Monday, 25 June 2018 12:52

የአዲስ አበባውን የቦንብ ጥቃት የአሜሪካው FBI ሊመረምር ነው *ተጠርጣሪዎቹ ነገ ፍ/ቤት ይቀርባሉ

Written by 
Rate this item
(32 votes)


ባለፈው ቅዳሜ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም ወደ ጠ/ሚኒስትርነት ሥልጣን ከመጡ ሦስት ወራት ያስቆጠሩትን ዶ/ር
ዐቢይ አህመድን ለመደገፍ በተዘጋጀው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የደረሰውን የቦንብ ጥቃት ለማጣራት፣ አሜሪካ፣ የኤፍቢአይ
ባለሙያዎችን ወደ አዲስ አበባ እንደምትልክ አስታወቀች፡፡
ከቦንብ ጥቃቱ ጋር በተያያዘ ከ30 በላይ ተጠርጣሪዎች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋላቸው የተገለጸ ሲሆን እነዚህ
ተጠርጣሪዎች በነገው ዕለት ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሏል፡፡
አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣን እንዳረጋገጡት፤ የአሜሪካ የፌደራል ምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) ባለሙያዎች
በአዲስ አበባ የደረሰውን የቦንብ ጥቃት ይመረምራሉ፡፡
በዕለቱ ከደረሰው የቦንብ ጥቃት ጋር በተያያዘ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ግርማ ካሣ
እንዲሁም የአዲስ አበባ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አስተባባሪ አቶ ተጋሩ ጎሃድባ ጨምሮ፣ ከ30 በላይ
ተጠርጣሪዎች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ሆነው፣ ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑ ታውቋል፡፡
ባለፈው ቅዳሜ በመስቀል አደባባይ ጠ/ሚኒስትሩ ከተቀመጡበት መድረክ በግምት በ40 ሜትር ርቀት ላይ በፈነዳው
ቦንብ 165 ሰዎች ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን ሁለቱ በህክምና ላይ እያሉ ህይወታቸው አልፏል፡፡ 15 ያህሉ
ለከፍተኛ ጉዳት መዳረጋቸው የታወቀ ሲሆን ለአካል ጉዳት ከተዳረጉት መካከል በዲላ ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ
ሆስፒታል ሃኪም የሆኑት ዶ/ር መኮንን ብርሃኑ በአደጋው አንድ እግራቸውን ማጣታቸውን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
አብዛኞቹ ተጎጂዎች እግራቸው፣ እጃቸውና ጭንቅላታቸው አካባቢ መጎዳታቸውን የህክምና ባለሙያዎች የገለጹ ሲሆን 3
ሰዎች እግራቸው መቆረጡም ታውቋል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ጠ/ሚኒስትሩ በቦንብ ጥቃቱ ህይወታቸው ያለፈውን ሁለት ወጣት ቤተሰቦች በስልክ
አጽናንተዋል፡፡ በጥቃቱ ህይወታቸውን ያጡት የወላይታ ሶዶ ተወላጁ፣ የ28 ዓመቱ  ወጣት ዮሴፍ አያሌው እና
የምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ተወላጁ፣ የ25 ዓመቱ ጉሳ ጋዲሳ መሆናቸው ታውቋል፡፡
የአዲስ አድማስ ዝግጅት ክፍል፤ በቦንብ ጥቃቱ ለደረሰው ሞትና የአካል ጉዳት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን
እየገለጸ፣ለተጎጂ ቤተሰቦችና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መጽናናትን ይመኛል፡፡

Read 11854 times