Print this page
Sunday, 01 July 2018 00:00

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(4 votes)

  “ሰውን ማሸነፍ የሚቻለው በኃይል ሳይሆን በፍቅር ብቻ ነው”
        
   ሰውየው ‹ግራ የተጋባ ነገር› ነው፡፡ ትንሽ ሲቀማምስ ያዙኝ ልቀቁኝ የሚያበዛ፡፡ አንድ ቀን ለአደን ወጣ። ራቅ ወዳለ ቦታ፡፡ ‹ኮሽ› ባለበት ሁሉ መተኮስ ጀመረ። … በሰማይ በሚበሩ አእዋፍ እንኳ ሳይቀር፡፡ ብዙም ሳይቆይ ጠጠሮቹ አለቁበት፡፡ አጋጣሚ ጣለበትና ደግሞ አንድ ትልቅ አውሬ ከጥሻው ውስጥ ብቅ አለ። እየተካለበ መሮጥ ጀመረ፡፡ ሮጦ፣ ሮጦ ዞር ሲል፣ አውሬው የተከተለው ይመስለዋል፡፡ ፍጥነቱን ይጨምራል፡፡ መንገድ አልነበረምና ተደናቀፈ፡፡ ክፉኛ ወደቀናም ሞተ፡፡ እንደ ሞተ ከእግዜር ጋር ተገናኙ፡-
“ምን በደልኩህ ጌታዬ?” ሲል ጠየቀው፡፡
“ሰው ሆኖ የማይበድል አለን?”
“ማለቴ .. እንዲህ ድፍት ስል ምነው ዝም አልከኝ?”
“ያ ሁሉ ሩጫ የት ለመድረስ እንደነበር ገርሞኝ ነው”
“አውሬ እንዳይበላኝ ስሸሽ ነበር፡፡”
“ምን አይነት አውሬ?”
“አንበሳ ወይ ነብር ሊሆን ይችላል፡፡ በደመ-ነፍስ ስተኩስ ስለነበር ሳላቆስለው አልቀርም፡፡ … እየተጎተተ ነበር የሚመጣው፡፡” አለ ሰውየው፡፡
እግዜርም፡- “ሰዎች ስትባሉ አስቸጋሪዎች ናችሁ። ሳይመጡባችሁ የምትሄዱ፣ ሳይነኳችሁ ጠብ የምትፈልጉ፡፡ ያየሃት አውሬ ነፍሰ-ጡር ነበር ነበረች። በግድ ነበር የምትራመደው፡፡ የምትወልድበት ቦታ ፍለጋ፡፡ አንተ የሞትከው በራስህ ሃሳብ ተጠልፈህ፣ ራስህን በራስህ ስታሳድድ ነው፡፡” ብሎ ተቆጣው፡፡ ፡
ሰውየውም፡- “እባክህ ይቅርታ አድርግልኝ፡፡ እንደገና የመኖር ዕድል ስጠኝ፡፡ ከአሁን በኋላ ማንንም አልበድልም” ሲል ለመነው፡፡
“እሽ ይሁንልህ” ብሎት … እግዜር ወደ ጉዳዩ ሄደ፡፡
… ከዚያስ?
***
ወዳጄ፡- ስህተት ትምህርት መሆኑ አያጠራጥርም። ተመሳሳይ ስህተት ግን ጥፋት ነው፡፡ ሳይታረሙ መኖር የነፍስ እስር ቤት ነው፡፡ በጥፋት ላይ ጥፋት መጨመር ደግሞ ጨርሶ አለመኖር ነው ያሰኛል። ሰው መሆንን ያሳንሳል፡፡ ‹አለማወቅ ነው› ተብሎ ማለፍም ያስቸግራል፡፡ መታረም ተገቢ ቢሆንም ይቅርታ መጠየቅ ነፃነትን ያቀዳጃል፡፡ ይቅርታ ራስንም ሌላውንም ማሸነፍ ነው፡፡ እንደገና የመኖር፣ እንደገና የመወለድ ያህል ያስደስታል፡፡ … ይቅርታ መጠየቅም ሆነ ይቅርታ ማድረግ አያስፈራም!!
ወዳጄ፡- የጥፋት ምንጩ ስሜታዊነት ነው፡፡ አንዳንድ ሊቃውንት፤ ስሜታዊነትን በሰባት ክፍሎች ይመድቧቸዋል፡፡ የቅናትና የምቀኝነት፣ የፍቅርና የመውደድ፣ የሃዘንና የብስጭት፣ የፍላጎትና የጉጉት፣ የቁጣና የንዴት፣ የደስታና የፈንጠዚያ … ወዘተ እያሉ። አንድ ሰው ትዕግስተኛ የሚባለው እነዚህን ስሜቶች በቀላሉ መቆጣጠር ሲችል ነው (Patience means holding back your inclination against the seven emotions) ይላሉ፡፡
ታዋቂ ቡጠኛ የነበረው ቻክ ኑሪስ፤ “ሰዎች እንደ ብረት ናቸው፤ ሲሞቁ ይቀልጣሉ፣ ሲቀልጡ ሌላ መልክ ያወጣሉ” ብሎ ነበር፡፡ “ራስን መቆጣጠር፤ ራስን መግዛት እንደ ድሮ ባቡር ፍሬን ነው፤ አቅጣጫውን ሲስት ታቆምበታለህ፣ ትክክለኛውን መስመር ይዞ እየተጓዘ ብትይዘው ግን ሊገለበጥ ይችላል” በማለት የሚመክረን ደግሞ በርትላንድ ሩሰል ነው፡፡ ሩሰል እንደሚለው፤ ‹ልክ መሆን› ስሜት አይደለም፤ተፈጥሯዊ አንተነትህ ነው፡፡ ተፈጥሮ የምትከተለው ወይ የምትነዳበት ጉዳይ አይደለም፡፡ … ሁሌም ልትኖረው የሚገባህ እንጂ!! … ስሜታዊነት ‹ልክ አለመሆን› ነው፡፡ ልክ አለ መሆን ደግሞ አለመኖር!!
“ደስታና ፈንጠዝያ (happiness and pleasure) የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ ደስተኛ የሚባል ሰው፤ የአስተሳሰብ ከፍታ ላይ የደረሰ ነው፡፡ በማናቸውም ጉዳይ ራሱን የመግዛትና የመቆጣጠር ብቃት ሲኖረው፤ በመከራ፣ በህመምና በስቃይ ላይ መሳቅ ሲችል፣ ሙሉ በሙሉ ነፃና የራሱ ባለቤት መሆኑን ሲያረጋግጥ (Stage of liberation) ነው፡፡ የአዕምሮ ምጡቅነቱ ብቻ ሳይሆን ልበ ንፁህነቱም ጭምር ነው፡፡ ቡረቃና ፈንጠዝያ (Pleasure) ግን የስሜት ውልዶች ናቸው። ስሜታችንን ተከትለው ይመጣሉ፣ ስሜታችን ሲቀየር ይሄዳሉ፡፡” የሚሉን ደግሞ ዳላይ ላማ ናቸው- “ዘ አርት ኦቭ ሃፒነስ” በሚለው መጽሐፋቸው፡፡ ሰውየው ህንድ ውስጥ በስደት የሚኖሩ የቲቤት መሪ ናቸው፡፡ “ሰውን ማሸነፍ የሚቻለው በኃይል ወይም በድርድር ሳይሆን በፍቅር ብቻ ነው፡፡” የሚለው ከእነ አርስቶትልና ፍሬዴሪክ ኒቼ የተለየውን የሞራል ኤቲክስ አራማጅ ከሚባሉት፣ ለአስተምህሮታቸውም ራሳቸውን አሳልፈው ከሰጡትና መስዋዕት ከሆኑት እንደ ማህተመ ጋንዲና ኢየሱስ ከመሳሰሉት ተርታ ተሰልፈዋል- በእምነት መስመር ቡድሂስት ቢሆኑም፡፡
ወዳጄ፡- ፍቅር በሌለበት ሃገር፣ ፍቅር በሌለበት ቤተሰብ፣ ፍቅር በሌለበት መስሪያ ቤት ሁከት፣ ንትርክና መናናቅ ይነግስበታል፡፡ ቀደም ሲል በመላው ዓለም፣ ዛሬም ጎረቤቶቻችን ደቡብ ሱዳንና ሶማሊያን ጨምሮ በብዙ ቦታዎች እንደምናየው፤የሰው ልጆች  የማይገባቸውን፣ ያልተፈረደባቸውን ቅጣት እየተቀበሉ ናቸው- በጦርነት፣ በረሃብ በበሽታና በስደት!! … ለዚህ ደግሞ የተደራረቡ ብዙ ምክንያቶች ቢቀርቡም አሳማኝና ዋና ሆኖ የሚቆጠረው ግን ለፍቅርና ለመቻቻል ሰፊ ቦታ አለመኖሩ ነው፡፡
ኢየሱስና ጋንዲ፤ አንዲት ጥይት አልተኮሱም፣ ጎራዴ አልመዘዙም፣ ጦር አልሰበቁም፡፡ ሃሳባቸው ግን አለምን አስገብሯል፡፡ ትልልቅ ጦረኞች ሲንበረከኩ፣ እነሱ አሸንፈዋል፡፡ ትልልቅ ጦረኞች ከታሪክ መስመር ሲሰረዙ፣ እነሱ ታሪክ ሆነዋል፡፡ ትልልቅ ዕምነቶች፣ አማልክቶችና ጣኦታት ሲፈረካከሱ፣ እነሱ ሃይማኖት ሆነዋል፡፡ ወዳጄ፡- የናሽናል ጂኦግራፊ ቴሌቪዥን ዕውነቱን ያሳይሃል፡፡ ነብርና ፍየል እየተላፉ ያድጋሉ፣ አንበሲት የአጋዘን ልጅ ታጠባለች፣ እባብ ከህፃን ጋር ይጫወታል። ‹ፍቅር ያሸንፋል!› ሲባል ያለ ምክንያት እንዳይመስልህ፡፡ ችግር ያለው አስተሳሰባችን ላይ ነው። ስህተት መድገማችን፣ አለመታረማችን!!
“ትልቁ ድል ራስን ማሸነፍ ነው” (the highest victory is victory over oneself) ይላሉ ሊቃውንት፡፡ ራስህን ለማሸነፍ አስተሳሰብህን ትገራለህ እንጂ ራስህ ላይ አትተኩስም። ሌላው ‹አሰበ› ብለህ፣ ለምን ትተኩስበታለህ? … እሱንም ስማው። ተከራክሮ ካሸነፈህ እመነው፣ ተከራክረህ ካሸነፍከው ፍቅር ስጠው፡፡ አየህ ወዳጄ፤ አንዳንዱ በጠመንጃ፣ አንዳንዱ በፍቅር ያድናል፡፡ የጠመንጃው ህመምና ስቃይ አለው፣ ጠላት ታፈራበታለህ፡፡ … መሞትም አለ፡፡ በፍቅር ሚሊዮኖች ይታደናሉ፣ ደስ እያላቸው ይሞታሉ፡፡ ልትነግስባቸውም ትችላለህ!!
***
 ወደ ተረታችን እንመለስ፡- ሰውየው እግዜርን ለሁለተኛ ጊዜ የመኖር ዕድል እንዲሰጠው ለመነውና “እሽ ይሁንልህ” ተባለ። በዛው ቅጽበት ራሱን አወቀ። የማንኳረፍ ድምፅ ሰምቶ ዞር ሲል፣ ነፍሰ ጡሯ ነብር ራቅ ብላ ታምጣለች፡፡ ባዶውን መሳርያ አንስቶ፣ ደብድቦ ሊገድላት ፈለገ-መድከሟን አይቶ፡፡ ተመልሶ መጥቶም፣ ቆዳዋን ገፎ ሊወስድ፡፡ … ወደ እርሷ ሲሄድ ትልቅ የአጋም እሾህ ተሰነጠረበት፣ ሊራመድ አልቻለም። ታመመ፣ ቆሰለ፣ ሁለት ቀን ቆየ፡፡ ረሃብና ጥማት ወደ ሞት ጥግ እየጎተተ አደረሰው፡፡ ስቃዩን ያዳመጠችው አራስ ነብር፣ ተጠግታ ጡቷን ሰጠችው። ጠባና ነፍሱ ተመለሰች፡፡ ወተቷን ደጋግሞ ጠጣና ተሻለው፡፡ በእኩይ ሃሳቡ ተፀፀተ፡፡ ሁለተኛውን ዕድል ለመልካምነት አለመጠቀሙ አሳዘነው፡፡ መሳሪያውን ወርውሮ ወደ ሰፈሩ ተመለሰ፡፡ በመንገዱ ላይ ኮቴ የሰማ መሰለውና ዞር አለ፡፡ ማንም አልነበረም፡፡ መንገዱን እንደቀጠለ እንደገና የኮቴውን ድምፅ ሰማ። ዞር ቢል ምንም የለም፡፡ እግዜር መሆኑን አወቀ፡፡ እግሩን እየጎተተ ሮጠ … ሮጠ … ከራሱ እየሸሸ መሆኑ አልገባውም፡፡
ወዳጄ፡- “ፍቅርና ደግነት የታላቅነት ምልክት ነው” (Love and generousity is a mark of superiority”) ያለውን ታስታውሳለህ?
ሠላም!!

Read 2209 times