Sunday, 24 June 2018 00:00

ቁጥር 3 የአገር የሕልውና አደጋ - በቅይጥ አስተሳሰብ የተፈጠረ ቀውስ

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(2 votes)

ለዶ/ር አብይ፣ በብርቱ አደራ የሚቀርብ ተጨማሪ የስራ ሸክም! ለሚሰራ ሰው፣ ስራ ይጨመርለታል - ግን ከአድናቆትና ከምስጋና ጋር ነው!
የብሽሽቅና የማዋረድ እሽቅድድም እየበዛ፣ ለጭፍን ውንጀላና ለምቀኝነት እየተመቸ፣ በጅምላ ፍረጃና በጥላቻ ወደ ጥፋት የሚያደርስ የአስተሳሰብ ቀውስ፣ ከዘረኝነት ያልተናነሰ ክፉ የሕልውና አደጋ ነው።
እየተዘባረቀና እየተደረተ የተምታታውን የአስተሳሰብ ቀውስ የማስወገድ፣ በጠራና በነጠረ ትክክለኛ አስተሳሰብ አማካኝነት የማስተካከል፣ ኢትዮጵያን የማዳንና ወደላቀ ስልጣኔ የማምጠቅ ታሪክ መስራት ይቻላል! እንደሚቻልም እያየን ነው። እንዴት?
ጠ/ሚ አብይ አህመድ፣ በዘረኝነት ላይ በጀመሩት ዘመቻ፣ ኢትዮጵያን የሚያነቃንቅ፣ ከልጅ እስከ አዋቂ ዜጎችን የሚነቃ ተዓምር እየሰሩ ነው።
እያንዳንዱ ሰው በዘር ሃረጉ ሳይሆን፣ በመልካም ተግባሩ፣ በበጎ ባሕርይውና በድንቅ ብቃቱ የሚከበርባትና የሚወደድባት ቅድስት አገር እንድትሆንልን፣ኖረን፣ “የሰው ማንነት ማለት የግል ማንነት እንደሆነ፣ የሰው ክብር ማለት በራሱ ስራ የሚያገኘው የእኔነት ክብር መሆኑን በመገንዘብ የቁጥር 1 የሆነውን የዘረኝነት አደጋ ማጥፋት የሚቻለው።
የግል ብቃትን የሚጣጥል፣ የግል ሃላፊነትን የሚያሽቀነጥር፣... በተገኘው ሰበብ ሁሉ በመንጋ መቧደንና መንጋጋት፣ አጥፊ የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ ተንሰራፍቶ ዘረኝነት የጦዘበት፣ የቅይጥ ማንነት ቀውስ!   
የግል ኢንቨስትመንትን የሚያሽመደምድና ሃብት ማፍራትን የሚያንኳስስ፣ የገናና መንግስት አክሳሪ ፕሮጀክቶች የተፈለፈሉበትና “የሃብት ክፍፍል” የሚል ምቀኝነት የሚራገብበት፣ የቅይጥ ኢኮኖሚ ቀውስ!
ይህንን ቁጥር 2 የሕልውና አደጋ፣ ስራ አጥነትንና የዋጋ ንረትን በማባባስ የዜጎችን ኑሮ ያናጋና አገርን ያቃወሰ የውድቀት ቁልቀለት መመለሻ ወደሌለው የለየለት ጥፋት ከመድረሱ በፊት ለመግታት የሚደረግ አዲስ ጥረትና መልካም ጅምር፣ ከሰሞኑ የጠ/ሚ አብይ የፓርላማ ንግግር ሰምተናል።
ስለ ፕራይቬታይዜሽ፣ የግል ኢንቨስትመንትን ነፃ ገበያ ስርአትን ስለማስፋፋት በአፅንኦት ሲነገር ከሰማን ስንት ዓመታችን! ይሄውና ሰሞኑን ሰምተናል። ያዝልቁልን፣ ያብዙልን።  
ቁጥር 3 የሕልውና አደጋም አለብን - የቅይጥ አስተሳሰብ ቀውስ! “የሃሳብ ብዝሃነት”፣ “የሃሳብ ፍጭት” ምናምን እየተባለ፣ “የሃሳብ ልዩነት”ን የጣዖት ያህል በሚያመልክ ጭፍን እምነት፣ “የሃሳብ እኩልነት” በሚል ፈሊጥ፣ “ተቃራኒና የሚጣረሱ ሃሳቦችን ተቀብለው እኩል ማስተናገድና እኩል ማክበር” የሚል የተሳከረ የሃሳብ ግርግር፣ የጭፍን አስተሳሰብ ቀውስ አለብን!
ትክክለኛ ሃሳብም ሆነ የተሳሳተ ሃሳብ መያዝና መናገር፣ በእያንዳንዱ ሰው አእምሮና ምርጫ የሚወሰን እንደመሆኑ፣ የሃሳብ ነፃነትን አለመጣስና መጠበቅ አንድ ነገር ነው። እውነትን ሃሰትን፣ ትክክለኛና የተሳሳተ ሃሳብን እኩል እያስተናገዱ እኩል መደገፍና ማክበር ግን የተሳከረ የአስተሳሰብ ቀውስ ነው።
ይህንን ለማስተካከል መዝመትስ የማን ሸክም ነው? ሁሉም ሃሳብ እኩል እንዳልሆነ፣ በግላጭ እያየንና እየሰማን!...
“የሃሳብ ብዝሃነት”፣ ከሁሉም የላቀ ተመራጭ የፖለቲካ አላማና ድንቅ ራዕይ እስኪመስለን ድረስ፣ ነገር አለሙ ሁሉ ተምታትቶብናል።
ኢትዮጵያ የተረጋገጠ እውነት፣ የነጠረ ሃሳብና በቅጡ የጠራ እውቀት የበዛላት፣ ከስልጣኔ ወደ ላቀ የስልጣኔ ብርሃን የሚትገሰግስ አገር እንድትሆንልን መመኘት እየቻልን፣...
የእያንዳንዱ ሰው ነፃነት ተጠብቆ፣ በዚያው መጠንም እያንዳንዱን ሰው በብቃቱ፣ በስራውና በባሕሪው የሚመዝን ቀና መንፈስ ከአብዛኛው ሰው ጋር እየተዋሃደ፣ ኢትዮጵያ ይበልጥ ውብ አገር ስትሆን የማየት ድንቅ ሕልምና ውድ አላማ መያዝ እየቻልን፣...
ኢትዮጵያ፣ “በላቀ ብቃትና በውጤታማ ትጋት መንፈሳችንን የሚያነቃቁና በስኬት በአርአያነታቸው የሚያበረታቱንን ጀግኖች” ከልብ እያደነቅን፣ የመንፈስ ሕብረትና የስልጣኔ ባህል የምናጣጥምባት ቅድስት አገር እንድትሆንልን ብሩህ ራዕይ ጨብጠን ለስኬት መትጋት እየቻልን፣...
ለምን ለምን በተሳከረ የአስተሳሰብ ቀውስ ተጠምደን ለውድቀት እንጣደፋለን? “የሃሳብ ፍጭት፣ የሃሳብ እኩልነት፣ የሃሳብ ብዝሃነት” በሚሉ ፈሊጦች፣... ከአንድ እውነተኛ መረጃ ጋር እልፍ አሉባልታ የሚናፈስባት፣ ከአንዲት ትክክለኛ ሃሳብ ጋር እልፍ ሃሰትና ስህተት የሚያግተለትባት የምናብ አገርን መመኘት፣... ከአንዲት ቁምነገር ጋር በእልፍ ረብየለሽና ዝባዝንኬ መነባንቦችም “በእኩል አድናቆትና በእኩል ድጋፍ” የሚግበሰበሱባት የቅዠት አገርን የመናፈቅ አባዜ... እንደ ቅዱስ ራዕይ ሲቆጠር፣... የአስተሳሰብ መሳከር እንጂ መቃናት አይደለም።
ክፋቱ፣ አብዛኞቹ የዘመናችን ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች፣... “የሃሳብ ብዝሃነት”፣ “የሃሳብ ፍጭት”፣ “የሃሳብ እኩልነት” የሚሉ አባባሎችን በሚያመልክ ተመሳሳይ አቋምና በተመሳሳይ የቃዠ ራዕይ ላይ በህብረት እየተስማሙ፣... ክፉኛ አዘውትረው ይወዛገቡበታል። “በሚስማሙበት ተመሳሳይ አባባል፣ ሳያሰልሱ መፋጨትና መወዛገብ”! ይሄ መሳከር አይደለም? እና ደግሞ፣ ይህንን እንደ ውጤታማ ተግባር፣ እንደ አኩሪ ሙያ ይቆጥሩታል - “የሃሳብ ፍጭት”ን የሚወዳደር አኩሪ ሙያና የጥበብ ተግባር የሌለ ይመስላቸዋል።     

“የሃሳብ ፍጭት” የጎን ቅጥያ ቅርንጫፍ ከመሆን አልፎ፣ “ዋና አላማና አውራ መንገድ” ሲሆን፣... የውድቀት ሩጫ
የታመመ ሰው፣ በሽታውንና መድሃኒቱን ለማወቅ፣... ሃኪሞችን ከማነጋገር ይልቅ፣ ሰፈርተኛውን ሰብስቦ በማከራከርና በማፋጨት መፍትሄ አገኛለሁ ቢል አስቡት። ሁለት ሃኪሞችን ሲያነጋግር፣ “ዋናው አላማ” የሁለቱንም የሙያ እውቀትና የሙያ ትጋት አዳምሮ ለመጠቀም እንጂ፣... በዚሁ አጋጣሚ ልትፈጠር የምትችል አንዲት ነጠላ የሃሳብ ልዩነትንና ክርክርን፣ አንዲት ቅጥያ ቅርንጫፍን በመናፈቅ አይደለም። “የተረጋገጠ እውነት፣ ትክክለኛ ሃሳብና በቅጡ የተጣራ እውቀት” ነው ዋናው ነገር - በሳይንሳዊ ዘዴ የሚገኝ። እግረመንገድ የሚያጋጥም፣ “የሃሳብ ልዩነትና ፍጭት” ቅንጣት ቅጥያ ነው።
በተቃራኒው “የሃሳብ ፍጭት” ዋነኛ የማወቂያ ዘዴ እንዲሆንለት የሚጠብቅ ታማሚስ? ሰፈርተኞችን በማጨቃጨቅና በማፋጨት በሽታውንና መድሃኒቱን የማወቅ ጭፍን ምኞት፣ ሌላ ትርጉም የለውም - “የመዳን እድሉን የመዝጋት ሩጫ፣ እድሜውን የማሳጠር ትጋት” እንደማለት ነው።
ፖለቲካ ላይ ግን፣ “የሃሳብ ፍጭት” ከቅንጣት ቅጥያ ከመሆን ያለፈ፣ እንደ ዋና አላማና እንደ ዋና ዘዴ የሚታይ ሆኗል። ማርና ወተት ከሚያፈልቅ ምናባዊ ምንጭ ጋር ቢነፃፀር እንኳ፣ “የሃሳብ ፍጭት ይበልጥብናል” እንድንል፣ ከሁሉም የላቀ ተመራጭ ተዓምር መስሎ እንዲታየን፣ እለት ተእለው ይሰበክለታል።
በምናባዊም ሆነ በእውኑ አለም፣ አቻ የሌለው ሁነኛ የማወቂያ መንገድና አስተማማኝ የመፍትሄ ዘዴው ይሄው ነው? እርስበርስ በሚቃረኑ ሃሳቦችና በሚጣረሱ እምነቶች፣ በጭፍንም ይሁን በፈጣጣ የሚጦዙበት “የሃሳብ ፍጭት” ነው ወደር የለሽ የእውቀትና የመፍትሄ ማፍለቂያ? “የሃሳብ ፍጭት” በተሰኘው የጡዘት ጎዳና፣ የሚቃረኑ ሃሳቦችን ለማብዛት እየተጋን፣ የሚጣረዙ አቋሞችን ለማላተም እየተረባረብን፣... ከብዙ ጥረት በኋላ የምናገኘው ውድ ፍሬ፣ የምንገነባው አገርስ ምን አይነት ይሆን?
የመሬት ክብነትን የሚያስረዳ ትምህርትና ጠፍጣፋነቷን ለማሳመን የሚሰብክ ንግግር፣... በእኩል ድጋፍ እኩል እየሚከበሩ ዘወትር የሚፋጩባት አገርን ነው የምንናፍቀው?
በአንድ በኩል፣ “በጥረት አምርቶ ሃብት የማፍራት ሃሳብ”፣ በሌላ በኩል “የሃብት ክፍፍል የሚል መፈክር”... በእኩል ድጋፍ እየተፋጩ፣... “በጥረትህ ሃብት ማፍራት ትችላለህ”፣... “ያለ ጥረት ሃብት መካፈል ትችላለህ” እየተባለ፣... መስራትና መዝረፍ በእኩል ፈረቃ ተቻችለው የሚኖሩባት አገር ለመፍጠር ነው የምንመኘው?
በአንድ በኩል፣ የሳይንስ ግኝቶችንና እውቀቶችን የሚያስገነዝብ ማብራሪያ ወይም የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን ከአሰራራቸውና ፋይዳቸው ጋር ያመዛዘነ አድናቆት ይኖራል። በሌላ በኩል በተቃራኒው፣ “አገር በቀል እውቀት” የሚል ማዕርግ ለጥንቆላ መሸለም፣ “እውቀትን በሞኖፖል የመቆጣጠር አምባገነንነት” የሚል ውግዘት በሳይንስ ትምህርት ላይ ማውረድም አለ። አፍቃሬ እውቀት እና ፀረ እውቀት ሃሳቦች፣... “በሃሳብ እኩልነት መርህ” ድጋፋችንን በእኩልነት እየሰጠን፣ ዘላለም እያፋጨን መኖር?
የሃሳብ ፍጭት ወይም የሃሳብ ብዝሃነት ሲባል፣ ጉዳዩ “እልፍ አእላፍ ተቃራኒ ሃሳቦች የመኖራቸው ጉዳይ” ሳይሆን፣... የሃሳቦች ልዩነቶች ተበራክተው ተትረፍርፈው፣ እኩል እየተስተናገዱ የሚበረታቱበትና እኩል የሚከበሩበት “የሃሳብ ብዝሃነት” ምድረ ገነት እውን ሲሆን ማየት ማለት ነው! ወይ ምድረ ገነት!
ለምድረ ቅዠት፣ የተዘጋጁ ግብአቶች ሞልተዋል። ያለተጨማሪ ሰበብ፣ ያለተጨባጭ ሃሳብ፣... “ተለዋጭ ቃላት”ን ማምጣት እንኳ ሳያስፈልግ፣... በዚያ ላይ ክርክርን የሚያሳጥር እልባት እንዳይገኝ ሳይጨነቁና ንትርክን በአጭር የሚቀጭ ነገር እንዳይመጣ ሳይሰጉ፣ “የተንበሻበሸ ውዝግብ እንደልብ መፋጨት” መቻል፣... አስገራሚ ጥበብ ሊመስለን ይችላል። ግን አይደለም። በጣም ቀላል ነው።
“የሕዝብ ጥያቄ!” በምትል ሃረግ ብቻ፣ ደርዘን ፓርቲዎችና እልፍ ፖለቲከኞች፣ ሌላ ሰበብ ሳያስፈልጋቸው፣ ከአመት አመት ክረምት ከበጋ፣ እየተፋጩ መቀጠል ይችላሉ። አንዱ ምክንያት፣... ያው፣ “የሕዝብ ጥያቄ” ብለው ሲናገሩ፣ ምን ማለታቸው እንደሆነ እቅጩን መግለፅ አይጠበቅባቸውም። ማን እና እነማን እንደየጠቁ፣ ጥያቄው በእውነት ላይ መመስረት አለመመስረቱ፣ ትክክለኛና ተገቢ መሆን አለመሆኑ፣ ፋይዳ ይኑረው አይኑረው በማስረጃ ማረጋገጥም ሆነ ማብራራት አይጠበቅባቸውም። ጥያቄው ምን እንደሆነ በጨረፍታ ለመጠቆም እንኳ ጊዜ ማባከን አይኖርባቸውም።
ሚስጥሩ ይሄው ነው። በቃ፣ በደምሳሳው፣ በክንብንቡ፣ በደፈናው፣... ያለማቋረጥ መፋጨት ይችላሉ። በተለያየ የድምፅ መጠንና የቅላፄ አይነት ያቺኑን አባባል በመደጋገም ብቻ እንደልብ እየጦዘ የሚሄድ “የሃሳብ ፍጭት” መፍጠር፣ አስገራሚ የዘመናች ልዩ ፈጠራ ከተባለ ይሄው ነው።

በሕብረት በሚያስማማቸው አባባል፣ በጋራ እየተፋጩ መናቆር!
“የሕዝብ ጥያቄ” በሚል ሃረግ ተስማምተው የመፋጨታውን ያህል፣ “መልካም አስተዳደር” በተሰኘው አባባልም ተስማምተው ሲወዛገቡም፣ ያው ነው። “መልካም አስተዳደር”፣... በደምሳሳው “አንዳች ጥሩ ነገር” እንደሆነ በመገመት በአዎንታዊ ስሜት እስከተቀበልናቸው ድረስ፣ በቂ ነው። ምንነቱን እንደመሰለን ዘርዝረን፣ እንደፈቀደን አራምባና ቆቦ ብንተረጉመው ደንታ ያላቸው አይመስሉም። በትክክል ምን ማለት እንደሆነ ሲነገር ባንሰማ እንኳ፣ “የመልካም አስተዳደር እጦት” የሚል እሮሮ፣ ውግዘት፣ ስድብ፣ ዋይታ፣ ፉከራ፣ ዛቻ፣... ለስንትና ለስንት ዓመታት፣... እንዲችው በደፈናው መፋጨት አላቃታቸውም። አንዳንዴ ለለውጥ ያህል፣
አዲስ ቃል ማምጣትም ይቻላል - ደሊቨሮሎጂ! ወይም ነባሮቹን መከለስ ይቻላል። ብሔራዊ እርቅ ወይም አገራዊ መግባባት፣ የፖለቲካ ምህዳር መጥበብ ወይም መስፋት፣... የማይነጥፍ የፍጭት ማመንጫ ሞልቷል።  
ያለሃሳብ እንደልብ የሚያናክሱና የሚያናቁሩ፣ “የሃሳብ ፍጭት” መፈልፈያዎች በሽ ናቸው። “ነፃነት” እና “የሕግ የበላይነት”፣ ቅንጣት ግንኙነትም ሆነ ቅርበት የሌላቸው፣ የተለያየ ፕላኔት ፍጡራን እንደሆኑ ማስመሰል፣... “የሃሳብ ፍጭት” መፈልፈያ ዘዴ ነው።

ሃሳቦችን በጣጥሶ በመደረት የሚገኝ፣ “የሃሳብ ፍጭት”!
ነፃነት ማለት፣ እያንዳንዱ ሰው ነፃነት፣ ማለት የሌላ ሰው ሕይወት ላይ የመወሰን ሰበብ የማግኘት ዘዴ ሳይሆን፣ የየራሱን ሕይወት የመምራት ነፃነት ማለት እንደሆነ፣ ይህንንም ነፃነት ማግበር የሚቻለው፣ የትኛውም ሰው የሌላ ሰው ሕይወትን እንዳይነካ በሚከለክል ትክክለኛ አስተሳሰብ፣ ትክክለኛ ህግ እንዲኖርና፣ መንግስት “የሕዝብ ጥያቄ”፣ “የሕዝብ ፍላጎት”፣ “የብሔር ብሔረሰብ ጥቅም” ምናምን እያለ በቅስቀሳም ሆነ በስሜት አገሬውን እያጋጋለ፣ በትክክል የተዘረዘረውን ሕግ ከማስከበር ውጭ ሌላ ስራ እንዳይኖረው በመገደብ፣...  ማለትም የህግ የበላይነት በማስፈን፣... የእያንዳንዱን ሰው ነፃነት የመጠበቅ፣ ለዚህም ሕግን የማስከበርና የሕግ ዳኝነትን የማስፈፀም ተግባርም ነው ፍትህ የሚባለው።
ነፃነት፣ ሕግ፣ ፍትህ እና የሕግ የበላይነት የዚህን ያህል ከመነሻ እስከ መድረሻ ተዋድደው መሰናሰል የሚገባቸው ሃሳቦች እንደሆነ ከመገንዘብ ይልቅ፣... በተግባርም እውን ወደሚሆኑበት ስልጣኔ ለመራመድና ለመጓዝ ከመትጋት ይልቅ፣... በተቃራኒው፣... እንደመበሻሸቂያ ምልክት እንደመቆመሪያ ካርድ የሚያገለግሉ ቃላት እንዲመስሉና ትርጉም እንዲያጡ ተደርገዋል። “ሕግ” ብሎ መጮህ “ነፃነት”ን የማጣጣል አስተማማኝ ዘዴ የሚሆንላቸው ይመስላቸዋል።
“ሕግ”ን እያጥላሉና “ከሕግ በላይ” ለመሆን እየተመኙ የሰውን ሕይወት ወይም ንብረት ለማጥፋት አንዳች ማመካኛ ሲፈልግም፣ “የሃሳብ ነፃነት፣ የመቃወም ነፃነት ይከበር” የሚል መፈክር ያስተጋባል - “የሃሳብ ነፃነት፣ የመቃወም መብት” የሚሉ ቃላት በአንዳች ተዓምር ሰውን የመግደልና ንብረት የማቃጠል ልዩ ፈቃድ፣... ማለትም የሌሎች ሰዎችን ነፃነት የማጥፋት ልዩ ስልጣን የሚያስገኝ ይመስል! “የሕዝብ ጥያቄ”፣ “የሕዝብ ፍላጎት”፣ “የብሔር ብሔረሰብ መብት” ብሎ መጮህም እንዲሁ፣... ያሰኘውን ወንጀል ለመፈፀም የሚያስችሉ ምትሃተኛ ቃላት ሆነው ይታዩታል።
“የሃሳብ ልዩነትን” የጣዖት ያህል ከማምለክ ባልተለየ ጭፍን እምነት፣ “ተቃራኒ ወይም የሚጣረሱ ሃሳቦችን ተቀብለው እኩል ማስተናገድና እኩል ማክበር”... ምናምን እያሉ የሚሰብኩ የአገራችንም ሆነ የውጭ ፖለቲከኞች፣ የአገራችን ገዢ ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣... በጋራ ተስማምተውና ተባብረው የሚያስተጋቧቸው ቃላትና ሃረጋትን የንትርክ ፋብሪካዎች፣ የማይነጥፉ የፍጭት ምንጮች እንደሚሆኑላቸው በሙሉ ልብ፣ በፍፁም እምነት፣ በሙሉ ተስፋ ይተጋሉ።
ይሄ ወደ ምድረገነት የሚያደርስ የስኬት መንገድ ሳይሆን በተሳከረ ቅዠት የሚያተራምስ የውድቀት መንገድ ነው።
የግል ማንነትንና የግል ሃላፊነትን እየደፈቀ፣ በትውልድ ሃረግና በቋንቋ እያቧደነ ዘረኝነትን የሚያጦዝ የብሔር ብሔረሰብ ፓለቲካ፣ ለኢትዮጵያ ቁጥር 1 የሕልውና አደጋ የመሆኑን ያህል፣... የግል ኢንቨስትመንትንና የግል መተዳደሪያ ስራን የሚያመናምኑ፣ መንግስት አለቦታው ቢዝነስ ውስጥ እየገባ ሃብትን የሚያባክኑ አክሳሪ ፕሮጀክቶችን እየፈለፈለ፣ ስራ አጥነትን አባብሶ፣ የዜጎችን ኑሮ አናግቶ አገርን ለትርምስ የሚዳርግ የቅይጥ ኢኮኖሚ ቀውስ፣ ለኢትዮጵያ ቁጥር 2 የሕልውና አደጋ የመሆኑን ያህል፣ ከነዚህ የማይተናነሰው ሌላኛው ቁጥር 3 የሕልውና አደጋ፣ የቅይጥ አስተሳሰብ ቀውስ ነው።

መሳከር የበዛበት የቅይጥ አስተሳሰብ ቀውስ
“የተረጋገጠ እውነት፣ ትክክለኛ ሃሳብ፣ በቅጡ የተጣራ እውቀት”... የሚሉ የስልጣኔ ስረመሰረቶችን የሚሸረሽሩ፣... “ስልጣኔ ጊዜው አልፎበታል” የሚል ፈሊጥ በሚያስተጋቡ “የፖስትሞደርን” የተሳከሩ ፍልስፍናዎች በዓለም ደረጃ የገነኑበት ዘመን ላይ ነው።
እውቀትን ከማብዛት ይልቅ “የሃሳብ ብዝሃነት” ነው እንደአለማ የተያዘው። እውነትን ከሃሰት፣ ትክክለኛ ሃሳብን ከስህተት ለመለየት አመሳክሮና አረጋግጦ ከመገንዘብ ይልቅ፣... “የሃሳብ ልዩነቶችን” እኩል ማስተናገድና እኩል ማክበር የሚል ፈሊጥ ነው የገነነው። ከነማስረጃውና ከነማብራሪያው ትክክለኛ ሃሳብ በማቅረብ ለመማማርና ለመተማመን ከመጣር ይልቅ፣... ከብሽሽቅ አንስቶ አገርን የሚያተራምስ ጭፍን የመናቆር አባዜ ድረስ የሚዘልቅ “የሃሳብ ፍጭት”፣ እንደ ድንቅ ሙያና እንደ ትልቅ ስራ ተቆጥሯል። እናም፣ በቅጡ ማሰብ እየቀረ፣ መሳከር የበዛበት የቅይጥ አስተሳሰብ ቀውስ ተንሰራፍቶ፣ ለኢትዮጵያ ቁጥር 3 የሕልውና አደጋ ሆኖባታል። ካለፉት ሦስት የቀውስ ዓመታት ወዲህ፣ መንግስት ዘግይቶም ቢሆን፣ አደጋዎቹን መገንዘብ ጀምሯል።
ጠ/ሚ አብይ አህመድ ባለፉት ሦስት ወራት ለብዙ ኢትዮጵያውያ የተስፋ ብርሃን መፍጠርና ከፍተኛ ድጋፍ ለማግኘት የቻሉት፣ ከሰሞኑም በፓርላማ ንግግራቸው የብዙዎችን ቀልብና ስሜት የገዙት፣... የዘረኝነትን ክፉት፣ ፀያፍነትና አደገኛነት በአፅንኦት አስረድተውና ኮንነው፣ ዘረኝነትን ለማስወገድ መጣር እንዳለብን አብራርተው፣ ለትጋት ማነሳሳትና ማነቃቃት ስለቻሉ ነው። በዘረኝነት ላይ በጀመሩት ብርቱ ዘመቻ፣ ኢትዮጵያን ከዳር ዳር አነቃንቀው፣ ሚሊዮኖችን አነቃቅተዋል።
የመንግስት ቢዝነሶችንና ፕሮጀክቶችን በተመለከተም፣ የመንግስት ቢዝነስ በተፈጥሮው አባካኝና አክሳሪ መሆኑን በመጥቀስ፣ እድገት የሚገኘው የግል ኢንቨስትመንትንና የነፃ ገበያ ስርዓትን በማስፋፋት እንደሆነ ተናግረዋል። “የግል ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት”፣ “የነፃ ገበያ ስርዓትን መገንባት” የሚሉ አባባሎች ለዓመታት ጠፍተው፣ ከስንትና ስንት የቅይጥ ኢኮኖሚ ቀውስ በኋላ ነው፣ አሁን እንደገና ሲነገሩ፣ እንደገና በኢህአዴግ ወይም በመንግስት ሲጠቀሱ የሰማነው።
እንዲህም ሆኖ፣ በብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካ ከሚጦዘው የዘረኝነት አደጋም ሆነ በመንግስት ፕሮጀክቶች አማካኝነት ከሚባባሰው የቅይቅ ኢኮኖሚ ቀውስ፣ እንዲህ በቀላሉ ማምለጥ ይቻላል ማለት አይደለም። የዘረኝነትን አደጋ መግታት የሚቻለው፣ መሰረታዊው የስህተት አስኳልና ዋናው ነቀርሳ፣ “የቡድን ማንነት” የሚባለው የተሳከረ ሃሳብ መሆኑን ለይቶ በመገንዘብ፣ መሰረታዊው የመፍትሄ አስኳልና ፍቱኑ መድሃትንም፣ “የሰው ማንነት፣ የግል ማንነት ነው” የሚል ትክክለና ሃሳብ መሆኑን በማወቅና ለማስረዳት በመትጋት ነው።
ከቅይጥ ኢኮኖሚ ቀውስና ትርምስ ለመዳንም እንዲሁ፣ “የሃብት ክፍፍል” ምናምን የሚሉ የሶሻሊዝም የዝርፊያና የምቀኝነት ማሳበቢያ ሃሳቦችን በማስወገድ፣... እያንዳንዱ ሰው የአቅሙን ያህል በጥረቱ እያመረተ ሃብት የሚያፈራበት፣ የንብረት ባለቤትነቱም የሚከበርበት፣ የሚገበያይበት፣ እንደ ራሱ ፈቃድም የሚደጋገፍበት የነፃ ገበያ ስርዓትን ለማስፋፋት ትክክለኛ ሃሳቦችን አጥርቶ በሙሉ ልብ በመትጋት ነው።
የስህተት አስኳልንም ሆነ ዋናውን ነቀርሳ ለይቶ ለመገንዘብ፣... የመፍትሄ ሃሳብ አስኳልንም አንጥሮ ለማወቅ፣ ትክክለኛ ሃሳቦችንም በስርዓት ቅጥ አስይዞ በሙሉ ልብ ለመስራት ግን፣... የቅይጥ አስተሳሰብ ቀውስን ለማስወገድ ጥረት መጀመር ያስፈልጋል። የመጀመሪያዎቹን ሁለት የሕልውና አደጋዎች መግታት የሚቻለው፣ ሦስተኛውንም የሕልውና አደጋ ለመከላከል በመትጋት ነው።

Read 2863 times