Sunday, 01 July 2018 00:00

ዘመናዊ የመዝናኛና የገበያ ማዕከል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 ከመገናኛ ወደ ሲኤምሲ በሚወስደው መንገድ ላይ ጉርድ ሾላ ከመድረስዎ በፊት፣ አንድ ግዙፍና ለአይን
የሚማርክ ህንፃ ተኮፍሶ ይታያል፡፡ ሴንቸሪ ግራንድ ሞል ይባላል፡፡ በውስጡ ደረጃውን የጠበቀ ሲኒማና የህፃናት
የጨዋታ ዞንን ጨምሮ በርካታ ሬስቶራንቶች፣ ሱቆችና መደብሮችን ይዟል፡፡ ለመሆኑ ሞሉ እንዴት ታስቦ ተገነባ? ምን አገልግሎቶችን ይሰጣል? በመዲናዋ ላይ የጨመረው ዕሴት ምንድነው? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ ሴንቸሪ ግራንድ ሞልን ከጎበኘች በኋላ ከሞሉ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ከአቶ ካሳዬ ለማ ጋር ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ራሳቸውን በማስተዋወቅ ይጀምራሉ፡፡

    ካሳዬ ለማ እባላለሁ፡፡ የሴንቸሪ ሞል ዋና ስራ አስፈፃሚ ነኝ። ተወልጄ ያደግሁት ሰሜን ሸዋ ነው።  የመጀመሪያ ዲግሪዬን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአካውንቲንግ፣ ሁለተኛ ዲግሪዬን ከኦፕን ዩኒቨርስቲ በቢዝነስ አድሚንስትሬሽን አግኝቻለሁ፡፡ ከ25 ዓመት በላይ በተለያዩ ድርጅቶች በተለያየ የኃላፊነት ቦታ ላይ ሰርቻለሁ፡፡ ትልልቅ የቢዝነስ ድርጅቶችንም በማማከር ሥራ ላይ ለረዥም ጊዜ ሳገለግል የቆየሁ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት  የዚህ ግዙፍ እና ዘመናዊ ሞል ዋና ስራ አስፈፃሚ ሆኜ እየመራሁ እገኛለሁ፡፡
እስቲ ስለ ሴንቸሪ ሞል አፈጣጠር ይንገሩን?
ሴንቸሪ ሞል፤ የስቲሊ አርኤምአይ ብረታ ብረት አምራች ኩባንያ ታናሽ እህት በሆነውና በሪልስቴት ዘርፍ ላይ በተሰማራው ኔህኮ ትሬዲንግ የተገነባ፣ በከተማችን፣ በአገራችንም ጭምር፣ እጅግ ግዙፍና ዘመናዊ ሞል ነው፡፡ የግንባታው ሀሳብ የመጣው፣ ከተማዋ እያደገችና እየዘመነች በመጣች ቁጥር የብዙ ዲፕሎማቶችና የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ እንደመሆኗ፣ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት የሚሰጥ የገበያና የመዝናኛ ማዕከል በማስፈለጉ፣ ይህንን ክፍተት ለመሙላት ታስቦ ነው፡፡ በጉብኝትሽ እንዳየሽው፤ የጥራት ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የተገነባ ሞል ነው፡፡
ሞሉ በ5 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ስለመገንባቱ ሰምቻለሁ፤ ነገር ግን ቦታውን ከመንግስት በድርድር እንደወሰዳችሁ የሚነገር ነገር አለ፤ ትክክለኛው የቱ ነው?
አሁን የምትይው ጉዳይ ፍጹም ስህተትና ከእውነት የራቀ ነው፡፡ እንግዲህ ይህ ሃሰተኛ መረጃ፣ እዚህ ቦታ ላይ ግንባታ ለማካሄድ ፍላጎት ካላቸው ሰዎች የመነጨ ይሁን ሌላ ጉዳይ የምናውቀው ነገር የለም፡፡ ወሬው ግን እኛም ጆሮ ደርሷል፤ ነገር ግን ቦታው የተገኘው በድርድር ሳይሆን በ2003 ዓ.ም በወጣው 8ኛው ዙር የሊዝ ጨረታ፣ ከ17 ተጫራቾች ጋር ተወዳድሮ፣ ድርጅታችን ኔህኮ ትሬዲንግ አሸንፎ፣ 5 ሺህ ካሬ ሜትር ወስዶ ነው የገነባው፡፡ መሬት በድርድር ወስደን ትልቅ የገበያና የጉብኝት ሞል ለመስራት ባለፉት 15 ዓመታት ለመንግስት ጥያቄ ስናቀርብ ቆይተናል፡፡ ነገር ግን ምላሽ አላገኘንም፡፡ ስለሆነም ወደ ጨረታ ገብተን ካሸንፍን በኋላ ባለ 16 ወለል ለመገንባት አቅደን፣ የተፈቀደልን ግን ባለ 12 ወለል ነው፤ ከዚያ በላይ እንድንገነባ አልተፈቀደልንም፡፡
ከሞሉ ግዙፍነት ባሻገር እጅግ ዘመናዊ የሚያስብሉት ነገሮች ምንድን ናቸው?
ሞሉ እንግዲህ ሁሉም ነገሩ ዘመናዊና ደረጃውን የጠበቀ ነው ስንል ዝም ብለን አይደለም፡፡ ለምሳሌ ሶስት ደረጃቸውን የጠበቁ የሲኒማ አዳራሾች አሉን፡፡ ትልቁ 360 ሰዎች የሚይዝ ሲሆን ሁለቱ እያንዳንዳቸው 180 ሰዎች ይይዛሉ፡፡ ሳውንድ ሲስተሙ የዘመኑ ቴክኖሎጂ ያፈራው ሲሆን ወንበሮቹ ከፈረንሳይ አገር የመጡ፣ እጅግ ምቹና ዘመናዊ ናቸው፡፡ ሌላው ለየት የሚያደርገው፣ የአገር ውስጥም ሆኑ የሆሊውድ ፊልሞች የሚከፈቱ ቀን፣ እኛም ሲኒማ ቤት እኩል መክፈትና መመልከት የሚቻልበት ሁኔታ ነው ያለው። በዚሁ መሰረት የሆሊውድ አንድ ፊልም ሲመረቅ፣ እዚህ በተመሳሳይ ቀንና ሰዓት የሚከፈትበትን አሰራር ዘርግተናል፡፡ በተመሳሳይ ቀን እዚህ ማሳየት እንችላለን።
ቪአይፒ የሲኒማ ቤቶቹን ጨምሮ፣ ሁሉ ነገር እጅግ ዘመናዊና የተሟላ ነው፡፡ የልጆች መጫወቻ ዞንን ብንወስድ የውስጥ ዲዛይኑ ሳይቀር የተሰራው ከውጭ በመጡ ባለሙያዎች ነው። እቃውን ከመገጣጠምና ከመስራት ጀምሮ በዘርፉ የተካኑ የውጭ ባለሙያዎች ተጠብበውበታል፡፡ የቦታው ስፋት ልጆች እንደ ልባቸው እንዲንሸራሸሩና የተለያዩ አይነት ጨዋታዎችን እንዲያገኙ ተደርጎ የተሰራ ነው፡፡ በዚያ ላይ ዘመናዊ የሙቀት መቆጣጠሪያ (AC) የተገጠመለት በመሆኑ፣ ከመታፈንና ከተበከለ አየር የፀዳ፣ ፍጹም ሰላማዊ ነው፡፡  
በሌሎች ሞሎች ያልተለመደ ያየሁት ነገር፣ “ፉድኮርት” በተባለው ዞን ላይ የተለያዩ ሬስቶራንቶች በአንድ ወለል ላይ መገኘታቸው ነው፡፡  
በጣም ጥሩ! እኛ ዘመናዊ ሞል ገነባን ካልን፣ አዲስ አሰራር መፍጠርንም ጭምር ያካትታል፡፡ ለምሳሌ አንቺ ፒዛ መብላት ትፈልጊ ይሆናል፤ እኔ ሌላ የሀበሻ ምግብ ፍላጎት ይኖረኛል፡፡ ሌላ አብሮን ያለ እንግዳ ደግሞ “አይ እኔ ምሳ ሰዓቴን በጭማቂ ማሳለፍ እፈልጋለሁ” ሊል ይችላል፡፡ ስለዚህ እኛ ሶስት የተለያየ ሬስቶራንት መሄድ አለብን ማለት ነው፡፡ ወይንም ያለ ፍላጎታችን ሁላችንም ወደ አንደኛው ምግብ ቤት ልንሄድ ነው፡፡ ስለዚህ እኛ ይህን 6ኛውን ወለል ፉድ ኮርት አደረግነው፡፡ እንዳየሽው ቃተኛ ሬስቶራንት አለ፣ ቺክን ሀት አለ፣ የቻይና ሬስቶራንት አለ፣ አይስ ክሬም አለ፣ ጭማቂ ቤት አለ፡፡ ምግብሽን ታዥና የሆነች ክብ ማሽን ትሰጥሻለች፡፡ እሷን ይዘሽ ወንበርሽ ላይ ትቀመጫለሽ፡፡ ከዚያ ምግብሽ ሲደርስ ከሬስቶራንት ምልክት ሲሰጥ፣ እጅሽ ላይ ያለው ማሽን ምልክት ያሳይሻል፣ ሄደሽ ራስሽ ምግብሽን ይዘሽ ትመጫለሽ። ራስሽን ነው የምታስተናግጂው፤ ነገር ግን ሁላችንም የምንፈልገው አይነት ምግብ በአንድ ዞን ውስጥ አለ ማለት ነው፡፡
የህፃናት አልባሳትና ቁሳቁስ፣ የቤትና የቢሮ እቃዎች፣ የሴትና የወንድ አልባሳት፣ የቤት ውስጥ የመመገቢያና ሌሎች እቃዎች፣ እንደ ዌስትፖይንት፣ ቴክኖ፣ ሳምሰንግ እና ሌሎችም ኤሌክትሮኒክስ፣ ጌጣጌጦች፣ የስጦታ እቃዎች … እያንዳንዳቸው በዞን በዞን፣ በአንድ ወለል ላይ ነው የሚገኙት፡፡ አንዱ የህፃናት አልባሳት ሱቅ አንድ ወለል ላይ፣ ሌላው ሌላ ወለል ላይ አይደለም ያሉት፤ አንድ ላይ ነው፡፡ በዞን በዞን ያደረግንበት ምክንያት ደንበኛው፣ አማራጮችን በአንድ ቦታ ያለ ድካም እንዲያገኝ ነው፡፡ ሻጩም ቢሆን አንደኛ ፎቅና ሶስተኛ ፎቅ ላይ ከሆነ፣ ገዢው አንደኛ ፎቅ ላይ የሚፈልገውን እቃ ካገኘ ለምን ሶስተኛ ፎቅ ላይ በመውጣት ይደክማል፡፡ ስለዚህ አንደኛ ፎቅ ላይ የሚሸጠው ተጠቃሚ፣ ሦስተኛ ፎቅ ላይ ያለው ተጎጂ ይሆናል ማለት ነው፡፡ በአንድ ዞን ሲሆን የገበያ ስርዓቱ ያልተዛባና ሚዛኑን የጠበቀ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በሱቅ በሚጠቀሙ ተከራዮች የሚኖረው የዋጋ እና የጥራት ጉዳይ መፎካከሪያ መድረክ ይሆናል፡፡
በአዲስ አበባ በብዙ ህንጻዎች የሚያጋጥመው ችግር የመኪና ማቆሚያ ነው …
እኛ በብዙ ቦታዎች እንደ ትልቅ ክፍተት የምንመለከተውና እኛም ለስራ ስንሄድ የምንቸገርበት ከላይ የተነሱት ጉዳዮች ናቸው፡፡ በተለይ ደግሞ ብዙ ትኩረት የማይሰጠው የመፀዳጃ ቤት ጉዳይ አለ። ከትላልቅ ሆቴሎች ያላነሰ የዕረፍት ቤት በመኖሩ ተገልጋዩ ደስ ብሎት ይስተናገዳል፡፡ የመኪና ማቆሚያን በተመለከተ፣ ሶስት ወለሎች ከመሬት በታች (ቤዝመንቶች) አሉን፡፡ አንዱ 2 ሺ ካ.ሜ ስፋት ያለው ከፊል ቤዝመንት የተያዘው በሸዋ ሀይፐር ማርኬት ነው። ሁለቱ ከስር ያሉት ከ300 በላይ መኪኖችን ዘና ባለ ሁኔታ በአንድ ጊዜ ማስተናገድ ይችላሉ፡፡ በተጨማሪም በፊት ለፊት፣ በጎንና በጀርባ በቂ የመኪና ማቆሚያ አለን፡፡
የደህንነትን ጉዳይ በተመለከተ አጠቃላይ ህንፃው ዘመኑ ያፈራቸው ከ120 በላይ “ሲሲቲቪ” የደህንነት ካሜራዎች ተገጥመውለታል፡፡ ስለዚህ የደህንነት ጉዳይ በጣም አስተማማኝ ነው፡፡ አገራችን ላይ አምስት ኮከብ ደረጃ ያላቸው ሆቴሎች ካላቸው የሚመጣጠን ማረፊያ /መፀዳጃ ቤቶች/ አሉት - ሴንቸሪ ሞል፡፡ ይህ ብዙ ቦታ ትኩረት የማይሰጠው ነገር ግን መሰረታዊ ችግር ነው። እኛ በዚህም በኩል እጅግ የተዋጣለት ስራ ሰርተናል፡፡ ወደ ሴንቸሪ ሞል የሚመጣ ሰው የፈለገውን ገብይቶ፣ በዘመናዊና አዕምሮን በሚያጎለብቱ መጫወቻዎች ልጆችን አጫውቶ፣ ቡና ማኪያቶውን ጠጥቶ፤ የሀበሻም ሆነ የውጭ ምግቦችን ተመግቦ (በነገራችን ላይ በቅርቡ ፒዛ ሀትም ፉድ ኮርቱን ይቀላቀላል)፣ የሚል ግምት አለን፡፡ የውጭ ፊልሞችን ከዓለም ህዝቦች እኩል ተመልክቶ፣ ሁሉን በአንድ ላይ ከውኖ የሚኬድበት፣ የአውሮፓ ደረጃን የተላበሰ ትልቅ የገበያ ማዕከል ነው። ይሄ ለባለሀብቶቹም ለከተማዋም ለአገርም ኩራት ነው።
እንዲህ ደረጃውን የጠበቀ ሞል ሲሰራ፣ብዙ ሰው ገብቶ ለመገልገል ዋጋውን እንደ ጦር ይፈራዋል፡፡ ሴንቸሪ ሞል ዋጋው እንዴት ነው?
በጣም ጥሩ ሀሳብ አንስተሻል! ሴንቸሪ ሞል እጅግ ዘመናዊ ነው፡፡ ሲኒማ ቤቱም ሆነ የልጆች የጨዋታ ዞን ከተለያዩ አገራት በመጡ ዘመናዊ መሳሪያዎች የተሞላ፣ የውስጥ ማስጌጡም ሆነ ዲዛይኑም በውጭ ባለሙያዎች የተሰሩ ናቸው ብለናል፡፡ በአንድ ጊዜ ከ1200 በላይ ህፃናትን የማስተናገድ አቅምም አለው። ይሄን ለማሟላት በርካታ ወጪ ወጥቷል፤ ነገር ግን የሞሉ ባለቤቶች አላማ እነዚህን ውድ መሳሪያዎች ቢገጥሙም ማህበረሰቡን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማገልገልና ደህንነቱ ተጠብቆ ወደ ቤቱ እንዲደርስ ነው፡፡ አላማቸው ለአገር ገፅታም ሆነ ለማህበረሰቡ አማራጭ የሆነ አገልግሎት ማቅረብ ነው፡፡ የልጆችን ማጫወቻ እንውሰድ፡- ደንበኛው በ10 ብር አንድ ኮይን መግዛትና ልጁን ማጫወት ይችላል፡፡ ብዙ ጨዋታዎችን በአንድ ላይ የያዘው ግራውንድ ፕሌይ (መጫወቻ) ላይ ለማጫወት 90 ብር ነው፤ በቃ፡፡ ትልቁ ክፍያ 90 ብር ነው፡፡ በአጠቃላይ የምናስከፍለው በከተማችን ውስጥ ከሚገኙት የመዝናኛ ቦታዎች ዋጋ የተለየ አይደለም፡፡ የተሰራው ለማህበረሰባችን ነው፡፡ ሞሉ የህዝብ ሀብት ነው እንጂ የማህበረሰቡን አቅም የሚፈትን አይደለም። ፊልምን በተመለከተ የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ፊልሞች፤ እዚህ አገር ያሉ ሲኒማ ቤቶች በሚያሳዩበት እንጂ የተለየ ክፍያ የለንም፡፡ ለምሳሌ 50 ብር የአንድ ጊዜ ፊልም መግቢያ ነው፤ለዚያውም ሙሉ ምቾትሽ ተጠብቆ፡፡ ዋናው የሴንቸሪ ሞል አላማ፤ በውጭው ዓለም ያለውን የግብይትና የመዝናኛ ቦታ ተሞክሮና እሳቤ፣ አገራችን ላይ መፍጠርና ለአገራችን ህዝብ ማቅረብ ነበር፡፡
ሞሉ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ አንድ ዓመት ሆኖታል። አጠቃላይ እንቅስቃሴው ምን ይመስላል? ሁሉም ሱቆቻችሁ ተይዘዋል ወይስ ክፍት ቦታ አለ?
እንቅስቃሴው ጥሩ ነው፡፡ ከ90 በመቶ በላይ ሱቆች ተይዘዋል፡፡ ቀሪዎቹን ያቆየናቸው እኛው ራሳችን ነን፤ ምክንያቱም በሞሉ ውስጥ ሁሉም ነገር እንዲኖር ስለምንፈልግ፣ ገና ያልገቡ ዘርፎችን ለማካተት ነው ያቆየናቸው፡፡ በተጨማሪም ለቢሮዎች ተብለው የተመደቡ ቦታዎች፣ ሙሉ በሙሉ በተለያዩ ድርጅቶች አገልግሎት እየሰጡ ናቸው፡፡
ምን አይነት የአገልግሎት ዘርፎች እንዲገቡ ነው የሚጠበቀው?
ለምሳሌ ባህላዊ የስጦታ እቃዎች፣ በጣም ዘመናዊ ኤሌክትሮኒክ (ኤሌክትሪካል ኢኪዩፕመንትስ) ቢጨመሩ በጣም ደስ ይለናል፡፡ እነዚህ ከመጡ የበለጠ ግብይቱን ሙሉ ያደርገዋል፡፡ ሌላው የዋይ ፋይ አገልግሎት ለማቅረብ ዝግጅት አልቋል፡፡ ሰሞኑን ሙሉ የዋይፋይ አገልግሎት ይጀመራል። በነገራችን ላይ ቅድም ያልነገርኩሽ፣ በዘመናዊ ካሜራ ከሚጠበቀው የደህንነት ስራ በተጨማሪም ሞሉ ዘመናዊ የእሳት አደጋ አላርም ሲስተምም ተገጥሞለታል፡፡ እና በሁሉም አገልግሎቱና አቅርቦቱ ዘመናዊ ነው ብለን ስንናገርም በኩራት ነው። ለምሳሌ የራሳችንን ጉድጓድ ቆፍረን ባወጣነው ውሃ ስለምንጠቀም፣ የ24 ሰዓት የውሃ አቅርቦት አለን፡፡ ሁለት ትልልቅ፣ አንድ መለስተኛ ጀነሬተሮች ስላሉንም የመብራት አቅርቦት የሚያሳስበን ጉዳይ አይደለም፡፡ እዚህ ላይ አንዱ ችግር ጀነሬተር ስምንት ሰዓት የሚሰራ ቢሆንና 12 ሰዓት ያህል መብራት ቢጠፋ፣ የአራት ሰዓት ያህል ክፍተት ሲፈጠር፣ በዚህ መሀል ደንበኞች ቅር እንዳይሰኙና ይህንን እንዲረዱልን እንፈልጋለን፡፡
ሞሉ በ541 ሚ. ብር ወጪ መገንባቱን ሰምተናል። በራስ አቅም የተሰራ ነው ወይስ የባንክ ብድር ተወስዷል? ለመሆኑ ሞሉን የገነቡት ባለሀብቶች እነማን ናቸው?
ባለሀብቶቹ ከ60 እና 70 ዓመት በላይ የንግድ ልምድ ባካበቱ ቤተሰቦች የተገኙ ተተኪ ኢትዮጵያውያን ናቸው። ስማቸውን መጥቀስ ባያስፈልግም፣ የቤተሰባቸውን ፈለግ ተከትለው በንግዱና በኢንቨስትመንቱ ለአገሪቱ ትልቅ አስተዋፅኦ በማድረግ ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ ግንባታው ከላይ በገለፅሽው የገንዘብ መጠን የተገነባ ነው፤ ነገር ግን ከገንዘቡ ግማሽ ያህሉ ከባንክ ብድር ተወስዶ ነው፡፡ እንግዲህ ብድሩ ከዛሬ 6 ዓመት በፊት የተወሰደ ሲሆን በወቅቱ የወለዱ መጠን 14 በመቶ አካባቢ ነበር፤ አሁን 17 በመቶ ደርሷል፡፡ እሱንም እየከፈልን እንገኛለን፡፡ በውጭ ምንዛሬ ለውጥ ምክንያት የመጣው ይሄው የወለድ ጫና አሁን ፈተና ሆኖብናል፡፡ ሌላው ለኢንቨስተሮች፣ መሬት በማቅረብ በኩል ችግር አለ፡፡ በራሳቸው አቅምና ጥረት የተለየ ስራ እየሰሩ ላሉ ኢንቨስተሮች ቅድሚያ ሰጥቶ የመሬት አቅርቦት መመቻቸት አለበት እንላለን፡፡
ቀደም ሲል ትልቅ ፕሮጀክት ለመስራት 20 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ እንደጠየቃችሁ ነግረውኝ ነበር። የጠየቃችሁት ቦታ የት ነው? ምን ለመስራት ነው የታቀደው? ቦታው ቢፈቀድ በምን ያህል ኢንቨስትመንት ነው ፕሮጀክቱ እውን የሚሆነው?
ከተማ አስተዳደሩ እንዲሰጠን የጠየቅነው ቦታ ካዛንቺስ ነው የሚገኘው፡፡ ሲፈቀድልን ቀጥታ ወደ ስራው ለመግባት ዝግጁ ነን፡፡ ፕሮጀክቱ የውጭ ቱሪስትን ለመሳብ የሚችል ግዙፍ ፕሮጀክት ነው። በዚህ ፕሮጀክት ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል፣ አፓርትመንት፣ ሲኒማ ቤቶች፣ የልጆች የመጫወቻ ዞኖችና የቢሮ ህንፃዎችን ጭምር ያካትታል፡፡ ፕሮጀክቱ 2.7 ቢሊዮን ብር ይጠይቃል፡፡ ከቻይና ኩባንያዎች ጋር በሽርክና ለመስራት ነው የታቀደው፡፡
 

Read 2888 times