Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Sunday, 06 May 2012 15:32

ጊዜ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የሌሊቱ ጸጥታ የነፍስን አጥንት ይሰረስር ይመስላል።ብርዱ የዋዛ አይደለም።ከሰዓታት በፊት ስስ ካፊያ ነበር። ከቤቱ ክዳን አሸንዳ የታቆረ የጠፈጠፍ አንኳር ከታዛው ሥር ባለው ጉርድ ጣሳ ውስጥ ‘ጧ! ጧ!’ እያለ ይንከባለላል። የግድግዳው ሠዓት ‘ቀጭ! ቀጭ!’ እያለ ከጠፈጠፉ የጣሳ ድምፅ ጋር አብሯል። ሌሊቱ ይፈጥናል።“ልክ የዛሬ ሳምንት የኢትዮጵያውያን ምዕተ-ዓመት ነው!” አልኩ ለራሴ።“የጊዜ ወሰን የጊዜ ገደብ ከጥጉ ደረሰ። አሁን ደግሞ ሌላ የጊዜ ወሰን ሌላ የጊዜ ገደብ ተቆጥሮ ሊሰጠን ነው።” አልኩ ለራሴ። ሌላ ዕድሜ! ሌላ ዓመት…ሌላ እየተተካካ የሚሔድ ምዕተ-ዓመት፤የትውልድ ዕድሜ፤የታሪክ ዕድሜ፤የግለሰብ ዕድሜ፤የአገር ዕድሜ፤የዕድሜ ዕድሜ…ደነገጥኩ።

የጊዜን ወሰን ጀምሮ መጨረስ የዋዛ ሆኗል። ካጎነበሱበት ቀና ሲሉ “አበባዬ ሆይ!” ነው።የጊዜን ሰረገላ ላንድ አፍታ ልጓሙን ስቤ ጊዜን ፊት ለፊት እያየሁት አንዳች ልጠይቀው አማረኝ።“ጊዜ ሆይ ባንተ ላይ የሰለጠነ፤ያንተን አቅም የፈተነ፤…አንተን የረታ ማነው?” ልለው።ከፈገግታ በቀር ጊዜ መልስ የለውም። ጥያቄው በሚነሳበት ቦታ ሁሉ ብርሐን ከጨለማ ሳይለይ ጊዜ ምላሹ ፈገግታ ብቻ ነው- ፈገግታ።“ለምን?” ብሎ ከመጠየቅ የላቀ ጊዜን ሊያስፈግግ የሚችል ምናለ? “ለምን?” ብሎ መጠየቅ የመልስ ግማሽ ነው። “ለምን?” ብሎ ጠይቆ ከጊዜ ላይ ፈገግታን ያገኘ የፈገግታውን እማሬያዊና ፍካሬያዊ ገጽ ይለይ እንጅ መልሱ ቅርቡ ነው።

ጊዜን የረታ ማነው? አንስታይን? ኒቼ? ኒውተን? ኤዲሰን? ዘርዓ ያዕቆብ? ቡድሓ? ባሓኡላህ?-ማን?

እኮ ማን? ማነው የረታው? እግዜር ራሱ? እንዴት አድርጎ? “እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን ፈጠረ። ምድር ባዶ ነበረች አንዳችም አልነበረባትም።…” ቃሉ ይህን ይላል። ከጊዜ በፊት ተግባር ነበረ። ሥራ ነበረ። ከሥራ በፊት ግን ምንም።ሰማይና ምድር በይሁንታ፣

በምኞትና ፈቃድ ብቻ አልመጡም። አማኒያኑ ከወዴት አምጥተው ይሆን የሚናገሩት? የብርሃንና የጨለማ ፈረቃ የሆነው ጊዜ የሚሉት ጉድ ብቻ ነው በመሻት የመጣ። “...ብርሃን ይሁን አለ ብርሃንም ሆነ-ብርሃኑም መልካም እንደሆነ አየ። ብርሃኑን ‘ቀን!’ ብሎ ጠራው ጨለማውንም ‘ሌሊት!’።” ከዚያ ወዲያ ‘ፈጠረ፣ አደረገ፣ ሠራ!...’ ይከተላሉ።እጅግ ጥቂት መሻት እጅግ ብዙ ተግባርና ሥራ። እግዚአብሔር በመመኘቱና በመሻቱ የመጣለትን ጊዜ የሚሉት ነገር ሊረታ ፈለገ። እናም ምሥሉን ምናልባትም በሁሉም ነገሩ እርሱን የሚመስል ‘ሰው!’ የተባለ ፍጡር ሠራ። ይሔ ሰው የተባለ ፍጡር እጅግ ሞጋችና አታካች ሥራው ሊሆን እንደሚችል መጠርጠር ይቻላል። እናም ሕያው ሊያደርገው እስትንፋሱን እፍ አለበት። ሌላ መሻት፤ ሌላ ፈጠራ፤ ሌላ ፍለጋ የሞላበትሰው ይሉት ሕያው ፍጡር ዕውን ሆነ።፫አዳም  “ለምን?” ብሎ ጠየቀ። “እኮ! መከልከል ለምን?” አለ። እግዚአብሔር የአዳም ሕያው ነፍስ ትርጉም እንደአላት አወቀ። ያደረገው ሁሉ ልክ ነበር - ደስም አለው። አዳም አቅሙን ይፈትን ዘንድ

 

ማሰነ። አዳም ጊዜን ይረታ ዘንድ ተነሳ። ጊዜን ሊቀድም ፈጠነ።

የሰናዖር ሰቀላ፤ የባቢሎን ደርብ፤ የቻይና ግንብ፤ የግብፅ ፒራሚድ፤ የሰሎሞን ቤተ- መቅደስ፤ የናቡከደነፆር ሕንፃ፤ የአክሱም ሐውልት፤ የላሊበላ ቤተ-ክርስቲያን፤የሆሜር ኦዲሴ፤ የሔሮዶቱስ ትረካ፤ የሶፎክሊስ ተውኔት፤…ሰው ጊዜን ሊያሸንፍ የወረወራቸው ቀስቶች። የዘመን አድማሳትን

አልፈው ዛሬ ድረስ መጡ…ወደ ነገም ሔዱ…መጨረሻ  ወደሌለው ነገ። እግዚአብሔር ደስ አለው። በሰው በኩል ጊዜን መርታቱ አኮራው።ኒቼ ተነሳ “እግዚአብሔር ሞቷል!” አለን። እንደ በረዶ ቀዝቅዘው እንደ አለት የበደኑትን ከሥራቸው ሊነቀንቃቸው ያለው እንጅ ዛራቱስትራን ያህል ግዙፍና ለፈጣሪ የታመነ ሥራ ሠርቶ የተከሰተበትን ጊዜ ሊያሸንፍ የተጋው ፍሬዴሪክ ኒቼ ዕውን ይህን ከልቡ ያለው አልመሰለኝም። የሆነ ሆኖ ነገራቸውን ሁሉ በፈጣሪ ላይ ጥለው በጊዜ ተሸንፈው ለጊዜ እጃቸውን የሰጡ ሁሉ በኒቼ አዲስ ወሬ ደነገጡ።

“አንድዬ ያውቃል!” እያሉ መጠየቅን ሁሉ ሲያመክኑ የኖሩ ሁሉ በቀትር ብርድ ተንዘፈዘፉ።  ጭንቅላታቸውን በጥቁር ጨርቅ ከፍነው ነገራቸውን ሁሉ መሥቀሉ ሥር የጣሉ ሁሉ ተንቀጠቀጡ። በኒቼ ላይ የእሳት ለበቅ ሰበቁ ቢሆንም የሚበዙቱ ከቀን እንቅልፋቸው ባንነዋል።

ከጊዜ ጋር ግብግብ ገጥሞ ከድሉ ሠገነት ላይ የወጣው ሶቅራጥስ አማልክት የሚችሉትና የማይችሉት ያለውን በድፍረት ቢናገር የግሪክ ወጣቶችን ሥነ-ምግባር የደመጠጠ ከሓዲ ተብሎ ሆምሎክ ተጋተ። በሶቅራጥስ የጊዜ ድል ፈጣሪ ፈገግ አለ። የግሪክ ቤተ መቅደስ ካህናት በጊዜ ተሸነፉ። ሶቅራጥስ ግን ጊዜን ረትቶ ዛሬም መካከላችን አለ።

ከጣሪያ ክዳን አሸንዳ የታቆረ የዝናብ ጠብታ አንኳር ከታዛው ሥር ባለው ጉርድ ጣሳ ውስጥ ይንጧጧል። የቤቱ ግድግዳ ሠዓትም አብሮት “ቀጭ! ቀጭ!” ይላል። የድምፆቹ ኅብር አንዳንዴ መሳ ይገጥማል ሌላ ጊዜ ይፋለሳል። ሌሊቱ ይፈጥናል። ልክ የዛሬ ሳምንት የኢትዮጵያውያን  ምዕተ-ዓመት አንድ ብሎ ይጀምራል። መስከረም አንድ ሁለት ሺህ ዓመተ ምህረት! አክሱም ዘመን የጊዜ ድል ድልድይ ከተሰበረ የት የለሌ ዓመታት፤ የላሊበላ ቤተ መቅደስ እንዴት ነበር የተሠራው? ዛጉዌዎች እንዴት ነበር ጊዜን ያንበረከኩት? ኧረ እኔ እንጃላቸውሥ ጊዜስ እንዴት

 

ይሆን ያንበረከካቸው? የቱስ ስሌት ላይ ይሆን የሳቱት?

ደረቅ አቁማዳ፤ ክው ያለ ጮጮ፤ ጊዜ ያሸነፈው አድባር፤ ‘ለምን?’ አልኩ ለራሴ። “ብርሃን ይሁን አለ። ብርሃኑን ቀን ብሎ ጠራው፤ ጨለማውን ደግሞ ሌሊት።” ይህ ሁሉ አላረካውም፤ ሰማይንና ምድርን ፈጠረ፣ ሠራ፣አደረገ…። ጊዜ በእኛ በኢትዮጵያውያን ሲሸነፍ ለማየት!! ጓጓሁ።

ነሐሴ 1999 ዓ.ም

 

 

Read 3304 times Last modified on Sunday, 06 May 2012 15:41