Sunday, 01 July 2018 00:00

ዛሬ በአዳማ፣ ነገ በባህር ዳር የድጋፍ ሠልፎች ይካሄዳሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

  ዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን ጠ/ሚኒስትሩን እያደነቁ ነው

   ዛሬ እና ነገ በባህርዳር፣ ደብረብርሃንና አዳማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድን የሚደግፍ ሠላማዊ ሠልፍ እንደሚደረግ የታወቀ ሲሆን ባለፈው ሣምንት ከአዲስ አበባው ግዙፍ ሠልፍ በተጨማሪ በወልቂጤ፣ ሆሳዕና፣ ድሬዳዋ፣ ጅግጅጋ፣ አፋርና ጎንደር የድጋፍ ሠልፎች ተካሂደዋል፡፡
የየሠልፎቹ አስተባባሪዎች ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ በዋናነት ሠልፉን ማዘጋጀት ያስፈለገው ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን በመጡ 3 ወራት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ላስመዘገቧቸው ፖለቲካዊ ማሻሻያዎች እውቅና ለመስጠት ነው። በሌላ በኩል በአሜሪካ ዋሺንግተን ዲሲ እና በአውሮፓ የሚኖሩ ዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን ሰሞኑን ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን በመደገፍ ታላላቅ ሰልፎች አድርገዋል፡፡ ዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን ጠ/ሚኒስትሩን እያደነቁ ነው፡፡ “የዶ/ር ዐቢይ የፍቅር ባቡር ፍሬን የለውም፤ ቶሎ መሳፈር ነው፤ እሚያደርሰውም አዲሲቷ ኢትዮጵያ ጋር ነው፤” ብለዋል - በዋሺንግተን ለጠ/ሚኒስትሩ ድጋፋቸውን የገለፁ አንድ ምሁር፡፡
በነገው ዕለት በባህርዳር በሚደረገው ሠላማዊ ሠልፍ ላይ ግማሽ ሚሊዮን ያህል የከተማዋና አካባቢዋ ነዋሪዎች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የአስተባባሪ ኮሚቴ አባላት ለአዲስ አድማስ የገለፁ ሲሆን፤ ዛሬ በአዳማ በሚካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ላይም ተመሣሣይ መጠን ያለው ህዝብ ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የድጋፍ ሠልፉ በባህርዳር መስተዳደር እውቅና ማግኘቱ የተገለፀ ሲሆን የከተማዋ ወጣቶች ሠልፉን የተሣካ ለማድረግ ሣምንቱን ሙሉ ሲዘጋጁ መሠንበታቸውን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ሠልፉ በባህርዳር ብሄራዊ ስታዲየም ከጠዋቱ 12 ሠዓት ጀምሮ ይካሄዳል ተብሏል፡፡ ህብረተሰቡ በሠልፉ ላይ ከጥቃት ፈፃሚዎች ራሱን እንዲጠብቅና ለደህንነት አስጊ ሁኔታዎች ሲመለከት ለፀጥታ አስተባባሪዎች እንዲያመለክት የከተማ አስተዳደሩ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡ “ተደምረናል” በሚል መርህ በሚካሄደው በዚህ ሰልፍ ላይ ህብረተሰቡ ኢትዮጵያዊ አንድነትን በሚያንፀባርቅና የአማራን ህዝብ በሚመጥን መልኩ ይካሄዳል ብለዋል - አቶ በሠላም ይመኑ፤ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ኮሚኒኬሽን ኃላፊ፡፡
በተመሳሳይ በአዳማ ከተማ በዛሬው እለት ለዶ/ር አብይ አህመድ ደማቅ የድጋፍ ሠልፍ እንደሚካሄድ ታውቋል፡፡ በደብረ ብርሃንም ተመሳሳይ ዓላማን ያነገበ ሠልፍ ይደረጋል ተብሏል፡፡

Read 5493 times