Print this page
Sunday, 01 July 2018 00:00

ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከኪነ ጥበቡ ማህበረሰብ ጋር

Written by  ብሩህ ዓለምነህ
Rate this item
(0 votes)

• ‹‹ጥበብ ሚናዋን ስትጫወት ብቻ ነው ማህበራዊ ሽግግር የሚመጣው”
       • ‹‹አርት የማህበረሰቡን ህመም የሚያስተጋባ ነው››
    
ረቡዕ ሰኔ 20 ቀን 2010 ዓ.ም ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ ከኪነ ጥበቡ ማህበረሰብ ጋር በጠ/ሚኒስትር  ጽ/ቤት አዳራሽ፣ ከጠዋቱ 03፡00-05፡30 ድረስ በኪነ ጥበብ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡ ምንም እንኳ አስቀድሞ ከባህልና ቱሪዝም ሚ/ር የታደለው የመጥሪያ ደብዳቤ፤ ‹‹ሥልጠና›› ቢልም፣ ነገሩ ግን ‹‹ስልጠና›› ሳይሆን ውይይት ነበር፤ የውይይት ጊዜ ቢያንስም፡፡ ከዚህ በፊት ‹‹ሰተቴ›› እና ‹‹እርካብና መንበር›› የተሰኙ መፃህፍቶች የዶ/ር አብይ ናቸው ወይስ አይደሉም የሚል ውዝግብ በህዝቡ ውስጥ እንደነበረ ይታወቃል። በዚህ ውይይት ላይ ጠ/ሚኒስትሩ፣ መፅሐፎቹ በእርግጥም የራሳቸው መሆናቸውን የተናገሩ ሲሆን በዕለቱም ከሁለተኛው መፅሐፋቸው የተወሰኑ ኮፒዎችን በነፃ አድለዋል፡፡
እውነቱን ለመናገር ዶ/ር አብይ የኪነ ጥበብ ፅንሰ ሐሳብ ላይ ባላቸው ጥልቅ ግንዛቤ ተገርሜያለሁ። አርት በአሜሪካ የጥቁሮች የእኩልነትና የነፃነት ትግል ውስጥ የተጫወተውን ሚና ያሳዩበትና በማርከስ ጋርቬይ፣ በማልኮም ኤክስ፣ በማርቲን ሉተር ኪንግ፣ በፕሬዚዳንት ኬኔዲ እና በቦብ ማርሌ መካከል የነበረውን የመንፈስ ትስስር ያቀረቡበት መንገድም በጣም መሳጭ ነው፤ አንባቢነታቸውንም ያሳያል። ‹‹የዚምባብዌን ነፃነት ከቦብ ማርሌ ‘ዚምባቡዌ’ ዘፈን ውጭ ማሰብ አይቻልም›› ብለዋል፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
ውይይቱ በኪነ ጥበብ ዘርፎች (ሙዚቃ፣ ስዕል፣ ሥነ ፅሁፍ፣ ፊልም፣ ቲያትር ወዘተ) ውስጥ ያሉ 500 ባለሙያዎችን ያሳተፈ ሲሆን እኔም በፀሐፊነቴ ከተጋበዙት ውስጥ ነበርኩ፡፡ ውይይቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻቸውን የመሩት ሲሆን የኪነ ጥበብ ፅንሰ ሐሳብና ፋይዳ ላይ የተፃፉ ከመቶ በላይ የኮምፒውተር ስላይዶችን አዘጋጅተው ነበር የጠበቁን፡፡ ይሄም የሚያሳየው የጠቅላይ ሚኒስትሩን ትጋት ብቻ ሳይሆን ለአርትም ያላቸውን ከፍተኛ ዝንባሌ ጭምር ነው፡፡ በውይይቱ ላይ የሀገሪቱን አርት ለማጎልበት ሲባልም ለ50 ባለሙያዎች የአንድ ሳምንት የቻይና ጉዞና ጉብኝት (የልምድ ልውውጥ) እንደሚኖርም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። በውይይቱ ላይ ያቀረቧቸው አጠቃላይ ሐሳቦች የሚከተሉት ሲሆኑ በዚህ ፅሁፍ ውስጥ በትምህርተ ጥቅስ አሊያም ‹‹ጠ/ሚኒስትሩ እንዳሉት…›› ብዬ ከምገልፀው ውጭ ያለው ሐሳብ የኔ ጭማሪ መሆኑን ከወዲሁ መግለፅ እፈልጋለሁ፡፡
የአርት ፅንሰ ሐሳብና አተያዮች
አርትን አርቲስቶች በተግባር ቢሰሩትም ንድፈ ሐሳባዊ ትንታኔው ግን የአርት ሐያሲያን፣ የማህበራዊ ሳይንቲስቶችና የፈላስፎች ርዕሰ ጉዳይ ነው፡፡ አርት (ኪነ ውበት) ከፍልስፍና ቅርንጫፎች ውስጥ አንደኛው ሲሆን መጠናት የጀመረውም ከጥንት ዘመን ጀምሮ ነው፡፡ በዚህም የአርትን ሚና በተመለከተ ሁለት ዓይነት አመለካከቶች እንዳሉ ጠ/ሚኒስትሩ አስታውሰዋል። ‹‹የመጀመሪያው፣ አርትን ለልማት የሚል ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ አርትን ለአርት የሚል ነው፡፡ የመጀመሪያው አስተሳሰብ በዋነኛነት አርትን ለፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ የሚጠቀም ነው፡፡››
እንደምናስታውሰው የአቶ መለስ ዜናዊ የልማታዊ መንግስት ፅንሰ ሐሳብ፤ አርትን በተመለከተ የመጀመሪያውን አመለካከት ብቻ የሚደግፍ ነበር፡፡ ዶ/ር አብይ ግን በዚህ ጉዳይ ላይ አቋም አልወሰዱም፤ ይልቅስ ሁለት ግንዛቤዎች እንዳሉ ብቻ ነው ያስረዱት፤ ሁለቱ ሚናዎች ግን እርስበርስ የሚጣሉ እንዳልሆኑ ለማሳየት ሞክረዋል፡፡ በፍልስፍና ውስጥ ይሄ አመለካከት ‹‹ፕሌቶናዊ የአርት አስተሳሰብ›› ተብሎ ይጠራል፡፡ በፕሌቶ አመለካከት አርት የሚጫወተው፣ የሰው ልጅ ስስ ስሜት ላይ ስለሆነ፣ በአመክንዮ የሚገነባን ማህበረሰብ እንዳያፋልስ፣ የቅርብ ክትትልና ቁጥጥር ሊደረግበት ይገባል፡፡
ይህ ፕሌቶናዊ አመለካከት ግን ብዙ ውግዘቶችን አስተናግዷል፡፡ ዋነኛ ችግሩም የአርትን ባህሪ መገንዘብ አለመቻሉ ነው፡፡ የአርት ስራዎች የሚመነጩት ከአርቲስቱ የፈጠራ ምናብ (imagination) ነው። አርቲስቱ እዚህ ፈጠራ ላይ ለመድረስ በመጀመሪያ በስሜት መነካት አለበት፡፡ የአርቲስቱን ስሜት በህግ መያዝ አሊያም የሚፈስበትን አቅጣጫ መቀየድ የፈጠራ ምናቡን ያኮላሽበታል፤ የሚፈነቅል ስሜቱንም ያደርቅበታል፡፡ ዶ/ር አብይ፤ አዲስ አበባ፣ የአርቲስቱን ስሜት የሚያወጣ፣ የንባብና የጥሞና ቦታ እንደሚያንሳት ጠቆም አድርገዋል፡፡
ኪነ ጥበብና ማህበረሰብ
ዶ/ር አብይ ሰፋ ያለ ውይይት ያደረጉት የኪነ ጥበብን ማህበራዊ ፋይዳ በማስረዳት ሲሆን አቀራረባቸውና ግንዛቤያቸውም መሳጭ ነበር፡፡ ‹‹ይህ ትውልድ በባለፈው ጥበብ የተሰራ ነው፡፡ የዕድገትና የስልጣኔ መለኪያው ህንፃ ሳይሆን አርት ነው፡፡›› ዶ/ር አብይ እዚህ ጋ የምዕራባውያንንና የመካከለኛው ምስራቅ ውብ ኪነ ህንፃዎችን በማሳየት፣ የስልጣኔያቸውን ከፍታ አስገንዝበዋል፡፡ ‹‹አርት ረቂቅ ሰብዓዊ ስሜቶችን የምንገልፅበት መሳሪያ ስለሆነ ጥበብ ያለበት ቦታ በተፈጥሮ ምድረ በዳ ቢሆን እንኳ ገነት ያደርገዋል። ጥበብ የሌለበት ቦታ ግን በተፈጥሮ ለምለም ቢሆን እንኳ ገሀነም ይሆናል፡፡ ለአካል ብርታትን፣ ለመንፈስም እድሳትን የሚሰጠው ጥበብ ነው፡፡››
‹‹ጥበብ ሚናዋን ስትጫወት ብቻ ነው ማህበራዊ ሽግግር የሚመጣው፡፡ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በዘረኝነት፣ በሃይማኖት … ቅርጫ ሆናለች፡፡ አርት እንዴት ከዚህ ጨለማ መውጣት እንደምንችል አቅጣጫ የሚያሳየን እንጂ ችግሩን እንደ ማንኛውም ሰው የሚዘግብ አይደለም፡፡ አርቲስት በጨለማ ውስጥ ያለውን ጭላንጭል የብርሃን ተስፋ የሚያይና ለህብረተሰቡም የሚያሳይ እንጂ የድሮ መሪዎች እንዲህ አደረጉ እያለ ትውልዱን በባለፈ ነገር ውስጥ እንዲዘፈቅ የሚያደርግ አይደለም፡፡ አርቲስት ከእንደዚህ ዓይነት ችግር ትውልድን የሚያሻግር ነው፡፡ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በተሰባበረ ድልድይ ላይ ናት፤ ድልድዩን የሚሰራው ግን አርቲስቱ ነው፡፡ አርት ድምፅ ለሌላቸው ድምፅ የሚሆንና የማህበረሰቡን ህመሞች የሚያስተጋባ ነው፡፡ ሚዲያም አርት ሲኖርበት ኃይሉ ይጎለብታል፤ ሚዲያ ያለ አርት የሚጮህ ቆርቆሮ ነው፡፡››
‹‹አርት የማህበረሰቡን ህመም የሚያስተጋባ ነው›› የሚለው የጠ/ሚኒስትሩ አነጋገር፣ ፍልስፍናዊ ድጋፍም አለው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በስፋት የፃፈው አርስቶትል ነው፡፡ በአርስቶትል አመለካከት፤ አርት በተለይም አሳዛኝ ድራማዎች፣ ፊልሞች ወይም ቲያትሮች ማህበረሰብን የማከም ኃይል አላቸው። ትራጄዲ በኑሮ ውጣ ውረድ የተነሳ በውስጣችን የሚፈጠሩትን ጭንቀቶችንና ፍርሃትን የማስወገድ ኃይል (Catharsis) ሲኖረው፣ በምትኩም የአዛኝነትና የሰብዓዊነት ስሜቶችን ለመኮትኮት ይረዳል፡፡ ጠ/ሚኒስትሩም ‹‹አርት የሰውን ልጅ ከጥላቻ፣ ከዘረኝነት፣ ከክፋትና ከቂም በቀል ይፈውሰዋል›› ብለዋል፡፡
የዶ/ር አብይ ሀገራዊ ፕሮጀክት በፍቅር፣ በይቅር ባይነትና በሰብዓዊነት ሁሉንም ኢትዮጵያውያንን ማስተሳሰር እንደሆነና ከዚህም አልፎ በአፍሪካ ቀንድ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ማጠናከር እንደሆነ በተደጋጋሚ ተነግሯል፡፡ ይህ ፕሮጀክት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያና በኤርትራ ህዝቦች ላይ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡ በውይይቱ ላይም ጠ/ሚኒስትሩ፣ አርቱ የዚህ ፕሮጀክታቸው አካል እንዲሆንና መጪው ትውልድ አሁን ያለውን መከራና ችግር እንዳይወርስ፣ አርቲስቶች ጠንክረው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ኪነ ጥበብና የኢትዮጵያ መንግስታት
ሌላው ጠ/ሚኒስትሩ በውይይታቸው ላይ ያነሱት ነገር፣ የሀገራችን መሪዎች ለአርት የነበራቸውን ፍቅር ነው፡፡ ‹‹የሀገራችን የቀድሞ መሪዎች ለምሳሌ አፄ ምኒሊክ፣ ጅማ አባ ጅፋር፣ አፄ ኃይለስላሴ፣ አቶ መለስ የአርት ዝንባሌ ነበራቸው፡፡ ቤተ መንግስታቸውን የሚያሳምሩበት መንገድና ኪነ ህንፃው ይሄንን ይመሰክራል፡፡” ዶ/ር አብይ፣ ጂማ አባ ጅፋር ለጥበብ የተለየ ፍቅር እንደነበራቸው አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም፣ ልክ የጥንት ነገስታት፣ ኢትዮጵያ በእየሩሳሌም ቦታ እንዲኖራት እንዳደረጉ ሁሉ፣ ጂማ አባ ጅፋርም ኢትዮጵያ በመካ ቦታ እንዲኖራት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
‹‹ምንም እንኳ የቀድሞ መሪዎቻችን የአርት ፍቅር ቢኖራቸውም፣ አርትን ሲፈልጉ የነበረው ግን በአብዛኛው ሀገራዊ ችግር ሲገጥማቸው ብቻ ነው፤ በተድላ ዘመናቸው ላይ ግን አርትን ይረሳሉ። አርት የአንድ ማህበረሰብ ድምር የታሪክ ክምችት ማስቀመጫና social capital ስለሆነ ምንጊዜም ቢሆን — በክፉ ሆነ በደጉ ጊዜ — መረሳት የለበትም፡፡ አርት የዘር፣ የሃይማኖት፣ የፆታና የዕድሜ አጥር ሳይወስነው፣ ሁሉንም መንካት የሚችል በመሆኑ ህብረተሰብን ማንቀሳቀስና ማሸጋገር (transform ማድረግ) ይችላል። አርት የትውልድ ቅብብሎሽ እንዳይቋረጥና ያለፈው በጎ ታሪክ በአሁኑ ትውልድ ላይ እንዲታወስ የማድረግ ኃይል አለው፡፡ መሪዎች ራሳቸው የአርት ውጤት ቢሆኑም፣ ከኩራታቸው የተነሳ አሊያም ካለማወቅ፣ ይሄንን ሀቅ ግን አይናገሩም፡፡››
ኪነ ጥበብና ፈጠራ
ሌላው ዶ/ር አብይ ያነሱት ነገር፣ አርት ከቴክኖሎጂ ፈጠራ ጋር ያለውን ጥብቅ ቁርኝት ነው፡፡ ‹‹ማንኛውም ዓይነት የቴክኖሎጂ ፈጠራ የጥበብ ውጤት ነው፡፡ የፈጠራ ምናብ የሚሰፋው በጥበብ ነው፤ መጀመሪያ በምናብ ያልተሰራን ነገር፣ በተግባር ማሳየት አይቻልም። ልጆቻችን በፊዚክስም ሆነ በሒሳብ ትምህርት ጎበዝ የሚሆኑት፣ ጎን ለጎን፣ በአርት እየተኮተኮቱ ሲያድጉ ብቻ ነው፡፡››
ጠ/ሚኒስትሩ፣ ይሄንን የአርት ኃይል መረዳታቸው በግሌ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ ምክንያቱም በአሁኑ ወቅት እየተጠቀምንበት ያለው የ70/30 የትምህርት ፖሊሲ፣ 70 በመቶ የሚሆኑትን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርቶች ላይ የሚመድብ ሲሆን፤ ቀሪውን 30 በመቶ ደግሞ ለአርትና ለማህበራዊ ሳይንሶች የሚያከፋፍል ነው፡፡ ከዚህ የትምህርት ፖሊሲ ጀርባ ያለው አስተሳሰብ፤ ‹‹በአርትና በተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርቶች መካከል ምንም ዓይነት ግንኙነት የለም›› የሚል ነው፡፡
ይሄ አስተሳሰብ ግን አላዋቂነት ብቻ ሳይሆን ‹‹ልማት ብቻውን በቁሳዊ ትምህርቶች ብቻ ይመጣል›› ከሚል የአቋራጭ አስተሳሰብ የሚመጣ ነው፡፡ በአለም ላይ ስመ ጥር የሆነው የቴክኖሎጂ የትምህርት ተቋም የሚገኘው በማሳቹሴትስ የቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ (MIT) ነው፡፡ የሚገርመው ነገር ይህ የቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በጣም ጠንካራ የአርት ትምህርቶችም የሚሰጥበት ተቋም መሆኑ ነው፡፡
በዓለም ላይ ስመ ጥር የሆኑ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ሐሳቦችን ያፈለቁ ሰዎች፤ በአርት ትምህርቶች ተኮትኩተው ያደጉ ናቸው፡፡ የእኛ የትምህርት ፖሊሲ ግን የአርትና የስነ ሰብዕ ትምህርቶችን (Arts and Humanities) ጭራሽ ከኮመን ኮርስነትም አስወግዷቸዋል፡፡ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ፤ የ70/30ው  የትምህርት ፖሊሲ በወጣበት ወቅት ተቃውሟቸውን የገለፁት፤ ‹‹6ኪሎ ሲሞት፣ 5ኪሎም ይሞታል›› በሚል ነበር፡፡ ዶ/ር አብይ፤ በውይይታቸው ላይ የ70/30ውን የትምህርት ፖሊሲ ባይጠቅሱም ከግንዛቤያቸው መረዳት እንደሚቻለው፣ የ30 በመቶ ድርሻ ከፍ ማለት እንዳለበት የሚፈልጉ ይመስላሉ፡፡
የኢትዮጵያ አርቲስቶች በጠ/ሚኒስትሩ እይታ
እንደሚታወቀው አብዛኛዎቹ አርቲስቶቻችን በአርቱ ይኖራሉ እንጂ የፅንሰ ሐሳቡ ረቂቅነትና ፋይዳ ላይ ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ ነው። ዶ/ር አብይም እንዳሉት፤ ‹‹በአሁኑ ጊዜ የአርቲስቶቻችን ዋነኛ ችግር ጊዜ ሰጥተው ዕውቀታቸውን ለማሳደግ አለመጣራቸውና በዋነኛነት አርትን ለገንዘብ ማግኛ ብለው መስራታቸው ነው፡፡ በዚህም ሥራዎቻችሁ የቀጨጩና የአንድ ሳምንት ወሬ ብቻ ሆነው እየቀየሩ ነው፡፡ እናንተ ከልባችሁ ስለማትሰሩ ትውልዱ እናንተን ትቶ፣ ወደ በፊቶቹ ስራዎች እየተመለሰባችሁ ነው፤›› ብለዋል። ከዚህ አንፃር የጠ/ሚኒስትሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ፣ ለአርቲስቶች በጣም ጠቃሚ ይመስለኛል። ‹‹በአንፃሩ የበፊቶቹ አርቲስቶች ለምሳሌ ፀጋዬ ገ/መድን፣ አሊ ቢራ፣ ጥላሁን ገሰሰ፣ ሎሬት አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ፣ ገብረ ክርስቶስ ደስታ፣ ሐዲስ ዓለማየሁ፣ በዓሉ ግርማ … ስራዎቻቸው ዘመን ተሻጋሪ መሆን የቻሉት በትጋት፣ ከውስጠትና አርቱን ለአርት በሚል ውስጣዊ ስሜት ስለተሰሩ›› እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
ሌላው ጠ/ሚኒስትሩ ለአርቲስቶች የሰጡት አደራ፤ ‹‹አርት ትውልድን መፍጠሪያ መሳሪያ ስለሆነ ኩራታችሁን ትታችሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ት/ቤቶች እየተዘዋወራችሁ፣ለተማሪዎች ታሪካችሁን ብትነግሯቸው፣በአእምሯቸው ውስጥ ትልቅ ራዕይን ታስቀምጣላችሁ›› በማለት የራሳቸውን ልምድ አካፍለዋል፡፡ “እኔ በጅማ አጋሮ ተማሪ እያለሁ፣ አርቲስት አረጋኸኝ ወራሽ በት/ቤታችን መጥቶ ግንባሬን ስሞኛል። አሁን አረጋኸኝ (ውይይቱ ላይ ነበር) ያንን ላያስታውስ ይችላል፣ ሆኖም ግን ያ ነገር ለኔ ትልቅ ትርጉም ነበረው፤ አነሳስቶኛልም። በዚህ መንገድ ልጆቻችንን ጎብኟቸው፡፡”
ዶ/ር አብይ፤ በዚህ አጋጣሚ ለሎሬት ፀጋዬ ገ/መድን ትልቅ አድናቆት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹ፀጋዬን ያልተጠቀምንበት፣ ያልተረዳነውና ያለ ዘመኑ የኖረ ሰው ነው፡፡ ፀጋዬን ከእኛ ይልቅ የውጭ ሰዎች ያደንቁታል።›› ጠ/ሚኒስትሩ የፀጋዬን ሁለት አበርክቶዎች እንደ ምሳሌ ጠቅሰዋል፡፡ የመጀመሪያው፤ ፀጋዬ ኢትዮጵያን የሰፋበት መንገድ ነው፡፡ ‹‹ፀጋዬ ኢትዮጵያን የሰፋበት መንገድ በጣም አስገራሚ ነው፤ እኛ ግን አሁን እሱ የሰፋውን እየፈታን እንገኛለን፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ፀጋዬ፤ እኛ ኢትዮጵያውያን ሰውን የምናጀግንበት መንገድ ላይ ሒስ ማቅረቡ ነው፡፡ ‹‹ኢትዮጵያውያን ሰውን የምናጀግንበት መንገድ የአንበሳና የጦጣ - የገዳይና የብልጣብልጥ ቀማኛ - ዓይነት ነው፡፡ ይሄ የተሳሳተ እሳቤ ነው፡፡ ፀጋዬ ይሄንን ስህተት በማረም ነው አፄ ቴዎድሮስን በተለየ መንገድ- በንግድ ሂሳብ ሳይሆን በኢትዮጵያዊነት ስሌት- ያጀገናቸው -ብዙ ቴዎድሮሶችን ለመፍጠር›› ብለዋል፡፡
ስለ ሰኔ 16ቱ (2010) የግድያ ሙከራ
‹‹ኢትዮጵያ አሁን የለውጥ ፕሮጀክት ላይ ነች፡፡ ይሄንን ሪፎርም ደግሞ ብዙ ህዝብ ደግፎታል፡፡ ከአሁን በኋላ ኢትዮጵያን ከፍቅር፣ ከእኩልነት፣ ከፍትህና ከዲሞክራሲ ውጭ ማስቀጠል አይቻልም፡፡ ሁሉም ብሄር ይሄንን ነው የሚፈልገው፡፡ የትግራይም ህዝብ ከዚህ ውጭ የሆነ ፍላጎት የለውም፤ የትግራይ ህዝብ በተለየ ሁኔታ ተጠቅሟል እየተባለ የሚወራው ነገር ስህተት ነው፡፡
‹‹ሪፎርማችን እነዚህን እሴቶች ያካተተ ነው፡፡ ከእንግዲህ ከዚህ ወደ ኋላ መመለስ አይቻልም፤ ጥይት የሚገለው ሪፎርመሩን እንጂ ሪፎርሙን አይደለም›› በማለት፤ ‹‹እኔም ብሞት ሪፎርሙ ይቀጥላል›› የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ውይይቱ የተጠናቀቀው፣ 40 ሔክታር ላይ ያረፈውን ቤተ መንግስት እየተዘዋወርን በመጎብኘት ነው፡፡ በዚህም በአፄ ምኒልክ ጊዜ ጠጅ መጣያ የነበረውን፣ በኋላ ላይ ግን ደርግ ‹‹ሰው መጣያ›› ያደረገውን ቀዝቃዛ የመሬት ሥር ቤት፣ አፄ ኃ/ስላሴ በደርግ ታፍነው የተገደሉበትን ቤት፣ እንዲሁም 5000 ሰው የሚይዘውን የአፄ ምኒልክ የእልፍኝ አዳራሽ ጎብኝተናል፡፡ በውይይቱ ወቅት ጠ/ሚኒስትሩ፤ የአፄ ምኒልክ የእልፍኝ አዳራሽ ኮርኒሱ የተሰራው ከጠፍር መሆኑንና ጠፍሩ ሲቀጣጠልም 8000 ኪ.ሜ እንደሚደርስ በአድናቆት ነግረውናል። ከጉብኝቱ በኋላ የምሳ ግብዣ ተደርጎ፣ ፕሮግራሙ ወደ 09:00 አካባቢ ተጠናቋል።

Read 1535 times