Saturday, 23 June 2018 12:01

ስደተኛው የደቡብ ሱዳን ሚኒስትር በጋምቤላ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(5 votes)

  “የአገሬን ዕጣ ፈንታ ሳስብ በጣም አዝናለሁ”

    አገር ሰላሟ  ሲደፈርስ፣ ወጥቶ መግባት ብርቅ ሲሆን፣ ግጭቶች ሲከሰቱና ሰላማዊ የመኖሪያ ቀዬ የጦርነት ቀጠና ሲሆን፤ ህይወትን ለማዳን ማቄን ጨርቄን ሳይሉ መሰደድ ግድ ይሆናል፡፡ ሰሞኑን በጋምቤላ ክልል ከሚገኙ የስደተኞች መጠለያ ካምፖች አንዱ በሆነው የውኝየል መጠለያ ካምፕ ውስጥ በ “ፕላን ኢንተርናሽናል” በተዘጋጀው የጉብኝት ፕሮግራም ላይ የተገኘችው ጋዜጠኛ መታሰቢያ ካሳዬ፤የደቡብ ሱዳን የፋይናንስ ሚኒስትር የነበሩ ከፍተኛ ባለሥልጣን አግኝታ ነበር፡፡ እኚህ ስደተኛ ማን ናቸው? እንዴትስ ለስደት ተዳረጉ? ከስደተኛው ሚኒስትር ጋር የተደረገው አጭር ቃለ ምልልስ እነሆ፡-

    እስቲ ራስዎን ያስተዋውቁ…?
ኤቫንስ ዶክተር አሊ ሩባ እባላለሁ፡፡ የደቡብ ሱዳን የዌስተርን ኢኳቶሪያል ስቴት ፋይናንስ ሚኒስትር ነበርኩ፡፡ በስደት ወደዚህ እስከመጣሁበት ጊዜ ድረስ ማለቴ ነው፡፡
ወደዚህ  መጠለያ ካምፕ የመጡት መቼ ነው?
አንድ ዓመት ከሁለት ወር አካባቢ ይሆነኛል፡፡
እንዴት ወደ ኢትዮጵያ ሊመጡ ቻሉ?
በአገሬ መንግስትና በአማፅያኑ መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት እየተባባሰ ሄደ፡፡ ከዛሬ ነገ ነገሮች ይሻሻላሉ ብዬ ብጠብቅም፣ የበለጠ አስከፊ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ በመሄዳቸው ምክንያት፣ ከሰዎች ጋር ወደ ኮንጎ ሄድኩ። ከኮንጎ ወደ ካርቱም፣ ከካርቱም ወደ ፓምዶንግ ገባን። ፓምዶንግ ላይ ጊዜያዊ የስደተኞ መጠለያ ካምፕ ነበር። እዛ ገባሁና ተመዝግቤ በUNCHR አማካኝነት ወደ ውኝየል የስደተኞች መጠለያ ካምፕ መጣሁ፡፡
ወደ ሌላ አገር ማለትም የተሻለ ዕድል ሊያገኙ ወደሚችሉበት… አውሮፓና አሜሪካ አገራት እንዴት አልሄዱም? በእርስዎ ደረጃ ይህን ለማድረግ አያስቸግርዎትም ብዬ ነው?…
የትም መሄድ አልፈለኩም፡፡ እንዳልሽው ወደተለያዩ አገራት ለመሄድ እችል ነበር፡፡ ግን አልፈለኩም፡፡ ፍፁም ደህንነት ሊሰማኝ የሚችለው፣ በዚህ መንገድ ስደተኛ ሆኜ ወደዚህ ብመጣ እንደሆነ አመንኩ፡፡ እኔ በአገሬ እያለሁ፣ ጥሩ ኑሮ የምመራና ከመንግስት ኃላፊነት ውጪ፣ በራሴ የግል ሥራዎችን የምሰራ ሰው ነበርኩ፡፡ ኑሮዬም ደህና በሚባል ደረጃ ላይ ነበረ፡፡ አምስቱ ልጆቼ በጥሩ ሁኔታ ተምረው፣ ጥሩ ጥሩ ደረጃ ላይ ነው ያሉት፡፡ እነሱ እንኳን ወደተለያዩ ቦታዎች ሊወስዱኝ ሞክረው ነበር… ይህ የእኔ ምርጫ ነው፡፡ እዚህ ደህንነት ይሰማኛል፡፡
የስደተኞች መጠለያ ጣቢያውን እንዴት አገኙት?
በጣም ጥሩ ነው፡፡ ለእኔ የጎደለብኝ ነገር የለም፡፡ ወደዚህ እንደገባሁ ከኢትዮጵያ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር ጋር አብሬ ለተወሰነ ጊዜ ሰርቻለሁ፡፡ በኋላ በካምፑ ውስጥ የማያቸው የአገሬ ልጆችና ወጣቶች በእጅጉ አሣዘኑኝ፡፡ እኔም አቅሜ በሚፈቅደው መጠን ላግዛቸውና ልረዳቸው ወሰንኩ፡፡ ሁኔታውን ለሰዎች ሳማክር፣ በመጠለያ ካምፑ በትምህርት ጉዳዮች ላይ የሚሰራው “ፕላን ኢንተርናሽናል” የተባለው ድርጅት በመሆኑ፣ ለእሱ አመልክት አሉኝና አመለከትኩ፡፡ ያለኝን የትምህርት ማስረጃዎችና ሁኔታውን ሲያውቁ በጣም ተገረሙ። እናም በካምፑ ውስጥ ለሚገኙ ስደተኛ የደቡብ ሱዳን ወጣቶች፣ የሂሣብ ትምህርት እንዳስተምርና የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር ሆኜ እንዳገለግል ፈቀዱልኝና ማስተማር ጀመርኩ፡፡
አሁን እየሰሩ ባሉት ስራ ምን ያህል ደስተኛ ነዎት?
በጣም በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ በእርግጥ እኔ ከነበርኩበት ህይወት ወጥቶ፣ ዛሬ ባለሁበት ሁኔታ መቆየትና ህይወትን መቀጠል ከባድ ነው፡፡ ግን እንደ አቀባበላችን ነው፡፡ እኔ አሁን በጣም ደስተኛ ነኝ። በነፃነት እተኛለሁ፣ በነፃነት እነሳለሁ፣ የምፈልገውን ነገር አደርጋለሁ፣ ያለ ስጋት እኖራለሁ፡፡ ይህ ማለት ለእኔ በጣም ብዙ ነገር ማለት ነው፡፡ አሁን ደግሞ ያው ህይወት እንደ አዲስ በሌላ መንገድ ቀጥላለች፡፡… የምወዳትን ሴት አግኝቼ ጋብቻም መስርቻለሁ፡፡
ባለቤትዎን እዚሁ ካምፕ ውስጥ ነው የተዋወቁት ማለት ነው?
አዎ፡፡ እዚሁ ካምፕ ውስጥ ነው ያገኘኋት፡፡ የኑዌር ብሔረሰብ አባል የሆነች፣ ቆንጅዬ ወጣት ነች። እንደውም በቅርቡ የሴት ልጅ አባት አድርጋኛለች፡፡
አገር ቤት  ካሉት ቤተሰቦችዎ ጋር አይገናኙም?
አሁን አንገናኝም፡፡ ከቀድሞዋ ባለቤቴ ጋር ከተለያየን አንድ አምስት አመት ሆኖናል፡፡ ልጆቼን ግን በአካል አላገኛቸውም እንጂ በተለያዩ መንገዶች እንገናኛለን፡፡
አሁን ህይወት በስደተኞች ካምፕ ውስጥ ምን ይመስላል?
በጣም ደስ ይላል፡፡ እኔ ራሴን በጣም ባተሌ አድርጌ ነው የምውለው፡፡ ስለ ምንም ነገር ማሰብ አልፈልግም፡፡ የድሮ ህይወቴን እያሰብኩ፣ ራሴን መረበሽም አልፈልግም፡፡ ባለሁበት ሁኔታ ደስተኛ ነኝ። አሁን ባለበት ሁኔታ ወደ አገሬ መመለስ እንደማልችል አውቃለሁ፡፡ ለደህንነቴ ምንም መተማመኛ የለኝም፤ ስለዚህ ባለሁበት ቦታ ያገኘሁትን እየሰራሁ መኖር ግዴታዬ መሆኑን ተቀብየዋለሁ፡፡ በአጋጣሚ ግን ያለሁበት ሁኔታም ሆነ አሁን እየሰራሁት ያለው ነገር አስከፊ አይደለም፡፡
ስለ ወደፊቱስ ምን ያስባሉ?
ስለ ወደፊቱ የአገሬ እጣ ፋንታ ሳስብ በጣም አዝናለሁ፡፡ ምንም ጠቀሜታ በሌለው ግጭት፣ ምንም ምክንያት በሌለው ነገር፣ በርካታ ወገኖቼ እያለቁ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ መቋጫ የሚያገኝበትን ጊዜ እናፍቃለሁ፡፡ እኔ ፖለቲከኛ ነኝ፡፡ ግን ሁልጊዜም ሰላምን እናፍቃለሁ፡፡ የፖለቲካ ህይወት ውስጥ ከዚህ በኋላ መግባት አልፈልግም፡፡ ተራ የዜጋ ህይወት ነው መኖር የምመኘው፡፡ ምናልባት አገሬ ሰላሟን አግኝታ፣ ነገሮች ተሻሽለው ወደ አገሬ ብመለስ፣ ፍፁም ከፖለቲካ ነፃ የሆነ ህይወት ነው መኖር የምፈልገው፤ ራሴን ችዬ በግሌ ሰርቼ፣ መኖር ብቻ ነው ምኞቴ፡፡
በግልዎ ምን ተስፋ ያደርጋሉ?
-ኦ- ተስፋ አለኝ፡፡ አገሬ ወደቀደመው ሰላሟ ተመልሳ፣ የተበታተኑት ዜጎቿ ተሰባስበው፤ በሰላም የሚኖሩባት አገር እንደምትሆን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ህዝቦቿም አገሬን ይገነቧታል፡፡ በዚህ ደግሞ እርግጠኛ ነኝ፡፡

Read 6456 times