Saturday, 07 July 2018 10:40

በጌድኦ እና ጉጂ ዞን ግጭት የተፈናቀሉ ዜጎች ከ8 መቶ ሺህ ይልቃሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

  118 ሚሊዮን ዶላር አስቸኳይ እርዳታ ያስፈልጋል

    በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን እና በደቡብ ክልል ጌድኦ ዞን በተፈጠረ ግጭት የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር 818 ሺ 250 (ስምንት መቶ አስራ ስምንት ሺህ ሁለት መቶ ሃምሳ) መድረሡን የገለፀው የተባበሩት መንግስታት የሠብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ፤ ለተፈናቃዮች የእለት እርዳታ 118 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ብሏል፡፡
ተፈናቃዮቹ በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያና በደቡብ ክልል የተለያዩ ወረዳዎች ተበትነው እንደሚገኙ የጠቀሰው ተቋሙ፤ በፌደራል መንግስቱ ለጉዳዩ የተሠጠው ትኩረት አነስተኛ መሆኑን ተከትሎ፣ ዜጎች ላይ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ ስጋት አለኝ ብሏል፡፡ አብዛኞቹ ሴቶችና ህፃናት መሆናቸው የተጠቆመ ሲሆን የተላላፊ በሽታ ወረርሽኝ ሊከሰት አስታውቋል-የተባበሩት መንግስታት የሠብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ፡፡
አሁን በአካባቢው ግጭቶች የቆሙ ቢሆንም፣ ለዜጎች ተጨማሪ ስጋት የሆኑ ውጥረቶችና አለመረጋጋቶች መኖራቸውንም ተቋሙ አስገንዝቧል፡፡
የአካባቢው ባለስልጣናትና ጥቂት ግለሠቦች የፈጠሩት ነው በተባለው በዚህ ግጭት ከተፈናቀሉ መካከል 642,152 ያህሉ በደቡብ ክልል ጌድኦ ዞን በሚገኙ ሠባት ወረዳዎች በተዘጋጁ ጊዜያዊ መጠለያዎች ይገኛሉ፡፡ በደቡብ ክልል ጌድኦ ዞን በቡሬ ወረዳ 38,459 ተፈናቃዮች፣ በዲላ ዙሪያ 12,751፣ በገደብ ውረዳ 306,572፤ በኮቸሬ ወረዳ 82,423፣ በመናጎ ወረዳ 32, 784፣ በይርጋ ጨፌ 106,832 እንዲሁም በዲላ ከተማ 62,511 ተፈናቃዮች በጊዜያዊ ማቆያ ተጠልለው ይገኛሉ፡፡
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉዲ ደግሞ በጠቅላላው 176,098 (አንድ መቶ ሠባ ስድስት ሺህ ዘጠና ስምንት) ተፈናቃዮች በስድስት ወረዳዎች ተጠልለው ይገኛሉ፡፡ በአባያ ወረዳ 9,377፣ በበርቢርሣ ከጆዋ ወረዳ 9,767፤ በቡሌ ሆራ 15,330፣ በገላና 43,224፣ በሃምቤላ ዋሜና 29,086 እንዲሁም በቀርጫ 69,264 ተፈናቃዮች በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ ይገኛሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት ተፈናቃዮች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ይፈልጋሉ ያለው የመንግስታቱ ድርጅት፤ አብዛኞቹ ህፃናትና ሴቶች የሚተኙበት ፍራሽና የሚለብሡት ብርድ ልብስ የላቸውም፣ ባዶ ቀዝቃዛ መሬት ላይ እየተኙ ነው ብሏል፡፡

Read 7397 times