Sunday, 01 July 2018 00:00

ብህትውናና ዘመናዊነት

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(4 votes)

  ክፍል- 3 ከአክሱም ቁዘማ ኢትዮጵያ ተወለደች!
             
   ብህትውና ላይ የጀመርነውን ወግ እንደቀጠልን ነው። በዛሬው ፅሁፌ ደግሞ አክሱም ከሐብት ምንጯ እንደተገነጠለችና በብህትውናም እንደተፅናናች፣ እንዲሁም ብህትውና እንዴት አክሱም ላይ ባህል ሆኖ እንደወጣ ቅዱስ ያሬድን እየጠቀስን ወጋችንን እንቀጥላለን፡፡
ፍልስፍና፣ ሃይማኖትና ባህል እጅግ የተሳሰሩ ነገሮች መሆናቸውን በግልፅ የሚያስረዳን ነገር ቢኖር፣ የብህትውና ፅንሰትና ዕድገት ነው፡፡ ብህትውና አቴንስ ላይ ከፍልስፍና ተወልዶ፣ አሌክሳንደሪያ ላይ ሃይማኖት ውስጥ ሰረፀ፤ አክሱም ላይ ደግሞ ከሃይማኖት አልፎ የህዝብ ባህል ሆነ፡፡
በታሪክ ውስጥ ብዙ ጊዜ እንደታየው ጥንታዊቷ አክሱም እስትንፋሷ ከመካከለኛው ምስራቅና ከግሪኮ-ሮማን ዓለም ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነው፡፡ አክሱም አራቱን የጥንት ሥልጣኔዎች - ሜዲትራኒያንን፣ መካከለኛው ምስራቅን፣ ሩቅ ምስራቅንና ደቡባዊ አፍሪካን በንግድ ስታስተሳስር የነበረች የንግድ ኮሪደር ነበረች፡፡
ዩሪ ኮቢሽቻኖቭ የተባለው ሩሲያዊው የታሪክ ተመራማሪ፤ “Axum” በተባለው ዝነኛ መፅሐፉ ውስጥ (1979፡ 59፣ 185-6) እንዲህ ይላል፡- ‹‹አክሱም ከዚህ የንግድ ኮሪደር ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሐብት አጋብሳለች፡፡ የዚህ መገለጫው ደግሞ የወርቅ ሳንቲሞችን ማሳተሟ ነው፡፡ ሀገራት ብዙ ጊዜ ለመገበያየት የሚጠቀሙባቸው ሳንቲሞች ከተራ ብረት የተሰሩ ናቸው፡፡ የወርቅ ሳንቲም የሚያሳትሙ ሀገሮች ግን በኢኮኖሚ በጣም ሐብታም፣ በፖለቲካ በጣም ኃያል፣ በቴክኖሎጂም በጣም የላቁ ናቸው፡፡ በ3ኛውና በ4ኛው ክ/ዘ ላይ ገናና የነበረው የአክሱም ሥልጣኔ የመነጨውም ይህ የንግድ ኮሪደር ከፈጠረለት የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የቴክኖሎጂ የበላይነት ነው፡፡››
በመሆኑም፣ በእነዚህ የሥልጣኔ ቦታዎች ላይ (በተለይም ደግሞ በሜዲትራኒያንና መካከለኛው ምስራቅ ላይ) የሚፈጠር ማንኛውም ዓይነት የፍልስፍና፣ የሃይማኖት፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ለውጦች ጥንታዊቷን አክሱምን ሳይነካት አልፏት አያውቅም፡፡ ስለ አክሱም የፃፉ በርካታ የታሪክ ምሁራን በግልፅ እንደነገሩን፤ በቅድመ ክርስትና ዘመናት የጥንት ግሪካውያን ቋንቋ፣ ባህልና ሃይማኖት (አማልክቶች) ሳይቀሩ አክሱም ላይ ይተገበሩ ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር፣ በ4ኛው ክ/ዘ የሜዲትራኒያን ዓለም ላይ የተነሳው የብህትውና ማህበራዊ ንቅናቄ ወደ አክሱም ቢዛመት የሚገርም አይሆንም፡፡ ንቅናቄውም 6ኛው ክ/ዘ አክሱም ላይ ተደላድሎ መቀመጥ ችሏል፡፡
በሁለት ምክንያቶች 6ኛው ክ/ዘ በአክሱማውያን ታሪክ ውስጥ እጅግ ወሳኙና አዲስ ምዕራፍ የተጀመረበት ዘመን ነው፡፡ የመጀመሪያው፣ አክሱማውያን ከብህትውና ህይወት ጋር መተዋወቃቸው ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ከቀይ ባህሩ ዓለማቀፍ የንግድ መስመር መጀመሪያ በፐርሺያኖች ቀጥሎ ደግሞ በሙስሊሞች ተገፍትረው መባረራቸው ነው፡፡ አክሱማውያን ግን ከቀይ ባህር በመባረራቸው የቆጫቸውም፣ የከፋቸውም አይመስሉም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሐብታም ካደረጋቸው የንግድ መስመር ቢባረሩም አንድ መፅናኛ ግን አግኝተዋል- ብህትውና፡፡
ብህትውና የውጭውን ዓለም ንቆ ወደ ውስጥ መመልከት ነው፤ ወደ ውጭ መንጠራራትና መስፋፋትን ትቶ ወደ ውስጥ መኮማተር ነው፤ ዓለማዊ ፈንጠዝያን ንቆ ወደ ውስጥ መመሰጥ ነው፤ ስጋዊ ተድላና ደስታን ትቶ ወደ ውስጥ መቆዘም ነው፡፡ በመሆኑም፣ አክሱም ከቀይ ባህር ብትገፈተርም ከዚህ ዓለም ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ የበላይነትም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ሳትፈልግ የምትኖርበትን የብህትውና ህይወት አግኝታለች፡፡ ምክንያቱም ፍሬድሪክ ኒቸ እንዳለው፤ ‹‹ብህትውና ምንም ነገር አለመፈለግ ነው- asceticism is to will nothingness›› ብህትውና በጣም በአነስተኛ የተፈጥሮ ሐብት ውስጥ ወይም ደግሞ በድህነትና በተፈጥሮ ንፉግነት ውስጥ ራስን የማኖር ጥበብ ነው። ይህ ጥበብ ከሐብት ምንጯ ለተገነጠለችው አክሱም ጥሩ መፅናኛ ሆኖላታል፡፡
ምንም እንኳ አክሱም ከሐብት ምንጯ ጋር በነበረችበት ወቅት አፄ እለ አሚዳ፣ አፄ ታዜናና አፄ ካሌብ ብህትውናን እንደ እምነት የተቀበሉት ቢሆንም፣ አክሱም ከቀይ ባህር ከተባረረች በኋላ የመጡት አፄ ገብረ መስቀልና ሌሎች ተከታታይ ነገስታት ግን ብህትውናን ከእምነት አንፃር ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውንም ሳያሰሉት አይቀሩም። በዚህ ኢኮኖሚያዊ ስሌትም ብህትውናዊ የህይወት ጥበብ ከኢኮኖሚ ምንጩ ለተነቀለው አክሱማዊው ህዝብና መንግስት ጥሩ ዘዴ ሆኖ ሳያገኙት አልቀረም። ምክንያቱም በሰፊው የለመደ ህዝብ፣ ያለ አንዳች መፅናኛ፣ ድንገት ድህነትን አሜን ብሎ ሊቀበል አይችልም፡፡
ከቀይ ባህር የተገፈተረችው አክሱም፤ ‹‹ከዚህ ዓለም ምንም ነገር አለመፈለግ›› በሚል የህይወት መርህ ቀሪ ዘመኗን ወደ ውስጥ በመመሰጥ፣ በመብሰልሰል፣ በመተከዝና በመቆዘም አሳለፈች፡፡ ከዚህ ተመስጦ፣ ትካዜና ቁዘማም ኢትዮጵያን ወለደች፡፡ አክሱም ኢትዮጵያን የፀነሰችው በተድላ ዘመኗ ላይ ቢሆንም፣ የወለደቻት ግን በብህትውና ዘመኗ ላይ ነው። በኢትዮጵያ ስነ ቃል፣ ስነ ፅሁፍ፣ ሙዚቃ፣ ስዕል፣ ፍልስፍና፣ ሃይማኖት፣ ባህልና ፖለቲካ ላይ ቁዘማና ትካዜ (ብህትውናነት) የሚበዛውም በዚህ የተነሳ ነው፡፡
ይህ የብህትውና አሻራ እንደዚህ በሁሉም የህይወት መስኮቻችን ላይ ተስፋፍቶ ሊገኝ የቻለውም (በክፍል-2 ፅሁፌ ላይ ጠቆም እንዳደረኩት) ብህትውና ቀድሞ የአክሱም ቤተ መንግስት በመግባቱ ነው፡፡ ይሄም ለብህትውና ሦስት ጥቅሞችን አስገኝቶለታል። የመጀመሪያው፣ ያለ ምንም ዓይነት ግጭትና መስዋዕትነት አስተሳሰቡ በሰላም እንዲስፋፋ መሆኑ ነው፡፡ ይሄ ማለት ግን በአዲሱ አስተሳሰብና በቀድሞው ባህል መካከል ምንም ዓይነት ውስጣዊ ተቃርኖ አልነበረም ማለት አይደለም፡፡ እንዲያውም፣ በአክሱም ለመጀመሪያ ጊዜ በመንፈሳዊና በዓለማዊ ህይወት መካከል ቅራኔ መፈጠር የጀመረው ከዚህ ወቅት ጀምሮ ነው፡፡ ሁለተኛ፣ የብህትውና አስተሳሰብ የመስፋፋት ኃይል (Expansive power) እንዲጎናፀፍ አስችሎታል። በዚህም የታሪክ ተመራማሪው David Phillipson, “Foundation of an African Civilization” በሚለው መፅሐፉ ውስጥ እንደሚለው፤ አስተሳሰቡ ከአክሱም ተነስቶ፣ ከሰሜን ወደ ደቡብ ምስራቅ 100 ኪ.ሜ ሬድየስ ያለውን አካባቢ በአጭር ጊዜ ውስጥ መድረስ ችሏል፡፡
ሦስተኛ ደግሞ፣ የብህትውና አስተሳሰብ የመስፋፋት ብቻ ሳይሆን ወደ ውስጥ ወደ ስነ ልቦናም የመጥለቅ ኃይል (Penetrative power) እንዲያገኝ አድርጎታል። ፖለቲካ የዜጎችን ሰብዕና የመቅረፅና አዲስ ማንነት የመፍጠር ኃይል አለው፡፡ ብህትውናም አስቀድሞ በነገስታቱ ፖለቲካዊ ቅቡልነትን ማግኘቱና መተግበሩ፣ ዜጎችም ያንን ፈለግ እንዲከተሉ አድርጓቸዋል፡፡
ብህትውና ‹‹አዲስ ሰው›› የመፍጠሪያ መንገድ ነው፡፡ ለዚህም እንዲረዳው የራሱ የሆኑ በዓላት፣ ሃይማኖታዊ ሥነ ስርዓት፣ ስነ ምግባራዊና ስነ መለኮታዊ አመለካከቶችን ፈጥሯል፡፡ እንግዲህ እነዚህ ሁሉን አቀፍ የሆኑ አዲስ አመለካከቶቹ ናቸው አስተምህሮቱ ወደ ውስጥ፣ ወደ ስነ ልቦና የመጥለቅ ኃይልንና በስነ ምግባር፣ በሰብዕናና ከዓለም ጋር ባለው ግንኙነትም ‹‹አዲሱን ሰው›› የሚፈጥረው፡፡
ብህትውና በዚህ ሁሉ ኃይሉ አዲስ ባህል የመፍጠር ችሎታን ይጎናፀፋል፡፡ እንግዲህ በዚህ መንገድ ነው ዘጠኙ ቅዱሳን መነኮሳት በአክሱምና አካባቢዋ ላይ አዲሱን ሰውና ባህል (ላሊበላዊነትን) የፈጠሩት። ቅዱስ ያሬድ የተነሳው በዚህ መንገድ ላሊበላዊው ባህል መሰረት ከያዘ በኋላ ነው፡፡ ያሬድ ‹‹አክሱማዊው ሰው›› ሳይሆን ‹‹ላሊበላዊው ሰው›› ነው፡፡ ስራዎቹም የሚመሰክሩት ይሄንኑ ነው፡፡
6ኛው ክ/ዘ መጀመሪያ ላይ ብህትውና ከእምነት አልፎ ጠንካራ የባህል መሰረት መያዙን የምንረዳውም አዲሱ ባህል በቅዱስ ያሬድ አማካኝነት የራሱን ዜማና ሃይማኖታዊ ሥርዓት መፍጠር መቻሉ ነው። ምክንያቱም ሙዚቃም ሆነ ማንኛውም ዓይነት የኪነጥበብ ሥራ የፈጠራ ምናቡን የሚቀዳው ማህበረሰቡ ውስጥ ከተነጠፈው ባህል ነው፡፡ ወይም ደግሞ ፍሬድሪክ ኒቸ “The Genealogy of Morals” መፅሐፉ ላይ እንደፃፈው፤ ‹‹ኪነ ጥበብ በሌላ ባለስልጣን- ሃይማኖት ወይም ፍልስፍና- ላይ ጥገኛ ነው፡፡››
ይሄም ማለት ኪነ ጥበብ የፈጠራ ምናቡን የሚያገኘው ከዚህ የስልጣን መሰረት ነው፡፡ በመሆኑም፣ ኪነ ጥበባዊ ሥራዎችን አይተን፣ ሥራዎቹ የተንተራሱበትን የስልጣን መሰረት፣ ምን እንደሆነ ማወቅ እንችላለን። ለዚህም ነው የቅዱስ ያሬድን የሚያራራ፣ ልብን የሚሰረስር፣ የትካዜና የቁዘማ ዜማዎችን ተመልክተን የስልጣን መሰረቱ የብህትውናው ባህል መሆኑን በቀላሉ መናገር የምንችለው፡፡ ያለ ብህትውናዊ ባህል፣ የያሬድ የትካዜ ዜማዎች ሊፈልቁ አይችሉም፡፡ ከላይ ‹‹ቅዱስ ያሬድ አክሱማዊ ሰው ሳይሆን ላሊበላዊው ሰው ነው›› ያልነውም ለዚህ ነው፡፡
የያሬድን ነገር አልጨረስኩም፡፡ በዛሬው ፅሁፌ ላይ ኢትዮጵያ እንዴት ከያሬድ የትካዜ (የብህትውና) ዜማ እንደተወለደች ተመልክተናል፡፡ በክፍል-4 ፅሁፌ ላይ ደግሞ የያሬድ የትካዜ ዜማዎች እንዴት ከእየሱስ የመጨረሻዎቹ የመከራ ቀናት እንደተቀዱ እንመለከታለን፡፡ በሌላ አነጋገር፣ ኢትዮጵያ የተወለደችው ከእየሱስ የመጨረሻዎቹ የእንግልትና የመከራ ቀናት ከፈጠሩት የትካዜ ስሜት (ሰሞነ ሕማማት) መሆኑን እንመለከታለን፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊው በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር እና ‹‹የኢትዮጵያ ፍልስፍና›› መፅሐፍ ደራሲ ሲሆኑ በኢ-ሜይል አድራሻቸው This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 2582 times