Saturday, 23 June 2018 11:46

ለጠ/ሚኒስትር ዐቢይ የፓርላማ ንግግር የተሰጡ ምላሾች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

  ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ፣ ባለፈው ሰኞ በፓርላማ ቀርበው፣ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሳላቸው ጥያቄዎች ምላሸና ማብራሪያ መስጠታቸውን ተከትሎ፣ በርካቶች በማህበራዊ ድረ-ገፆች አዎንታዊ ምላሽና ድጋፋቸውን ሰጥተዋቸዋል፡፡ አብዛኞቹ ፖለቲከኞችና የፖለቲካ ተንታኞችም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሾች መርካታቸውን ሲገልፁ ሰንብተዋል፡፡ ጥቂቶቹን በፌስ ቡክ ገፃቸው ካሠፈሩት፣ ቀሪዎቹንም በስልክ በማነጋገር፣ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች የሰጧቸውን አስተያየቶች፣ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ እንደሚከተለው አጠናቅሯቸዋል፡፡

    “ጠ/ሚኒስትሩን በሙሉ ልቤ እደግፋቸዋለሁ”
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተዘጋጀላቸውን ፈተና በድል ተወጥተዋል፡፡ የፖለቲካ ብቃታቸውን ለመፈተንና ተቀባይነታቸውን ለማሣጣት፣ የተቃጣባቸውን ጥረቶች፣ በፓርላማው በሰጡት ማብራሪያዎች ማክሸፍ ችለዋል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ ለጥያቄዎች ምላሽ የሰጡበት መንገድ፣ የበሰለና ተራማጅ  ነው፡፡ ምንም እንኳ በቀጥታ በህዝብ የተመረጡ ባይሆኑም፣ እኔም በቀጥታ ባልመርጣቸውም፣ በሙሉ ልቤ እደግፋቸዋለሁ፡፡
ዮናታን ተስፋዬ (ፖለቲከኛ)

“የጠ/ሚኒስትሩ ምላሽ አርኪ ነው”
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተናገሯቸው ነገሮች ውስጥ የባድመ ጉዳይ እንኳር ነው፡፡ ሠውየው ቦታውን በተግባር ያየው፣ የተፈተነበት ቦታ፣ መስዋዕትነት የከፈለበት ቦታ እንደሆነ፣ በዚያ ጉዳይም የመናገር ሞራል አንዳለው በግልፅ አሣይቷል፡፡ ይሄ ምላሽ አርኪ ነበር፡፡ በጥቅሉ የተናገራቸውን ስንመለከታቸው፣ ስለ መንግስት ሳይሆን ስለ ሃገርና ስለ ህዝብ ጥቅም ነው ማስቀደም የፈለገው፡፡
ህዝቡም ይሄን ጠብቆት ስለነበር፣ ኳስ ጨዋታ የሚመለከት ያህል ነው በየቦታው ሲከታተለው የነበረው፡፡ ህዝብ የሃገሩን ጉዳይ ስታስቅድምለት ቦታ ሰጥቶ ያዳምጥሃል፡፡ እኔ ራሴ ሙሉ ለሙሉ በስልኬ ነው ስከታተል የነበረው፡፡ በልዩ ትኩረት ነበር የተከታተልኩት፡፡ እኔ ራሴ የማወራ ነበር ይመስለኝ የነበረው፡፡ ሌላው ሰው የማይረዳው፣ እኔ ብቻ የምረዳው ይመስል ስከታተለው ነበር፡፡ የኔን የልቤን ብቻ የሚናገርልኝ ነበር የመሠለኝ፡፡ ስንመኝ የነበረውን ነው ከንግግሮቹ ያገኘነው፡፡
ስዩም ተሾመ  
(የዩኒቨርሲቲ መምህርና አክቲቪስት)

“ሃገሪቱን ከፖለቲካ ቀውስ ለማላቀቅ ዕድል አለ ”
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቀማጭነታቸውን በኤርትራ አድርገው፣ በትጥቅ የሚንቀሣቀሱ የተቃዋሚ ፖለቲካ ሃይሎችን፡- ግንቦት 7፣ ኦነግ፣ ኦብነግ ብለው ስማቸውን በመጥራት፣ ወደ ሃገር ቤት ተመልሠው፣ በሠላማዊ መንገድ እንዲንቀሳቀሡ ጥሪ ሲያቀርቡ አድምጠናል፡፡ መደራደር እንደሚፈልጉም አሳይተዋል፡፡ አሁን ፓርላማው እነዚህን ድርጅቶች በአስቸኳይ ከሽብርተኛ ድርጅቶች ዝርዝር ውስጥ መሰረዝ አለበት፡፡ ድርጅቶቹም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተቀብለው፣ ወደ ሃገር ቤት ተመልሰው ሊደራደሩ ይገባል፡፡ ጊዜ ማባከን አያስፈልግም፡፡
ማስታወስ ያለብን እነዚህ ድርጅቶች መሳሪያ ያነሡት፣ መንግስት ልዩነት በሠላም ከማስተናገድ ይልቅ በሃይል ለመጨፍለቅ ጥረት በማድረጉ ነው። አሁን ደግሞ በመሳሪያ ሃይል ማመኑን ትቶ፣ መንግስት አዲስ አይነት አቀራረብ እያሣየ ነው። አማፅያኑም ተመሳሳዩን እርምጃ መውሰድ አለባቸው፡፡ ሃገሪቱን ከፖለቲካ ቀውስ ለማላቀቅ አሁን ዕድሎች ያሉ ይመስላሉ፡፡ ጊዜውን በሚገባ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡
ጀዋር መሃመድ
(የፖለቲካ ተንታኝና አክቲቪስት)

“የትግራይ ህዝብ ከጠ/ሚኒስትር አብይ  ጋር ነው!”
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የኤርትራ ጉዳይ ድሮ ያለቀ ጉዳይ ነው ያሉት የሚያስማማ ነው፡፡ በወቅቱ ነው ለተፈፀሙ ስህተት፣ ህዝቡን ሳያወያዩ፣ ወደ አልጀርስ ስምምነት ጉዳዩን የወሰዱት፡፡ በስልጣኑ ላይ የነበሩ ሰዎች ናቸው ተጠያቂዎቹ፡፡ እራሳቸው ተፈራርመው፣ እራሳቸው ወስነው ያከረሙትን ጉዳይ፣ አብይ ላይ ሲደርስ ጩኸት የሚበረክትበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ህዝብ ሳይወያይ ተብሎ፣ ከህወኃትም ይሁን ከአረና አባላት የሚነሳው ጉዳይ ተገቢ አይደለም፡፡ ህወኃትም ሆነ አረና እውነታውን እያወቁ ነው ይሄን የሚሉት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያቀርቡት ሃሳብ ሊደገፍ የሚገባው ነው የሚል አቋም አለኝ፡፡ በተለይ ከእንግዲህ በኋላ የመንግስት አስፈፃሚዎች፣ ህዝቡን ተደብቀው የሚያሳልፉት ውሳኔ አይኖርም፤ ህዝብ ይናገራል አስተያየት ይሠጥበታል፡፡ አብረን እናበስላለን፣ አብስለን አብረን እንበላለን እንጂ እኛ ተደብቀን አብስለን፣ የበሠለ ኬክ የምናቀርብበት ሁኔታ አይኖርም ያሉት ጉዳይ፣ በጣም የሚደገፍ ነው። በተለይ የትግራይ ህዝብ ይሄን ጉዳይ በውስጡ ይዞ ነው ያለው፡፡ ግን ባለው የሰለላ መዋቅር የተነሣ መናገር አይችልም፣ ሃሣቡን መግለፅ አይችልም። የትግራይ ህዝብ በዚህ የአቶ አብይ አቋም መረጋጋቱንና መስማማቱን በግሌ ታዝቤያለሁ። አሁንም ህዝቡ ከእሳቸው ጎን ነው ያለው፡፡ እኔ አሁን በስልክ ነው ለእናንተ ሀሳቤን እየሠጠው ያለሁት፤ ስልኬንና አድራሻዬን አሳልፋችሁ ብትሠጡ ህልውናዬ አደጋ ላይ ነው የሚወደቀው። በትግራይ ያለው ሁኔታ ይህ ነው፡፡ የትግይ ህዝብ የኢትዮጵያውያን ወንድሞቹን ሃሳብ ሙሉ ለሙሉ የሚደግፍ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎትና ሃሳብ በተቃራኒው ቆሞ አያውቅም፡፡
ለምሣሌ ዶ/ር ዐቢይ በፓርላማ ያቀረቡት ሪፖርት በድምፅ ወያኔ አልተላለፈም፡፡ ህዝቡ ግን በአማርኛ የተላለፈውን ተከታትሏል፡፡ ደጋግሞ እያደመጠው ነው፡፡ ስለዚህ የትግራይ ህዝብ ዶ/ር አብይ እያከናወነ ላለው የለውጥ እርምጃ፣ ልባዊ ድጋፍ አለው፡፡ ይሄን ማንም ጋዜጠኛ፣ በነፃነት ህዝቡ ውስጥ ገብቶ ቢፈተሽና ሃቁን ቢያሣውቅ ጥሩ ነው። ዶ/ር አብይ ላይ እምነት አለን፡፡ የሚገርመው ግን አረና እና ህወኃት የህዝቡን ስሜት ሳያውቁ ነው እየተንቀሳቀሰ ያሉት፡፡
ሃይሉ ከትግራይ
(በስልክ የተሰጠ አስተያየት)

“ከሂደቱ ተጠቃሚ እንሆናለን የሚል ተስፋ ሠንቀናል”
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ የተወሠነውን ውሳኔ፣ በፓርላማው ማብራራታቸውን ተከትሎ ጉዳዩ ግልፅ ሆኖልናል፡፡ በማብራሪያቸው የኢትዮጵያ ህዝብ ሳይሳተፍበት የሚፈፀም ጉዳይ እንደሌለ ማስረገጣቸው ጥሩ ተስፋ ሰጥቶናል፡፡
እኛም ያልነው የሚመለከተው ህዝብ ይወያይ ነው፡፡ በድንበር አካባቢ ያለው የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝብ ፍላጎት ካልታከለበት፣ አስተማማኝ ሠላም አይመጣም፡፡ ይሄ በጠቅላይ ሚኒስትሩ መገለፁና መታሠቡ ተስፋ ሰጥቶናል፡፡ ከዚህ ሂደት ተጠቃሚ እንሆናለን የሚል ተስፋ ሰንቀናል፡፡ ባለፉት ሦስት አመታት ከገባንበት ስጋት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሩ ሃሳብ ታክሎበት፣ ሰላም እየሆነ መምጣቱ፣ በሃገራችን የበለጠ ተስፋ እንድናደርግ እረድቶናል፡፡
አቶ ስዩም ዮሃንስ
(የኢሮብ ተወላጆች አስተባባሪ ኮሚቴ አባል)
“እስካሁን ትላልቅ ዕድሎች አምልጠዋል”
ፖለቲካችን ብልሽትሽቱ ወጥቶ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች? በሚል ህልውናዊ ጥያቄ ዙርያ ሲሽከረከር እንደነበር አንስተውም፡፡ ህዝቡም የተስፋ ጭላንጭል ሲያይ፣ እፎይ ያለው፣ የነበረበትን ሁኔታ በቅጡ ስለሚረዳ ነው፡፡ ከእንግዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ አንዱ ጎድቶ፣ ሌላውን ጠቅሞ የሚሄድ ፖለቲካ ሊኖር አይችልም፡፡ ባለፉት ሦስት አመታት ያየነው፣ አገር ሲታመስ ከሞት፣ ከመፈናቀል፣ ከስጋት የተረፈ ህዝብ አልነበረም፡፡ ደሴት ውስጥ ያለ ህዝብ የለም፡፡ ነገሩ ሰከን ብሎ ላስተዋለ፣ የዶክተር አብይ እርምጃዎች፣ አገሪትዋን ከምንም አይነት ስጋት እንደገላገላት ለመገንዘብ የሚቸገር አይመስለኝም፡፡
እንደ ማንኛውም የለውጥ ሂደት፣ በአሁኑ ሰዓት ግራና ቀኝ፣ የተለያየ አስተያየት ቢሰማ አይገርምም፡፡ ነጭ ጥቁርና ግራጫ ያልለመደው ፖለቲካዊ ባህላችን ተጨምሮበት፣ መካረሮች ቢታዩም ባህርያዊ ይመስለኛል፡፡ ከብሽሽቅና ከ”ልክ ልኩን ልንገረው” ካልወጣን፣ ለውጡን የምንገመግምበት መለኪያችን ልክ አይመጣም። በድጋፍም ይሁን በጥርጣሬ ወይም እልም ባለ ተቃውሞ ብንሆንም፣ መለኪያችን ልክ ካልሆነ፣ ድጋፋችንም ጥርጣሬያቸውንም ተቃውሟችንም እርባና አይኖረውም፡፡ ጭፍን ደጋፍም ሆነ ተቃውሞ የስሜት እንጂ የስሌት አይደለም፡፡
ስሙን እማላስታውሰው ፈረንጅ፣ የለውጥ ባለቤት ወይም በለውጡ የምትወናበድ ለመሆን የምትወስነው ዛሬ ነው ይላል፡፡ የዶክተር ዐቢይን  እንቅስቃሴ፣ ጠቧል ብለን ለዓመታት ከጮህንለት የዴሞክራሲ ምህዳር አንፃር፣ ለዓመታት ቂም በቀልና ጥላቻ ይወገድ ብለን ከተመኘነው የመቻቻል ፖለቲካ፣ እውን ሆኖ ማየት ከምንፈልገው የህዝቦች ቀና ግንኙነት ወይም እንዲጠፋ ከምንፈልገው የእልህ፣ የፍረጃና፣ የማግለል ፖለቲካ አንፃር ካየነው፣ ከምንጠብቀው በላይ መልካም ነገር ነው። አሉባልታ፣ መረጃ አልባ ወሬ ትተን የት ደርሰን ነበርን፣ አሁንስ የት ነን? ፊታችንስ ምን ይሆናል ብለን ብናስብ፣ መልሱን አናጣውም፣ ቢያንስ ቢያንስ ጨለማ የሚሳልብን አይመስለኝም፡፡
ብዙ ጊዜ ሰፊ ህዝቡ ፍላጎቱን በተደራጀ መልኩ የሚገልፅባቸው መንገድ ባለመኖራቸው፣ ልሂቃን የራሳቸውን ግላዊ ፍላጎት የህዝቡ በማስመሰል፣ በግላዊ ምቾታቸው ዘመን፣ የራሱን ህዝብ መበዝበዛቸው ሳያንስ፣ ጥቅማቸው በተነካ ጊዜ የህዝቡን ጥቅም እንደተነካ በማስመሰል የረሱትን ህዝብ መነገጃ ሲያደርጉት ማየት የተለመደ ነው፤ ይህ ህወሓትም፣ ኦህዴድም፣ ብአዴንም፣. ዲህዴንም አጋር እሚሉት ፓርቲዎችንም ይመለከታል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ መገንዘብ ያለበት ዋስትናው፣ የህግ የበላይነት እንደ ግለሰቦች አለመሆናቸው ነው፡፡ ህዝብ የራሱንና  የልሂቃንን ፍላጎት መለየት ካልቻለ የሞላጮች መጫወቻ መሆኑ አይቀርም፡፡
ፀረ ዴሞክራሲያዊነት ብሄር የለውም፣ ሙሰኛነት ዘራፊነት ብሄር የለውም፡፡ ገራፊነትና እብሪት ዘር አይደለም፡፡ እነዚህም ምግባሮች የሚነግሱት የህግ የበላይነት ሲጠፋ ነው፡፡ ከዚህ በፊት በዝርዝር የተወያየንበት ቢሆንም አሜሪካዎች ህገ መንግስታቸውን ሲያረቁ፣ ታሳቢ ያደረጉትን ስልጣን የሚይዝ አካል፣ ተቋማዊ የክትትልና የቁጥጥር ስርዓት ካልተበጀለት ያጠፋል ብለው ነው። ዴሞክራሲያዊ የምንላቸው አገራት፣ ዴሞክራቲክ የሆኑ የተለየ ዲኤንኤ ስላላቸው ወይም መለኮታዊ ሃይል ረድቷቸው አይደለም፣ የህግ የበላይነት ማስፈን ሰለቻሉ ነው፡፡ የስልጣን ቆንጆ የለም፡፡ ስርዓት ተበጅቶም ጥቁሮች፣ ስደተኞች ስንት መከራ ያያሉ፣ ሆኖም የ50ዎቿ አሜሪካ አሁን የለችም፡፡
አሁን ጥያቄው፣ አዲሱን ምዕራፍ የምንገመግመው፣ እየተፈፀመ አለ ብለን ከምናስበው/ከምንገምተው ችግር እየተነሳን ነው ወይስ ትልቁን የለውጥ ስእል እየደገፍን፣ ችግር አለ ብለን ስናስብም አማራጭ ሃሳብ እያቀረብን፣ በዚህ ትልቅ የለውጥ ሂደት፣ የራሳችንን ድርሻ እያበረከትን፣ የለውጡ ባለቤት መሆን ነው፣ የኔ ምርጫ፡፡ ታሪካችን እንደሚነግረን፤ ጥቃቅን ነገሮች ላይ እያተኮርን፣ ትላልቅ እድሎች አምልጠዋል፡፡ አሁን ከዚህ አዙሪት የምንወጣበት ዕድል አለ ብዬ አስባለሁ፡፡ ዶ/ር አብይ አሕመድ ተመችተውኛል።
ናሁሠናይ
(የዩኒቨርሲቲ መምህር)

“በመንፈስ አብሬያችሁ መሆኔን አረጋግጣለሁ!”
ለተከበራችሁ ኢትዮጵያዊ ወገኖች፤ በቅድሚያ የከበረ ሠላምታዬን እያቀረብኩኝ፣ ላለፉት 27 ዓመታት ኢትዮጵያዊነትን በማፈንና ብሄራዊ ስሜትን በማደብዘዝ፣ አገራችንን ለአደጋ ከዳረገው ስርዓት ለመላቀቅና በምትኩ አንድነት፣ መተባበርንና ፍትህን ለማስፈን ከምንም በላይ ደግሞ ኢትዮጵያዊነት ለማዳን በተለያየ አቅጣጫ ብዙ እንቅስቃሴዎች በሚካሄድበት በአሁኑ ወቅት፡-
በዚህ የታሪክ አጋጣሚ ኢትዮጵያዊነትና ይቅር መባባልን ይዘው ብቅ ላሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አሕመድና ባልደረቦቻቸው፣ አጭር በሚባል የሰልጣን ቆይታቸው፣ ለወሰዷቸው በጎ እርምጃዎችና ላሳዩት ኢትዮጵያዊ አለኝታነት፣ አጋርነትን ማሳየትና ከጎናቸው መቆም ጊዜው የሚጠይቀው አስፈላጊ ተግባር መሆኑን ስገልፅ፣ በሚደረጉት የድጋፍ እንቅስቃሴዎች ላይ በስራ አጋጣሚ በቦታው ባልገኝም፣ በመንፈስ አብሬያችሁ መሆኔን ሳረጋግጥ በታላቅ ኢትዮጵያዊ ስሜት ነው፡፡
ድል ለኢትዮጵያዊነት ፍቅር ያሸንፋል
ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ)

“እንደ ኢትዮጵያዊነቴ
በኢትዮጵያዊነቴ፤ ሀቁን ብናገር…”
“በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ እንኳን መገንባት ማፍረስም ይከብዳል”
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓቢይ የእግዚአብሄር ስም የሚጠሩ፤ በትህትና ሕዝብን የሚመክሩ ልዩ ስጦታ ያላቸው መሪ ናቸው፡፡ ዶ/ር ዓቢይ እስካሁን በሁለት ወር ውስጥ የሠሩት ስራ በሁለት አመት እንኳን የማይሠራ ነው፡፡ ሁለት ወር እንኳን ለመገንባት ለማፍረስም እኮ ከባድ ነው፡፡
የታሰሩ ሰዎችን ከባዕድ ሀገር አስፈትቶ፣ ከራሱ ጋር በአውሮፕላን ይዞ አምጥቶ፣ ለሃገራቸው ማብቃት ትልቅ ዓቢይ-ሥራ ነው፡፡ ይሄ እውነተኛ የወገን መሪነት ነው፡፡ ማንኛውንም ብሄር ብሄረሠብን ሲያነጋግሩ፣ የእግዚአብሄር ስም እየጠሩ የልብ -“አውቃም” ናቸው። የኢትዮጵያ ህዝብ በኢትዮጵያ አንድነት ያምናል ከምንም በላይ ሃብታችን የኢትዮጵያ አንድነት ነውና...። ይሄን የሚናገር መሪ መፈጠሩ በጣም የሚያስደስት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ፈጣሪውንና ሃገሩን ይወዳል። ወደፊትም ከረሀብና፣ ከስደት፣ ከስራ እጥነት ይዳን- ፈጣሪ በቃህ ይበለው፡- ሀገራችን  ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ሁሉን ነገር ማድረግ የሚችል ቅዱስ-እግዚአብሔር ይባርክ!!
ውብሸት ወርቃለማሁ
በሚሊኒየሙ የትውልዱ የክብር  አምባሳደር    የማስታወቂያ ባለሞያ

Read 6956 times