Saturday, 23 June 2018 12:13

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(1 Vote)

 “የነፃነት ፋና፣ የዴሞክራሲ ወጋገን፣ የዕኩልነት ጎህ፣ የዕርቅና የሰላም ኮከብ ብቅ ብሏል--”
        
    በድሮ ቀልድ እንዝናና፡፡ … በአንድ የአውሮፓ ከተማ ላይ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ተደርጎ ነበር - የሁሉም አገር ወሳኝ ባለስልጣናት የተካፈሉበት፡፡ በስብሰባው አዳራሽ አጠገብ ዘመናዊ ካፌ አለ፡፡ ካፌው በር ላይ በየመድኃኒት ቤቱ የምናየው፣ የክብደትና የቁመት መለኪያ (Body mass index machine) የሚመስል መሳሪያ ቆሟል፡፡ መሳሪያው ላይ ስትቆም የፖለቲካ እምነትህን ወይም ዝንባሌህን (Status) ያሳውቃል፡፡ …
ተሰብሳቢዎቹ በእረፍት ሰዓታቸው፣ ሻይ ቡና እያሉ ሲዝናኑ አንደኛው፤ “እስቲ አቋማችንን እንፈትሽ” አለና ማሽኑ ላይ ቆመ፡፡ ማሽኑም ‹Capitalist› ብሎ ፃፈለት፡፡ … እየሳቀ ወረደ፡፡ … የአሜሪካ መንግሥት ተወካይ ነበር፡፡ የሶቪየቱ ተወካይ ሲወጡበት ‹Social Revisionist› በማለት ፃፈላቸው፡፡ ቻይናውን ሰውዬ ‹Communist› አላቸው፡፡ አንዳንዶቹን ሶሺያሊስት፣ ሞናርኪ፣ አምባገነን … እያለ የኛ ሰውዬ ተራ ደረሰ፡፡ … “ምን ይፅፍብኝ ይሆን?” እያሉ ተጠጉና፣ በቀስታ አንድ እግራቸውን ሲጭኑበት፣ ‹C› የምትባለው ፊደል ብቅ አለችባቸው፡፡ “S” ነበር መምጣት የነበረባት፤ እኛ ሶሺያሊስት እንጂ ካፒታሊስት አይደለን” በማለት እያሰቡ፣ ያንኑ እግራቸውን በደንብ ጫን ሲሉት ፊደል ‹O› ተከተለች፡፡ ሰውየውም፤ “ለካንስ አድገናል፣ ከሶሻሊዝምም ከፍ ብለናል” ብለው ደስ አላቸው፡፡ በልበ ሙሉነት ማሽኑ ላይ በሁለት እግራቸው ቆሙ። … ምን ብሎ የፃፈላቸው ይመስልሃል?
***
“ከሰዎች ባህሪ መንግሥት ይቀረፃል፡፡ መንግሥትም በተራው የሰዎችን ባህሪ ያንፃል፡፡ የጥሩ መንግሥት አቋም፤ህዝባዊ አስተሳሰብ፣ ፍላጎትና የለውጥ ጥማትን ማርካት መቻል ነው፡፡ አስተዋይ መሪም ሲመረጥ በዚህ መንፈስ ይጠቀማል” ይላሉ ሊቃውንት፡፡
አስተዋይና ብልህ መሪ የህዝብ ልጅ መሆኑን የሚያረጋግጠው … የሚመራውን ህዝብ ህመም ሲታመም፣ ዴሞክራሲያዊነቱ … ዕኩልነትና ነፃነትን በተግባር መተርጎም፣ ፍትሃዊነቱ የህግ የበላይነት የተረጋገጠበት አስተዳደር ማዋቀር፣ ማንነቱ የአገሩ አንድነትና ብልፅግና ነፀብራቅ መሆኑ፣ ክብርና ማዕረጉ ድህነትና ጭቆና ያላሸማቀቃቸው ህዝቦች ፍቅር ሲሆን ሃይልና ጉልበቱ ደግሞ … ዕውነት፣ ዕውቀት፣ በራስ መተማመንና ከጎኑ የቆመው ለውጥ ፈላጊ ህዝብ ነው፡፡ … እናም ማንም አያቆመውም!!
“መንግሥት የእያንዳንዱን ዜጋ ሰላም፣ ነፃነት፣ መብትና ጥቅም ማስከበር ግዴታው ነው፡፡ መስመሩን ስቶ የአገሩን ህዝብ ሊጨቁነውና በኃይል ሊገዛው ከሞከረ፣ ህዝቡ ለልማትና ለዕድገት ማዋል የሚገባውን ዕምቅ ኃይል፤ ለጥላቻና ለተቃውሞ፣ ለቁጣና ለአመፅ ያውለዋል” … ይለናል ታላቁ ጠቢብ … ስፒኖዛ!!
ወዳጄ፡- የእኛ አገር መንግሥትና ፖለቲካው መስመሩን ለቋል፡፡ የምናውቀው ነገር ቢሆንም መንግሥት በራሱ በተደጋጋሚ አረጋግጦልናል። በስብሰናል! ገምተናል! የተባለበት ጊዜም ነበር፡፡ … አልተሻሻለም እንጂ፡፡ … ህዝባዊና መንግሥታዊ አገልግሎቶች ሙስና ፖዘቲቭ ሆነዋል፡፡ ዘረኝነትና ጠባብ አስተሳሰቦች ስር ሰደዋል፡፡ ግጭት፣ መፈናቀልና መሰደድ የዕለት ተዕለት ጉዳያችን እየሆነ ነው። የንግግር፣የጽሁፍና ሰልፍ የማድረግ ነፃነት የለም፤ ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያና ነፃ ፕሬስ ኢምንት የሚሰኙ እንኳ አይደሉም፡፡ … እውነት እውነት እልሃለሁ … ህገ መንግሥታችን ተቀስፏል፡፡
አገራችን የ24 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ ተሸክማ ታቃትታለች፡፡ የኑሮ ውድነት አይናችን ውስጥ የተደረገመ ሚጥሚጣ ሆኗል፡፡ ስራ አጥነት ጣራ ነክቷል፡፡ ከተማችን በኔቢጤዎችና በጎዳና ተዳዳሪ ልጆቻችን ተጨናንቃለች፡፡ ዘራፊና አዘራፊ ግን “አገራችን አድጋለች” እያለ ይሰብከናል፡፡ አገር ማለት እኛ አይደለንም እንዴ? ወይስ የማናውቃት ‹ህቡዕ› አገር አለች? … አስተማሪ፣ መካሪና አስታራቂ መሆን የሚገባቸው አንዳንድ የእምነት ተቋማት፤ በጉያቸው የሚያስገናግዱት ውዝግብና የእርስ በርስ ሽኩቻ ሳያንስ የሌባና የወሮበላ ምሽግ ሆነዋል፡፡ የትምህርት ተቋሞቻችንም የሙሰኞችና የአድርባዮች መቅደስ እየሆኑ ነው፡፡ ስም የሚያስጠራ ሳይንቲስትና አርቲስት፣ ለዕውነትና ለመብት የሚሟገት የህግ ሰው ማፍራት ዕዳ ሆኖባቸዋል፡፡ የግዢና ፎርጅድ ማስረጃዎች ለመንግሥት አስተዳደር ሰራተኞች፣ በነፍስ ወከፍ የታደለ እንደሚመስል የፌደራልና የክልል መንግሥታት ነግረውናል፡፡ አለም አቀፍ መስፈርትን የማያሟላ ‹አለም አቀፍ ማዕረግ› የሚሰጡ ቡድኖችም ተፈልፍለዋል። ተሿሚዎቹና ማዕረግ ተቀባዮቹ ራሳቸው እንዲጨንቃቸውና ግራ እንዲገባቸው ያደረጉ!!
መከላከያ ተቋሞችም ታመዋል፡፡ ሙስናና ኋላ ቀር በሆነው የማን አለብኝ አስተሳሰብ ተበክለዋል። ደህንነቱ ኢትዮጵያዊ መሆኑ ያጠራጥራል፡፡ ባሰማራቸው አውደልዳዮች የሚያደርሰው ጥቃት አንሶ፣ የሰላማዊ ዜጎችን ስልክ በመበርበርና መልዕክት በመጥለፍ (bugging) የዜጎች ነፃነት እንድታጣጥር እያደረገ ነው፡፡ … በእርግጥም ህገ መንግሥታችን ተቀስፏል፡፡
ወዳጄ፡- ዘመኑ መቀየሩን ልብ በል እንጂ፡፡ ታሪክ የምትለው የጦርነትና የደም መፋሰስ፣ የመውረርና የመወረር፣ የማሸነፍና የመሸነፍ፣ ግዛት የማስፋፋትና ኢምፓየር የመገንባት ጉዳይ ጊዜው አልፎበታል። አነጣጥሮ መታኮስና ‹ጀግና› መባል የሚችለው በልጆች የተረት መጽሃፍ ላይ ሆኗል፡፡ … እንደ ሮቢን ሁድ!! … ቀስት፣ ጎራዴና ጦር ለጠመንጃና ለመድፍ ቦታቸውን እንደለቀቁ፣ ጠመንጃና ታንክም ቦታቸውን ኮሚፒተራይዝድ ለሆኑ ድሮንስ፣ ሚሳኤሎችና ለመሳሰሉት ሰው አልባ ማሽኖች እየለቀቁ ነው፡፡ ስለላም በረቀቁ ሳተላይት ካሜራዎች፣ ጂፒኤስ እና በዓይን በማይታዩ ሮቦቶች ተተክቷል፡፡
የዚህ ዘመን ጀግኖች፤ አዳዲስ የሳይንስና የጥበብ ፈጠራዎችና ግኝቶችን የሚያስመዘግቡ ናቸው፡፡ ጨዋታው ተጀምሮ የሚያልቀው ጭንቅላት ውስጥ ሆኗል - በአስተሳሰብ ልሂቅነት!! … የፌስቡክ፣ የአፕልና የመሳሰሉትን ቴክኖሎጂዎች የፈጠሩትን አስባቸው። የዘመኑ ጀግኖችና ሃብታሞች እንደነሱ ዓይነት ናቸው።ሀብት የሚፈጠረው በጭንቅላት ነው። በዘረፋና በማጭበርበር ከሰበሰብክ ሌባ ነህ!! የሌባ ቦታ ደግሞ የት እንደሆነ፣ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ነግረውሃል፡፡
ወዳጄ፡- ለማንኛውም ህገ ወጥነት መሽቶበታል። አገራችንና ህዝባችን ለውጥ ይፈልጋል፡፡ የሁዋላ ቀርነት፣ የጭቆናና የፀረ ዴሞክራሲ አተላ ተወግዶ፣ ኩልል ያለ ሪፎርም የጊዜው ጥያቄ ነው፡፡ የነፃነት ፋና፣ የዴሞክራሲ ወጋገን፣ የዕኩልነት ጎህ፣ የዕርቅና የሰላም ኮከብ ብቅ ብሏል፡፡ የዛሬው ሰልፍ የዚሁ ምስክር ነው። BRAVO OUR PM!!
***
ወደ ቀልዳችን ስንመለስ፤ የአገራችን ተጠሪ፣ ማሽኑ ላይ አንድ እግራቸውን ሲጭኑ፣ ‹C› የምትባለው ፊደል ብቅ ማለቷን፣ ጫን ሲሉ ደግሞ ፊደል ‹O› መከተሏን ነግሬህ ነበር፡፡ አሁን በልበ ሙሉነት፣ በሁለት እግራቸው ቆሙበት፡፡ … የተቀሩት ፊደሎች ተደረደሩ፡- …. c, f, u, s, e, d …  እያሉ፡፡ አንድ ላይ ሲነበቡ “CONFUSED!!” የሚሉ ነበሩ፡፡
ወዳጄ ልቤ፡- አንድ ጥቅስ ልመርቅና እንሰነባበት። “ነፃነትና አንድነት አሁንም መቼም አንድና የማይነጣጠሉ ናቸው፡፡ “Liberty and Union, now and forever one and inseparable” የሚለን ታላቅ ሰው … ዳንኤል ዌብስተር ነው፡፡
ሠላም!!

Read 794 times