Print this page
Sunday, 17 June 2018 00:00

ዳኝነቱ በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

 ~99 ዳኞች ከ46 አገራት ተመርጠዋል፡፡
    ~36 ዋና ዳኞች በነፍስ ወከፍ 57ሺ ዩሮ (በየጨዋታው 2500 ዩሮ)
    ~63 ረዳት ዳኞች በነፍስ ወከፍ 20ሺ ዩሮ (በየጨዋታው 1600 ዩሮ)
    ~ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ባምላክ ተሰማና ዳኝነት በኢትዮጵያ 13 VAR ዳኞችና ሌሎች ባለሙያዎች በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ
    ~ሃብሎት የሰዓት መቆጣጠርያ በተለይ ዳኞች የሚጠቀሙበት በዓለም ገበያ እስከ 5200 ዶላር ያወጣል፡፡
    ~99 ዳኞች ከ46 አገራት (36 ዋና ዳኞች ፤ 63 ረዳት ዳኞች)~


    ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽኖች ማህበር (ፊፋ) በራሽያ ለሚካሄደው 21ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ  46 አገራትን የሚወክሉ 99 ዳኞችን የመደበ ሲሆን 36 ዋና ዳኞች እና 63 ረዳት ዳኞች ናቸው፡፡ በሌላ በኩል በዓለም ዋንጫ ታሪክ የመጀመርያው ለሚሆነው በቪዲዮ ቴክኖሎጂ (VAR) የሚታገዝ  ዳኝነት ላይ የሚሰማሩ ደግሞ 13 ዳኞች እና ሌሎች ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ከ36 የዓለም ዋንጫው ዋና ዳኞች መካከል የአውሮፓ አህጉር 10 በማስመረጥ ግንባር ቀደም ቢሆንም  ከእንግሊዝ አንድም ዳኛ አለመመረጡ ሲያነጋግር ሰንብቷል፡፡ በዓለም ዋንጫ የ88 ዓመታት ታሪክ እንግሊዝ ዳኞቿን ያለስመረጠችው ለመጀመርያ ጊዜ ሲሆን  አገሪቱ ከራሽያ ጋር የገባችው እሰጥ አገባ ምክንያት መሆኑን የተለያዩ መረጃዎች አመልክተዋል። ፊፋ የዓለም ዋንጫ ዳኞቹን የመረጠው ከስድስቱ አህጉራዊ ኮንፌደሬሽኖች ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን በመምራት ሰፊ ልምድ ያላቸው ፤ በተለይ በፊፋ ውድድሮች ማለትም በወጣቶች የዓለም ዋንጫዎች፤ በዓለም ዋንጫ እና የኦሎምፒክ ዋና እና የማጣርያ ውድድሮች፤  በአህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ፕሮፌሽናል የክለብ ውድድሮች ያገለገሉ ዳኞች ለኛው የዓለም ዋንጫ ዳኝነት በተለያዩ መስፈርቶች እና የምርጫ ሂደቶች ተወዳድረውበታል፡፡ ምርጫውን ያከናወኑት ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ የእግር ኳስ ህግና ደንብ እውቀት ያላቸው ባለሙያዎች የተሰባሰቡበት የፊፋ ዳኞች ኮሚቴ አባላት ናቸው፡፡ የ21ኛው የዓለም ዋንጫ ዳኞች ለመሆን የበቁት 99 ዳኞች በፊፋ የዳኞች ኮሚቴ በስፖርታዊ ጨዋነት፤ የተጨዋቾችን ደህነነት በመጠበቅ፤ የስፖርቱን ገፅታ በሚያጠናክሩ ተግባራትና መልካም ስብዕናቸው የተገመገሙ ሲሆን  ለ3 ዓመታት በተለያዩ ሴሚናሮች እና ስልጠናዎች ልዩ ስልጠናዎች እየወሰዱ፤ ክትትል የተደረገባቸውና ደረጃቸውን ያሳደጉ  ናቸው። የዓለም ዋንጫ ዳኞቹ የአካል ብቃታቸው፤ ለእያንዳንዱ ጨዋታ የሚያደርጉት ዝግጅት፤ ዳኝነትን በሚተገብሩባቸው ቴክኒኮች እና የጨዋታ አመራር ብልሃቶች  እንዲሁም በእግር ኳስ ህጎች አተረጓጎማቸው የሚገኙበት የላቀ ደረጃ በጥልቀት ተፈትሿል፡፡ በፊፋ የዳኞች ኮሚቴ የመምረጫ ሂደት የተሳካላቸው ኢንተርናሽናል ዳኞች በተለያዩ የብቃት መመዘኛ ፈተናዎች፤ በወቅታዊ የዳኝነት ብቃት ልኬቶች እና መስፈርቶች ተገምግመው ወደ የዓለም ዋንጫ ዳኝነት የሚመደቡ ይሆናሉ።  በዓለም ዋንጫ ወቅት  ልምዳቸውን፤ የላቀ ብቃታቸውና ከጥቅም ግጭት ነፃ የሚሆኑባቸውን ሁኔታዎች በመንተራስ በመጀመርያው የምድብ ጨዋታዎች ለሚመሯቸው ጨዋታዎችበፊፋ የዳኞች ኮሚቴ ይመደባሉ፡፡ ከመጀመርያ የምድብ ጨዋታዎች በኋላ ደግሞ አፈፃፀማቸው ተገምግሞ በቀጣይ ለሚካሄዱት የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች የሚመደቡም ይሆናል፡፡
በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ የተመደቡት የዓለም ዋንጫ ዳኞች በአገልግሎታቸው የሚያገኙት ጠቅላላ ገቢ ውድድሩ ካለቀ በኋላ የሚታወቅ ቢሆንም በታላቁ የስፖርት መድረክ ላይ እንዲሳተፉ በመመረጣቸውና በየጨዋታው የሚታሰብላቸው አበል ይታወቃል፡፡ ለ36ቱ ዋና ዳኞች በዓለም ዋንጫ ተሳትፏቸው 57ሺ ዩሮ ለእያንዳንዳቸው ሲታሰብላቸው በየጨዋታ የሚከፈላቸው ደግሞ በነፍስ ወከፍ 2500 ዩሮ ነው፡፡ በሌላ በኩል ለ63ቱ ረዳት ዳኞች በዓለም ዋንጫ ተሳትፏቸው 20ሺ ዩሮ ለእያንዳንዳቸው ሲከፈላቸው በየጨዋታ የሚከፈላቸው ደግሞ በነፍስ ወከፍ 1600 ዩሮ ነው፡፡
*   *   *
ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ባምላክ ተሰማና ዳኝነት በኢትዮጵያ
በ21ኛው ዓለም ዋንጫ ላይ ከአፍሪካ ከተመረጡት 6 ዋና ዳኞች መካከል አንዱ ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ ሲሆን ሌሎቹ መሂድ አብዲ ቻሪፍ ከአልጄሪያ፣ ማላንጋ ዲሂቡ ከሴኔጋሌ ባካሪ ፓፓ ከጋኔቢያ ገሂድ ጌርሻ ከግብጽ ጃኒ ከዛምቢያ   ናቸው፡፡ የ38 ዓመቱ ባምላክ ተሰማ በፊፋ በዓለም አቀፍ ጨዋታዎች በመስራት የ9 ዓመታት ልምድ ያለው ሲሆን ከአፍሪካ 10 ምርጥ ዳኞች ተርታ የተሰለፈና  በኤሊት ኤ ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ከ21ኛው የዓለም ዋንጫ በፊት ባምላክ  በዋና እና ረዳት ዳኝነት የሰራባቸው ዓለም አቀፍ ጨዋታዎች ብዛት ከ65 በላይ ሲሆኑ ፤ በ3 የዓለም ዋንጫ የአፍሪካ ዞን ማጣርያዎች፤ በፊፋ ሀ-17 የምድብ እና  የሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች፤  በ3 የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች  እንዲሁም በ3 የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ እና የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች መስራቱ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
እስከ 2018 ዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰጥቷቸው በዋና ዳኝነት እና በረዳት ዳኝነት በሁለቱም ፆታዎች በፊፋ የተመዘገቡት 22 ኢትዮጵያን ዳኞች ናቸው፡፡ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው ኢንተርናሽናል ዋና ዳኞች ወንዶች 7ና ሴቶች 4 ሲሆኑ፤ በኢንተርናሽናል ረዳት ዳኝነት የተመዘገቡት ደግሞ 7 ወንዶች  4 ሴቶች ናቸው። በፊፋ ድረ ገፅ ዋና ኢንተርናሽናል ዳኞች ሆነው የተመዘገቡት 7 ወንድ ዳኞች የሚከተሉት ሲሆኑ  በ2009 እ.ኤ.አ የተመዘገበው በአምላክ ተሰማ፣ በ2015 እ.ኤ.አ የተመዘገበው ወርቁ አማኑኤል፤ በ2014 እ.ኤ.አ የተመዘገበው ለማ ንጉሴ፣ በ2015 እ.ኤ.አ የተመዘገበው የማነ ብርሃን፤ በ2015 እ.ኤ.አ የተመዘገበው ግርማ ዘካርያስ እና በ2012 እ.ኤ.አ ኃይለየሱስ ግዛቸው ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ በአንድ የውድድር ዘመን በ11 ዋና የእግር ኳስ ውድድሮች በሚካሄዱ 1669 ጨዋታዎች እስከ 8385 ዳኞች፤ ኮሚሽነሮች እና ሌሎች ሙያተኞች ይመደባሉ፡፡ የፌደራል ዳኞች ብዛት ከ410 በላይ ሲሆን ለዳኝነት ክፍያ ከተወዳዳሪ ክለቦች ቡድኖች የሚሰበሰበው 19.35 ሚሊዮን ብር፤ ለዳኞች የውሎ አበል የሚከፈለው እስከ 30 ሚሊዮን ብር እንደሚሆን ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ዓመታዊ ሪፖርት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
*   *   *
13 VAR ዳኞችና ሌሎች ባለሙያዎች በታሪክ  ለመጀመርያ ጊዜ
በ21ኛው ዓለም ዋንጫ በውድድሩ ታሪክ  ለመጀመርያ ጊዜ ተግባራዊ ከሚሆኑ ቴክኖሎጂዎች ዋንኛው በቪዲዮ ቴክኖሎጂ የተደገፈ ዳኝነት (VAR) ነው፡፡ ፊፋ ከዓመት በፊት ባካሄደው ልዩ ኮንግረስ በቪዲዮ ቴክኖሎጂ የተደገፈ ዳኝነት (VAR) በዓለም ዋንጫው እንዲተገበር  በሙሉ ድምፅ የወሰነ ሲሆን በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ በዚሁ ተግባር ላይ እንዲሰሩ 13 ዳኞች እና ሌሎች ባለሙያዎች እንደተመደቡ ታውቋል፡፡  በቴክኖሎጂው አጠቃቀም እና ብቃት ላይ ላለፉት 2 ዓመታት በርካታ ሙከራዎች ተደርገዋል።  በተለይ  በ4 የፊፋ ውድድሮች የቴክኖሎጂው አተገባበር በስፋት የተገመገመ ሲሆን  የ2017 ኮንፌደሬሽን ካፕ፤ የ2017 የፊፋ ሀ -17 ሻምፒዮና እንዲሁም በ2016 እና በ2017 የተደረጉት የዓለም ክለብ ዋንጫዎች ናቸው፡፡
በቪዲዮ ቴክኖሎጂ የተደገፈ ዳኝነት (VAR) በዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች ላይ አዎንታዊ ለውጥ ሊፈጥር እንደሚችል ብዙዎች ተስፋ አድርገዋል።  ለከፍተኛ ውዝግብ የሚዳርጉ ግልፅ ስህተቶች እና ድብቅ ጥፋቶችን በትኩረት በመከታተል የዳኝነት ውሳኔዎችን  ትክክለኛ እና  የተሟሉ የሚያደርግ ለውጥ እንደሆነም ይገለፃል፡፡ ፊፋ የዓለም ዋንጫ ዳኞች የመጨረሻውን ውሳኔ የሚያሳልፉበትን መብት በግልፅ ያከበረ ሲሆን የቪድዮ ቴክኖሎጂው የሚተገበርበት ዋና ዓላማ ዳኞችን ለመጠቆም፤ለማንቃት፤ ለመምከር እና ለማገዝ መሆኑንም በተለያዩ መረጃዎች መረዳት የሚቻል ነው፡፡   በቪዲዮ ቴክኖሎጂ የተደገፈ ዳኝነት (VAR) በተለይ 4 የጨዋታን ውጤት በሚቀይሩ ሁኔታዎች ማለትም ጎል በማፅደቅ፤ የመለያ ምት ውሳኔ በመስጠት፤ የቀይ ካርድ ውሳኔዎችን በማሳለፍ እና በተጨዋቾች ትክክለኛ ማንነት ላይ በተመሰረቱ  ውሳኔዎች ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዲኖረው ታስቧል፡፡ ፊፋ በቪዲዮ ቴክኖሎጂ የተደገፈ ዳኝነት (VAR) በዓለም ዋንጫው እንዲተገበር የወሰነው የዳኞችን ውሳኔ ለመደገፍ እና ትክክለኛ ለማድረግ ነው፡፡ አንድ የቤልጅዬም ዩኒቨርስቲ ቴክኖሎጂው በዳኝነት ትክክለኛ ውሳኔ የመስጠቱን እድል ከ93 ወደ 98.8 በመቶ የሚያሳድግ መሆኑን በጥናት አረጋግጧል፡፡ በ21ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ በቪዲዮ ቴክኖሎጂ የተደገፈ ዳኝነትን (VAR) የሚሰሩት ዳኞች እና ሌሎች ባለሙያዎች ሲሆኑ በእያንዳንዱ ጨዋታ ዋና ዳኛውንና ረዳት ዳኞቹን በማገዝ የሚመደቡት 4 ናቸው፡፡ ዋናው ተቆጣጣሪ VAR የሚባለው ሲሆን አብረውት ደግሞ AVAR1 AVAR2 እና AVAR3 ተብለው የሚመደቡ የካሜራ፤ የሪፕሌይ ኦፕሬተሮች ናቸው፡፡
ፊፋ በቀጥታ ስርጭት በሁሉም 12 ስታድዬሞች የሚሰሩ 33 ግዙፍ ካሜራዎችን በመጠቀም በቪዲዮ ቴክኖሎጂ የተደገፈ ዳኝነት (VAR) በሁሉም 64 የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች ላይ የሚተገብር ሲሆን የሚሰራው በሞስኮ ከተማ ከፍተኛ ደረጃ ያለውን ስቱድዮ በመትከል እንደሆነ ታውቋል፡፡ አንዳንድ የእግር ኳስ ባለሙያዎች ከጎል ላይን ቴክኖሎጂ በኋላ በዓለም ዋንጫው በቪዲዮ ቴክኖሎጂ የተደገፈ ዳኝነት (VAR) ተግባራዊ መሆኑ የስፖርቱን ተፈጥሯዊነት የሚያጎድልና ሰዓት የሚያባክን በማለት ቢነቅፉትም  የቴክኖሎጂው መተግበር በውድድሩ የሚያጋጥሙ ውዝግቦችና ንትርኮችን እንደሚቀንስ የታመነበት ሲሆን በአፈፃፀሙም ከውሳኔ በፊት ከአንድ ደቂቃ ያነሰ ጊዜ መውሰዱን በመጥቀስ የፊፋ ባለሙያዎች ትችቶች ተከላክለዋል፡፡
*   *   *
ሃብሎት የዓለም ዋንጫው ኦፊሴላዊ ሰዓት
 የ21ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ ኦፊሴላዊ ሰዓት የስዊዘርላንዱ ኩባንያ ሃብሎት የሚያቀርበው BBR2018FWCR ‹‹ቢግባንግ ሬፈሪስ 2018 ፊፋ ዎርልድ ካፕ›› ነው፡፡ ሃብሎት እነ ፔሌ፤ ማራዶና፤ እንዲሁም ሞውሪንሆ የሚገለገሉበት የሰዓት ብራንድ ሲሆን  ቤነፊካ፤ ጁቬንትስ እና አያክስ ከክለቦች ከኩባንያው ጋር በስፖንሰርሺፕ አጋርነት የሰሩ ናቸው፡፡ ሃብሎት የዓለም ዋንጫ ኦፊሴላዊ የሰዓት መቆጣጠርያ ከመሆኑ ባሻገር ለውድድሩ ዳኞች ዋንኛ መገልገያም ነው፡፡ በዓለም ዋንጫው ወቅት ሁሉም ዳኞች የሚያደርጉት የሃብሎት ሰዓት ከጎል ላይን እና በቪዲዮ ቴክኖሎጂ የተደገፈ ዳኝነት (VAR) በቀጥታ የሚገናኝ፤ የ32 የዓለም ዋንጫ ተሳታፊ ብሄራዊ ቡድኖች ሰንደቅ ዓላማ ያለው፤ ጎልና የተጨዋቾች የካርድ ቅጣትና የተጨዋቾች ቅያሪ ወዲያው የሚመዘግብ ከመሆኑም በላይ ከእያንዳንዱ የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች መጀመር 18 ደቂቃ በፊት አገልግሎት የሚሰጥ ነው፡፡ ሃብሎት ከዓለም ስፖርት በተለይ ከእግር ኳስ ጋር ላለፉት 12 ዓመታት የሰራ ኩባንያ ሲሆን ለዓለም ዋንጫ በልዩ ትዕዛዝ የሰራው የሰዓት መቆጣጠርያ በተለይ ዳኞች የሚጠቀሙበት በዓለም ገበያ እስከ 5200 ዶላር ያወጣል፡፡

Read 4188 times