Print this page
Sunday, 01 July 2018 00:00

ሃይሌ ፊዳ ማን ነው? (የትግል ጓድ ምስክርነት)

Written by  ከፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ
Rate this item
(2 votes)

 • የመቻቻልና የመከባበር ባህል ሳንላበስ ነው፣ በድፍረት ፖለቲካ ውስጥ የገባነው
    • ”እውነቱና መፍትሄው እኔ ጋ ብቻ ነው” የሚለውን አስተሳሰብ መተው አለብን
    • የኛ ትውልድ፤ ለአዲሱ ትውልድ አበርክቷል ብዬ የምጠቅሰው ነገር የለም
      
    ዶ/ር አማረ ተግባሩ ይባላሉ፡፡ የሃይሌ ፊዳ የቅርብ ወዳጅና የትግል ጓድ እንደነበሩ ይናገራሉ፡፡ በቅርቡ “ሃይሌ ፊዳ እና የግሌ ትዝታ” የሚል መጽሐፍ ለአንባቢያን አቅርበዋል፡፡ በዚህ መፅሐፍ፣ በብዙዎች ዘንድ የጠባብ ብሔርተኝነት አስተሳሰብ ባለቤት ነው ተብሎ ስለሚወቀሰው ሃይሌ ፊዳ፣ እውነተኛ ማንነት ለማስገንዘብ የጣሩት ዶ/ር አማረ፤ ስለ 60ዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ፣ ስለ መኢሶን እና የሃይሌ ፊዳ ቁርኝት እንዲሁም መኢሶንና ደርግ ስለነበራቸው ግንኙነትና ልዩነት በስፋት አትተዋል፡፡
ዶ/ር አማረ ተግባሩ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሣይንስ ተማሪ በነበሩ ጊዜ የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች ህብረትና ዋና ፀሃፊ ነበሩ፡፡ በዚህም ለእስር ተዳርገዋል፡፡ ከእስር ከተፈቱ በኋላ ከሃገር የተባረሩትና ወደ ሃገር እንዳትገባ የሚል ትዕዛዝ የተላለፈባቸው ዶ/ር አማረ፤ ወደ ፈረንሳይ በማቅናት በፖለቲካል ሳይንስ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ በነበረበት ሰዓት የዘውድ ስርአት ተገርስሶ በወታደራዊው ደርግ ተተካ፡፡ እሳቸውም በሃገሪቱ የፖለቲካ ሂደት ውስጥ ለመሳተፍ ትምህርታቸውን አቋርጠው የመጡ ሲሆን የጠበቃቸው ግን ድጋሚ እስር ነበር፡፡ ለአምስት ዓመታት በደርግ ከታሠሩ በኋላ ሲፈቱ፣ በድጋሚ ወደ ስዊድን በመጓዝ ሶሻል አንትሮፖሎጂ መማር እንደጀመሩ ይናገራሉ - ዶ/ር አማረ፡፡ ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁም በዚያው በስዊድን ሃገር ስቶክሆልም ዩኒቨርሲቲ ለ10 ዓመታት ያህል አስተምረዋል፡፡ ከዚያም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሶሽዮ ኢኮኖሚክ አማካሪ ሆነው በርካታ ጥናቶችን አከናውነዋል፡፡
እነዚህ ጥናቶቻቸውም በበርካታ ዩኒቨርሲቲዎች በማስተማሪያነት እያገለገሉ እንደሚገኙ ምሁሩ ይገልጻሉ፡፡ ለአብነትም “Forest and State” እና “Environment and Resistant” የሚሉ የዩኒቨርሲቲ የማስተማሪያ መፅሃፍቶቻቸው ይጠቀሳሉ፡፡ በታይላንድና ቡታን በርካታ ጥናቶችን ያከናወኑት ዶ/ር አማረ፤ በኬንያ የእርሻ ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ እና የፖሊሲ ስትራቴጂ ነዳፊ ሆነው አገልግለዋል፡፡ በእርሻ መስክ በተለያዩ ዓለማቀፍ ተቋማት የሠሩት ምሁሩ፤ በሩዋንዳ ናይጄሪያ፣ ጋና፣ ላይቤሪያ፣ ታንዛኒያና ሴራሊዮን  የተለያዩ ምርምሮችን አከናውነዋል፡፡
ከ27 ዓመት የውጭ አገራት ኑሮ በኋላ በቅርቡ ወደ ሃገር ቤት የተመለሱት ዶ/ር አማረ፤ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር በአዲሱ መፅሐፋቸው፣ በሃይሌ ፊዳና በመኢሶን እንቅስቃሴ፣ እንዲሁም በወቅታዊ የአገሪቱ ፖለቲካ ጉዳዮች ላይ  ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡
በቅርቡ “ሃይሌ ፊዳ እና የግሌ ትዝታ” የተሰኘ መፅሐፍ ለአንባቢያን አቅርበዋል፡፡ መፅሐፉን ያዘጋጁበት ዓላማ ምንድን ነው?
ብዙ ጊዜ ስለ ሃይሌ ፊዳ የተዛቡ ነገሮች ሲነገሩ እሠማለሁ፡፡ ሃይሌን ከጠባብ ብሄርተኝነት ጋር አያይዘው የሚያነሱት አሉ፡፡ እኔ ደግሞ ከሃይሌ ጋር የቅርብ ወዳጆች፣ በአንድ የፖለቲካ ማህበር ስር የነበርንና ቅርርባችን የሠፋ በመሆኑ፣ ስለ እሡ የማውቀውን ሃቅ ለማስረዳት ነው፡፡
ሃይሌ ፊዳ ማን ነው? በሃገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ተሣትፎው ምን ነበር?
ሃይሌ ፊዳ ማን ነው? የሚለው ጥያቄ፣ የመፅሐፌም የመጀመሪያ ጭብጥ ነው፡፡ ሃይሌ ፊዳ  የማያልቅ ትዕግስት ያለው አዳማጭ ሰው ነው፡፡ ሊያስቆጣ ወይም ስሜትን ሊነካ የሚችል የግል ጉዳይን እንኳ በበጎ የሚያይ ሰው ነበር፡፡ ሃይሌ ቃልና ቁጣ የራቁት ሰው ነው፡፡ ከዚህ ሌላ ሃይሌ ሁልጊዜ ጠያቂ ሠው ነው፤ በትምህርት ከልጅነቱ ጀምሮ ጎበዝ ነበር፡፡ 8ኛ ክፍል ሚኒስትሪ ወስዶ፣ በአገር ደረጃ አንደኛ ወጥቶ ነው በማዕረግ፣ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የተሸጋገረው። ሰብዕናው ሙሉ የነበረ ሰው ነው፡፡ ወደ ፖለቲካ ጉዳዮች በስፋት የገባው፣ ጀነራል ዊንጌት ት/ቤት ሲገባ ነው፡፡ አብረውት የተማሩ የቅርብ ዘመዶቼ እንደነገሩኝ ከሆነ፤ ሁሉም ሠው ሊወዳጀው የሚጓጓለት፣ ጨዋና አስተዋይ ነበር፡፡ በዚህ ላይ በኢትዮጵያ ጉዳይ ገና በለጋነቱ ማሰብ የጀመረ ሰው ነው፡፡ የአለም የፖለቲካ ሃሣቦችን መመርመር የጀመረው፣ ገና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለ ነው፡፡ 12ኛ ክፍልን የጨረሰው በከፍተኛ ነጥብና ማዕረግ ነበር፡፡ ዩኒቨርሲቲም ገብቶ፣በልዩ ማዕረግ ነበር የጨረሰው፡፡ ወዲያውኑም በዩኒቨርስቲ የጂኦሊጂ እና የፊዚክስ መምህር ሆነ፡፡ በፊዚክስ እና በጂኦሎጂ ምርምር፣ በጣም ተስፋ የተጣለበት፣ የኢትዮጵያ የምርምር ሰው ይሆናል ተብሎ የሚታሠብ ነበር፡፡ ልጅ ካሣ ወ/ማርያም በወቅቱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ነበሩ፤ እሳቸው ናቸው በዚህ እሣቤ፣ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ውጭ የላኩት። ግን እሡ ወደ ፖለቲካና ፍልስፍና ያደላ ስለነበር የተላከበትን የጂኦሎጂ ትምህርቱን ትቶ ይበልጡን ጊዜውን በተማሪዎች የለውጥ እንቅስቃሴ ላይ አደረገ፡፡ የማርክሲስት ሌኒኒስት ፍልስፍናን በተለይም የሶቪየት ህብረትንና የቻይናን ፍልስፍና ያጠና ነበር፡፡
በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ከሃገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር እያገናኘ ሰፊ ጥናት ሲያደርግ ነበር የቆየው፡፡ ሃይሌ ይበልጥ ወደ ቻይና ኮሚኒዝም ያዘነብል ነበር። የማኦ ዜ ቱንግ ፍልስፍናን ለኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ እንዲመች አድርጎም ያጠና ነበር፡፡ በተቻለ አቅም ፍልስፍናዎችን ከሃገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር እናገኙ እያለ እኛንም ይመክረን ነበር፡፡ እይታው ኢትዮጵያ እንደ ቻይና ገናና የምትሆንበትን፣ የምትደመጥበትን፣ የምትከበርበትን፣ ከአካባቢዋ ሃገሮች ጋር በሠላም የምትኖርበትን ሁኔታ አስፍቶ የሚያስብ ሰው ነበር ሃይሌ፡፡ ግን ይሄ አስተሳሰብ ያለውን ሰው ነው እንግዲህ ከጠባብ ብሄርተኝነት ጋር ሊያነካኩት የሚሞክሩት፡፡ ከዚህ ሲያልፍም አንዳንዶች ከደርግ ጋር አጠጋግተው፣ ለ17 ዓመታት ደርግ ለፈፀመው ጥፋት፣ የእሱ እና የመኢሶን ድጋፍ አለበት ብለው የሚወነጅሉት፡፡ እነዚህ ሠዎች መረጃ ይዘው ቢቀርቡ ጥሩ ነበር፡፡ እውነቱን ለመናገር፣ ከደርግ ጋር እኛም ሆንን መኢሶን የሠራው ለአሥራ ሦስት ወራት ብቻ ነው፡፡ እሡም ደርግን ወደ ትክክለኛ ሁኔታ ለማምጣት በሚል ሙከራ ነበር፡፡ እንግዲህ እኔም ይህን መፅሐፍ ለመፃፍ የተነሣሣሁት፣ አግባብ ያልሆነ ፍረጃ በማውቀው ሰው ላይ ሲደረግ፣ ህሊናዬ እረፍት ስላጣ ነው፡፡  
ሃይሌ ጠባብ ብሄርተኛ አይደለም ለሚለው የእርስዎ ማስረጃ ምንድን ነው? ስለ ኢትዮጵያ የነበረው ራዕይ ምን ነበር?
ሃይሌ ስለ ኢትዮጵያ ያለውን ራዕይ በሚገባ ነው ያስቀመጠው፡፡ እርግጥ ነው ማንኛችንም የመጣንበት ብሔረሰብ አለ፡፡ አንድ ሰው በጉራጌነቱ፣ በአማራነቱ፣ በኦሮሞነቱ፣ በትግሬነቱ ወይም በሌላ የብሄር አባልነቱ የሚደርስበት በደል ካለ አይቀበልም፡፡ ሃይሌ እኔ የማልቀበለውን የብሔረሰብ ጭቆና፣ እሱ የሚቀበልበት ምክንያት የለም፡፡ ሃይሌ ስለ ብሄረሰቦች ጭቆና ሲናገር፤ በዲሞክራሲያዊነት በተመሰረተች ኢትዮጵያ ውስጥ እነዚህ ሁሉ ይፈታሉ ብሎ ያምን ነበር፡፡ ሃይሌ ከአንድ ብሄረሠብ በላይ፣ አለማቀፋዊነት ሰብዕናን የተላበሰ ሰው ነው፡፡ የዘመናዊነት ዕይታዎቹ፣ የኢትዮጵያዊነት አስተሣሠቡ ጥልቅ ነበሩ፡፡ ራሱ ስለ ጠባብ ብሄርተኝነት የፃፋቸውን ቁም ነገሮች በመፅሐፉ ውስጥ ለማካተት ሞክሬያለሁ፡፡ ሃይሌ ሁሉንም የኢትዮጵያ ህዝቦች በእኩል የሚያይ፣ በዚህ ላይ ደግሞ በኦሮሞነቱ ኩሩ የሆነ ሰው ነው፡፡ ለኢትዮጵያ የሚያስበው እኩልነትና ዲሞክራሲያዊነትን ነበር፡፡ አንዲት ለእኩልነት መርህ የቆመች ሶሻሊት፣ ከአካባቢው ሃገሮች ጋር ተሳስራ ልትኖር የምትችል፣ የምትደመጥ፣ የምትፈራ እንዲሁም የምትከበር ሃገር እንድትሆን ነበር ህልሙ፡፡ እኔ የብሄር ጉዳይ የሚከብደኝ ሰው ነበርኩኝ፡፡ ዛሬ አማራነትን የተማርኩት ከኢህአዴግ ነው፡፡ ለኔ አሁንም አማራነትና ኢትዮጵያዊነት የሚለያዩ አይደሉም፡፡ ሃይሌም ኦሮሞነቱና ኢትዮጵያዊነቱ የሚለያዩ አልነበሩም። ከዚህ ባለፈ ሃይሌን በጠባብ ብሄርተኝነት መፈረጅ ስህተት ይሆናል፡፡ ፍፁም ኢትዮጵያዊነት የተላበሰ ሰው ነው፤ ሃይሌ፡፡
ሃይሌ አዲሲቷ ኢትዮጵያን መመስረት የሚል ሃሳብ ነበረው፤ ለእሱ አዲሲቷ ኢትዮጵያ እንዴት ትገለጻለች?
እንግዲህ በወቅቱ ትግል የተጀመረው በፊውዳል ስርአት ስር ባለች ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ 90 በመቶ ገበሬ በጭሰኛነት ነው የነበረው፡፡ ይሄ ስርአት አልፎ ገበሬውን ባለመሬት የሚያደርግ፣ በእኩልነት ላይ የተደላደለ፣ ህዝብ ወሳኝ የሚሆንበት ስርአት፣ በአብዮታዊ ለውጥ አምጥቶ፣ በዜጓቿ እኩልነት ላይ የቆመችን ዲሞክራሲያዊ ኢትዮጵያን እውን የማድረግ ፍላጎት ነበረው፡፡ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ህልሙ ይህ ነበር። ይሄ ደግሞ የሃይሌ ህልም ብቻ ሳይሆን ከዳግማዊ ምኒልክ ጀምሮ የነበረ ህልም ነው፡፡ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ምስረታ ጉዳይ ዛሬም ያላለቀ ጉዳይ ነው፡፡
የግዕዝ ፊደልን አልጠቀምም በሚል ዛሬ ጥቅም ላይ የዋለውን የላቲን ፊደላት የተጠቀመው ሃይሌ ፊዳ ነው ይባላል… እርስዎ ደግሞ ቁቤን ሃይሌ አይደለም የፈጠረው የሚለውን ለማስረዳት በእማኝነት የጠቀሱት ባለቤቱን ነው---
ከባለቤቱ ሌላ ማን ቅርበት ይኖረዋል ታዲያ? እሷ ታውቃለች፡፡ በሌላ በኩል እነ አመሃ ዳኘው በፃፉት መፅሐፍ ላይ የጀርመን ሚሲዮናውያን ለአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ላቲን ፊደላትን ከእሡ በፊት ለመጠቀም ሞክረው እንደነበር ተነግሯል፡፡ ሃይሌ ቁቤን በመጠቀም የመጀመሪያ አይደለም፡፡ ምንም እንኳ እኔ የቁቤን ጉዳይ በቀጥታ አንስቼበት ባላውቅም፣ በዚህ ዙሪያ ከተደረጉ ንግግሮች፣ ውይይቶችና ክርክሮች፣ ሃይሌ ብቻ ይህን ፊደል እንዳልተጠቀመ ነው የተረዳሁት፡፡ ቁምነገሩ በቀላሉ ወደ ቴክኖሎጂና ስልጣኔ ለመግባት፣ ላቲን ፊደላትን ብንጠቀም ይረዳናል የሚል እሳቤ ነበረው፤ ሃይሌ፡፡ ይሄን ደግሞ ቻይናዎችም ቬትናሞችም የሞከሩት ጉዳይ ነው፡፡ ሃይሌም የግዕዝ ፊደል፣ ኦሮሚኛ ቋንቋ ውስጥ ያሉ የሚጠብቁና የሚላሉ ድምፀቶችን አያሟላም ከሚል ምልከታ በመነሳት፣ ላቲን ፊደላት መጠቀምን ይደግፍ ነበር፡፡
ሃይሌ በድርጅታችሁ በመኢሶን ውስጥ የነበረው ሚና ምን ነበር?
ሃይሌ ከመኢሶን (የመላው ኢትዮጵያውያን ሶሻሊስት ንቅናቄ) መስራቾች አንዱ ነው፡፡ ዋና ፀሃፊም ነበር። ለዚያ ድርጅት መመስረት ትልቅ ሚና የተጫወተ ሰው ነው፡፡ በርካቶችንም ወደ ድርጅቱ ያመጣ ሰው ነው። በመኢሶን አመራር ደረጃ የነበረውን ጥንቅር አሁን ባለው የብሄር እሣቤ እንለካው ቢባል፣ የበርካታ ብሄር ተወካዮች የተሰባሰቡበት ነበር፡፡ አብዛኞቹ ከውጭ ተምረው የመጡ ናቸው፡፡ ከሃይሌ በላይ ስልጣን የነበረው ዶ/ር ከበደ መንገሻ የወሎ አማራ ነበር፡፡ በድርጅታችን ውስጥ አሁን እንዳለው በብሄር መለካካት አልነበረም፡፡ አላማችን አንድና አንድ ነበር። እሡም አዲሲቷን ሶሻሊስት፣ የተከበረች ኢትዮጵያን ማቆም ነበር፡፡ የኢህአፓ አመራሮች ከነበሩት ከእነ ብርሃነ መስቀል ረዳ ጋር ስለ ሃገር ጉዳይ ውይይት ያደርግ ነበር፡፡ ሃይሌ ፊዳ በውይይት የሚያምን ሰው ነው፡፡ እኛ የህዝብ ነፃ አውጪዎች አይደለምን፤ ከህዝቡ መማር ነው ያለብን፣ ያንንም መልሠን ማስተማር አለብን፣ ከዚያ በኋላ ህዝቡ ራሱ፣ የራሱ ነፃ አውጪ ይሆናል የሚል ጥልቀት ያለው አመለካከት ነበረው፡፡ ከደርግ ጋር በነበረው ሁኔታም፣ ወታደራዊ መንግስቱን ከጅምሩ አይንህን ለአፈር ካልነው ችግሩ ይብሳል እንጂ ወደሚሻል አቅጣጫ አይሄድም፤ አብዮቱን አንድ ላይ ሆነን ብንመራው ይሻላል የሚል አመለካከት ነበረው፤ ሃይሌ፡፡ ሃይሌ በአጭሩ የቀረ ትልቅ ህልም የነበረው፣ ዘመናዊ ሰው ነበር፡፡ በስነ ፅሁፍ፣ በሙዚቃ፣ በአርት፣ በፍልስፍና ረገድ ሁላችንንም መመሰጥ የሚችል ሰው ነው፡፡ እኔ በግሌ ዘመናዊ አስተሳሰብ ምን ማለት እንደሆነ በሃይሌ ውስጥ ነው ያየሁት፡፡
የመኢሶን እና የደርግ ግንኙነት እስከ ምን ድረስ ነበር?
ሠራዊቱ በእጅጉ ሃገር ወዳድ እንደሆነ እናውቃለን። የካቲት 66 አብዮቱ ሲቀጣጠል ሠራዊቱ ፈራ ተባ እያለ ነው ወደ ፖለቲካው የተጠጋው፡፡ በወቅቱ ደግሞ ጠንካራ የተደራጀ የፖለቲካ ሃይል አልነበረም። ወታደሮቹ በሚፅፏቸው በሚናገሯቸው ነገሮች ሲታዩ፣ ተራማጅ ሃገር ወዳዶች እንደነበሩ ያስታውቁ ነበር። እነዚህን ሰዎች ብንረዳ የተሻለ ነው፤ ከማደናገር ይልቅ ብናግዛቸው የሚል እሣቤ ነበረን፡፡ ብቻቸውን በነበሩበት ጊዜ የሆነውን አይተናል፤ 60ዎቹን ገድለዋል፡፡ በዚያ የሚቆምም አልነበረም፣ የባሠም ሊያጋጥም ይችል ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎች ዝም ብለው ወርደው፣ በምርጫ መንግስት ይምጣ ቢባል አስቸጋሪ ነው፡፡ ከኢህአፓ በፊት መኢሶን ነበር - ምርጫ ይደረግ፣ ህዝባዊ መንግስት ይቋቋም፣ ወታደሩ ድንበር ይጠብቅ የሚል አቋም ያራመደው፡፡ በኋላ ግን ይሄን አቋም ለመቀየር ተገደድን፡፡ ደርግ በፖለቲካ ጉዳዮች የማይገባ፣ ዲሞክራሲያዊ ሁኔታዎችን የሚያመቻች፣ ለተራማጅ የፖለቲካ ድርጅቶች ቦታውን የሚለቅ ሆኖ እንዲንቀሳቀስ ማገዝ ያስፈልግ ነበር፡፡ የደርግ ሰዎችም ቢሆኑ በዚህ በኩል አግዙን ብለው መጀመሪያ ኢህአፓዎችን ነበር ያነጋገሩት፣ ግለሰቦችንም አነጋግረዋል፡፡ ነገር ግን መኢሶን ይበልጥ ተጠግቶ ነበር፤ በኋላ የመኢሶን ተደማጭነት እየጠነከረ ሲሄድ ግን መጠራጠር እየተፈጠረ መጣ፡፡ ከዚያም ጥርጣሬው ወደ ማሣደድና መግደል እርምጃዎች ነው የዞረው። ሃይሌም እንግዲህ በዚህ ሁኔታ ነው በ36 ዓመቱ በአጭሩ የቀረው፡፡ በነገራችን ላይ በሶማሊያ ወረራ ወቅት  ከየቦታው በስፋት እየሠበሠበ ሚሊሻ ጦር ወደ ማሠልጠኛ ያስገባ የነበረው መኢሶን ነበር፡፡ ከኢህአፓ በኋላ መኢሶንን ወደ መምታት ነው፣ ኮሎኔል መንግስቱ ፊታቸውን ያዞሩት፡፡ በደርግ ውስጥ እውነተኛ ሶሻሊስቶች ነበሩ፡፡ በዚያው ልክ ደግሞ ፍላጎቱ ብቻ የነበራቸውም ነበሩ፡፡ አምባገነኖች ብቻ የሆኑም ነበሩ። ደርግ እንደዚህ ነው፡፡
የ60ዎቹ ትውልድ፣ ለአዲሱ ትውልድ አበርክቷል የሚሉት አስተዋፅኦ ምንድን ነው?
በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ የእኛ ትውልድ ለዚህ ትውልድ አበርክቷል የምለው ነገር የለኝም፡፡ የምንጋራው ነገር ግን አለ፡፡ ከኛ ጀምሮ ያለው ወጣት ትውልድ፣ ለለውጥ መስዋዕትነት ለመክፈል የቆረጠ ነው፡፡ አደባባይ ይወጣል ይታገላል፣ ይገደላል፡፡ ላመነበት ዓላማ ወጥቶ፣ መስዋዕት ለመሆን የተዘጋጀ ትውልድ ዛሬም አለ፡፡ በምንም አይነት ለሞት የማይበገር፣ ጠንካራ የትግል መንፈስ ዛሬም ይታያል። ለትውልዱ አበርክተናል ከምለው አስተዋጽኦ ይልቅ ምናልባት የምንቆጭበትና የምንጸጸትበትን ብናገር ይሻለኛል፡፡
ምንድን ነው የምትቆጩበትና የምትፀፀቱበት?
በፖለቲካ አመለካከቱ የጠላነውን ሰው፤ ማንነቱንም፣ ምንነቱንም አብሮ የማጠልሸት ባህላችን ይፀፅታል፡፡ እኔ የሃይሌ ፊዳን መፅሐፍ ለማዘጋጀት የተነሳሳሁት፣ ይሄን ሰው የሚያውቁቱም የማያውቁትም ሰዎች በምን አይነት መልኩ ነው የሣሉት? የሚለው አስጨንቆኝ ነው። የሰዎችን ሃሳብ የመቃወም ነገር ግን ሰውነታቸውን የማክበር ባህል አልተገነባም። የመቻቻልና የመከባበር የፖለቲካ ባህል ውስጥ አለማለፋችን ነው የሚያስቆጨው፡፡ ይሄን የመቻቻልና የመከባበር ባህል ሳንላበስ ነው ዝም ብለን በድፍረት ፖለቲካ ውስጥ የገባነው፡፡ የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመን ፖለቲከኞች ምን እንደሚያስቡ እንኳ በቅጡ ሳናውቅ ነው፣ እኛና እነሱን የሚያገናኝ ነገር ሳይኖር፣ ጭልጥ ብለን ወደ አዲስ ልማድ የገባነው፡፡ በጭፍን ነው መፈረጅ የጀመርነው፡፡ ነገሮችን የመመርመር የማጣራት፣ የማቻቻል ልምድን አልወረስንም። ኢትዮጵያን እኔ ብቻ ነኝ ቀድጄ የምሰፋት የሚል አመለካከት ነበር ቦታውን የያዘው እንጂ የቀደመውንና አዲሱን ለማገናኘት ጥረት አላደረግንም፡፡ ይሄ ይፀፅተኛል፡፡
ላለፉት 40 እና 50 ዓመታት  ፖለቲካችን መጠፋፊያ ሆኖ የዘለቀው----
ምናልባት አዲሱ ትውልድ ይለውጠው ይሆናል፡፡ ምክንያቱም የትውልዱ እንቅስቃሴ ከፖለቲካ ርዕዮተ አለም ጋር የተገናኘ አይደለም፡፡ ከሠብአዊነት፣ በህግ ስር ተከብሮ ከመኖር ጋር፣ ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጋር የተያያዘ ነው፣ የአዲሱ ትውልድ እንቅስቃሴ። የኛ ትውልድ ግን “እኔ የያዝኩት ርዕዮተ አለም ነው ትክክለኛው፣ እኔ ነኝ ትክክለኛው ሶሻሊስት” በሚል ነው የተጠፋፋው፡፡ አሁንም ቢሆን “እውነቱና መፍትሄው እኔ ጋ ብቻ ነው” የሚለውን አስተሳሰብ መተው አለብን፡፡
በአገሪቱ ውስጥ እየታዩ ያሉ የፖለቲካ ለውጦችን እንዴት አገኟቸው?
አሁን የሚታየው ነገር የሚገርም ነው፡፡ ኢትዮጵያ መሪ አላጣችም፡፡ አሁን እየሆነ ያለው ፍፁም ያልጠበኩት ነው፡፡ የፖለቲካ ጨዋ አንደበት፣ ግልፅነትና ቅንነት ያለው መሪ፣ በእኔ የእድሜ ዘመን በኢትዮጵያ ምድር ላይ አያለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም፡፡ በዚህ ረገድ ብዙ ተስፋ የሚሰጡ ምልክቶች ይታያሉ፡፡ መሪ ግለሰብ ብቻ አይደለም፡፡ የመሪነት ብቃት ከሌሎችም ጋር አብሮ መጓዝ ይጠይቃል፡፡ ግን እውነት ኢህአዴግ ለውጥ አድርጎ፣ እንዲህ ያለውን መሪ አወጣ ወይስ ሳያስበው ድንገት ብቅ አለበት? ይሄ መቼም አጠያያቂ ጉዳይ ነው፡፡ አሁን ከእኒህ ሰው የሚወጡ ሃሳቦችና እርምጃዎች ተቋማዊ መሆን አለባቸው፡፡ ተቋማትም የአስተሳሰቡ ባለቤትና ተግባሪዎች መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ በፍጥነት ወደ ህግ፣ ወደ ስርአት፣ ወደ ዲሞክራሲ ተቋማት መገባት አለበት፡፡ የፖለቲካ አካሄዱ ሁሉን አካታች መሆን ይገባዋል፡፡ አንዱን ወገን ለመካስ ወይም ሌላውን አንተ ነህ የበደልከው ብለን የምንጠቋቆምበት እንዳይሆን መጠንቀቅ ይኖርብናል። በተቻለ አቅም አዲሱን መሪ ማገዝም፣ መጠቆምም፣ መገሰፅም አለብን፡፡  

Read 3595 times