Monday, 25 June 2018 00:00

“ሁለት እግሬን አጥቼ ለእስር ተዳርጌ ነበር”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

  (የማሰቃያ ምርመራ ተጎጂው ማስታወሻ)

    የኦነግን የሽብር አላማ ተቀብለው፣ ቦንብ ሊያፈነዱ ነበር በሚል፣ ዕድሜ ልክ የተፈረደባቸውና ለ12 ዓመታት ከታሠሩ በኋላ ከሰሞኑ በይቅርታ የተፈቱት አቶ ከፍያለው ተፈራ፤ በምርመራ ወቅት አሰቃቂ ኢ-ሰብአዊ
ድርጊት እንደተፈጸመባቸው በአንደበታቸው ይገልጻሉ። ተጎጂው እንዴት ለእስር እንደተዳረጉ፣ በማዕከላዊ ተፈጸሙብኝ ስላሏቸው ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች፣ ሁለት እግራቸውን እንዴት እንዳጡ፣ ስለ ማረሚያ ቤት አያያዝ--- ወዘተ ለአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ እንዲህ አውግተዉታል፡፡ እነሆ፡


   በእንዴት ያለ ሁኔታ ነበር ተይዘው የታሰሩት?
ሳልታሰር በፊት በዩኒቨርሲቲ 3ኛ አመት ተማሪ ነበርኩ፡፡ የበጋውን ትምህርት ጨርሼ፣ የክረምት እረፍት ላይ ነበርኩ፡፡ ከአዲስ አበባ ወደ ክፍለ ሃገር ለመሄድ፣ ወደ አውቶቡስ ተራ እያመራሁ እያለ፣ ካራቆሬ ላይ ጠብቀው፣ ዝም ብለው ተኩስ ከፈቱብኝ። በወቅቱ ከሦስት ጓደኞቼ ጋር ነበርኩ፡፡ በተከፈተብኝ ተኩስ እኔ እግሬን ተመትቼ ስቆስል፣ ሁለቱን ደግሞ አሯሩጠው በጥይት ደብድበው ነው የገደሏቸው። አንደኛውን ወዲያው ነበር የገደሉት፡፡ እኔ እግሬ እንደተጎዳ ወደ ሆስፒታል ተወሰድኩ፡፡ የግራ እግሬን ነበር የተመታሁት፡፡ ወደ ሆስፒታል እንደሄድኩ በጣም ስለተጎዳ ይቆረጥ ተባለና ተቆረጠ፡፡ ቀኝ እግሬ ጤነኛ ነበር፤ ቁርጭምጭሚቴ ጋ ትንሽ ቁስል  ነበር። እሡንም ከጉልበቴ ዝቅ አድርገው ቆረጡት፡፡ ይህ እግሬ ሲቆረጥ ፍቃደኝነቴን አልጠየቁም፡፡ ቤተሰቦቼም አልተጠየቁም። ይህ ቅድመ ሁኔታ ሳይሟላ ነው እግሬ የተቆረጠው፡፡ ግራ እግሬ ሦስት ጊዜ ነው የተቆረጠው፡፡
ሦስት ጊዜ ማለት?
በመጀመሪያ ቁርጭምጭሚቴ አካባቢ ተቆረጠ፣ ትንሽ ቆይቶ ደግሞ ከጉልበቴ በታች ቆረጡኝ፣ በኋላም ከጉልበቴ በላይ ነው የቆረጡኝ፡፡ ህክምናው  ፖሊስ ሆስፒታል ነበር፡፡
የእርስዎ ፍቃድ ሳይጠየቅና ሳይፈርሙ እንዴት ተፈጸመ?
እግሬ ሲቆረጥ ፍቃደኛ መሆን አለብኝ፤ እኔ ካልቻልኩ እንኳ ቤተሰቦቼ ሊጠየቁ ይገባ ነበር፡፡ ፍቃደኝነቴ ሳይጠየቅ ነው፣ ማደንዘዣ እየወጉኝ እግሬ ሲቆረጥ የነበረው፡፡ እኔ፤ እንኳን ፍቃደኝነቴን ልገልጽ፣ መሞት እፈልጋለሁ እያልኩ፣ የተሰካልኝን ጉሉኮስ እነቅል ነበር፡፡ እነሱ ደግሞ ማደንዘዣ ይወጉኛል፤ ስነቃ እግሬ ተቆርጦ አየዋለሁ፤ እንዲህ ነው ሲደረግ የነበረው።
ከሆስፒታል ከወጡ በኋላስ ወዴት ነው የተወሠዶት?
እግሮቼ ተቆርጠው ከሆስፒታል ከወጣሁ በኋላ፣ ወደ ፖሊስ ኮሚሽን ማዕከላዊ ነበር የወሰዱኝ፡፡ ቁስሌ ሣይደርቅ ነው ከእነ ቁስሌ የወሰዱኝ፡፡ እዚያም ከእነ ቁስሌ ሠቅለውኝ ሲደበድቡኝ ነበር፡፡ የሰው ልጅ ላይ የማይፈጸም ነገር ነው ሲፈጽሙብኝ  የነበረው፡፡ በኛ ባህል፣ ያልተለመደ ማሠቃየት ነው የተፈጸመብኝ። ቁስሌን በፒንሳ ይጎትቱ ነበር፣ አጥንቴን በፒንሣ እየጎተቱ ያሠቃዩኝ ነበር፡፡ እጄ ወደ ላይ ተሠቅሎ  ደርቆ ነበር፡፡ ይህ ሲሆን እኔ ብቻ አይደለሁም የነበርኩት፤ ብዙ ልጆችም አሉ፤ ተመሳሳይ ድርጊት ሲፈፀምባቸው የነበሩ፡፡ የወንድሜ  ልጅ ከኔ ጋር ታስሮ ነበር፡፡ ሃያውንም የእጅና የእግሮቹን ጥፍሮች በፒንሳ ነቅለውበታል። ዛሬ ሰውነቱ በሙሉ ጠባሣ ሆኖ ይታያል፡፡ ሽንት ቤት ስወጣ፣ አንድ ሰው ግራ እጄን፣ አንዱ ቀኝ እጄን ይይዝና፣ መሬት ላይ ይወረውሩኛል፡፡ እንደገና ከመሬት ያነሡኛል፤ መልሰው ግራና ቀኝ እየያዙ፣ ወደ መሬት ከእነ ቁስሌ ይወረውሩኛል፡፡ እንዲህ እያደረጉ ነው ያሠቃዩኝ፡፡ በዚህ ድርጊት የመቀመጫዬ ቆዳ ሁሉ ተልጦ፣ መቀመጥ የማልችልበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር፡፡
ለስንት ጊዜ ነው በማዕከላዊ የቆዩት?
ይህ ሁሉ ማሠቃየት እየተፈፀመብኝ፣ የቆየሁት ለ8 ወር ያህል ነበር፡፡ ዛሬ የማልገልፃቸው፣ ከዚህም የባሱ ብዙ ድርጊቶች ተፈፅመውብኛል፡፡
ለምንድን ነው ይህ ሁሉ ማሰቃየት ሲፈጸምብዎ የነበረው? በምርምራ ወቅት አላምንም ያሉባቸው ጉዳዮች ነበሩ? ምን እያሉ ነበር ይጠይቁዎት  የነበረው?
ቦንብ ይዘው ሲሄዱ፣ ቦንቡ ራሳቸው ላይ ፈነዳ ነው ያሉት፡፡ እኔ፣ እንኳን ቦንብ በእጄ ልይዝ ቀርቶ፣ በወቅቱ ስለ ቦንብ ምንነትም የማውቀው ነገር የለም፡፡ እኔ የገበሬ ልጅ ነኝ፤ የዩኒቨርስቲ 3ኛ አመት ተማሪ ነበርኩ፡፡ አንድም ቀንም ከትምህርቴ ቀርቼ አላውቅም፡፡ የቦንብ ስልጠናም ወስጄ አላውቅም፡፡ በሚዲያ ጭምር “ቦንብ ሊያፈነዱ ነበር” ተብሎ ነው የተዘገበው፡፡ “ተማሪዎች ለአመፅ ያነሳሱ ነበር” በሚልም ስንጠየቅ ነበር፡፡ ጠቅላላ ለኔ የቀረበልኝ ክስ ልቦለድ ስለነበር፣ እንዴት ማመን እችላለሁ? ብቻ ብዙ ነው የተሰቃየሁት… እንደውም እኔን ከእነ ቁስሌ አንጠልጥለው ሠቅለውኝ፣ ሌሎች ሰዎች ለማስፈራራት ይጠቀሙብኝ ነበር፡፡ እነ ኮሎኔል ዳንኤል ተሰማ፣ እነ ዶ/ር ላቀው ሌሎችም ነበሩ፤ እኔን ሰቅለውኝ በፒንሳ ቁስሌን እየጎተቱ፣ እነሱን ያስፈራሩበት ነበር፡፡
ሰቅለውኝ ሲሉ እንዴት ነው?
ሁለት እጄን ያስሩና ግድግዳ ላይ የተመታ ሚስማር ላይ በገመድ አስረው ያንጠለጥሉኛል፡፡ እኔ ይሄን ሳስታውስ አሁንም ህመም ይሠማኛል፡፡ አካሌም እስካሁን ታማሚ ነው፡፡ ጆሮዬ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከድብደባ ብዛት ፈሳሽ ይወጣው ነበር፡፡ ነገሩን ባወራሁ ቁጥር ስሜታዊ ያደርገኛል፡፡ እናም ከዚህ በላይ ብዙ ባልል እመርጣለሁ፡፡ ከኔ አልፎ የወንድሜ ልጅ  ዛሬ ድረስ በጠባሣና ቁስሎቹ እየተሠቃየ ነው፡፡
እርስዎ  የፖለቲካ ተሣትፎ ያደርጉ ነበር? የፓርቲስ አባል ነበሩ?
በምንም የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ ተሣትፎ አላደርግም ነበር፡፡ ነገር ግን የኦሮሞ ተማሪዎች ከዩኒቨርስቲ ሲባረሩ፣ ሲደበደቡ እናገር ነበር፡፡ ለምንድን ነው መብታቸው የማይከበረው? የመናገር፣ የመሰብሰብ፣ ሃሳብን የማራመድ መብታችን ለምን አይከበርም? እያልኩ እናገር ነበር፡፡ ዩኒቨርሲቲ ውስጥም ይሄን ሃሳብ በማንገብ ሠልፍ እንወጣ ነበር። ሠልፍ ስንወጣ ግን በሠላማዊ መንገድ ነበር። ከዚህ ውጪ ከየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ጋር ግንኙነት አልነበረንም፡፡ እነሱ ግን ሲከሱኝ ኦነግ ነው ብለው ነው። መቼም እንቅስቃሴዬ ሁሉ ይታወቃል። ከትምህርት ገበታ ላይ ሶስት አመት ሙሉ ቀርቼ አላውቅም፡፡ ታዲያ የቱ ጋ ነው ከኦነግ ጋር ተገናኝቼ፣ ጭራሽ ስልጠና ወስዷል የተባልኩት፡፡
ጉዳዩ ወደ ፍ/ቤት ካመራ በኋላ የነበረው ሂደት ምን ይመስላል?
ሲጀመር ለኔ በወቅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ህግ የለም። አንድ ለምሣሌ ብጠቅስ፣ አቃቤ ህግ ተገቢ ማስረጃ ሣያቀርብ፣ ረጅም ጊዜ በመቆየቱ፣ አካልን ነፃ የማውጣት የህግ ጥያቄ በፍ/ቤት አቅርበን፣ ፍ/ቤቱ ቢፈቅድም ያ አልተፈፀመም፡፡ ፍ/ቤት ስቀርብ ደግሞ ቁስሌ አልደረቀም፣ ቁስሌ በፒንሳ እየተጎተተ እየተሠቃየሁ ነው፡፡ ቢያንስ የተሻለ ህክምና አግኝቼ፣ ነፍሴን ላትርፍ ብዬ የዋስትና መብቴ እንዲጠበቅልኝ ብጠይቅም አልተፈቀደልኝም፡፡ መቼም ሁለት አካሌ ጎድሎ ከሃገር አልጠፋም፤ ቁስለኛ ነኝ ልታከም ብላቸውም፣ ጥያቄዬ ተቀባይነት አላገኘም፡፡ “ሰው ሁሉ ህግ ፊት እኩል ነው፤ ላንተ የተለየ ዋስትና አንሠጥህም” ነው ያሉኝ፡፡ ፍ/ቤቱ ሦስት አመት ካመላለሰኝ በኋላ የዕድሜ ልክ እስራት ነው የፈረደብኝ፡፡ ቁስሌን ተመልክተው ለፍርድ ማቅለያ አልያዙልኝም፡፡
እርስዎ ለፍ/ቤቱ የደረሰብዎትን ኢ-ሰብአዊ ድርጊት በተገቢው አላስረዱም?
እኔ እንደውም ፍ/ቤቱ አንድ ቡድን አቋቁሞ የደረሠብኝን ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ያጣራልኝ ብዬ ጠይቄ ነበር፡፡ የተሠጠኝ ምላሽ ግን “እኛ የሠው እግር የሚቆርጥ ፖሊስ የለንም” የሚል ነው፡፡ ለኔ አቃቤ ህግና ዳኛ እኩል ከሣሽና ፈራጅ ናቸው፡፡ በኋላ ይግባኝ ጠይቄ፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ስቀርብ፣ በወቅቱ የነበሩት የመሀል ዳኛ፤ ”እዚህ ሰው ላይ የተፈረደው በምን ማስረጃ ነው?” ብለው አቃቤ ህጉን በመገረም ነበር የጠየቁት። ግን “ተጠርጣሪው የሰጠው ቃል አለን” የሚል ነበር የአቃቤ ህግ ምላሽ፡፡ “በስህተት ከመዝገቡ ጋር ሳያይዝ ቀረ፤ አሁን ማቅረብ እንችላለን” አለ አቃቤ ህግ፡፡ ፍ/ቤቱም ድጋሚ ማስረጃ እንዲያቀርብ ነው የፈቀዱለት። ለኔ ይሄ ምን ያህል ፍ/ቤትና አቃቤ ህግ እኩል መረጃ አቅራቢና ፈራጅ እንደሆኑ ነው ያሣየኝ፡፡ በኋላም አቃቤ ህግ፤ ማስረጃውን ከሬጅስተራል ማግኘት አልቻልኩም እያለ፣ በየጊዜው ቀጠሮ እየሰጠው፣ አንድ አመት ከአራት ወር ከቆየ በኋላ በድጋሚ፣ ፍ/ቤቱ፣ ፖሊስ ተገድዶ፣ በእኔ ላይ ማስረጃ እንዲያቀርብ ነው የታዘዘው፡፡ በኋላ ማስረጃው እጃችን ላይ ስላልደረሰ፣ የሥር ፍ/ቤት ውሳኔ የፀና ይሁን አሉ፡፡ አንደኛ፤ እኔ የቀረበብኝን ማስረጃ መመልከትና መከራከር ነበረብኝ፣ ሁለተኛ፤ እኔ ይግባኝ ጠይቄ ባለበት ነው፣ ፍ/ቤት፣ በኔ ላይ ተጨማሪ ማስረጃ እንዲቀርብ ሲያስገድድ የነበረው፡፡ ይሄ አሳዛኝ ነበር፡፡
የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ቆይታዎስ እንዴት ነበር? ለአካል ጉዳተኞች ምን ያህል እንክብካቤ ይደረጋል?
ቃሊቲ ስገባ ዊልቸር ላይ ሆኜ ነበር፡፡ ዞን ሶስት የሚባል አለ፡፡ አንድ ክፍል ውስጥ ከ700 በላይ ሰዎች ናቸው ያሉት፡፡ እዚያ ውስጥ ነው የከተቱን፡፡ ቤቱ ደግሞ ሰው በሰው ላይ ተደራርቦ የሚተኛበት፣ መላወሻ እንኳን ቦታ የሌለው ነው፡፡ ሽንት ቤት ራሴን ችዬ መሄድ አልችልም ነበር፡፡ ሳይነስ ያመኝ ነበር፡፡ በአጋጣሚ ዶ/ር ከበደ የሚባሉ እስረኛ ነበሩ፤ እሣቸው ለመኑልኝ፡፡ ከ3 ወር ቆይታ በኋላ ሌላ ቦታ ገባሁ፡፡ ቀጥሎ “ቅጣት ቤት” የሚባል በኮንክሪት የተሠራ ቤት አለ፤ እዚያ ወሰዱኝ፡፡ እዚያ ጨለማ ቤት ሁለት ዓመት ያህል ቆየሁ፡፡ ሁለት እግር የሌለው ሰው፣ እንዴት ለብቻው ሽንት ቤት መሄድ በማይችልበት ሁኔታ እንዲህ መቆየቱ፣ ለሁሉም የሚገርም ነው፡፡
በዚህ አጋጣሚ በቦታው የነበሩ እስረኞችን አመሠግናለሁ፡፡ ብዙ ድጋፍ ሲያደርጉልኝ ነበር፡፡ የመጨረሻዎቹ አራት አመት ቂሊንጦ ወስደውኝ ነበር፤ በኋላም ደርጎች ሲታሠሩበት ወደነበረው ቃሊቲ ነው የመለሱኝ፡፡ ትንሽ የተሻለ ነበር መጨረሻ አካባቢ። በዚህ አጋጣሚ እስር ቤት ያሉ ብዙዎቹ ንፁሃን ናቸው። በእጅጉ የተጎዱት ናቸው፡፡ መንግስት በነካ እጁ የእነዚህንም ሰዎች ጉዳይ በትኩረት ቢመለከት ጥሩ ነው፡፡
ያንን ሁሉ የስቃይ ጊዜ ካሳለፉ በኋላ በይቅርታ እፈታለሁ ብለው አስበው ያውቃሉ?
አሁን ትንሽ ጭላንጭል የሆኑ ነገሮችን እያየን ነው። ብዙ ለውጦች አሉ፡፡ ግን አሁንም የሞት ፍርደኛ የሆኑ፣ በራሳቸው መንቀሳቀስ የማይችሉ ሽማግሌዎች፣ የአካል ጉዳተኞች አሉ፡፡ የህግ የበላይነት መከበሩ እንዳለ ሆኖ፣ እነዚህ ሰዎች ሰው በመሆናቸው ብቻ፣ ህግ ፊት እኩል የሚሆኑበት ሁኔታ ቢፈጠር ጥሩ ነው፡፡ የተመኘነውን ዲሞክራሲ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ቢያገኝ ምኞቴ ነው፡፡
ያቋረጡትን የዩኒቨርሲቲ ትምህርት፣ እስር ቤት ሆነው ለመቀጠል አልሞከሩም?
ደጋግሜ በርቀት እንድማር ጠይቄ፣ እስካለፈው ዓመት ድረስ ተከልክዬ ነው የቆየሁት፡፡ የምማረው ፕላንት ሳይንስ ነበር፡፡

Read 5705 times