Friday, 22 June 2018 00:00

በጠ/ሚ የድጋፍ ሰልፍ 4.ሚ. ህዝብ ይሳተፋል ተብሎ ይጠበቃል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

- ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ በዛሬው ሠልፍ ላይ ንግግር ያደርጋሉ

    የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣናቸውን ከተረከቡ 3 ወር ገደማ ያስቆጠሩት ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ “ጊዜ የለም በሚል መንፈስ መስራት ያስፈልጋል” ባሉት መሰረት በሳምንት  7 ቀን በትጋት እየሰሩ ሲሆን በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ስኬቶችን እያስመዘገቡ ነው፡፡ በርካታ እስረኞች ተፈተዋል። ስኬታማ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ተደርገዋል፡፡ ለ20 ዓመታት የዘለቀውን የኢትዮ-ኤርትራ ፍጥጫ ለማሻሻል ጠ/ሚኒስትሩ ያደረጉት ጥሪ ውጤታማ ምላሽ አግኝቷል። የነፍጥ ትግል ሲያካሂዱ የቆዩ የፖለቲካ ኃይሎች በዶ/ር ዐቢይ ጥሪ ወደ ሰላማዊ ትግል ተመልሰዋል፡፡ የነፃነትና ዲሞክራሲ ተስፋ ተፈጥሯል፡፡ ሰልፉ ከእኚህና ሌሎች ስኬቶች ጋር ይያያዛል፡፡  “ለውጥን እንደግፍ ዲሞክራሲን እናበርታ” በሚል መሪ ቃል፣ በዛሬው ዕለት ለጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ በአዲስ አበባ በሚደረገው የድጋፍ ሰልፍ ላይ  4 ሚሊዮን ዜጎች ይሣተፋሉ ተብሎ እንደሚገመት አስተባባሪ ኮሚቴው ለአዲስ አድማስ አስታውቋል፡፡
በሠልፉ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ንግግር እንደሚያደርጉ ታውቋል፡፡ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት እንዳረጋገጠው፤ ከሠልፉ አስተባባሪዎች የቀረበላቸውን ግብዣ ተከትሎ ጠ/ሚ ተገኝተው፣ ንግግር ያደርጋሉ፡፡
የሠላማዊ ሠልፉ አላማ በዋናነት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያደርጓቸውን የለውጥ እንቅስቃሴዎች ማበረታታትና ቀጣይ አዳዲስ ለውጦች እንዲመጡ ድጋፍ ማድረግ መሆኑን የጠቆመው የሠልፉ አስተባባሪ ኮሚቴ፤ እስካሁን የሃገሪቱን ፖለቲካ ለማሻሻል እንዲሁም በሃገር ውስጥና በውጪ የሚገኙ ዜጎችን ክብር ለማስጠበቅ ለተደረጉ ጥረቶች እውቅና መስጠትንም ያካትታል ብለዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚደረገውን ለውጥ ለማደናቀፍ የሚደረጉ ጥረቶችንም መቃወም አንዱ የሠልፍ አላማ መሆኑን አዘጋጆች አስታውቀዋል፡፡
ሌላው የሠልፉ አላማ ሠላማዊ ሠልፍ ዲሞክራሲያዊ መብት መሆኑን በተግባር ማረጋገጥ መሆኑንም አስተባባሪዎቹ አስረድተዋል፡፡
በሠላማዊ ሠልፍ ላይ ተቃውሞ እና ግጭትን ከሚያነሣሱ ድርጊቶች መቆጠብ እንደሚገባ እና የፓርቲ አጀንዳን በመድረኩ ላይ ማራመድ እንደማይቻል ተገልጿል፡፡
 የድጋፍ ሠልፍ እንደሚካሄድ በማህበራዊ ገፆች ከተነገረበት ጊዜ ጀምሮ በርካቶች ዝግጅት ሲያደርጉ የሠነበቱ ሲሆን ሠልፉ ላይ የሚለበሱ የጠ/ሚንስትሩ ፎቶግራፍ የታተመባቸው ቲ-ሸርቶች ከ100 እስከ 500 ብር ሲሸጡ መሠንበታቸውን እንዲሁም በተሽከርካሪዎች ላይ የሚለጠፉ የስቲከር ፎቶ ግራፎች ከ20 እስከ 50 ብር መሸጣቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በዚህ ሠላማዊ የድጋፍ ሠልፍ ላይ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ጨምሮ በአዲስ አበባ አንድ መቶ ኪሎ ሜትር ራዲየስ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ይሣተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አስተባባሪ ኮሚቴው አስታውቋል፡፡
ለሰላማዊ ሠልፍ እውቅና የሠጠው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በበኩሉ ሠልፉ ነገ ከጠዋቱ 4 ሠዓት እስከ ቀኑ 7 ሠዓት በመስቀል አደባባይ እንደሚካሄድ ጠቁሞ የፀጥታ ሃይሎች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቋል፡፡ ወደ መስቀል አደባባይ በ6ቱም አቅጣጫ የሚያደርሡ መንገዶች ለተሽከርካሪ ዝግ ሆነው እንደሚቆዩም ታውቋል፡፡
በሃገር ውስጥ በዜጎቻቸው እያከናወኑ ላሉት የፖለቲካ ለውጦች ሠፊ ድጋፍ እያገኙ የመጡት ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ በሚያደርጓቸው ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴዎችም ከፍተኛ ተሠሚነትና ድጋፍ እያገኙ ነው፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ስኬቶችን በማምጣት ኢትዮጵያውያንን ያስደመሙት ጠ/ሚኒስትሩ ከዓለም አቀፍ ማህበረሰብና በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ድጋፍና አድናቆት እየጎረፈላቸው ነው፡፡ የቀድሞ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌየር፤ አፍሪካ ተስፋ የምታደርግበት የለውጥ አራማጅ መሪ ናቸው ሲሉ ያደነቋቸው ሲሆን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቲዊተር ገፃቸው ባሠፈሩት መልዕክት፤ “ለዶ/ር አብይ አህመድ በሣል አመራር ያለኝን አድናቆት እገልፃለሁ፡፡ አፍሪካ የምትፈልገው ትክክለኛ መሪ ነው። ይህ ለኢትዮጵያና ህዝቦቿ መልካም አጋጣሚ ነው፡፡ ትክክለኛ ለውጥ እንዲሆን ምኞቴ ነው” ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል በደሴ፣ ደብረማርቆስ፣ ጎንደርና ዱራሜ ከተሞች በዛሬው ዕለት ለጠ/ሚኒስትሩ የድጋፍ ሠልፍ እንደሚካሄድ የየከተሞቹ የሠልፍ አስተባባሪዎች አስታውቀዋል፡፡

Read 3486 times