Saturday, 07 July 2018 10:52

ፍቅር አይጠላም፤ ፍቅር አይገፋም

Written by  ከዳግላስ ጴጥሮስ
Rate this item
(5 votes)


     “--በፍቅር አዋጁ ላይ ፊታችሁና ልባችሁ የጠቆረ፣ የይቅርታና የምህረት አዋጁ የጓጎጣችሁ፣ የመደመሩ ፍልስፍና ያጥወለወላችሁ፣
የፈካችው የሀገራችን ፀሐይ ሙቀት የበረዳችሁ፣ የሙስናው በር ሊዘጋባችሁ ገርበብ ያለባችሁ ወገኖቼ ሆይ! ፍቅር አይጠላም፤ ፍቅር አይገፋም፡፡ መፍትሔው ተፀፅቶ፣ ንስሃ መግባትና እጅንም አመልንም መሰብሰብ ነው፡፡--”
 
   የዛሬን ዕውነታ ትናንት እና ከትናንት ወዲያ ከተፈፀሙ ክስተቶችና ድርጊቶች ጋር እያነፃፀሩና እያወዳደሩ “እንዲህ መሆን አልነበረበትም ነበር፤ እንዲህ ቢሆን ኖሮ” እያሉ ብያኔ መስጠት ተገቢ አይደለም። የአንድ ዘመን ድርጊት የሚዳኘው በዚያው በራሱ ጀንበር፣ በዚያው በራሱ ዐውድ ነውና፡፡  “ክፉውንም ሆነ ደጉን” የኋላ ታሪክ እያጣቀሱ ለማመሳከሪያነት መጠቀም ግን በፍፁም የተከለከለ ነው ማለት ግን አይደለም፡፡
“ትናንት እንዲህ አልነበራችሁም፤ ዛሬ ዕልል ልትሉ ይገባል” ብሎ መሟገትና መከራከር የልጅነትን ዕድሜ ድርጊት ከጉልምስና “በሳል” እድሜ ድርጊት ጋር የማነፃፀር ያህል ርቀቱ የትየለሌ ነው፡፡ ቢቻልና ቢሆንማ “ከሀገራዊ ታሪካችን መሰዊያ ላይ አመዱን ሳይሆን ፍሙን ብንጭር” ቀዳሚዎቹን ክፉ ትውስታዎቻችንን፣ አንድም ለበጎ ብርሃን ምንጭነት፣ አለያም የዛሬውን አስቆዛሚና ዕርባና ቢስ፣ ሀገራዊ ክስተቶቻችንን ለማስወገጃነት ብናውለው መልካም በሆነ ነበር፡፡
አለመታደል በሉት ወይንም ሌላ፣ የቀዳሚዎቹ የሀገራችን ፖለቲከኞችና መሪዎቻችን፣ የፍልስፍና ቅኝት የተቀመረው “በለው፣ ግረፈው፣ አሰቃየው፣ የሞቱን ዋንጫ አስጨብጠው ወዘተ.” በሚሉ የግፍ ኖታዎችና የዜማ ስልቶች ነበር፡፡ የዘመነ ፊውዳሉን በርካታ መጠላለፎችና መጠፋፋት በተመለከተ ዳግም እየጎረጎርኩ መተረኩ “እጅ እጅ እንዳለ ምግብ ስለሚያቅር” የአንባቢዬን ስሜት በብዕሬ ማጠልሸት አልፈልግም፡፡ አመድ ነዋ! ዘመነ ደርግም ቢሆን ፊቱንና መላ ሰውነቱን ሲለቃለቅ የባጀው በንፁሃን የወገኖቼ ደም ስለነበር የእርሱንም ዕኩይ የግፍ ዜና መዋዕል በዝርዝር እየነቀስኩ ማስታወሱ፣ የብዙዎችን የህሊና ቁስል መደነቋቆል እንዳይሆን፤ “ሆድ ይፍጀው፤ ታሪክ ያቆየው” ብሎ ማለፉ ይመረጣል፡፡ ይህም ቢሆን አመድ ነዋ!
ከላይ በመልከ ጥፉነት የጠቃቀስኳቸው በነበር የሚዘከሩት የሀገራችን ሥርዓቶች፣ አንዳችም መልካም ተግባር አልነበራቸውም ማለት እንዳልሆነ ግን ማረጋገጥ እወዳለሁ፡፡ ይህንን ባልመሰክር፣ ከራስ ህሊናም ጋር ሆነ ከታሪክ ጋር መጋጨት ይሆናል፡፡ የቀዳሚ ሥርዓቶች መታወቂያ የሆነውንና የከፋውን ታሪካቸውን እሾህ እየነቀስን እውነታውን ገለጥለጥ አድርገን ብንፈትሽ፣ ክፉ ብለን በምንፈርጃቸው ሥርዓቶች ውስጥም እንኳ ቢሆን “መልካም” የሚሰኙ በርካታ ሀገራዊ ትሩፋቶች እንደተመዘገቡ በፍፁም አይዘነጋም፡፡ የሀገራችንን ዱር በቀል የበለስ ፍሬ ለማነፃፀሪያነት ማስታወስ ይቻላል፡፡ የበለስ ፍሬ መላ ሰውነቱ በእሾህ የተሸፈነ ነው፡፡ ተፈጥሮ እሾህ ያለበሰችውን ይህንን የበለስ ፍሬ ለመብላት፣ በቅድሚያ በእግር በማሸትም ይሁን በስለት መሳሪያ እሾሁን ማስወገድ የግድ ይላል፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ጣፋጩን ፍሬ መግመጥ የሚቻለው፡፡ ያለፈ ታሪክም እንደ በለስ ፍሬ ምንም እንኳ በተዋጊ እሾህ የታጠረ ቢሆንም፣ እሾሁን ለማረገፍ ትዕግስት የተላበሰ ሰው፣ ልብ ቢሰጠውና ልብ ቢል፣ ብዙ መልካም ነገሮችን ማስታወስ ይቻላል፡፡
በዘመነ ኢህአዴግም ቢሆን “ተሠርተዋል፣ ተከናውነዋል፣ ሕዝባችንንና ዓለምን አስደንቀዋል ወዘተ.” እየተባሉ በቁጥር ከሚሽሞነሞኑት ሀገራዊ ትሩፋቶች በስተጀርባ፣ በሀዘን ከል ያስለበሱን፣ የሕዝብን ስሜት የኮሰኮሱና ጉዳተኛ ያደረጉን በርካታ ኢ-ሰብዓዊ እና ኢ-ፍትሐዊ ድርጊቶች መፈፀማቸውን የምንመሰክረው እኛ “ተራ ተብዬ የሕዝብ ጀማዎች” ብቻ ሳንሆን፣ በትረ ሥልጣኑን የጨበጡት ጎምቱ ፖለቲከኞቻችንና መሪዎቻችን ጭምር ስለተፈፀሙትና እየተፈፀሙ ስላሉት ክፉ ድርጊቶች ንስሃ በመግባት፣ እኛንም “ፈጣሪንም” በየአደባባዮቻችንና በየሚዲያው ማሩን ብለው ተማፅነውናል፡፡ እኔን መሰሉ “ተራ ሕዝብም” መቼስ ከልባቸው ይቅርታ ብለው ከሆነ፣ ምህረት ቢሰጣቸው ምናለ ብለን በአደባባይና በየጓዳችን የውይይት ርዕስ መክፈታችን አልቀረም፡፡
ሀገሬ በእንዲህ ዓይነቱ “ግማሽ ልጩ፤ ግማሽ ጎፈሬ” በሆነ ታሪካዊ ወቅት ላይ እያለች ነው፣ የፍቅር፣ የምህረትና የመደመር ዐዋጅ ነጋሪ፣ አብሪ ኮከብ፣ በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ብልጭ ያለው፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዶ/ር ዐብይ አህመድ፣ የሥልጣናቸውን መወጣጫ መሰላል በማነፅ ላይ ያሉት፣ “የፍቅር፣ የምህረት፣ የይቅርታ፣ የመደመር፣ የልብ ስፋት፣ የሕዝብ አክብሮት፣ የመደማመጥና የትህትና ወዘተ.” መሰል ርብራቦችን በመሰደርና በመተግበር ነው፡፡
የማከብራቸውን የኮሌጅ መምህሬን የዶ/ር ኃይሉ አርአያን አንዲት ግጥም ጥቂት አንጓዎች ጠቅሼ፣ ስዕላዊ ምስል በመፍጠር ሃሳቤን ላብራራ፡፡ ግጥሟን ለእኛ ለተማሪዎቻቸው፣ በክፍል ውስጥ ካነበቡልን ከሦስት ዐሠርት ተኩል ዓመታት በላይ ስለሆነ፣ ስንኞቹን ባወነጋግር፣ ይቅርታ ይደረግልኝ፡፡
እኔስ መስሎኝ ነበር ዘመድ የሞተባት፣
የእናት ሞት፣ የአባት ሞት፣ የልጅ ሞት ያጠቃት፣
ፊቷን ያጠቆረው ከልን ያስለበሳት፣
ለካ እርሷስ ኖራለች ዘመን የሞተባት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትራችን የሥልጣናቸውን ዘመነ ቆይታ ያስተዋወቁን በአጭር አገላለፅ፣ “ዘመን ሊሞትባትና ከል ልትለብስ ዳር ዳር የምትለውን” ሀገራችንን ለመታደግና ሰቅዞ የያዛትን የሙስና እባጭ ንፍፊት፣ ለብዙሃን ጉስቁልና፣ ለጥቂቶች ግን ብልጽግና ምክንያት የሆነውን ጥቁር የብሶት ከል ልብሷን ገፎ ወዲያ ለመጣል እጥራለሁ፣ አንገቷ ቀና እንዲልም እየሠራሁ፣ በማሠራት እደግፋታለሁ የሚል ማረጋገጫ በመስጠት ነበር፡፡
በታሪካችን ውስጥ ልጆቻችን እያፈሩ አንገት ደፍተው የሚተርኩት የዛሬው እንደ ጀግንነት የሚታመነው የጠራራ ፀሐይ ሙስናና ዝርፊያ፣ ያፈጠጠው አድልዎና እንደ ፀጋ የሚመኩበት ድርጊት፣ በየጉዳንጉዱ እየተፈፀሙ ያለት ኢ-ሰብዓዊ ተግባራት፣ ወደ ፀባዖት የደረሰው የሕዝብ ጩኸትና እዮታ፣ ጎሰኝነት አቆጥቁጦ፣ እንደ አድባር ዛፍ በማደግ፣ ሥር የሰደደበት ሁኔታ፣ የኑሮው ውድነት እንደ አፖሎ አሥራ አንድ እያስደነቀ ወደ ሰማይ የተምዘገዘገበት ወቅት፣ጥቂት ግለሰቦች በጥረት ሳይሆን በጠራራ ፀሐይ በዘረፉት ሀብት መሣፍንት የሆኑበት ዘመን ይጠቀስ ከተባለ፣ የእኛ ዘመን ምስክሮች ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት “እውነቱን ስለምንናገር፣ እኛን ግዑዛኑን አድምጡን” በማለት ለዋቢነት መሽቀዳደማቸው አይቀርም፡፡
እኒህን መሰል ድርጊቶች ናቸው ሀገሬን ጥቁር ከል ያለበሷት፣ የሕዝብ ቁጣ ጎምርቶ ፍሬ እንዲያፈራ መደላድሉን የፈጠረው፤ የንዴቱ ወላፈን ዳር እስከ ዳር፣ እንደ ወላፈን ተቀጣጥሎ፣ “አንገፈገፈን” የሚለው ድምፅ ሊሰማ የቻለው፤ ጠቅላይ ሚኒስትራችንም ገሀድ ተገልጠው፣ እንዲወለዱ ሰበብና ምክንያት የሆነው፡፡ “ግረፈው፣ አሳደው፣ እሠረው፣ አስወግደው!”  የሚል አዋጅ ሲያስነግር የኖረው መንበረ ሥልጣን፤ “ይውደም፣ በለው፣ አትማረው!” እየተባለ የጥፋት መፈክር ሲፈከርባቸው በነበሩት የሀገራችን አደባባዮች፣ ዛሬ ጥቁሩ ደመና ተገፎ፣ ፍቅር ሲርከፈከፍበት፣ የምህረትና የይቅርታ መልእክት ሲሰበክበት፣ መደመር ሲዜምበትና ትህትና ሲስተዋልበት ምንኛ ያስደስት፣ ምንኛስ ያኮራ?
ይህንን መሰሉ የፍቅር ዜማ የሚያጥወለውላቸው፣ የመደመሩ ፍልስፍና የሚኮሰኩሳቸው፣ የይቅርታው አዋጅ የሚጠዘጥዛቸው ጥቂት ወገኖቼ ሲወራጩ.፣ መመልከት፣ ከሆቸጉድ ያለፈ ግርምት ያጭራል፡፡ በበቀልና በቂም ሰንኮፍ ተለክፈውም በንቀትና በዛቻ ታጅበው፣ እየተፈወሰ ያለው የሀገሬ ደመና፣ እንደ ትናንት ከትናንት ወዲያው፣ የአሲድ ዝናብ እንዲያዘንብ ተግተው መወራጨታቸው፣ ከማስተዛዘብ የላቀ ስሜት ያሰርጻል፡፡
ፍቅር ይፈውሳል፣ ምህረት ጥላቻን ይገፋል። ይቅር ባይነት፣ የውስጥና የውጭ ሰላም ይሰጣል እንጂ እንደ ዕንቆቆ እየመረረ አያንገሸግሽም፡፡ “አከሌ በደለኛ ነበር - አዎን ሊሆን ይችላል፤ የከፋ ጥፋትም ፈጽሞ ነበር - በርግጥም ሊሆን ይችላል፤ በርግጥም ድርጊቱ ምህረትና ይቅርታ ላያሰጠውም ይችል ነበር - አዎን የሕግ አንቀፅ ተጠቅሶለት እንጦሮጦስ ማውረድ ይቻል ይሆናል፡፡” ግን ቢሆንስ --- ፍቅር ከእነዚህ ጭጋጎች የበለጠ አይበረታምን? እጅ ከፍንጅ የተያዘ አጥፊ እንኳ ቢሆን “ድርጊትህ ትክክል አልነበረም፤ ሊያስቀጣህም ሊያስተምርህም እንደሚገባ፣ የፍትህ አካሄዱ፣ እግር በእግር እየተከታተለህ፣ የሕግ አናቅፅ ሰድሮልህ እየተጠባበቀህ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ስህተትህን እንደማትደግም፣ በማመንና ዘመኑ የፍቅር አዋጅ የታወጀበት ስለሆነ፣ የወንጀለኛ ሕጉ ታጥፎ ምህረት ታውጆልሃል” መባሉ ከሰንሰለት የበረታ የፍቅር ቅጣት ሊሆን አይችልምን፡፡
ስለዚህም በፍቅር አዋጁ ላይ ፊታችሁና ልባችሁ የጠቆረ፣ የይቅርታና የምህረት አዋጁ የጓጎጣችሁ፣ የመደመሩ ፍልስፍና ያጥወለወላችሁ፣ የፈካችው የሀገራችን ፀሐይ ሙቀት የበረዳችሁ፣ የሙስናው በር ሊዘጋባችሁ ገርበብ ያለባችሁ ወገኖቼ ሆይ! ፍቅር አይጠላም፤ ፍቅር አይገፋም፡፡ መፍትሔው ተፀፅቶ፣ ንስሃ መግባትና እጅንም አመልንም መሰብሰብ ነው፡፡
የቅዱስ መጽሐፉ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ፣ በአንድ ወቅት መምህራቸውን ክርስቶስን አንድ ጥያቄ ጠይቆት ነበር፡፡ እንዲህ በማለት፤ “ወንድሜ ቢበድለኝ ሰባት ጊዜ ይቅር ልበለውን?” የክርስቶስ ድንቅ መልስ፣ ለሀገራችን የወቅቱ ሁኔታ ቢጠቀስ ዐውዱ ይገጥም ይመስለኛል። እንዲህ ነበር የመለሰለት፤ “ጴጥሮስ ሆይ! ሰባት ጊዜ አልልህም፣ ሰባት ጊዜ ሰባ እንጂ!” ይገርማል! ለበደለኛ ሰው ፣ሰባት ጊዜ ሰባ፣ አራት መቶ ዘጠና ጊዜ ይቅርታና ምህረት ሊደረግለት? አዎን!!
 ጠቅላይ ሚኒስትራችን ሆይ! ለአንድ በደለኛ አምስት መቶ ጊዜም ቢሆን ይቅርታ ማድረግን አያጓድሉ። ፍቅር ርቦን ነበር፡፡ የሰላም አዋጅ ናፍቆን ነበር፡፡ እርግማንና ትዕቢት ሰልችቶንም አማሮንም ነበር፡፡ ትምክህት አንገፍግፎን ነበር፡፡ “በመቃብራችን ላይ . . .
“የሚለው አጉል መሃላ፣ አንገት አስደፍቶን ነበር። የትናንቱን ትርዒት መመልከቱ፣ ከዛሬው እውነታ ጋርም መጋጨቱ አስተዛዝቦን ነበር፡፡ የጎሰኝነቱ ድርጊት ውጦን ነበር፡፡ የዘረፋው ጉዳይ ተስፋ አስቆርጦን ነበር። ስለዚህም ሀገራችንንና ሕዝባችንን የሚፈውሰው፣ ምህረትና ይቅርታ ብቻ መሆኑ ገብቶናል፡፡ በዓላማዎት ጠንክረው ይቀጥሉ፡፡ አረቦቹ ተረተኞች እንዲህ ይላሉ፤ “ውሾች ይጮሃሉ፤ ግመሎችም ይጓጓዛሉ” መልካም አባባል ነው፡፡
ሰላም!

Read 4600 times