Saturday, 23 June 2018 11:46

“ግንቦት 7” ትግሉን ማቆሙን በይፋ አስታወቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(15 votes)

ጠ/ሚኒስትሩ ወደ አስመራ ሊጓዙ እንደሚችሉ ተጠቆመ

   ላለፉት 10 ዓመታት የትጥቅ ትግልን ጨምሮ ማንኛውንም የትግል ስልት አማራጭ አድርጎ ሲንቀሳቀስ የነበረው አርበኞች ግንቦት 7፤ ከትላንት ሰኔ 15 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ የአመፅና የትጥቅ እንቅስቃሴ ማቆሙን አስታውቋል፡፡
“በሃገራችን የዲሞክራሲ ለውጥ ለማምጣት ተገደን የገባንበት ማንኛውንም ሰላማዊ ያልሆነ እንቅስቃሴ ገተናል” ያለው ንቅናቄው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ የሚመሩት የለውጥ ሂደት፤ ተስፋ ፈንጣቂና አበረታች በመሆኑ፣ ልዩ ስብሰባ በማድረግ፣ የትጥቅና የአመፅ ትግሉን ለማቆም መወሠኑን ገልጿል፡፡
ከትናንት ጀምሮም በኢትዮጵያ ምንም አይነት አመፅ ነክ እንቅስቃሴ ከማድረግ መቆጠቡን ንቅናቄው ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል፡፡  
የሃገሪቱን የወሠንና የክልል አስተዳደር ለማስተካከል ሊዋቀር በታሰበው ኮሚሽን ውስጥ ተሣትፎ በማድረግ አስተዋፅኦ ለማበርከት ፍላጎት እንዳለው ያስታወቀው ንቅናቄው፤ “ዶ/ር አብይ የትግራይ ህዝብንና ህወሓትን ለያይቶ መመልከት እንደሚገባ ያሳሰቡትን ሃቅ፤ እኛም የምንጋራው ነው” ብሏል፡፡
በአገሪቱ አዲስ የተጀመረው ለውጥ በአሻጥር እንዳይቀለበስ፣ አርበኞች ግንቦት 7 ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን እንደሚሠለፍም በመግለጫው አቋሙን ገልጿል፡፡
በሌላ በኩል የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነትን ተከትሎ፣ ለሁለት አስርት ዓመታት በሁለቱ አገራት መካከል የዘለቀውን ፍጥጫ በማስቆም ግንኙነታቸውን ለማሻሻል የተጀመረው ጥረት ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አድናቆትና ድጋፍ እየተቸረለት ነው፡፡ “ለ20 ዓመታት የዘለቀው ፍጥጫ የሚያበቃበት ምዕራፍ ተጀምሯል” ብለዋል-በጃፓን የኤርትራ አምባሳደር እስጢፋኖስ አፈወርቂ፡፡
የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሣያስ አፈወርቂ በበኩላቸው፤ በኤርትራ በየዓመቱ ሰኔ 13 በሚከበረው የሰማዕታት ቀን በዓል ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የሰላም ጥሪውን እንደሚቀበሉ ጠቁመው፤ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የሚነጋገር የልኡካን ቡድን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚልኩ አስታውቀዋል፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ፤ ከኤርትራ በኩል በተገኘው ምላሽ መደሰታቸውን ጠቁመው፤ “በቀጣይ ለኤርትራና ለኢትዮጵያ ህዝቦች ተባብረን እንደምንሠራ እምነቴ ነው” ብለዋል፡፡ “የልኡካን ቡድኑን እንደ ኤርትራውያን ሳይሆን እንደ ኢትዮጵያውያን በቢሮዬ ተቀብዬ በክብር አስተናግዳቸዋለሁ” ብለዋል፤ ጠ/ሚኒስትሩ በትግርኛ ቋንቋ በሰጡት ምላሽ፡፡
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር በበኩሉ፤ የኤርትራ የልኡካንን ቡድን በታላቅ አክብሮት ተቀብሎ ለማስተናገድ ዝግጅት መደረጉን አስታውቋል። የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል በሰጡት ምላሽ፣ የክልላቸው ህዝብና መንግስት ልኡካኑን በአክብሮት ለመቀበል መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል፡፡
 ሰሞኑን በወጣው ያልተረጋገጠ መረጃ፤ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ለመወያየት ወደ አስመራ ሊጓዙ እንደሚችሉ ተነግሯል፡፡

Read 11645 times