Sunday, 01 July 2018 00:00

ፓትርያርኩ የቤተ ክርስቲያኒቱን ካህናት እንዲያወያዩ ተጠየቁ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

- የአገልጋዮችን ሥነ ምግባርና የምእመናንን ጥያቄዎች ይመለከታል
   - የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ተነስተው አዲስ ተመድበዋል

   በኢ/ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ካህናትና ሠራተኞች፣ ቅዱስ ፓትርያርኩ፣ በሀገረ ስብከቱ አሠራሮችና የምእመናን አቤቱታዎች ጉዳይ ላይ ሰብስበው እንዲያነጋግሯቸው ጠየቁ፡፡
ካህናቱ ባለፈው ረቡዕ ለፓትርያርኩ በጻፉት ደብዳቤ፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በራሷ የውስጥ አስተዳደራዊ ችግር ምክንያት፣ ክብሯና ልዕልናዋ እየተዳከመ፣ ተደማጭነቷና ተጽዕኖ ፈጣሪነቷ እየቀነሰ ነው፤ ብለዋል፡፡
የቤተ ክርስቲያኒቱን የቀደመ ስም ለመመለስና መንፈሳዊ ተልእኮዋን በአግባቡ እንድትወጣ ለማስቻል፣ የአስተዳደር ችግሮቿን መፍታት ወሳኝ መኾኑን የጠቀሱት ካህናቱ፤ በአጠቃላይ በቤተ ክርስቲያኒቱ ወቅታዊ ችግሮች ላይ፣ ከቅዱስ ፓትርያርኩ እና ከቅዱስ ሲኖዶሱ ጋራ መወያየት እንፈልጋለን፤ ብለዋል፡፡
በዋናነትም በአገልጋዮች ሥነ ምግባር፣ በሠራተኞች የሥራ ላይ መብቶች እንዲሁም በሕዝበ ክርስቲያኑ መንፈሳዊና አስተዳደራዊ ጥያቄዎች ላይ መነጋገር እንደሚፈልጉ አመልክተዋል - ካህናቱ፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቱ በአገልጋዮች አስከፊ የሥነ ምግባር ብልሽት ምክንያት ክብሯን እያጣች ነው፤ ያሉት ካህናቱ፤ ይህን ችግር ለማረም ጥልቅ ውይይትና በመዋቅራዊ ለውጥ የተደገፉ የለውጥ እርምጃዎችን እንሻለን፤ ብለዋል፡፡
የሀገረ ስብከቱ የዋና ክፍሎች ሐላፊዎች በሙሉ እንዲነሡና የጥቅም መረቦቻቸው ተለይተው በሕግ እንዲፈተሽ የጠየቁት ካህናቱ፤ ከግለሰቦች መነሣት ባሻገር ሥርዓታዊ መፍትሔን መሠረት ባደረገና የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብርና ሃይማኖታዊ ተልእኮ በሚመጥን ደረጃ፣ ከዘረኝነትና ጥቅመኝነት የጸዳ ሥር ነቀል የአስተዳደር መዋቅር፣ አደረጃጀትና አሠራር እንደ አዲስ እንዲዘረጋ ጠይቀዋል፡፡
ከ150 ባላነሱ የአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ጸሐፊዎች፣ ካህናትና ልዩ ልዩ ሠራተኞች ፊርማ የተደገፈው ይኸው ጥያቄ፣ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ በተካሔደው የቋሚ ሲኖዶስ ሳምንታዊ ስብሰባ ላይ በንባብ እንደተሰማና ሀገረ ስብከቱን በበላይነት በሚመሩት በፓትርያርኩ በኩል ምላሽ እንደሚሰጥበት በቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ተገልጾልናል፤ ብለዋል - ካህናቱ፡፡
በተደጋጋሚ ከሀገረ ስብከቱ ካህናትና ሠራተኞች፣ አቤቱታ የቀረበባቸውና ከሥራ አስኪያጅነታቸው ባለፈው ሳምንት ዐርብ፣ በፓትርያርኩ የታገዱት የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መ/ር ጎይትኦም ያይኑ ከሓላፊነታቸው ተነሥተው፣ በምትካቸው መ/ር ይቅር ባይ እንዳለ ባለፈው ረቡዕ መመደባቸው ታውቋል፡፡
የሀገረ ስብከቱ ካህናትና ሠራተኞች፣ በመጪው ሰኞ ለአዲሱ ሥራ አስኪያጅ ከሚያደርጉላቸው አቀባበል በኋላ፣ ጽ/ቤቱን ጨምሮ የ7ቱ ክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነትንና የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት አገልጋዮችን ያሳተፈ ተከታታይ ውይይት ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

Read 6519 times