Sunday, 01 July 2018 00:00

ደራሲ ይስማዕከ ወርቁ የሰጠው ምላሽ

Written by 
Rate this item
(11 votes)

 • “ርካሽ ዝና ከኔ ትወስዳለች እንጂ ልጆቼን አታሳየኝም”
      • “የልጆቼ እናት ለማኝ ሆና እንቅልፍ የሚወስደው አዕምሮ የለኝም”
      • “እህቴ ለእርሷ እንጂ ለኔ አድልታ አታውቅም”

   ከአዘጋጁ
ለውድ አንባቢያን፡- ባለፈው ሳምንት የታዋቂው ደራሲ ይስማዕከ ወርቁ ባለቤት ፀጋ አንዳርጌ ምህረት ዝግጅት ክፍላችን ድረስ መጥታ “ህዝብ ብሶቴን ይስማ” በማለት፣ ደረሰብኝ ያለችውን በደል መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ወደ ማተምያ ቤት ከመሄዳችን በፊት ግን ደራሲ ይስማዕከ ወርቁን አግኝተን ምላሽ ወይም ማብራሪያ እንዲሰጠን ጥረን ነበር፡፡ ያደረግነው ሙከራ ግን ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ በዚህ ሳምንት ይስማዕከ ፈቃደኛ ሆኖ፣ ለጥያቄዎቻችን በፅሑፍ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ በኢ-ሜይል የላከልንን ከሞላ ጎደል እንዳለ አቅርነበዋል፡፡ ጥንዶቹ ችግሮቻቸውን በመነጋገር ይፈቱታል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡
ስለ ባለቤትህና ስላንተ ግንኙነት ባጭሩ ብትነግረኝ?
እኔም በትምህርትና በመፃፍ ነው ሕይወቴን ያሳለፍኩት። ሕይወቴ ከታመምኩ በኋላ ምስቅልቅሉ መውጣቱም ይህን ያሳያል፡፡ ጋብቻችንን የፈፀምነው ከክርስቶስ ልደት በፊት ነው ብትልም በጣም ጥሩ ነው፡፡ በ02/02/2008ዓ.ም-በተራ ቁጥር 031883፣ በክብር መዝገብ ላይ ተመዝግቦ ነው፡፡ የሚገኘው ጋብቻችን፡፡ ከዛም በኋላ አንድ ወንድ ልጅ፣ አንዲት ደግሞ ሴት ልጅ ወለድን፡፡ የጠቀሰችው ዓመተ ምህረት ግን ትክክል አይደለም፡፡ የሚገርመው ለዚህ ጋዜጣ የሰጠችውና ለፍርድ ቤት ያቀረበችው ተመሳሳይ አይደለም፡፡ በተለይም መላ ቤተሰብዋን ምስክር አድርጋ ካቀረበቻቸው ላይ ሁለቱ በጠቀሰችው አመተ ምህረት ይወለዳሉ ወይ ነው ጥያቄው፡፡ የልጆቼ እናት ናትና ምን እላለሁ፡፡
ባለቤትህ ባለፈው ሳምንት በአዲስ አድማስ ላይ ያቀረበችውን ቅሬታ እንዴት ታየዋለህ?
ባለፈው ሳምንት ጋዜጣ ላይ አሜሪካ ለኮሪያ ወይም ለራሺያ የማትሰጠው አቲካራ ሆኖ ባገኘውም የሰጠችው ቃለ ምልልስ፣ ምንም ብንለያይም፣ የልጆቼ እናት ናት፡፡ ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡ ልጆቼን የሚጎዳ ነገር እዚህ ላይ መናገር አልፈልግም፡፡ ልጆቼ በእኔ እንዲያፍሩ አላደርግም። ሁሉም ያልፋል፡፡ እኛም ራሱ እናልፋለን፡፡ ግን መጥፎ ታሪክ ሰርተን፣ ወይም የማይጠፋ ቃል ተናግረን ካለፍን፣ የእኛ ሸክም ልጆቻችን ላይ ይከመራል፡፡ እነሱ በማያውቁት ነገር ሲጎዱ ይኖራሉ፡፡ ስለዚህ አቀራረቡ ቢያሳዝነኝም አልፈዋለሁ፡፡ ሌላው ...የተካሰስነው እኔ እና እርሷ ነን፡፡ በእኔ ዙሪያ ማንንም እንድታይ ፈቃደኛ አይደለችም፡፡ ግን የመጨረሻ የማሳስባት ነገር ቢኖር፣ ከኮሚቴው ራስ ላይ ትውረድ፡፡ አንዱ ወይም መላ ኮሚቴው በስም አጥፊ ቢከሳት የለሁበትም፡፡ ሽመልስ አበራ ጆሮ ነው ሚያጭበረብር? ኮሜዲያን ደረጀ ኃይሌ ነው እሚያጭበረብር? መንገሻ ተሰማ ነው እሚያጭበረብር? ፍርያት አትክልት ነው እሚያጭበረብር? መሳይ ወንድሜነህ ነው እሚያጭበረብር?  እስከ ዛሬ ከሰማኋቸው ዜናዎች “አዬ ጉድ” የሚያስብል ወሬ ነው... እራሷ ገንዘብም ቆጥሬ አላውቅም፡፡ አዲስ አበባ ያሉትን ጓደኞቼን ... እስክድን እንኳ አቅቶሽ፣ ያለ ስሜ ስም ሰጥተሽ፣ ለጉዋደኞቼ ተናግረሽ ሲርቁኝ ጥሎኝ ያልሄደውን ፍርያትን “የእርሱ አፈ ጉባኤ” በማለትሽ ፀፀቱ ለራስሽ ነው፡፡  ሰይፉ ፋንታሁንም እስከ ዛሬ ተገናኝተን፤ “ህዝቡን እንዴት መዝረፍ አለብን” በሚለው ላይ ተገናኝተን አውርተን አናውቅም:: በኮሚቴው ላይ ያነሳሽው አሰስ ገሰስ ወሬ ጊዜውን ጠብቆ ትከፍይበታለሽ። ኮሚቴዎቸን በተመለከተ የራሳቸው ዝና ያላቸው ናቸው፡፡ እንኳን እርሷ ልታጎድፋቸው፣ እኔም ብሆን ቀና ብዬ ለማየት የማፍር፣ ከእነርሱ ጋር ብጣላ ከመላው ኢትዮጵያ ህዝብ ጋር እንደምጣላ አውቀዋለሁ፡፡ እነሱ ሲጠይቁኝ ነው መኖሬ የሚሰማኝ፡፡
ኮሚቴው ራሱ “እኛ ገንዘቡ ቢገባ እንተማማለን፣ በአንተ ስም በተከፈተ አካውንት ይግባ” ተብዬ ነው በእኔ ስም የተከፈተው፡፡ ከሰይፉ ሾው በሁዋላም አንዲት ሳንቲም ነክቼ አላውቅም፡፡ ሂዱና በብርሃንና ሰላም ቅርንጫፍ ንግድ ባንክ ተመልከቱ፡፡ የባህር ዳር ልጆች ምስክር ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ገንዘቡን በባንክ አስገቡ ሲልዋቸው፡፡ እኔ ጋ ቼኩ አልደረሰም። ቢጠፋበት አንድ ሰው ብለው፤ ተመንዝሮ ነው የተላከው፡፡ እኔም ለጤናዬ እንጂ ገንዘቡ የሚውለው፣ በፍፁም የኢትዮጵያ ህዝብን አላጭበረብርም፡፡ አንቺ እኮ እኔን ስታጭበረብሪ ነበር፡፡ ሁሉንም ባንቺ ሂሳብ አትለኪ። ፍርድ ቤቱ ባግባቡ ይፍረድና፣ እኔ ጤናዬን እንጂ ሁሉም ነገር ለልጆቼ ይውላል፡፡ እርሱንም በእኔ በአባታቸው ስም ከተጠሩ ብቻ ነው፡፡
ከባለቤትህ ጋር ለፍቺና ለፍርድ ቤት ያበቃችሁ ነገር ምንድን ነው?
ከዛ በፊት ታስሬ ነበር፡፡  ምክንያት በሌለው ምክንያት። በእርስዋ ምክንያት፡፡ ወይ ሐምሌ መጀመሪያ ላይ ወይም ሰኔ መጨረሻ ላይ፡፡ ሐምሌ ላይ ታሰርሽ ማለት ደግሞ ጉዳይሽ ጥቅምት መጨረሻ ላይ ነው የሚታይልሽ፡፡ መንግሥት በምን  ልሰረው እያለ፣ ወስዳ ከተተችኝ ሚስቴ፡፡ ብታሰር አሪፍ ነበር፡፡ ይህን ሁሉ ፈተና አላይም ነበር፡፡ ከባድ የመኪና አደጋ ያስተናገድኩትም ከዛ በኋላ ነው፡፡ ያው በእርሷ ምክንያት ማለት ይቻላል፡፡ ለምን? ሀዋሳ ውስጥ ነኝ ብላ ለእህቴ ተናገረች፡፡ እኔ እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ ነበርኩ ማተሚያ ቤት፡፡ ባንክ ቤት ሄድኩና “ወይ ሸጣችሁ ክፈሉ ወይም እኛ ጨረታ ልናወጣው ነው ቤቱን” ተባልኩ። ለባንኮቹ እንኩዋን ቤቱን ራሴንም ቢሸጡኝ ክብር አለኝ፡፡ አከብራቸዋለሁ፡፡ ረቡዕ ነበር፡፡ ወደ ሀዋሳ በዛው ነዳሁት፡፡ እህቴ ቤት አደርኩ፡፡ ሐሙስ በጥዋት ገዢ ፍለጋ ተነሳሁ፡፡ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ገዢ አገኘሁ፡፡ ከዛ ወደ ሻሸመኔ ሄድን፡፡ ወደ እህቴ ደወልኩና “በዓይኔ እየሄደብኝ ነው፣ ልጄን አሳይኝ፡፡” እላለሁ እኔ፡፡ “ሀዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል ናት ሰው ታሞባት” ትለኛለች እርሷ፡፡ “ትጨርስና አምጥቼ ልጅህን አሳይሃለሁ።” ከዛ ከጆሮዬ ጥልቅ አለ አንድ ነገር፡፡ ሀዋሳ ውስጥ የለችም፡፡ አብረን ለገዢው ብንሸጥለትስ? አዲስ አበባ ናት፡፡ እንዲያውም ለሃያ ሁለት ቀናት አዲስ አበባ ናት፡፡ ከዛ ወደ ይርጋለም እየነዳሁት ነበር፡፡ ያደፈጠ መኪና መጥቶ እስኪጋልበኝ ድረስ፡፡ ከዛ በኋላ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ነቃሁ፡፡ መናገር አልችል፣ መጻፍም አልችልም ነበር፡፡ ቀስ ቀስ እያልኩ ነው የተለማመድኩት፡፡ እንዲያውም… መቆም አይችልም ብለው ነበር አሉ ሀኪሞች፡፡ ይቅርታ አድርጉልኝና ከሰማይ ከምድር ያህል የሚከብደኝ ቂጤ ነበር፡፡ ሽንት ቤት አንድ ቀን ገባሁና ተቀመጥኩ፡፡ መነሳትም አልችልም፡፡ አልናገርም፡፡ እንዴት እህቴን ልጥራት፣ ብልጎመጎም፣ ብልጎመጎም፡፡ ከብዙ ሰዓት በኋላ እህቴ መጣች፡፡ ከዚሁ ጋር… ወንድሟ ሰው ገጨ ተብሎ ብትሰማ፣ እንባዋ ማባሪያ ጠፋው፡፡ ወንድሟ ታልቅስ፡፡… እንዲያውም በእኔ ጊዜ፣ አዲስ አበባ ሰምታ፣ “ኢየሱስን አመስግኑ” በማለት … አሁን ወደ ኋላ ታሪኬን ሳጠና፣ መላ የሀዋሳ ህዝብ አዝኖ፣ እነሱ ግን አልመጡም … ፀሎት ላይ ነበሩ፡፡ የልጃቸው አባት ነበርኩ፡፡
አዲስ አበባ ውስጥ ከቅርብ ጓደኛዬ ጋር ለ22 ቀናት ነበረች፡፡ እኔና እሱ በቀን በቀን እየተገናኘን ነበር፡፡ ለ22 ቀናት ባለቤቴን እንዳስቀመጠ ግን አልነገረኝም፡፡ አሁን የሚለው ግን “ልጅህ ታሞ” ብላ ደውላልኝ መጣች፣ እርሱ በችግሩ ጊዜ ከእኔ እንደማይወስድ፣ ልጅህን ላሳክምልህ ነው” የሚለኝ፡፡ ሆኖም እንደ እኔ ባጋጣሚ ሳይሆን፣ የሚፈልገውን ላሟላለት ነው ልጄን የወለድኩት፡፡ ደሜ የፈሰሰውም ለእርሱ ነው፡፡ የአራት ሰው ደም ነው የወሰድኩት፡፡ በዛ ላይ ቆንጆ ልጅ ነው፡፡ እንደምወደው እያወቀ፣ ሌሊት ሌሊት በህልሜ ከእርሱ ጋር እንደማድር እያወቀ፣ ባለቤቴን ከቤቱ እንዳስቀመጠ ሳላውቅ…፡፡ እሷ እሱ ቤት ሆና እንድትከሰኝ አመቻችቷል፡፡ እኔ ሳላዉቅ፡፡ እኔ ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ወጥቼ እያገገምኩ፣ ጠበቃ የሆነ አንድ ጓደኛ ነበረኝ፡፡ “አራዳ ፍርድ ቤት ባለቤትህ ስትመላለስ ነበር” አለኝ፡፡ ቅርብ ስለሆነ ሄድኩ፡፡ ቦርዱ ላይ ሳየዉ ከሳኛለች፡፡ ወደ ላይ ስወጣ፣ “ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ነው ያለው፡፡ እና ጉዳቱ የጭንቅላት ነው ይህን መስጠት የለብሽም፤” … ከብዙ ድራማ በሁዋላ ወደ መዝገብ ቤት ተመለሰ፡፡ “ለምን እኔ አልጠይቃትም” ብዬ ትዳር እኮ ማቆየት እንጂ አደጋው፣ ለማፍረስ ምንም እኮ ችግር የለውም፡፡ ትዳሩ ደበረኝ ብሎ እኮ ማፍረስም ይቻላል። እንኳን ይህ ሁሉ ምክንያት እያለኝ” እኔም በዛው ቀን የፍታህ ብሄር ክስ ይዤላት መጣሁ፡፡ እኔም ስለማልስራ አንቺም ስለማትሰሪ ፍርድ ቤቱ “ይህ ያንቺ፣ ይህ የእኔ” እስኪለን ድረስ አብረን እንኑር፤ ተባብለን አብረን መኖር ጀመርን፡፡ ማድረግ ያልነበረብኝ ነገር ነው … እስከ መጋቢት 29/2010 ድረስ፡፡ ወይ አንሰለጥን፣ ወይም ደግሞ…፡፡
ወደ ፍርድ ቤት ከመሄዳችሁ በፊት ችግራችሁን በሽምግልና ለመፍታት አልሞከራችሁም?
እኔ ከአስራ አምስት  ጊዜ በላይ ሽምግልና ሞክሬአለሁ። እነ ዶክተር እዝራ፣ እነ አየለ እምሩ፣ እነ ብርሃኔ ዘርው፣ እነ ሽመልስ አበራ ጆሮ…፡፡ እኔ እርሷን አልከሰስኳትም፡፡ ክስዋን የሰጠችው ለፖሊስ ነው፡፡ እኔ ታምሜ ምንም አላይም፡፡ ከዛ ወደ መዝገብ ቤት ተመለሰ፡፡ ደግሞ እኮ ይነገራል፡፡ እኔ ሄጄ ባየው ጊዜ በጣም ነው የተናደድኩት፡፡ ደግሞ ወዲያውኑ ነው የወሰንኩት፡፡ ሰው ከጠላቱ ጋር አይኖርም፡፡ እሷም ያሰበችው ይኖራል፡፡ እንዲህ በቀላሉ ትዳር የሚያስፈታ ነገር ምን አለ? እኔን ጨካኝ አድርገው የሳሉ ሰዎች ይኖራሉ፡፡ ምንም የማላውቀው ነገር  ስላለ ነው፡፡ ድርጅት ነበረን፣ እኔ ስተኛ አብሮ ተኛ፡፡ ሠራተኞች ነበሩ፤ እየነቃሁ ስመጣ ግን በሙሉ ተበትነዋል፡፡ ምን አለ አሁን ተቀምጦ ሂሳብ ከመስራት፤ እንደ ባለትዳር የማታስተዳድረው ድርጅቱን?... በጣም አሳዛኝ ነው፡፡ ሽምግልናው ሰልችቶኛል፡፡  ቃል ተጠብቆ፣ ይህን ያሉኝን አላደርግም ብሎ አይሆንም፡፡ ቂም አንድ ቀን እስኪያስተምራት መጠበቅ ነው፡፡
ፍቺ ከጠየቅህ በኋላ ከአንዴም ሁለት ጊዜ ፍርድ ቤት ያልቀረብክበት ምክንያት ምንድን ነው?
ይህን ህጻን ልጅም ይመልሰዋል፡፡ በውክልና፣ እራሴን ሆኖ ሚከራከር ጠበቃ ጉዳዩን ሰጥቻለሁ፡፡ እኔ አልናገርም። ዳኛዋን እንደ እርሷዋ በእንባ ለመብላት ነው እንዴ? ሳልናገር ተቀምጬ፣ ዳኛዋን ትክክለኛ ፍትህ እንዳትሰጥ አላደርጋትም። ለፍትህ መዛባት ሲሉ፣ የማይደረግ ነገር የለም።  ናፈቅኳት እንዴ?... ይህ የምትለውን ስታጣ ግራ ገብቷት ነው፡፡
ሰኔ 26 ለተያዘው ቀጠሮስ ትቀርባለህ?
እንዳልኩሽ ነው፡፡ ግን ጠበቃዬ በህመም ወይም በሌላ ነገር ከቀረ፣ እኔ ሄጄ በፅሁፍ የምጠየቀውን ልመልስ እችላለሁ፡፡ የከበደኝን “ጠበቃዬን ላማክርና እርሱ ይመልስላችኋል” ልል እችላለሁ፡፡ እኔ በፅሁፍ ይመለስ ወይም አይመለስ አላነበብኩም፡፡
በአሁኑ ሰዓት ባለቤትህና ልጆችህ በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ ታውቃለህ?
የእርሷን መኖሪያ አላውቅም፣ ልጆቼን ብታሳየኝም ጥሩ ነበር፡፡ አዲስ አበባ ነች ስላት ሌላ ሀገር ትሄዳለች፡፡ የአንተ ልጆች አይደሉም ነው የምትለኝ፡፡ ርካሽ ዝና ከእኔ ትወስዳለች እንጂ ልጆቼን አታሳየኝም፡፡ ለምሳሌ እስከ 17,000 ብር ይከራይ ነበር ቤቱ፡፡ ባለፈው እዚህ ጋዜጣ ላይ፣ ሰብራ ገባሁበት ያለችው፡፡ የኪራዩ ውልም እኔ ዘንድ አለ፡፡ እኔ ታምሜአለሁ፡፡ ነገርን ከማፋፋም ተቆጥባ፣ ሰብራ ከምትገባ እህቴ ሙሉ ውክልና አላት፡፡ እሷ አከራይታው መኖር አትችልም ነበር?... ወይስ የእኔን ስም ካላጠፋሁት ነው?... ስንቱ የተጣላ እየታረቀ፣ ፍርድ ቤት ንብረት አከፋፍሎ፣ ሰማኒያችንን እስኪቀደው ድረስ ለምን ሰላም ማጣት ያስፈልጋል? … እህቴ ለእርሷ እንጂ ለእኔ አድልታ አታውቅም። ግልፅ ናት፡፡ ሰከን ብላ ማሰብ አለባት፡፡ መካሪዎች ምንም ሊያደርጉላት አይችሉም፡፡ በባለፈው ጋዜጣ ላይ የመካሪ ቃላት ተሞልታ እንደ መጣች ግልፅ ነበር፡፡ ሁሉንም ስድብ ባለቤት ባለቤቱን እያወቅኩት ነበር፣ ይቺ የእገሌ ናት…ወዘተ።  ...አዶኒ ይስማዕከ፣ እና መልእክተ ይስማዕከ ብዬ ለልጆቼ ስም አውጥቼ ነበር፡፡ ሳልጠራችሁ ቀረሁ እንጂ፡፡ እነሱን ግን “ልጆችህም የአንተ አይደሉም” ብላለች፡፡ … አዲስ የእናቶችና የህፃናት ሆስፒታል ሂዱና አረጋግጡ (ከቀበና ገባ ብሎ ነው ያለው)… “Baby Tsega Andarge” የሚል ነው ስሙ፡፡ እኔ አባታቸው ቆሜ ነው ያዋለድኳቸው፡፡ የሚያስፈልገውን ነገር አደርጋለሁ ለልጆቼ፡፡ ልጆቼ ሲታመሙም፣ ትኩሳት ሲኖራቸውም ወስጄ አሳክማለሁ፡፡ እስከ ዛሬም ድረስ ያው በእኔ ስም አይጠሩም፡፡ ወደ ሶስት አመት ሊሆነው ነው፡፡ እኔ ግን አንገቴን ደፍቼ ነበር የማሳክመው፡፡ በጣም ነውሩን የሚያውቁት ብልህ ሴቶች ናቸው፡፡ አባታቸውን በመጠየቅ ሲያድጉ፣ መከራዋን የሚያበሏት እሷን፡፡ በጥቅሉ…  በሌላ ነገር ቢያስጠረጥራትም፣ እኔ ግን ልጆቼን ማንም አይነጥቀኝም፡፡  
የሚላስ የሚቀመስ በሌለበትና ለመኖሪያ በማይመች ቤት ውስጥ እንዳለች ነው የነገረችን …
ሰብራ የገባችበት ቤት ነው? በህግ ያስጠይቃታል፡፡ በቁጥጥር ስር ያዋለችው ሆቴል፣ ያው ከእንጀራ እናቱዋና ከአባቱዋ ቤት አጠገብ ነው፡፡ እኔ እኮ በፍትሀ ብሄር ነው የከሰስኩዋት፡፡ ፍርድ የእርሷ ነው ካለ፣ የእርሱዋ ነው አይደለም; … “እግዚአብሔር ሲያሸነፍህ፣ ራስህን ነው ቀድሞ ስህተት የሚያሰራህ” …የንግድ ቤት ነው፡፡ “መስተዋቱ ያንፀባርቅብኛል፣ መስተዋቱ ረበሸኝ” ብላለች፡፡ ሆቴል ነበረ። እኔ እንኳ ለመኖሪያ ቤት ተመኝቸው አላውቅም፡፡ ከባንክም ባለፈው ዓመት ተበድረንበታል፡፡ እኔ አዲስ አበባ ውስጥ ከከተማ እርቄ ተከራይቼ እኖራለሁ፡፡ እሷ ደግሞ ተከራይቶ ለባንኩ በሚከፈልበት ቤት ውስጥ ትኖራለች፡፡ እስከ 17,000 ብር ድረስ ይከራያል፡፡ የአንተ አይደሉም የምትለኝ ልጆቼ፣ በዚህ ያድጉበት ነበር፡፡ ይህ ሆኖ እያለ፣ ለልጆቼ ክፈል ትላለች፡፡ ብዙ የተከራየ እቃ ያለበት ነው፡፡ ነገ ለሚነሳው ጥያቄ መልሷ ምን ይሆን; ጥበቃውንም አባራዋለች፡፡ “እዛ ግድም አትድረስ ተብያለሁና፣ እኔ ለህይወቴ አደገኛ ነው” ብሎናል፡፡
ዋና መንገድ ላይ ያለ እና ለሆቴል ሲባል ነው የተሰራው እንጂ ለመኖሪያ አይደለም፡፡  መልእክቱ እሱን ለእኔ ስጠኝ እኮ ነው - የባለፈው ጋዜጣ ላይ የወጣው፡፡
1ኛ. እኔ ታምሜ እያለሁ ድርጅቴን ዘጋችው- ወደ ሶስት መቶ ሺህ ብር የቤት ኪራይ እያለበት፡፡
2ኛ. ቤት ሰብራ ገባችበት- የሚከራየውንና ለልጆቼም ለእኔም የሚያኖረንን፡፡
3ኛ.ከዚህ በፊት የወሰደችው 110,000 ብር አለ፡፡ ምስክሮች አሉ፡፡
4ኛ. በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙትን የባንክ አካውንቴን አሳግዳብኛለች፡፡ ይህ ራሱ በቂ ነው ለእሷ ላለመክፈሌ፡፡ በየትኛውም ባንክ ያለህ፣ ይስማዕከ ብለህ ግባማ አንድ ጊዜ ታግዷል አለህ? ..በቃ፡፡
ይህ ጭራሽ ምቀኝነት፣ ካልሆነ በቀር፣ ባለፀጋዋ ነው በእንባ አባብላ የነገረቻችሁ፡፡ እውነቱ ይውጣና ለልጆቼ እንጂ ለራሴ ምንም አልፈልግም፡፡ እኔ ከዳንኩ ከዜሮ ጀምሬ እጥራለሁ። አብረን ባንኖርም፣ የልጆቼ እናት ለማኝ ሆና እኔ እንቅልፍ የሚወስደው አዕምሮ የለኝም፡፡ ለዚህ ሁሉ ምክንያቱ ራሷ በመክሰሱዋና አብረን ስንት ወራት ስንኖር አለመናገሩዋ ነው፡፡ የቤቱ ጉዳይ ግን እየተከራየ ለባንክ ተከፍሎ ቢሆን ጥሩ ነው፡፡ አለበዚያ ነገ ደግሞ ሊሸጠው እንዳይመጣ፡፡ እኔ ታምሜአለሁ። በአስማት የምሰራ ይመስለዋል ሰው? እሱ “የኦጋዴን ድመቶች” ላይ ብቻ ነው ያለው፡፡ እኔ ደግሞ ደሙን በብድር ነው የወሰድኩት፡፡ የአራት ሰው ደም ተቀብያለሁ ማለቴ ነው፡፡  
መጨረሻ አካባቢ ትኖሩበት ከነበረው ባሻ ወልዴ ችሎት የጋራ መኖሪያ በሌለችበት ቤት ቀይረህ መሰወርህንና የማተሚያ ማሽኖችን ማሸሸህን ተናግራለች፡፡ እውነቱ ምንድን ነው?
በመጀመሪያ ፋሲካ ሲደርስ፣ “አንተ ካልሄድክ ወደ ሀዋሳ እኔ እሄዳለሁ” አለችኝ፡፡ መናገር አልችልም፣ አብረን ሄድን ሀዋሳ። አዲስ አበባ ሳለሁ የሚደውሉልኝን በነጋታው አገኘቻቸው። በሴት እንባዋ አደረቀቻቸው፡፡ (ፈፅሜ ካላዘንኩ እኔ እንባዬ አይመጣም)፡፡ ብዙዎቹ ደነገጡ፡፡ በእኔም ላይ አዘኑ፡፡ የእኔን መልስ ሳይሰሙ ማለት ነው፡፡ አንዳንዶቹ መደወል የጀመሩት አዲስ አድማስ ጋዜጣን ካነበቡ በኋላ ነው፡፡ ለእኔ እኮ እንደዚህ ነበር ያለችኝ፡፡ አሁን እሱን ገልብጣ ጋዜጣ ላይ አወጣቸው፡፡ የስራዋን ይስጣት፡፡ አስገድዶ ወሰደኝ ማለት ምን ማለት ነው; እኔ እኮ ግማሽ ጭንቅላቴ ባዶ ነው፡፡ ጠጠር ቢያገኘኝ እሞታለሁ። ውጪ አገር ቀዶ ጥገና የሚካሄደውም ለእርሱ ነው፡፡ የእኔን በሽታ ለማረጋገጥ ሆስፒታሎቹ ሁሉ ክፍት ናቸው፡፡ ጥቁር አንበሳ ለአይኔ በምኒልክ ሆስፒታል እንዲሰራ ሪፈር ፅፎ ነበር፡፡ የዓይኔ ቀዶ ጥገና ለሚጥለኝ በሽታ የምወስደውን ለሁለት ዓመት በቀን ሶስት ጊዜ፣ ማደንዣውን በመፍራት፣ ሌሎች ይደረጉ በሚል የምኒልክ ሆስፒታል ሌሎች እስኪደረጉ እየጠበቀ ነው፡፡
ሀ) አስቸኩዋይ የጭንቅላት ቀዶ ጥገና (Cranioplasy)
ለ) ለሚጥል በሽታ ጭንቅላት ውስጥ የሚወጣ (Eplepsy)
ሐ) የመናገር ልምምድ (Speech Therapy)
መ) የማገገምያ ህክምና (Rehablitation)
ይህ እውነት ለመሆኑ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል፣ ማንም ሰው ሄዶ ማረጋገጥ ይችላል፡፡ በተጨማሪም ለእኔ ማስረጃ ተሰጥቶኛል፡፡ ሁሉን ነገር ይዤ በተጠየኩት ቦታ ሁሉ እቀርባለሁ። …የጥቁር አንበሳ ሆስፒታልን ማስረጃ ማጣጣል ግን፣ በህግም ያስጠይቃል፡፡
እግዚአብሔር ልቦና ይስጣት፡፡ አንድ ሳምንት ብለምናት ወደ አዲስ አበባ አልሄድም አለች፡፡ እንዲያውም የሚጥል በሽታዬ ተነስቶ ጣለኝ፡፡ ቤታችንም ኪራዩ እየደረሰ ነው ወር በገባ በ16 ነው የቤት ኪራይ የምንከፍለው፡፡ የሦሥት ወር ነው 22,500 ብር ይህን ገንዘብ መክፈል አልችልም፡፡ በዚህ ጭንቀት ላይ እያለሁ፣ “ሀዋሳ ቤተሰቦቿ ጋር ሆና “ልብሴን ላኩልኝ፣ እኔ አልመጣም። የህፃናቶቹንም አንድም ሳታስቀሩ” ብላ ለእህቴ ደወለች። ጠበቃዬን ወዲያው አማከርኩ፡፡ የእለት ስለሆነ ትውሰድ አለኝ፡፡ ከአጎትዋ ጋር ናርዶስ የምትባል የአክስቷ ልጅ መጣች። መኪናው ሞላ ብለው አንዳንድ እቃ አስቀሩ፡፡ ከዛ ይመለሱ ከሆነ ቢሮ አስቀምጪላቸው አልኩዋት፤ ለእህቴ ነገርኩዋት፡፡ ከዚህ በኋላ እኔ ልጆቼን አሳድግበታለሁ ብዬ እንጂ ለእኔማ ምን ይሰራልኛል ብዬ ቤቱን ለቅቄአለሁ፡፡ በፍጹም የሱዋን እቃም አልነካሁም፡፡ ፖሊስ ይዤ ነው እቃውን ያወጣሁት፡፡  ይህን ነገር አታሎኝ መጣ ምናምን ያለችው ይህንን ነው፡፡ የሚገርመው ነገር፣ የእኔ ግማሽ ጭንቅላቴ በህመሙ ምክንያት ታውኳል፡፡ “እኔ አልመጣም” ብላ አታሎኝ ነው የምትለው? በእጅ በእግሬ ገብታ /እባክህ/ ብላ ቤተሰቦቹዋ ጋር ለወሰድኳት! እንዴት እኔ ከፈታኋት ሚስቴ ጋር አቲካራ እገጥማለሁ? እንደለመደችው ታሳስረኝ እንዴ? አንድ ነገር ብናገራት ስልኳ ላይ እኮ የፖሊስ ስልክ አለ፡፡ በአምስት ደቂቃ ውስጥ ነው የምታሳስረኝ፡፡
የሚጥል በሽታ ከመኪና አደጋው ጋር ካጋጠመኝ ወዲህ ጊዜ፤ “ልጄን በፍፁም ቆመህ እንዳትታቀፈው፡፡…ምን እንደ ህጻን ትንተባተብብኛለህ? ... ይህ ያልከው ነገር፣ አስተርጓሚ ይፈልጋል… ወዘተ” ትለኛለች በእናቴ ፊት፣ በእህቴ ፊት፡፡ ቢያንስ ህዝብ ይወቅውልኝ፡፡ ኧረ ብዙ ነው፡፡
ለህክምናህ አራት መቶ ሺህ ዶላር ያስፈልጋል። መባሉና መናገር ያለመቻልህ ጉዳይ እያነጋገረ ነው። ባለቤትህን ጨምሮ ሌሎችም መናገር ይችላል የሚል አስተያየት ይሰጣሉ። ለህክምና የተጠቀሰውን ያህል ገንዘብ እንደሚያስፈልግህና በትትክክል መናገር እንደማትችል የሚያረጋግጥ የሀኪም ማስረጃ አለህ?
በመጀመሪያ ለህዝብ ብለው በመቆርቆራቸው ደስ ይላል፡፡ ነገር ግን ይህን ራሳቸውም ያድርጉት፡፡ እኔ ህዝቤን ያስተማርኩ ሰው ግን እስከ ወዲያኛው ያሳዝናል፡፡ “የኦጋዴን ድመቶ”ን ስፅፍ እንኳ በመጀመሪያ ታስሬ፣ ተገርፌአለሁ፡፡ ለእኔ ከትርፉ ላይ ሰላሳ አምስት ከመቶ ነው የሚደርሰኝ፡፡ ግን ካልፃፍኩት አይኖርም ነበር፡፡ ከእኔ ውጪ ደግሞ ለማንም አልተሰጠምና አይፅፈውም፡፡ ነገር ግን እኔ የረካሁት አሁን በዘመነ አቢይ ነዳጅ ተገኘ ስባል ነው፡፡ በገንዘብ ማንም ኢትዮጵያዊ ደራሲ አይጠቀምም፡፡  ዶ/ር አቢይ እኔን ያስበኛል ብዬ አስባለሁ። ነገር ግን እኔ አንድ ልብ ወለድ ብፅፍ፣ የማንንም እጅ አላይም ነበር፡፡ በአሉ ግርማም አሳክሙኝ ቢል አንድ ቀን አሰብኩ። በእኔ ግምት ማንም አያሳክመውም  እላለሁ፡፡ ጠፋ ጠፋ ሲባል ጊዜ እንጂ ያሁኑን ያህል ዝነኛ እንደማይሆን እጠራጠራለሁ። ለእኔ ድንቁ መፅሐፍ አደፍርስ ነውና፡፡ ምን ማለቴ ነው? … መጋቢት 29/2010 ዓ.ም ሚስቴን አብሬአት የነበርኩት፡፡ ለ3 ወራት አይታመምም ያለው ማነው?... እንኳን እንደዚህ እንድሞት በጋዜጣችሁም በፌስ ቡክም ያለ ስሜ ስም ሰጥታ ህዝቡን ግራ ስታጋባው?... ሌሎች እኔን ለአንድ ቀን እንኳ አይተውኝ አያቁም። ሌሎችም የዘወትር ጠላቶቼ ናቸው። ጠላት አያሳጣን ነው፡፡ ወያኔን ያህል ጠላት ባይኖር ኖሮ፣ እኔ እኮ 13 መፅሀፍ አልፅፍም ነበር፡፡ እንኩዋን ለሁለቱ ብቻ፣ እንኩዋ እስከዛሬ 10 ወር ሞላኝ። አስቸኩዋይ የጭንቅላት ቀዶ ጥገና (Cranioplasy)፣ ለሚጥለኝ በሽታ ጭንቅላት ውስጥ የሚወጣ (Eplepsy)… እንኳ አልሳካልኝ ብሎ ነው፡፡  ግን የማያይዝልሽን (Attach) ሁሉንም እንዲያዩ ብታደርጊልኝ ጥሩ ነበር (የዶክተሮችን የምስክር ወረቀት)፡፡
ሌላው … አራት መቶ ሺህ ዶላር ብሎ የጠየቀኝም የለም። አዲስ አበባ ውስጥ እንኳ ህክምና ይለያያል፡፡ የኮሪያ ሆስፒታል እና የጥቁር አንበሳ እንኳ በገፍ ይለያያል፡፡ ስለዚህ እንዲያውም እስከ አምስት መቶ ሺህ ዶላርም ያለ የህክምና ሆስፒታል አለ። ይህን የኢንተርኔት አገልግሎትን በውል የሚያውቅ ሰው ይመልከተው፡፡ 400ሺ ብር ነው ያለችው? … “እንዲያውም ለሕዝብ ብላ አሳግደዋለች፡፡” ለካ፡፡ እኔ የህዝብ ጠላት ነኝ ለካ። ጥሩ ነው፡፡ ይህ ቀን ያልፍና ወይም ይገድለኝና እንተዛዘባለን፡፡  
ልጆችህን ለመጨረሻ ጊዜ ያየሀቸው መቼ ነው?
መጋቢት 29/2010 ዓ.ም፡፡ ከዚያ በኋላ ልታሳየኝ አልፈለገችም፡፡ ስልኬን አደለም በቃሉዋ…በሰይፉ ሾው ላይ አገር ያወቀው ነው፡፡
አፍሪ ሄልዝ ያመቻቸለትን ህክምና አልተቀበለም የሚል ነገር ተሰምቷል፡፡ በዚህ ላይ ምን ምላሽ አለህ?
አንድ የሚያቋቁሙት ቻናል  አላቸው መሰለኝ፡፡ የእኔ የጤና ጉዳይ አላሳሰባቸውም፡፡  ደግሞ ቃላቸውን አጥፈዋል፡፡ ለቻናላቸው ርካሽ ዝና ፈላጊዎች በመሆናቸው … አሁን ስናየው በእያንዳንዱ ስብሰባ ላይ ቃላቸውን ማጠፋቸው አስደንቆናል። እኔ ልሙት ተውኝ፡፡ አንዳንድ ሰዎች ግን ቃላችሁን አትጠፉ፡፡ ቃል ክቡር ነው፡፡ አምላክ እኮ መፍጠሪያው የነበረ ነው፡፡

Read 12731 times