Sunday, 01 July 2018 00:00

ኢትዮጵያ በአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ቁጥር በዓለም ቀዳሚ ሆናለች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 በሁለት ወር ውስጥ በጎሣ ግጭት 25 ዜጎች ሞተዋል

   በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ብሄርና ጎሣን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን ያፈናቀሉ ሲሆን፤ ይህም ሃገሪቱን በዓለም ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የአገር ውስጥ ተፈናቃይ ባለቤት አድርጓታል ተባለ፡፡
የሠብአዊ መብቶች ጉባኤ፤ ያለፉትን ጥቂት ወራት ወቅታዊ ሁኔታ በገመገመበት መግለጫው እንዳለው፤ ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ የእርስ በእርስ ግጭቶች 25 ሰዎች ሲገደሉ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ተፈናቅለዋል፡፡
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 7 ሰዎች “ከአካባቢያችን ውጡልን” በሚል ጎሰኝነት ሲገደሉ፤ በሃዋሳ በተመሳሳይ 10 ሰዎች መገደላቸውን መግለጫው ጠቁሟል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በቤኒሻንጉል ክልል ለዶ/ር አብይ ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩ 2 ወጣቶች በክልሉ ልዩ ፖሊስ ሲገደሉ፣ 40 ቆስለዋል፡፡ በለገንደቢ ወርቅ ማውጫ ማዕድን ላይ ከቀረበ ተቃውሞ ጋር ተያይዞም በነዚህ ወራት ውስጥ 3 ሰዎች መገደላቸውን ሪፖርቱ አትቷል።
ሠመጉ ባለፉት ሁለት ወራት በጎሣ ግጭት 17 ሰዎች መገደላቸውን  የገለፀ ሲሆን ሠሞኑን 12 ሰዎች በተመሳሳይ በአሶሳ መገደላቸው ይታወቃል፡፡
በቤኒሻንጉል፣ በደቡብና በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን በተፈጠረ የእርስ በእርስ ግጭት እንዲሁም በቄሊሞ ወለጋ እና በቡኖ በተከሰተ ብሄር ተኮር ጥቃት፣ ዜጎች ከቀዬአቸው ተፈናቅለው፣ በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ከፍተኛ የለውጥ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን የጠቆመው የሠመጉ መግለጫ፤ የሃገሪቱን የህግ እና የሠብአዊ መብት ጥሠቶች በማስቀረት ለውጡን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቋል፡፡
የሚዲያ ነፃነት እንዲጠናከር፣ የህግ አስከባሪ አካላት ገለልተኛ ሆነው እንደገና እንዲዋቀሩ፣ ቀሪ እስረኞች እንዲፈቱ እንዲሁም የበጎ አድራጎት፣ የፀረ ሽብርና የሚዲያ አዋጆች በአስቸኳይ እንዲሻሻሉ፤ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች ወቅት የተፈፀሙ የመብት ጥሠቶችም እንዲጣሩና ባለፉት ሁለት ወራት ህግ የጣሱ አካላት ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠይቋል- መግለጫው፡፡
ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ማህበራትና መላው ህዝብ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጀመሩ በጎ ለውጦችን እንዲያበረታቱ ሠመጉ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

Read 2475 times