ህወሓትም ሽንፈቱን አምኖ መቀበል አለበት። ካልሆነ ሁለት “ጉልቤ” ወጣቶች፣ አንዱ ሙሉ በሙሉ እስኪያሸንፍ ድረስ ሰፈር እንደሚረበሸው ወይም ሁለት “ጉልቤ ወይፈኖች” ባሉበት ከብቶች ተረጋግተው ሳር እንደማይግጡት ሁሉ፣ ሁለቱ ሀይሎች ተፋጠው፣ ሀገር ሰላም አትሆንም፤ የምንመኘው ለውጥም አይታሰብም። ህወሀት ሽንፈቱን አምኖ የማይቀበል ከሆነ (እንዳያያዙ አያደርገውም) ኦህዴድ ከሌሎቹ ጋር በመሆን መቀጠል ይችላል፡፡ ደግሞም አሁን በሚያሳየው አቋምና በሚመራበት የፍቅርና የአንድነት መርህ፣ ኦህዴድ እራሱን ወደ ሀገራዊ ፓርቲነት ቢያሳድግም ያዋጣዋል፤ ከክልሉ ውጭም የህዝብ ቅቡልነት (legitimacy) ሊያገኝ እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ ህውሓት ራሱን ዕጣፈንታ መወሰን ግን አለበት - ወይ መደመር ወይ መቀነስ!

Read 1358 times Last modified on Saturday, 07 July 2018 11:42